>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6716

ተመስገንን በጨረፍታ [በማሕሌት ፋንታሁን]

Journalist Temesgen Desalegn 04042016መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት ጋር ማቆራኘት ሳያስፈልገው የጻፈው ጽሑፍ ብቻ ተጠቅሶበት የተከሰሰ እና የተፈረደበት ብቸኛ ጋዜጠኛ ነው – ተመስገን ደሳለኝ። በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተመሠረተችው ፍትህ ጋዜጣ ጥቂቶቹን የግል ሕትመት ሚዲያ ውጤቶች የተቀላለችው በ2000 ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ የተከሰተውን የግል ሚዲያ እጥረት አሳስቦት እና የበኩሉን ለመወጣት ብሎ ነው ፍትሕን ለመመሥረት የተነሳሳው። ፍትሕ ጋዜጣ ሕትመት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2004 ሐምሌ ወር (ላይ እስክትታገድ ድረስ) ድረስ ከዓመት ወደ ዓመት የሕትመት ብዛቷ እየጨመረ መጨረሻ አካባቢ እስከ 35ሺ ኮፒ ትታተም ነበር።
ማንኛውም ዓይነት ቅድመ ሳንሱር እንደሌለ በሚደነግገው ሕገመንግሥት መተዳደር ያለበት ፍትሕ ጋዜጣን የሚያትመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ የሐምሌ 13/2004 ዓም እትም ላይ ስለ መለስ ዜናዊ የተጻፈ ዜና ካልወጣ እንደማያትሙ አሳወቁ። ይህን የሰማው ተመስገን እያረጉ ያሉት ቅድመ ሳንሱር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ በሕገመንግሥቱ የተከለከለ መሆኑን ከገለጸላቸው በኋላ የታዘዙትን 30ሺ ኮፒ ካተሙ በኋላ እንዳይሰራጭ ከፍትሕ ሚኒስቴር በተላለፈ ትዕዛዝ መሠረት ማገዳቸውን እና የታተመው ጋዜጣም መወረሱን በደብዳቤ ገለፁ። ለ30ሺ ኮፒ ሕትመት፣ ለጸሐፊዎች የሚከፈል እና ለተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች የወጣው ገንዘብ ወደ100ሺ ብር የሚጠጋ ከስሯል። ነሐሴ 2 ቀን 2004 ክስ እንደተመሠረተበት ፋና ዜና ላይ እንደሰማ የሚናገረው ተመስገን፣ በዜናው እንደሰማውም በቀጣይ ቀጠሮ ነሐሴ 9 ቀን 2004 ፍ/ቤት ቀረበ። በ2003 እና በ2004 በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በወጡ 5ት ጽሑፎች ሦስት ክስ እንደቀረበበት ተነግሮት የዋስትና መብቱንም ተነፍጎ የዛኑ ቀን ወደ እስር ቤት ገባ። ለስድስት ቀናት በቃሊቲ ጨለማ ቤት ከቆየ በኋላ ባልተጠበቀ ሰዓት እና ምክንያቱ ሳይነግው ነሐሴ 16/2004 ከእስር ተለቀቀ። በኋላ ሁላችንም እንደሰማነው ከእስር የተለቀቀው ክሱ ተቋርጦለት መሆኑን ነው።
ጋዜጠኛ ተመስገን የቀረቡበት ክሶች 1ኛ) ወጣቶች በአገሪቱ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ላይ እንዲያምፁ የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር፣ 2ኛ) የሀገሪቱን መንግሥት ሥም ማጥፋት እና የሐሰት ውንጀላ፣ 3ኛ) ክስ የሐሰት ወሬዎችን በማውራት ሕዝብን በማነሳሳት ወይም አስተሳሰባቸውን ማናወጥ ሲሆኑ ይህን ክስ ሊያስመሠርቱበት የቻሉት ጽሑፎች ደግሞ 1) የፈራ ይመለስ (በተመስገን ደሳለኝ) 2) የሁለተኛ ዜግነት ሕይወት በኢትዮጵያ እስከመቼ? (በተመስገን ደሳለኝ) 3) መጅሊሱና ሲኖዶሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ (በተመስገን ደሳለኝ) 4) ሞት የማይፈሩ ወጣቶች (በተመስገን ደሳለኝ) እና 5) የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመጨፈር የሚሉት ናቸው።
ፍትሕ በዚ መልኩ ከሕትመት ከታገደች በኋላ ተሜ እጅ እና እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም ወይም መሰደድን አልመረጠም። በ2005 ፍትሕን በአዲስታይምስ መጽሔት መልክ፣ እሱም እንዲዘጋ ሲደረግ በልዕልና ጋዜጣ እውነትን እንድናነብ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለፍቷል። ልዕልናም ቀኗ ደርሶ ከሕትመቱ ዓለም ስትሰናበት ደግሞ በ2007 በግሉ ዘርፍ ይታተሙ ከነበሩ ተመራጭ ጥቂት መጽሔቶች እና ጋዜጦች ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው እንዳይሠሩ ከታገዱት የሕትመት ውጤቶች መሐል አንዷ በሆነችው ፋክት መጽሔት ሥራውን ቀጥሎ ነበር።
በነሐሴ 13፣ 2004 ተቋረጠ የተባለው ክስ መቀስቀሱን አሁንም እሱ በሌለበት በታኅሣሥ ወር 2005 የዋለው ችሎት በፋና ሬዲዮ መዘገቡን ሰማ/ን። በቀጣዩ የቀጠሮ ቀን ሲቀርብ የ50ሺህ ብር የዋስትና ብር አስይዞ ክሱን ከውጪ ሆኖ እንዲከታተል ተፈቀደለት። ክሱን እየተከታተለም ነው ልዕልና ጋዜጣን እና ፋክት መጽሔትን ለኛ ላንባቢዎቹ ሲያደርስ የነበረው። ታኅሣሥ 2005 የተንቀሳቀሰበትን ክስ በዋስትና ሲከታተል ቆይቶ፤ በጥቅምት 3፣ 2007 ጥፋተኛ የተባለው እንዲሁም ጥቅምት 17፣ 2007 ላይ ደግሞ የ3 ዓመት ፍርድ የተፈረደበት።
ተመስገን የሥራ ሰዓት እና የእረፍት ሰዓት የለውም። ብዙውን ጊዜውን በመጻፍ ወይም በማንበብ ነው የሚያሳልፈው። የጻፈውን የኖረ እና እየኖረ ያለ ጋዜጠኛ ነው።
ዝዋይ ከመሄዱ በፊት ቃሊቲ በነበረበት ጊዜያትም ሆነ ዝዋይ ከሄደ በኋላ ተመስገን፣ ሌሎች እስረኞች እንዳይቀርቡት ይደረጋል። ቃሊቲ እያለ የአልሻባብ አባል ተብለው በሽብር ተከሰው ከሱ ጋር የሚኖሩ እስረኞች ከሱ ጋር ካወሩ ወይም ወክ ሲያደርጉ ከታዮ “እንዴት ከአሸባሪ ጋር ትሆናላችሁ?” ይባሉ እና የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እንደሚደርስባቸው ነግረውታል። የዝዋዩ ደግሞ የባሰ ሆኖ ነው ያገኘው። ከሱ ጋር ያወራ ማታ ማታ እየተወሰደ ይደበደባል። ይህን በመፍራት ብዙ እስረኞች ከሱ ጋር መሆን ይፈራሉ። መጽሐፍ አይገባለትም። ሕክምና ለማግኘት ሲጠይቅ “ቆይ ያንተን ጉዳይ እየተነጋገርንበት ነው” ከሚል ውጪ ያገኘው ምላሽ ስለሌለ ከጀርባ ሕመሙ ስቃይ ጋር አብሮ ይኖራል። ምንም ዓይነት መጽሐፍት አይገቡለትም። ከሌሎች እስረኞች ተውሶ ማንበብም አይችልም። እሱ ያለበት ዞን ላይብረሪ የለም። ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ እንዳይጠይቁት ይከለከላሉ። ብዙ ጓደኞቹ እና ወዳጆቹ ብዙ ርቀት ተጉዘው ከእናቱ እና ወንድሞቹ ውጪ እሱን መጠየቅ አይቻልም ተብለው ይመለሳሉ። የዛሬ ዓመት አካባቢ እናቱን እና ወንድሞቹን ጭምር ለሁለት ወር ያክል እንዳይጠይቁት ተከልክለው ነበር። በተለያዩ ጊዜያትም እነዚሁ የቅርብ ቤተሰቦቹ ገብተው እንዳይጠይቁት ተከልክለው ይመለሳሉ። በአንድ ወቅት ታናሽ ወንድሙ የሆነው ታሪኩ ደሳለኝ ሊጠይቀው በሄደ ወቅት መግባት እንደማይችል ከነገሩት በኋላ በማያቀው ምክንያት በዝዋይ እስር ቤት ፓሊሶች ተደብድቧል።
ምክንያቱን ባይገባኝም ከቅርብ ቤተሰቦቹ ውጪ መጎብኘት የሚፈቀድለትን አንዳንድ ወቅቶች ተከታትለው የሚጠይቁት ጓደኞቹ ብዙ አይደሉም። ተመስገንን የምንወደው ጓደኛችን ከሆነ ከቤተሰብ ውጪ መጠየቅ አይቻልም ብሎ ቁጭ ከማለት ዝዋይ መጠየቅ ከሚፈቀድለት ቤተሰብ ጋር ሄዶ መልዕክት መላክ ወይም መጠየቅ የሚፈቀድበትን ወቅት ጠብቆ መሄድ።
ተሜ በዝዋይ ከሌሎች እስረኞች በተለየ ብዙ ማእቀቦች ተጥሎበት እየኖረ የመንፈሱ ጥንካሬ የሚገርም ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አራት ፅሁፎችን አስነብቦናል። በእስሩ ወቅት ስላገኛቸው የኢትዮጵያ ሶማሌዎች የሚተርክ በሁለት ክፍል “የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና ከዝዋይ እስር ቤት” እንዲሁም አሁን በኦሮሚያ ስለተነሳው ሕዝባዊ አመፅ የጻፈው “ሁለተኛው ምዕራፍ” የሚሉት ጽሑፎች ይገኙበታል።
ከዓመት በፊት በላከው በአንደኛው ጽሑፉ እንዲህ ይላል “…ግና! ይህ መንግሥታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ሕዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡”
ተሜ እንደቃሉ ጉዞውን እስከቀራኒዮ ያደረገ ጋዜጠኛ ነው። አንድ ዓመት ከአምስት ወር በእስር አሳልፏል። የሚወጣበት ቀን እየቀረበ ነው እንጂ እየራቀ አይደለም የሚሄደው። በቀሪዎቹ ጊዜዎች እና ከወጣ በኋላ በብዕሩ የሚያካፍለንን የኢሕአዴግ መንግሥት ገበናዎች ለማንበብ በጣም ነው የምጓጓው። ተሜ ከዚህ በፊት በብዙ ኮፒ ታትሞ ለገበያ ያበቃው “የመለስ አምልኮ” የተሰኘው መጽሐፍ ተወዳጅነትን አትርፎለታል። በ2007 መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ከሙያ ባልደረቦቹ እና ከጋዜጠኛ እስክንድር ጋር (ከቃሊቲ እስር ቤት) በአንድነት በተለያየ ጊዜ የተጻፉ ጽሑፎችን በመጽሐፍ መልክ ታትሟል።

Temesgen Dessalegn with his foster children.
ተመስገን ደሳለኝ ከጋዜጠኝነት ሥራው በተጨማሪ ያለውን በማካፈል ይታወቃል። ለጓደኞቹ እና ለወዳጆቹ በችግራቸው ጊዜ ከጎናቸው ሆኖ ለመርዳት የሚችለውን ያደርጋል። በምስሉ ላይ ከተሜ ጋር የሚታዩት ሕፃናት ቤተሰቦቻቸው አቅመ ደካማ በመሆናቸው ወጪያቸውን በመሸፈን የሚረዳቸው ናቸው። ወጪያቸውን ከመሸፈን ባለፈም ባለው ትርፍ ሰዓት ያዝናናቸው፤ እንዲሁም በቋሚነት የሚማሩበት ት/ቤት በመሄድ የትምህርት ሁኔታቸውን ይከታተል ነበር። አሁን ጊዜው ተገልብጦ እነዚህ ህፃናት በወር አንድ ጊዜ ከእናቱ እና ወንድሙ ጋር በመሆን ዝዋይ ድረስ ሄደው ይጠይቁታል።
በነገራችን ላይ ተሜ እነዚህን ሕፃናት እና ቤተሰቡን እንደሚያስተዳድር ለፍ/ቤት ቢገልፅ የቅጣት ፍርዱ ይቀንስለት ነበር። ሆኖም ተሜ ጥፋት ስላላጠፋሁ አቅልሉልኝ ብዬ አልጠይቅም ብሎ ምንም አይነት ማቅለያ ሳያስገባ ነው 3 ዓመት የተፈረደበት።
ብርታትና ጥንካሬን ለተሜ እና ቤተሰቦቹ እየተመኘሁ ተሜን በጨረፍታዬን በዚሁ ላብቃ።
Filed in: Amharic