>

“ጅሃዲስቱ” ከማዕከላዊ እስከ ቂሊንጦ [በአጥናፉ ብርሃኔ - ዞን ፱]

Atinaf-Brhane - Zone 9አርብ ሚያዝያ 17፣ 2006 ዐሥር ሰአት አካባቢ ከጓደኛዬ በፍቃዱ ኃይሉ ጋር ከቀነኒሳ ሆቴል ወጥተን ትንሽ እንደተጓዝን የበፍቃዱ ስልክ ጠራ፤ ማነገር ጀመረ ቀስ እያለ ዓይኑ በድንጋጤ እየፈጠጠ ሲመጣ አየሁት ቀጥሎ “ምን?!” የሚል ድምፅ ተከተለ። ለበፍቃዱ በስልኩ የተላለፈለት አስደንጋጭ መልዕክት የእስር ወሬ መሆኑን በትንሹም ቢሆን ጠረጠርኩ። ወሩን ሙሉ በደኅንነት ተከበን ስንንቀሳቀስ ስለነበረ የፈራነው እንደደረሰ ገባኝ።
“ከማዕከላዊ ፖሊሶች መጥተው ማሂን ወሰዷት” አለኝ። ደነገጥኩ። ወድያው ሁለታችንም ስልካችን ላይ ተደፍተን ለተቀሩት ጓደኞቻችን መልእክት ለማስተላለፍ ስንፍጨረጨር አንድ ‘ሀይሉክስ ቶዮታ’ መኪና ከፊታችን ቆመ፤ ከመኪናው ውስጥ መደበኛ ልብስ የለበሱ ግለሰቦች ወርደው ስልካችንን በፍጥነት ተቀበሉን። በቆምንበት በፍጥነት ፎቶ አንስተውን ወደ መኪናው አስገቡን።
አስር የሚጠጉ ደህንነቶች የወላጆቼን ቤት በርብረው ከጨረሱ በኋላ ምሽት 3፡20 በፌደራል ፖሊሶች በታጨቀ ‘ፓትሮል’ መኪና ውስጥ ሆኜ በዝና ወደማውቀውና ባለፍኩ ባገደምኩ ቁጥር ቀና ብዬ ወደማየው “የስቃይ ማማ” ማዕከላዊ ገባሁ። ብርድ ልብስና ነጠላ ጫማዬን እንደያዝኩኝ ከመኪና እንድወርድ ተነገረኝ፡፡ ከዛም ወደ አንድ ክፍል አስገብተው ሙሉ ስሜንና ብሔሬን አስመዘገብኩ፡፡ በወቅቱ አርጌ የነበረውን የሸራ ጫማ ክር እንዳስረክብ ተጠየኩ፤ ቀበቶዬንም ተቀማሁ። ራሴን እንዳላጠፋ መሆኑ ነው። ማዕከላዊ ሞት የሚያስመኝ ቦታ መሆኑን ያወኩት ያኔ ነው። አቤልና ናትናኤል ተመሳሳይ ነገር አርገው ሲወጡ መንገድ ላይ ተገጣጠምን ሰለም ልንባባል ስንል “ዞር በል ከዚህ!” የሚል አንባራቂ ድምፅ ሰማሁ። ከዛም አንድ ኮማንደር ‘ሳይቤርያ’ ወደሚባለው የማእከላዊ ክልል ይዞኝ ሄደ። ድፍን ባለ ኮሪደር ውስጥ አስገብቶኝ በግራና በቀኝ ከተደረደሩት ክፍሎች በግራ በኩል ሶስተኛ ቤት የሆነውን ክፍል ቁልፍ መታገል ጀመረ። የክፍሉ በር በወፍራም ላሜራ የተሰራ ነው። የቁልፉ ብረትና በሩ ሲጋጩ የሚፈጥሩት ድምፅ ከአካባቢው ጨለማና ፀጥታ ጋር ተዳምሮ ጆሮ ያማል።
በሩ ተከፈተና ወደ ክፍሉ አስገባኝ፡፡ ዳር ላይ ቆምኩ። ያስገባኝ ኮማንደር በሩን እያንጋጋ ከጀርባዬ ዘጋው። ክፍሉ ውስጥ ትንሽዬ ጭል ጭል የምትል አንፖል ሰው ከማይደርስባት ዳር ላይ ተሰቅላለች፤ ግድግዳው በቁርአን ጥቅስ ተሞልቷል (ታሳሪዎች አሻራ ሰጥተው ሲመለሱ እጃቸው ላይ በተረፈው ቀለም ግድግዳው ላይ እንደሚፅፉ ጥቂት ቆይቶ ገባኝ)፤ መሬቱ አምስት ፍራሽ ያዘረጋል፤ በግራ በኩል አንድ ሰው ጥጉን ይዞ ቆሟል፤ አተኩሬ አየሁት በጣም አጭርና ጥቁር ነው። ልብሱ እላዩ ላይ የተበጫጨቀ፤ ጢሙ የረዘመና የራስ ፀጉሩ የገባ። ሙስሊም እንደሆነ ገፅታው ነገረኝ። ወድያውኑ ጭንቅላቴ እነ አቡበከር አህመድ ጋር ወሰደኝ። ከመታሰሬ በፊት በማዕከላዊ ምርመራ የደረሰባቸውን ስቃይ አንብቤ ነበር። ተስፋ ቆረጥኩ። የልጁ ፊት ላይ የሚነበበው የስቃይ ገፅታ “በቃ አለቀልኝ” ብዬ ለራሴ እንድነግረው አረገኝ። እቃዬን መጥቶ ተቀበለኝና አንዳርፍ ወደ ፍራሹ ጋበዘኝ ፣ ይህ ግለሰብ ሼህ ሳሂብ ይባላል ከጅማ ተይዞ የመጣ በግብርና የሚተዳደር የለየለት ‘ጅሃዲስት’ ነው።
የበሩ ጩኸት ተኝተው የነበሩ ሌሎች እስረኞች ከእንቅላፋቸው ቀሰቀሳቸው። በክፍሉ ውስጥ እኔን ጨምሮ አራት የሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጣሪዎች ስንኖር ሁለት በገንዘብ ነክ ወንጀል ተጠርጥረው የገቡም ነበሩበት። በሽብር ተጠርጥረን የገባነው ሁሴን አሊ (ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር አብሮ የታሰረና የቄራ መስጅድ ኢማምና በኋላም ከኮሚቴዎቹ ጋር 15 አመት ተፈርዶበት ቃሊቲ የሚገኘው የሰድ አሊ ወንድም) በጥሩ ሁኔታ አቀባበል ያረገልኝ፣ ኦታካ ኡዋር የሚባል የአኝዋ ተወላጅና ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው በዴቪድ ያው ያው የሚመራው ኮብራ አማፅያን ወታደርና በአሁኑ ወቅት በነ ኦኬሎ አኳይ መዝገብ ‘ጋምቤላን ከፌደሬሽኑ በትጥቅ ትግል ልታስገነጥል ሞክረሃል’ ተብሎ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለ፣ እንዲሁም ከላይ የገለፅኩላችሁ ሼኽ ሳሂብ የሚባል አገሪቷ በሸሪያ መተዳደር አለባት ብሎ የሚያምን ‘ጅሃዲስት’ አብረን ነበርን።
ግራ የገባው ‘ጅሃዲስት’?!
“አክራሪነትና ፅንፈኝነት” ለዘመናት ጆሯችንን ሲያደነቁሩ የከረሙ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ ቁልፍ ቃላቶች ናቸው። “የሀይማኖት ነፃነት ይከበር፣ በሀይማኖቴ ጣልቃ አትግቡብኝ” ያለና “ኢትዮጵያ በሸርያ ነው መተዳደር ያለባት፣ ሌላ ሀይማኖት መኖር የለበትም፣ ግብር ለመንግስት አልከፍልም፤ ሀራም ነው” የሚል በመንግስት አይን እኩል ፅንፈኛና አክራሪ ተብለው የአሸባሪነት ካባ ያስደርባል።
ከሼህ ሳሂብ ጋር በማዕከላዊ በቆየሁባቸው ሁለት ሳምንታት በምን እንደታሰረና አላማው ምን እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። ከቁርአን ትምህርት ውጪ ሌላ ትምህርት አልተማረም፤ መማር ለሱ ሀጥያት ነው። ጅማ ውስጥ ሚስትና ሶስት ልጆች አሉት። በእርሻ ላይ እንዳለ ፖሊሶች ሊይዙት ሲመጡ ለማምለጥ ቢሮጥም ጥይት ተኩሰው እንዳስቆሙትና ከተያዘም በኋላ ለማምለጥ በማስቸገሩ ጀርባው እስኪላጥ ድረስ እንደደበደቡት ጀርባውን ገልጦ ጠባሳውን አሳየኝ። ወደ ማእከላዊ ከገባም በኋላ በተለምዶነ‘ስምንት ቁጥር’ የሚባለው ቤት አንድ ሰው ብቻ የሚታሰርበት ክፍል ውስጥ ለሁለት ሳምንት እንዳቆዩትና ‘ምርመራም’ እንደጨረሰ በተኮላተፈው አማርኛ አስረዳኝ። እንደተግባባሁት ብዙ ታሪክ ከጀርባው እንዳለ ስላወኩ ጥያቄዎች አዘንብበት ነበር።
“ምርመራ ጨርሰሃል?”
“አዎ። ከገባሁ ሁለት ወር ሆኖኛል”
“በምን ጠርጥረው ነው የያዙህ?”
“በሽብር ነው። እስላማዊ መንግስት ልታቋቁም ነበር ነው የሚሉኝ።”
“አንተ እስላማዊ መንግስት ልታቋቁም ነበር?”
“አዎ። እኔ ምንም ወንጀል አልሰራሁም፣ ቁርአን ያዘዘኝን ነው ያረኩት።”
“እና ለመርማሪዎቹ ምን አልካቸው?”
“መሳርያ ይዘን ጫካ ለመግባት አላማ እንደነበረንና ይህን የምናረገው ኢትዮጵያ በሸርያ መተዳደር አለባት ብለን አስበን እንደሆነ ነው የነገርኳቸው።”
“አምነሃል ማለት ነው?”
“አዎ!”
“ደብድበውህ ነው ያመንከው?”
“የደበደቡኝማ መጀመሪያ ነው። ሲይዙኝ። እዚህ ከገባሁ በኋል ብዙ ልጆች ይደበደባሉ እኔን ግን አልደበደቡኝም”
“እዚህ ካመንክ እንደሚፈረድብህ ታውቃለህ አይደል? ብዙ ዓመት ነው የምትታሰረው።”
“አውቃለሁ። ግን መዋሸት አልፈለኩም። ይሄ ለእምነቴ የምከፍለው መስዋትነት ነው። አላህ ወደፊት ይከፍለኛል።”
“ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ህይማኖት ብቻ እንዲኖር ነው የምትፈልገው?”
“አዎ! እስልምና ብቻ ነው መኖር ያለበት፤ በመንግስት ሳይሆን በሸርያ ነው መተዳደር ያለብን”
“ሌላ ሀይማኖት ያለው ሰው ታድያ ምን ልታደርጉት ነው?”
ይህን ጥያቄ ስጠይቀው ለመመለስ ትንሽ አቅማማ። በጣም ‘ዲፕሎማት’ በሆነ አነጋገር “ሙስሊም እንዲሆን ይደረጋል” አለኝ። ምን ማለት እንደሆነ ገብቶኛል። እሱ እና ግብር አበሮቹ ለዚህ ዓላማ ተግባራዊ መሆን ጅማ ጫካ ውስጥ ሲደክሙ የነበሩ ናቸው፡፡
ይህ ሰው ሁለት ሳምንት አብሮኝ ቆይቷል። ለኔ ክፉ አልነበረም፤ ተደብደቤ ስመጣ አሽቶኛል። ሐየማኖታችን ሳያግደን አብረን ከቤቴ የመጣውን ምግብ አብረን በልተናል። ምንም አይነት የቀለም ትምህርት አልወሰደም፡፡ በክርስትያን የተባረከ ምግብ ይበላል። ‘ለምን የክርስትዯን ስጋ ትበላለህ?’ ስለው “በአስቸጋሪ ሁኔታ ከሆንክ አይከለከልም” ይለኛል።
እኔንና ሼኽ ሳይብን ችግር በአንድ አልጋ ላይ እንድንተኛ አረገን እንጅ፤ ሰንቆት የነበረውንና ሊሰራው ሲዘጋጅ የነበረውን ድርጊት ሳስበው ይዘገንነኛል። ሼኽ ሳሂብ ድርጊቱን አምኖ እየተከራከረ ነው። ‘ፈጣሪ አዞኝ ነው ያደረኩት’ ብሎ ስለሚያምን “የጀነት” በር ወለል ብሎ እንደሚከፈትለት ያምናል። ከሼኽ ሳሂብ ጋር የነበረኝ የማዕከላዊ ቆይታ የበቃው በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው። አንድ ቀን ጠዋት ኮተቱን ይዞ እንዲወጣ ተደረገና ‘ሸራተን’ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ወሰዱት።
ሀምሌ 11፣ 2006 ዓለም ላይ ያሉ ወንጀሎች ተደፍድፈውብኝ ወደ ቂሊንጦ እንድሄድ ከተደረኩ በኋላ ማዕከላዊ የማቀውን ሰው መፈለግ ጀመርኩ። ካገኝኋቸው ሰዎች መካከል ሸኽ ሳሂብ አንዱ ነው። በአንፃራዊነት የተሻለ ልብስ ለብሷል። “ኢስላማዊ መንግስት ልትመሰርት አስበሀል” ብለው በሽብርተኝነት ወንጀል እንደከሰሱት ነገረኝ። እኔም ከሱ እኩል መከሰሰ እየገረመኝ እሱ ከወጣ በኋላ ጨለማ ቤት ውስጥ ብዙ እንደቆየሁና ዱላቸውም ጠንክሮብኝ እንደነበር ነገርኩት። የደረሰብኝን ስነግረው አዘነልኝ።
ቂሊንጦን ትንሽ ከተለማመድኩ በኋላ ግቢው ውስጥ ብቻዬን መንቀሳቀስ ጀመርኩ። አንድ ቀን አናት የሚተረትረውን የቂሊንጦ የስድስት ሰዓት ፀሀይ ሽሽት የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደሚሰግዱበት ቦታ ቁጭ አልኩኝ። ጥግ ላይ ወደ አራት የሚጠጉ ሙስሊሞች ይሰግዳሉ። ከመካከላቸው ሼህ ሳሂብ አለ። በቁጥር ማነሳቸው ገርሞኝል። ስግደት ከጨረሱ በኋላ ሸህ ሳሂብ ወደኔ መጣ።
“ዛሬ ምነው አነሳችሁ አልኩት?”
“እኛ ሁሌም እንደዚህ ነው የምንሰግደው።”
“ብቻችሁን?”
“አዎ”
“መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች አሉ አይደል እንዴ? ከነ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ጋር ለምን አትሰግዱም?” ስለው ጭንቅላቱን እየወዘወዘ “እነሱ ሙስሊሞች አይደሉም! ከነሱ ጋር መሆን አልፈልግም።” አለኝ። የሃይማኖት ነፃነት ይከበር በማለቱ የ22 ዓመት ፍርድ የተበየነበት (በኋላ ቢፈታም) ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በሼሕ ሳህብ አስተሳሰብ ሙስሊም አይደለም። ይህ ‘ጅሃዲስት’ ሰይፉን ሲስል የነበረው ለሙስሊሙም ለክርስትያኑም እንደነበር ገባኝ።
አክራሪ፣ ፅንፈኛና አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የተወረወሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በብዙ ‘ጅሃዲስቶች’ ይጠላሉ። ሙስሊሞች በጋራ በሚሰግዱበት ሰዓትም “ከክርስትያኖች ጋር አልሰግደም” የሚል ‘ጅሃዲስትም’ አለ። በሊቢያ በርሃ በአይሲስ አንገታቸው ስለተቀላ ኢትዮጵያውያን ሰምቶ አንጀቱ ቅቤ የጠጣ፣ “እሰይ!፣ አይሲስ እስላማዊ ያልሆነ ነገር ሲሰራ አላየሁትም” ያለ ‘ጅሃዲስትም’ አለ። ከንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር መታሰር ጭንቅላትን ይጎዳል። ከዚህ በባሰ ሁኔታ ግን ሕጉን በፈለገው መንገድ የሚጫወትበት መንግስት ትክክለኛ ጥያቄ “የእምነት ነፃነት ይከበር” በማለት ያነሳውንና “አንድ ሀይማኖት ወይም ሞት” ብሎ ከንፁሃን አንገት በሚፈሰው ደም ለመፅደቅ ያሰበውን እኩል ይከሳል፣ እኩል ይፈርድባቸዋል።
Filed in: Amharic