>
5:13 pm - Wednesday April 19, 2175

የጓዳ ውስጥ ባሪያ እና የመስክ ላይ ባሪያ [ህይወት እምሻው]

Hiwot Emishaw(ይህ ፅሁፍ ከመጠነኛ ጭማሪ እና ቅናሽ በስተቀር ታዋቂው የጥቁር አሜሪካዊያን መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ በአንድ ወቅት ያደረገው ንግግር ትርጉም ነው ሊባል ይችላል)

ማልኮም ኤክስ በሰላሳ ዘጠኝ አመቱ በሰው እጅ ተገድሎ ከሞተ ሃምሳ አንድ አመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ንግግሩ ውስጥ ያለው ምሳሌ ግን ዛሬም ድረስ አለ፡፡

…እንግዲህ በአስከፊው የባሪያ ንግድ ዘመን ከአፍሪካ እንደ ከብድ እየተነዱ ወደ አሜሪካ ተወስደው በጥጥ እርሻ ላይ የተሰማሩ ባሪዎች ነበሩ፡፡ ባሪያዎች ሁሉ ግን አንድ አይነት አልነበሩም፡፡

በዘመኑ ሁለት አይነት ባሪያዎች ነበሩ- የጓዳ ውስጥ ባሪያ እና የመስክ ላይ ባሪያ፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ የሚኖረው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ጌታዬ›› እያለ ከሚያደገድግለት አሳዳሪው ጋር፡፡ ደህና ይለብሳል፡፡ ደህናም ይመገባል፡፡ ጌታው እግሩ ወጣ ሲል ለእርሱ የተዘጋጀውን ምግብ ስለሚቀላውጥ ደህና ምግብ ይመገባል፡፡

ከኩሽና ጥግ፣ መሬት ላይ ኩርምት ብሎ ቢተኛም የሚኖረው ግን ባሳዳሪው ጣሪያ ስር፣ ከጌታው ቤት፣ ከጌታው ጋር ነው፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ጌታውን ጌታው ራሱ ራሱን ከሚወደው በላይ አጥብቆ ይወዳል፡፡ የጌታውን ቤት ከመፍረስ ለመታደግ ከእሱ ቀድሞ አንገቱን ይሰጣል፡፡

ጌታው ‹‹እዩትማ ይሄን ቤታችንን…ግሩም ነው አይደል?!›› ብሎ የጠየቀ እንደሆን ፈጠን ብሎ ‹‹እንዴታ! ይሄ ቤታችንማ እጅግ ግሩም ነው!›› ብሎ ያሽቋልጣል፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ሁነኛ መለያም ይሄው ነው፡፡ ጌታው ‹‹እኛ›› ሲል ‹‹እኛ››፣ ‹‹የእኛ›› ሲል ‹‹የእኛ›› ይላል፡፡

ጌታው ታምሞ ባየ ጊዜ ‹‹ምነው ጌታዬ!? አመመን እንዴ?›› ብሎ በጭንቀት ይጠይቃል፡፡ አመመን እንዴ!

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ሕልውናውን ከጌታው ጋር ያቆራኘ ነው፡፡ ካለ ጌታው መኖርን ሊያስብ አይችልም፡፡ ያለ ጌታው አንድ ቀን የሚያድር አይመስለውም፡፡ ያለ ጌታው ፈቃድ ፀሃይ እሺ ብላ የምትወጣ፣ በጄ ብላ የምትጠልቅ አይመስለውም፡፡

እናም አንዱ የመረረው ወደ እሱ መጥቶ ‹‹…ይሄ ኑሮ አይደለም…! እባክህ ከዚህ እንጥፋ…እናምልጥ!›› ቢለው በመገረም አይቶት ‹‹አንተ ያምሃል እንዴ…?!ምንድነው እናምልጥ ማለት…?ከዚህ የተሻለ ቤት የት አገኛለሁ…?ከዚህ የተሻለ ልብስ ከየት አመጣለሁ…?ከዚህ የተሻለ ምግብስ የት አባቴ አገኛለሁ…?ሆ…ሆ…! እናምልጥ ይለኛል አንዴ?!›› ብሎ ይመልሳል፡፡

በተመሳሳይ የጥጥ እርሻ ፣የመስክ ላይ ባርያዎች ይኖራሉ፡፡ በቁጥር ሲሰላ የመስክ ላይ ባሮች ከጓዳ ውስጥ ባሪያዎች እጅግ ይልቃሉ፡፡

የመስክ ላይ ባሪያ ውራጅ ይለብሳል፡፡ የመስክ ላይ ባሪያ የጌታው እና የጓዳ ውስጥ ባሪያዎች ትርፍራፊን ይበላል፡፡ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ይኖራል፡፡ በዚህ ላይ፣ ከንጋት እስከ ውድቅት መባተሉ ሳያንስ ይደበደባል፡፡ ይቀጠቀጣል፡፡

ጌታውን ግን አጥብቆ ይጠላል፡፡ የጓዳ ውስጥ ባሪያ ጌታውን ሲያፈቅር፣ የመስክ ላይ ባሪያ ግን አምሮሮ ይጠላዋል፡፡

ብሩህ አእምሮ አለው፤ ምክንያቱም እንደእሱ ያሉ ባሪያዎች ከማንም በቁጥር እንደሚበልጡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

የመስክ ላይ ባሪያ፣ የጌታው ቤት በእሳት ሲያያዝ እግዜር የንፋሱን ጉልበት አንዲያበረታ ይፀልያል እንጂ በጭራሽ እሳቱን ለማጥፋት አይሞክርም፡፡

ጌታው ሲታመምም ‹‹አምላኬ ሆይ! ይሄንን ሰውዬ ዛሬ ገንድስልኝ!››እያለ እግዜርን ይማፀናል እንጂ አይጨነቅም፡፡

የመስክ ላይ ባሪያን ማንም ሰው መጥቶ ‹‹ከዚህ ቦታ እንጥፋ…ከዚህ ኑሮ እናምልጥ›› ቢለው፣ ፈጠን ብሎ ‹‹እሺ! እንሂድ…እናምልጥ! ከዚህ የማይሻል ቦታ የለም!›› ይላል እንጂ ፈፅሞ አያንገራግርም፡፡

…ይህ የማልኮም ኤክስ ምሳሌ ዛሬም፣ በእኛም ዓለም አለ፡፡

ዓለም ዛሬም የጓዳ እና የመስክ ላይ ባርያዎችን ይዛ ትኖራለች፡

Filed in: Amharic