>
5:13 pm - Monday April 20, 8116

ግልጽ ደብዳቤ ለኃይለ ማርያም ደሳለኝ [አቶ ኣሰፋ ጫቦ]

ግልጽ ደብዳቤ
ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ
ውድ ጠቅላይ ሚኒስቴር

Ato Assefa Chabo1. ይህን ደብዳቤ እንድጽፍልዎ ያስገደደኝ ዛሬ አገራችን የገባችበት ማጥ ነዉ። ከፖለቲካነትን ይልቅ የ ”እረ ምን ይሻላል!እረ ምን ይበጃል !” ደብዳቤ አድረገው ቢያዩልኝ ደስ ይለኛል።እንደመፍትሔ አፈላላጊ የአገር ሽማግሌ ድምፅ ሆኖ እንዲታይልኝ/ቢታይልኝ እወዳለህ። ነውም!! ”የጋራ ቤታችን” እንዲህ ማጥ ውስጥ ስትዘፍቅ የሚያይ አገር ወዳድ ሁሉ ድምጹን የማስማት ግዴታ ያለበት ወቅት ላይ ነን ብዬ አምናለሁ።ከፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ይልቅ የአገራችን የኢትዮጵያ መስነበት፤ ከዚያም “በነጻነትዋው ለዘላም ትኑር!” ማለት ይቅደም እንደማለት ነው። በደርግ ቋንቋ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እንደማለት!

2. ታዋቂዉና ዝነኛዉ የጥንቱ የቻይና ሊቅ ሱን ዡ(Sun Tzu )በ”የጦርነትጥበብ “ (The Art of War)መጽሐፉ ከጻፈው ጠቅሼ ብጀምር የሚሻል መስለኝ።
“..ጠላት ህን (የቃወመኛል የምትለውን )የምታውቅ ከሆነ ፤ደግሞም ራስክን የምታውቅ ከሆነ የግጥሚያ ወጤት ከቶም አያጠራጥርም::ሆኖም፤ራስክን ብቻ አውቀህ ጠላት ነው (ተቃዋሚ ነው) የምትለውን የማታውቅ ከሆነ አሸነፍኩ ባልክ ቁጥር ሽንፈትያጋጥመሀል።ከዚህ ውጭ ግን ራስክንም ጠላቴ (ተቃዋሚዬ የምተለውን )የማታዉቃቸው ከሆነ በገጠምክ ቁጥር ሽንፈት እጣህ ይሆናል”ይላል

3. ከነጉዳንጉዱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መንግስት ለማድረግ ሙከራ ያደርገ መንግስት ቢኖር ደርግ ብቻ ነበር ለማለት የምንችል ይመስለለኛል።የስልጣን መሠረቱ ብሔረሰብ አልነበረም።ያም ሆኖ የብሔረሰብ ጭቆና መኖሩን ተቀብሏል።ተቀብሎም በመላ- ምት ሳይሆን ጥናት ላይ በተመሠረት መፍትሔ ለመሻት ተንቀሳቅሷል። “የብሔረሰብ ጥናት ተቋም”(Institute)፤በምርጥ የኢዮጵያ ምሁራን የሚመራ፣ አቋቁሟል።የዚያ ጥናት ውጤት ሰባት የመፍትሔ አማራጮች ያቀፈ ነበር።በጊዚያዊነትም ቢሆን ከነዚህ አማራጮች አንዱን “የራስ ገዝ” የሚለውን በስራ አውሎ ኢትዮጵያን በዚያ ለማስተዳደር ሞክሯል።

4. ወያኔ/ኢሕአድግ ከዚህ የደርግ ጥናት ውስጥ ሰባተኛ የነበረውን አማራጭ ወስዶ አገሪቱን “ክልል” በሚል መጠሪያ ክልል አዋቀረ። ክልል ማለት በዚህኛው አገባቡ፣ለኔ፣”አጥር ታጠረ!” እንደማለት ነው።”ድርሽ ትልና! ድርሽ ትይና!” እንደማለት። ደርግ ለኃይለሥላሴ ሲል እንደነበረው “ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው” ይኸዉ ላለፈው አራት ወራት ቁርጡ ለይቶለት መፍረክክስ ጀመረ።መንግስትዎን ይህ ነገር” ወትሮ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ፤አሁን ምን ይባባል ድስትን ጥዶ ማልቀሰ!”ን አስታወሰኝ።በዚህ ላይ መንግስትዎ አሁንም ሐሳብ- ወለድ ጠላቶች ላይ ጣቱን መጠንቆሉን ቀጠለ። ያ የተለምደ ስለሆነ አይገርመኝም። ሆኖም አዲስ ኪዳን ውስጥ ያለ አንድ ነገር ያስታውስኛል።”ሌላው አይን ውስጥ ያለ ትቢያ ከመጠቆምህ በፊት አንተ አይን ውስጥ የተጋረጠውን ግንድ መጀመሪያ አስውግድ!” የሚለው ነው።

5. በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር።”ተከለለ” ማለት “ታጠረ” ማለትነው። ጋሞ “ካሎ” ይለዋል። ማስቃላ ከመድረሱ ወራት በፊት የከብቶች ማስማሪያ መሐሉ ላይ አንድ እንጨት ይተከላል። ያንን በምሳሌ ለማስረዳትልሞክር። ያ ቦታ/መስክ “ካሎ” ሆነ ማለት ነው። ያንን እንጨት መጀመሪያ የተከለው ባለስልጣን እስኪነቅለው ከብት ድርሽ አይልበትም። ጎሜ/ ኃጢአት ነው የሚሆነው። ወንጀል/እሽብርተኝነት እንድምትሉት! ጋሞ ውስጥ ካሎ አይጣስም። ምክንያቱም ቀላል ነው። ሕዝቡ የተቀበለው፣ለዘመናትም ተቀብሎት የኖረው፤ እምነቱ ፤ንብረቱ ስለሆነ ነው።

6. ዛሬ በአገሬ፤በኢትዮጵያ፣ያለው በግሪክ ተረታ-ተረት(Mythology)ያለውን የፓንዶራን ሙዳይ(Pandora Box ) ያስታውሰኛል። አማልክት እንደምርቃት/ እርግማን ሙዳይዋን በአለም ላይ በሚገኙ ክፋቶችና ተስፋ ሞልቶ ይስጣታል። ፓንዶራ ቸኩላ ስተከፍተው ክፋቶቹ ሁሉ በረው ወጡና እቡይ ስራቸውን ተያያዙት። ወያኔ በዚህ አዲስ የመንግስት አዋቃቀሩናን ሕግ መንግስቱ ያደረገው የፓንዶርን ሙዳይ እንደመክፈት መስሎ ይታየኛል። አንድ የሚያጽናናኝ ነጥብ ቢኖር ሙዳዩ ውስጥ አሁንም ተስፋ አለ።ወያኔ/ኢሕአድግ ብርታታትን፣ቅንንነትን፤”ለጋራ ቤታችን” ዘላቂነትን የሚፈልግ ቢሆን፤ይህችን ሙዳይዋ ውስጥ የተረፈቸውን ተስፋ አውጥቶ ተግባር ላይ ማዋል ብቻ ነው። የዚያን እለት፤በዚያ ወቅት ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃውሞ ሳይሆን በድጋፍ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይውጣል ብዬ አምናለሁ። እኔ ደግሞ በመሠረቱ ተስፋ መቁረጥ አላውቅበትም። ተስፋ የምቆርጥ ብሆን ይህንን ደብዳባቤ ባልጻፍኩም!!

7. ጠቅላይ ሚኒስቴር ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ፤የዛሬ ስንትና ስንት አመት በጻፍኩት ግልጽ ደብዳቤ አገሪቱን “አያድሩበት ቤት አያመሻሹበት አያደርጉት!” ብዬ ነበር።እርስዎን ደግሞ “ላለፈ ክርምት ቤት አይሰራም!” ለማለት እፈልጋለሁ። ያለፈው ክርምት ቤቱን ነካካው እንጅ አላፈራረውም፤ወይም ወደማፈራረስ አላቃረብውም ብዬ አምኜ ነው ይህንን ተረት የጠቀስኩት።እዚህ ተረት ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት ያለው፤ወይም አንድምታው “ያለፈው ክረምት ያናጋውን አይነት ቤት አይነትደግመህአትስራ!” የሚል ይመስለኛል። ማለትም እዚያ፤ያለፈው ክረምት ቤት አወቃቀር ላይ/ውስጥ የነበርውን ደካማ ጎን አትድግመው ነው። ማለትም “ካለፈው የግንባታ ስህተት ተማር!” ነው።

8. ከሆነደግሞየግንባታው ስህተት ምን ነበር? ዙሪውን ላለመምዞር ስህተቱ ሕገ መንግስቱ ነው! ስህተቱ ኢትዮጵያን በክልል ማዋቀሩ፤በብሔረ ሰብ ማዋቀሩ ነው!!

9. ኢትዮጵያን በብሔረሰብ ሲዋቅር ወያኔ የመጀመሪያ አልነበረም።በ1928 ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን፤የሙሶሉኒ አወቃቀር በብሔረሰብ ላይ የተመሠረት ነበር። “የጣሊይን የምስራቅ አፍሪካ ግዛት! (Africa Orientale Italiana” ይለዋል።ከ19ኛው ምእተ አመት ጀምሮ ብዙ የጣሊያን “ሊቃውንት” ያጠኑት ጥናት ውጤት መሆኑ ነበር። የጥናታቸው ውጤት ኢትዮጵያን በጎሳ በመክፋፈል እርስ በርሳቸው ማናቆርና እነሱ ሲባሉ እኛ አርፈን መግዛት ነው የሚል ነበር። ታሪክ እንደሚነግረን የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ተባብሮ፤ዱር-ገደል ገብቶ ጣሊያንን አዋርዶ አባረረው።እንግሊዝም በሰሜን በኩል የትግራይ- ትግሪኝን በምስራቅ በኩል የታላቂትዋን ሶማሌ መርዝ ቀበረች/ረጨች። ባጭሩ ይህ በብሔረሰብ መከፋፋል ከጠላቶቻችን የመጣ በመሆኑ ሞዴል አድርገን ልንቀበለው ከቶም አይገባም ለማለት ነው። ይህም ማለት ለአዲሱ፤መጭው ክርምት፣ የሚሰራው ቤት በጠላቶቻችን ንድፍ ላይ የተመሠረት ሳይሆን በኢትዮጵያ እሴት፤በኢትዮጵያ እውነት ላይ መሆን አለበት ለማለት ነው። መሠረቱ፤ጣሪያ ፤ግርግዳው፤ታዛው የኛው ይሁን ነው። ዞር-ዞር ብሎ የማየት እንጅ ታሪካዊ እሴት ሞልቶ የተረፈን አገር ነን።።ከልቤ ነው የምልዎት!!

10. ደርግን “ከነጉዳንጉዱ”ብዬ ነበር የገልጽኩት። ለጊዜው ለተነሳሁበት ጉዳይ ሲባል ጉዳንጉዱን ልተወውና በጎ ጎናቹ ሊባሉ ከሚችሉት ጥቂቱን ልጥቀስ።ከሁሉ ሁሌ ቁልጭ ብለው ከሚታዩኝ ውስጥ አብዮት አደባባይ ስልፍ በተደረገ ቁጥር ከደርግ ሊቃናተ መንበሮችት በስተቀኝ ጳትሪያርኩ አቡነ ተክለሐይማኖት፤ከግራ ሐጂ ያሲን የክበር ቦታ ይዘው ተቀመጠው የማየውነበር።በኢትዮጵያ ምድር የእምነት እኩለነት ለማየት ሲያልም ለነበረ እስልምና እንዲህ የክብር ቦታ አግኝቶ በአደባባይ ከማየት የተሻለ የሚያረካ ወቅት ይኖራል ብዬ አልገምትም።ክዚያም መስከርም 12ትን አረፋ፤ታህሳስ 13ትን መውሊድ፣ሰኔ29ንረመዳን ብሔራዊ በአል አድርጎ የደነገገዉ ደርግ ነበር።

11. የካቲቲ 25/1967 የገጠር መሬት አዋጅና የትርፍ ቤቶችና የከተማ ቦታ አዋጅ ሌላው የሚጠቀስ ነበር። የነዚህ አዋጆች ትርጉም “መሬት ለአራሽ/ለባለቤቱ የከተማ መኖሪያ ቤትን አናሳ ገቢ ያልቸው ጭምር ተከራይተው እንዲኖሩ ማደርግ ነበር። ደርግ ወያኔን ጉድፉን አጥርቶ፤መንገዱን ጠራርጎና ዘርግቶ ጠበቀው ልንል የምንችል ይመስለኛል።ወያኔን ከጥቂት ማሻሻል/በስተቀር “ግፋ በለው!” ብቻ ነበር የሚጠበቀው። ታዲያ ምን ሆነ?

12. ከዚያ የሆነውን እርስዎ ደጋግመውከተናገሩት አንዱን ብቻ ወስጄ ለመግለጽ እንድሞክር ይፈቀድልኝል።ቃል-በቃል ባልጠቅስዎትም”መንግስታችን የኪራይ ስብሳቢ መንግስት ሆነ!” አሉ። እኔም ልሁን ማንኛውም ተቃዋሚ ወይም መንግስትዎ አሸባሪ የሚላቸዉምቢሆኑ ይህንን መንግስት ከዚህ፣እርስዎከገለጹት በተሻለ ሊገልጡት የሚቻላቸው አይመስለኝም።

13. ለመሆኑ እኒህ ኪራይ ሰብሳቢዎቹ እነማንናቸዉ? የሚያከራዩት ምንን/ማንን ነው?ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል።ብቻ የሚያከራዩት ቢኖር ነው አከራይተው ኪራይ የሚሰበስቡት። ይህ ደግሞ ራሱን በራሱ ገላጭ እውነት ነው።ከሆነ ደግሞ የሚያከራዩት ኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵያን መሬትና ቤት መሆኑ ነው። ተሳስቼም ከሆነ ልታረም ፈቃደኛ ነኝ።ልማት በሚባል ታላቅ አሳሳች ቃል ስር ዛሬ ብር ወይም ጉልበት ያለው የፈለገውን ያክል የገጠር መሬትና ቦታ ማግኘት እንደሚችል መንግስትዎ በአደባባይ የሚናገረውና አስፈጻሚ አዋጅም ያወጣለት ነው። በቅርቡ ያነበብኩት አንድ የአፈሪቃ የባለሚልዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ገረሞኝነበር። ባለሚሊዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የአንደኝነት ስፍራ ይዘዋል። አሁን አንደኝነታችን በረዥም ሩጫ ብቻ ሳይሆን በዶላር ጭመር መሆኑ ነዉ/ሆነ።እንደኢትዮጵያዊነቴ በዚህ ልኩራበት ወይስ ልፈረበት? ይህ ሁሉ የተቻለዉን ‘በሕጉ’ መሠረት ባለመሬቶቹ ከመሬትና ቤት ንብረታቸው ተነቅለው ተጥለው ነው። የመሬት ለራሹ አዋጅ መሬት ለኪራይ ስብሳቢ በሚል አዋጅ የተተካ አይመስሎትም?የእስልምና ተከታዮችም ከብዛታቸው የተነሳ ስማቸውን ልጠራ የማልችለውን ወህኒ ቤት ሞለትውታል።

14. በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የተሰየመ አነሰም በዛ የመቶ አመት ታሪክ አለ።ይህም ማእከላዊ መንግስት የላላበት፤የአካባቢ መሳፍንት የነገሱበት ዘመን ማለት ነው። ግዛቱን ለማሳፋት፤ወይም ጉልብቱን ለማሳየት፤ወይም እኔ ካንተ በናቴም ባባቴም እብልጣለሁ በሚል ሰበብ አስባብ ጦርነት የሚከፋፈቱበት፤ ሚስኪኑ ኢትዮጵያዊ የሚያልቅበት ዘመን ነበር። ያንን ዘመን በር-ቀዳጅ የአድዋው ስሑልሚካኤልነበሩ።

15. ከዚያ ያለው እንደገና የመእከላዊ መንግስት መመስረት፤ወይም ግዛት ማሳፋት ዘመንነበር።የዚህ አይነት ብሔራዊ መንግስት የመመስረት ሂደት(The Formation of National State) የሰው ልጅ ታሪክ ወጥ አካልነዉ። ከነክፋቱ!! የአሁንዋ/የዛሬይቱ ኢትዮጵያም የዚያ ወጤት ነች። አሁን ከ120 አመት በላይ ሆኖታል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ኢትዮጵያ በሚባለው አገር ታይቶ ተስምቶ የማይታውቅ የብሔረሰብ አነባበሮ ተፈጥሯል። በዚህም 120 አመታት ውስጥ መጋባት፤መገባባት፣መግባባትና መዋለድ ብቻ ሳይሆን አብሮ የመኖርና የመቻቻል ስነ ልቦና(Psychological make up) ተፈጥሯል።

16. የህንን የወያኔ የክልል መንግስት የታሪክና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ነገ ሲተነትኑት ዘመን መሳፍንት ዳግማዊ የሚሉት ይመስለኛል። በአገር ደርጃ ወደፊት መራመድ ራሱ ከባድ መሆኑን ይሔው የምታዩት ነው።200 አመት ወደኋላ ለመውሰድ መሞከር ግን የጤና አይመስለኝም። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ዩጎዝላቢያ ይባል የነበረው አገር ህዝብ አይነት አይደለም። ያ ሕዝብና መንግስት እንደዚያ የተፈረካከሰው የዛሬ 500አመት በፊት የሆነ የታሪክ በደል በማንዠጉና አላምጦ ባለመዋጡ ነበር።ቱርክም፤ሊባኖስም፤ሶሪያም፤ኢራቅም አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቂም በቀል ፤የነበረ ያልነበረ የሚያመንዥግ ህዝብ አይደለም። አላምጦ ውጦ የታሪኩ አካል አድርጎ ወደፊት የሚራመድ ታላቅ “ይቅር ለግዜር!!” ተባባይ ህዝብ ነው። የታላላቅ እመነቶቹም ሆነ የባሕላዊ እመነቶቹ መሠረቱ ይሔው ነው።

17. የእስልምና እምነት በአላት በደርግ ዘመን ወደብሔራዊው በአልነት መሸጋገራቸውን አንስቼነበር።አሁን በወያኔ ኢሐአድግ ዘመን ደግሞ ምን እንደደርሰባቸውና በመድረስ ላይ እንዳሉ የሚያዉቁትና መላው አለምም የሚያዉቀው ስለሆነ ዝርዘሩ ውስጥ አለገባም። አንድ ነገር ብቻ ላስታውስዎት እወዳለሁ።ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት የመለስ ዜናውን “የመጨረሻ ኑዛዜ” ያንብቡ።ኑዛዜ ያልኩት ከማረፋቸው (ማረፋችን?)አንድ ይሁን ሁለት ወር በፊት ያደርጉት የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባዔነው።ይህንን ሚስጥራዊ ቃለ ጉባዔ ያነበብኩት ድሕረገጾች ላይ ተልጥፎ ነበር። ማመን ነበር ያቃተኝ!! ወይም አንድ ሰው “የመጨረሻው ደውል” እንደተደውለለት ሲያውቅ “እውነቱን ተናግሬ ልሙት!” ያሰኘዋል ይሉናል።በዚያ ስበስባ ላይ የአቶ መለስ አስተያየት ከማውቃቸውና ከሚታውቁበት መለስ ለየት ያሉ ነበር። እውነት ብቻ ሳይሆን የሚስጥር እውነት ነበር።ይህ እውነት የመጀመሪያቸውም የመጨረሻቸውም ነበር ብዬ እገምታለሁ።

18. አቶ መለስ ያሉት ቢጨመቅ” የህንን የእስልምና እምነት ችግር የቀየሰነውና የፈጠርነው እኛው (መንግስት) ስለሆንን ከዚህ በኋላ ይወገድ!” የሚል ይሆነል። የተቃወመ ሰው ቢኖር አንድ ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም የሚባሉ ነበሩ። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ መደገፍ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን አውግዘውና ይህንን ወሳኔ አድምቀው፤አክርረው ደግፈዋል። ያም ሆኖ የእስልምና እምነት ተከታዩች ዛሬም አክራሪ ይሁን አሸባሪ (ልዩነት አለልገባኝም የገባውም ሰውም አላገኘሁም) በሚል እንደታጎሩ፤ያልታጎሩትም “ማነህ ባለ ሳምንት!”ንበመጠባበቅ እንደተስቀቁ ናቸውና እባክዎን የአቶ መለሰን ኑዛዜ ስራ ላይ ያዉሉት።ከዚያ የተሻለ መፍትሔ የለምም!!

19. ይህንን ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መለሰ ዜናዊ አንዴ ከተናገሩት ጠቅሼ ማጠቃለል ፈለግህ።መለስ፤ በሆነ አጋጣሚ (ረስቸዋለሁ) በሩም መስኮቱም ከተዘጋ ህዝቡ ግድግዳውን ሰብሮም ቢሆን ይወጣል ነበር ያሉት። ቃለ በቃል መጥቀሴ ሳይሆን መነፈሱ ይሔው ነበር። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚታየው ቃል በቃል ይሔው መሆኑ የሚያከራክር አይመስልኝም። በምድር ላይ የምታየውማስረጃ ይሔው ነው። በሰነዶች ላይ የሚታየው ይሔው ነው። ተቃዋሚዎች፣ መንግስት ግን አክራሪ ወይም አሸባሪ የሚላቸውም፣ የሚናገሩት ይህንኑ ነው።አገርና አለም አቀፍ የሰብአበዊ መብት ተሟጋች አካላትም የሚሉት ይህንኑ ነው። እርስዎም በተደጋጋሚ በሚያደርጉት ንግግ ር የሚሉት መንፈሱ ሲነጠር ይሕንኑ ይመስላል።

20. ይህ ሁሉ ሲሰባሰብ አንድ እውነት የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህንን ወያኔ/ ኢሕአድግ ልማት/ እድገት ያለውን ሕዝቡ አልተቀበለውም።ይህንን ወያኔ/ኢሕአድግ መቶ-ከመቶ(100%) ድምጽ አግንቼ ምርጫ አሸንፊያለሁ ያለው ውሸት መሆኑ ነው። ውሸትም ባይሆን ትላንት መቶ-ከመቶ (100%) የደገፈ በማግስቱ መቶ-ለመቶ ፈንቅሎ አይነሳበትም ነበራ!ወደ ህዝቡ መግቢያ ሸፋን እንዲሆኑ የተፈጠሩት ለምሳሌም እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲዪ ድርጅት የተባለውን ሽፋን መስጠት ቀርቶ ራሳቸው የሚሸፈኑበት ያጡ መሆናቸውም እውነት ነው።”አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ያገላብጣል”ን አስታወሰኝ።እዚህ ያለነሳሁትን ሌሎች ማስረጃዎች ሰብሰብ አድርገን ብናበራያቸው ይህ ወያኔ/ኢሕአድግ ያመጣው ስረአት አልሰራም ማለት ነው።”ለማንም አልለበጀ!” ሆኗል እንደማለት ነው።አድሮ ከዋለ ደግሞ ካደረሰው በላይ ዘላቂና ጠላቂ ጉዳት ያመጣል የሚል ብርቱ ፍርሐት አለኝ።

21. እንደኔ እንደኔ መፍትሔው፤መውጫው ችግሩን በድፍረት ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው። አውቃለሁ! መጋፈጡ እንዲህ ቀላል አይመስለኝም! ድፍርቱም ብልሐቱም ላይኖር ይችላል። ያም ሆኖ ግን አማራጩ፤ማለትም አድሮ ውሎ ጊዜ ይፈተዋል በሚል የሚሰጥ የመተነፈሻ ጊዘ መግዣ ምክንያት መደርደር የሚጸጽት አማራጭ ይፈጥራል።

22. ትላንትና ያደመጥኩትን አንድ ነገር ልጨምር ፈለግህ::ከሶቪየት ህብረት ዘመን ጀምሮ ሩሲያን የሚውቁ፤አሁን ጡራት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኛ አን ጋረለስ (Anne Garreles)ሰሞኑን Public Broadcasting System(PBS) በተባለ ራዲዮ ጣቢያ Fresh Air በሚባል ፕሮግራም ላይ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። ለቃለ መጠይቁ ዋንኛ ምክንያኛት የፑቲን አገር (Putin Country ) የሚል መጽሐፍ ደርሰው ስለነበር ነው።ቭላድሚር ፑቲን(Valmir Putin) የሩሲያ የአሁኑ ፕረዚዳንትናቸው። ጋረልስ በዚህ ምልልስ በዚያ አገር፣በሩሲያ፣ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካና ሁሉ ዘርፍ አቀፍ ንቅዘት ይዘርዝራሉ።የፑቲንን ጨምሮ! “ይህ ሁሉ ጉድ እያለ ሕዝቡ ፑቲንን እንዴት ያያል?” ለሚለው በሰጡት መልስ “ዛሬ በአለም ላይ ከሚገኙት መሪዎች ሁሉ በመላው የሀገሪቱ ህዝብ በጣም ተወዳጅነት ያለው መሪ ቢኖር ፑቲን ናቸዉ”አሉ።ምክንያቱን ሲጠይቁ “ከሳቸው በፊት የነበረውፕሬዝዳንት፣ቦሪስ የልሲን፣ሰካራም ከመሆኑም ሌላዘራፊም ነበር። ዝርፊያው እንደቀጠለ ሆኑ ፑቲን በአገራችን፤በሩሲያዊነታችን እንድንኮራ፣ እንድንኩራራ፣አፋችንን ሞልተን ሩሲውያን ነን ለመለት አበቃን!” የሚል መልስ ሰጡ።ቃለ ምልልሱን ከጠቀስኩት ጣቢያ ማድመጥ የሚችሉ ይመስለኛል።

23. ለኛም የምንኮራባት፤በጠፍ ጨረቃ ጥለን የማንፈጥጥባት፤እንደወጣን የማምንቀረርባት፤ለመመለስየምንናፍቃትኢትዮጵያንእንዲያስቡ፤እንዲያልሙ፣ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ በሙሉ መስራት ባይችሉ እንኳን ጠረግ ጠርግ እንዲደርጉ ከልብ እመኛለሁ።እመኝሎታለሁም!
ብርታ፤ብልሐትእመኝላችኋለሁ!ለአገሬምየተሻለውን፤የሚበጀውን፤የሚያምረውን፣ የሚዘልቀውንና የሚያዘልቀን እመኝላታለሁ!

ኢትዮጵያ በህሕዝቦችዋ ተብብር በነጻነትዋ ለዘለ ዓለም ትኑር!

ከአክብሮት ጋር
አስፋ ጫቦ
Corpus Christi,Texas USA
መጋቢት 8,2008

Filed in: Amharic