>
5:13 pm - Friday April 20, 4096

COINTELPRO: ተቃዋሚዎችን የመከፋፈያ ቀላል ዘዴ (ከአሜሪካ የተኮረጀ) [በበፍቃዱ ኃይሉ]

*** ይህንን ባለፈው በእንግሊዝኛ ጽፌው «በአማርኛ እና በኦሮምኛ ብትተረጉመው ጥሩ ነው» ተብዬ ነበር። በአማርኛ ይኸው፤ አፋን ኦሮሞ የምትችሉ ተርጉሙት።) ***

BefeQadu Z. Hailuጋዜጠኛ ‪#‎እስክንድር_ነጋ‬ ነበር የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ልጠይቀው ቃሊቲ እስር ቤት ስሄድ ኮኢንቴልፕሮ (COINTELPRO) ስለሚባለው ነገር መጀመሪያ የነገረኝ። ቃሉ የአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ካውንተር ኢንተሊጀንስ ፕሮግራም ባጭሩ ሲጻፍ የተፈጠረ ነው። ፕሮግራሙ ድብቅ፣ አንዳንዴ ሕገ ወጥ፣ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶችን የመሰለል፣ ውስጣቸው ሰርጎ የመግባት፣ ተአማኒነት የማሳጣት እና የማስተጓጎል ተከታታይ ፕሮግራም ነው። ይህንን ጉዳይ አሁን ማንሳት ያስፈለገኝ ሰማያዊ ፓርቲ፣ እንደብዙዎቹ ከጨዋታ ውጪ እንደተደረጉ ፓርቲዎች በፈተና ውስጥ እያለፈ በመሆኑና ይህም የተቀናጀ ሴራ ውጤት ሊሆን ይችላል ብዬ መጠርጠሬ ነው።

«ማጋለጥ፣ ማስተጓጎል፣ ተአማኒነት ማሳጣት፣ ዝም ማሰኘት አሊያም ማጥፋት» ~ በወቅቱ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር – ኤድጋር ሁቨር ለአንድ የኤፍቢአይ ኤጀንት የተሰጠ ትዕዛዝ ነው።

በዚህ መንገድ፣ ኤፍቢአይ በከፊልም ቢሆን የጥቁሮች የዕኩል መብት ጥያቄን፣ የፀረ-ቪየትናም ጦርነት እንቅስቃሴን እና ፀረ-ቅኝ ግዛት ድርጅቶችን አዳክሟል። በማልኮም ኤክስ እና በኤልያስ መሐመድ መካከል ያለውን አለመግባባት ኤፍቢአይ ማልኮም እንዲገደል በማድረግ ፕሮግራሙን ተጠቅሞበታል የሚሉ አሉ፤ ባይጠቀምበት እንኳ መረጃው እየደረሰው ዝም ብሏል።

በተመራማሪዎች እንደተሰበሰው ከሆነ፣ ኮኢንቴልፕሮ በመንግሥት ያልተፈለጉ እንቅስቃሴዎችን እና ድርጅቶችን የሚያስተጓጉልበት የተለያዩ ተግባራት (functions) እና ቅርፆች (forms) አሉት። ዴቪድ ካኒንንግሃም የዘረዘሩትን እነሆ፣

ተግባራት፣
1) መጥፎ ገፅታ መስጠት፤
2) ውስጣዊ አደረጃጀትን መሰባበር፤
3) በቡድኖች መካከል የርስበርስ ቅራኔ መፍጠር፤
4) ቡድኑ ለእንቅስቃሴው የሚረዱት ነገሮችን እንዳያገኝ መገደብ፤
5) የመቃወም አቅምን መገደብ፤
6) የተመረጡ ግለሰቦች እንቅስቃሴውን እንዳይቀላቀሉ ማድረግ፤
7) ግጭቶችን ማስቀየስ፤ እና
8) ስለላ ናቸው።

ቅርፆች
A) ምንጫቸው ያልታወቁ ደብዳቤዎች መላክ፤
B) በውሸት ማሕተም የተፈረመባቸውን ደብዳቤዎች መላክ፤
C) መጣጥፎችን ለብዙኃን መላክ፤
D) ለባለሥልጣናት መረጃ መስጠት፤
E) የውሸት ማስረጃ መቅበር፤
F) መረጃ ሰጪዎች መመልመል፤
G) ሚዲያዎችን መጠቀም፤
H) ኤፍቢአይ ያዘጋጃቸውን መረጃዎች ማሰራጨት፤
I) ለተመረጡ ሰዎች ቃለመጠይቅ ማድረግ፤
J) የተሳሳተ መረጃ መስጠት፤
K) የውሸት የስልክ ጥሪዎችን ማድረግ፤
L) ያለማቋረጥ ክትትልና ጥቃት ማድረግ፤
M) ለተቀናቃኞቻቸው ድጋፍ መስጠት፤ እና
N) ሥም አጥፊ መረጃዎችን መላክ።

(እነዚህ ሁሉ ተቃዋሚዎችን የማስተጓጎል ሙከራዎች በኢትዮጵያ ታይተዋል።)

የዚህ አጭር ማስታወሻ ዓላማ ዴሞክራሲያዊ የሆኑት አገሮች ሳይቀሩ ምን ያህል ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥፋት እንደሚጓዙ ማስረዳት ነው። ኮኢንቴልፕሮ ከኤፕሪል 1971 ጀምሮ፣ በተግባር 15 ዓመት ከቆየ በኋላ፣ በይፋ ተዘግቷል። ነገር ግን፣ እንደኢትዮጵያ ላሉት ጨቋኝ መንግሥታት ትምህርት ሰጥቶ አልፏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶች መንግሥታቸው እነዚህን ሴራዎች እንደሚሸርብባቸው አውቀው ግብረመልስ ካዘጋጁ [ብቻ] በትግሉ ያሸንፋሉ።

እንግሊዝኛውhttps://m.facebook.com/story.php…

Filed in: Amharic