>
5:13 pm - Friday April 19, 0126

ጆሮ አይሰማው የለ! ኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታለች ተባለ!!! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

Artist Amsalu Gebrekidan photo from his facebook profileፋሽስት ጣሊያን 1888ዓ.ም. አድዋ ላይ ድባቅ መትተው ድል በመምታት የደረሰበትን ታላቅ ውርደትና ሽንፈት ለመበቀል አርባ ዓመታት ሙሉ ሲዘጋጅ ስንቅና ትጥቅ ሲያደራጅ ቆይቶ በ1928 ዓ.ም. ላይ ከታንክ (ብረት ለበስ ተሸከርካሪ) እስከ የጦር አውሮፕላን (በረርት) ድረስ በገፍ የታጠቀ ዘመናዊ የጦር ኃይል በማሰለፍ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ አደገኛ የመርዝ ጭስን ጨምሮ በስፋት በመጠቀም ድል አግኝቶ ኢትዮጵያን ለመውረር ቢችልም እናት አባቶቻችን ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለው በወቅቱ የተፈጠረው ዓለማቀፋዊ ሁኔታም ረድቶ ከአምስት ዓመታት በኋላ በ1933ዓ.ም. ከዚህ ወረራ ነጻነታችንን ልንቀዳጅ ችለናል፡፡
ብዙ ጊዜ በብዙኃን መገናኛዎች ስለ አምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራና በአርበኞቻችን ተጋድሎ ነጻነታችን ስለመመለሱ ሲነገር “ነጻነት ከተመለሰ በኋላ፣ ከነጻነት በኋላ” የሚለው አገላለጽ ብዙዎችን ሰዎች በቅኝ ግዛት እንደነበርንና ነጻ የወጣነውም ከቅኝ ግዛት እንደሆነ እንዲያስቡ ሲያደርጋቸው ይስተዋላል፡፡
ለሀገራችን ታሪክ በቂ ዕውቀት ግንዛቤ የሌለው ሰው እንዲህ ቢያስብ ብዙ የሚደንቅ ባልሆነ፡፡ ተምረናል በቂ ግንዛቤ አለን በሚሉ ሰዎች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ መያዙ ነው እንጅ አስገራሚው ነገር፡፡
ዘንድሮ ትዕዛዘዝ ተሰጥቷቸው በሚመስል ሁኔታ (እንደዛ ካልሆነ በስተቀር ነገሩ የሁሉም ቋንቋ ሊሆን እንደማይችል ስለገመትኩ ነው) የወያኔ አባል መሆናቸው በግልጽ የሚታወቁና እንዲሁም የምንጠረጥራቸው ሰዎች ይሄንን ዓመት በተለያየ አጋጣሚና በተለያየ መድረክ አጋጥሞኝ እንደሰማኋቸው ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ተገዝታ እንደነበር በሰፊው ማውራት ይዘዋል፡፡ እንደኔ ሁሉ ሌሎቻቹህንም እንዳጋጠማቹህ እገምታለሁ፡፡
ይሄንን አነጋገር በተመለከተ ከዚህ ሁኔታ በፊት የማስታውሰው ነገር ቢኖር ቆይቷል ከዓመታት በፊት ነው ምን ሆነ መሰላቹህ ከነጋሪተ ወግ (ከሬዲዮ) ጣቢያዎች የአየር ሰዓት ተከራይተው ዝግጅቶቻቸውን ከሚያቀርቡ ዝግጅቶች ስድስት ሻል ሻል ነቃ ነቃ ያሉ ሰዎች ሆነው በሚያዘጋጁትና በሚያቀርቡት ስሙን በማልጠቅሰው ከእሑድ በስተቀር በሁሉም የሳምንቱ ቀናት ዝግጅቶቻቸውን በትጋት በሚያቀርቡ ተወዳጅ ዝግጅት ላይ ያለ ሰው ነው ይህ ሰው ፒ.ኤች.ዲውን (ሊቀ ጥብናውን) እየሠራ ነበር አሁን ይያዝ አይያዝ እንጃ አላወኩም፡፡ ይህ ሰው ነው በአንድ የዓርብ ዝግጅቱ ላይ ከአንድ እንግዳው ጋራ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ስለነበረው የስፖርት (የፍን፤ ሲነበብ ን ትጠብቃለች) እንቅስቃሴ ሲያወሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከጣሊያን ቡድን ጋር ተጫውተው ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ስለመሸነፋቸው በሚያወሩበት ጊዜ ይሄው ሰው ምን ይላል መሰላቹህ “…ለነገሩ በቅኝ ግዛት ስር ሆነህ እነሱን ማሸነፍ ከባድ ነው!” የምትል ቃል ይናገራል፡፡
እኔ በወቅቱ ይህ አነጋገሩ ምን እንዳለ በሚገባ ሳያጤነው ካፍ አምልጦት ተሳስቶ የተናገረው ቃል መስሎኝ ለሌላ ጊዜ ከአቅሉ ጋር ሆኖ እንዲያወራ ለማሳሰብ ፈልጌ ወዲያው በስቱዲዮ (በመከወኛ ክፍል) ስልክ እሱን ለማግኘት በተደጋጋሚ ብደውልም ላገኘው ሳልችል ቀረሁ፡፡
በብዙኃን መገናኛዎቻችን በጣም ከባባድ ስሕተቶች እንደሚፈጸሙ በተለይም የአየር ሰዓት ተከራይተው በሚሠሩት ሳይሆን “የመንግሥት” ጋዜጠኞች የሚባሉት በሚያዘጋጇቸው ዝግጅቶች ሆን ተብሎ የወያኔን ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል በስፋት እንደሚፈጸም ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አውቀው ስለሚያጠፉም እንዲታረሙ መሞከር ከንቱ መድከም ነው ብዙ ሞክሬ ስላየሁት ነው፡፡ “ታዲያ እነኝህን ለምን እርማት እንዲወስዱ ለማሳሰብ ፈለክ?” ብትሉኝ ምክንያቴ እነዚህኞቹ እንደ “የመንግሥት” ጋዜጠኞች ለአገዛዙ ጥቅም ሲባል እንዲያብሉ፣ እንዲቀጥፉ፣ እንዲያጠፉ፣ ሐሰቱን እውነት እውነቱን ሐሰት፣ የሌለውን ያለ ያልነበረውን የነበረ አድርገው እንዲያወሩ እንደማይገደዱ የራሳቸውን ነጻ ሐሳብ ብቻ አስተናግደው እንደሚወጡ ስለሚያወሩ “ይሄ ከሆነ” በሚል ነው፡፡
እናም ያንን ቀን የዕለቱ ዝግጅታቸው አልቆ እንደወጡ ለዚህ ሰው በግል ስልኩ ደወልኩለት፡፡ ከዚህ ቀደምም በሚያቀርቧቸው ዝግጅቶች ላይ አንዳንድ ነገሮች ሲኖሩ እየደወልኩ አንዳንድ እርማቶችንና አስተያየቶችን ስለምነግራቸው የሆነ ነገር ልነግረው ፈልጌ እንደደወልኩ ገባው መሰለኝ ደጋግሜ ብደውልም ሊያነሣልኝ ሳይችል ቀረ፡፡
ለባልደረባው ደወልኩ፡፡ ከሱ ጋር አወራን፡፡ ለካ ይህ ሰው ያንን ቃል የተናገረው ተሳስቶ ካፉ አምልጦት ሳይሆን አምኖበት የተናገረው ነገር ኖሯል፡፡ ባልደረባው ምን ይለኛል “አዎ አምሳሉ ልክ ነህ ነገር ግን ሀገራችን በቅኝ አገዛዝ ሁኔታ አላለፈችም ማለት ይቻላል?” ሲል መለሶ ጠየቀኝ፡፡ እኔም በፍጹም በፍጹም እንዳላለፈች ፋሽስት ጣሊያን የጭካኔ ድርጊትና ግፍ ፈጸመ ማለት ቅኝ ግዛት ገዛ ማለት እንዳልሆነ፣ የቅኝ ግዛትንና የወረራን ልዩነት፣ የአምስት ዓመቱ ወረራ ወረራ የተባለበትና ቅኝ ግዛት ያልተባለባቸውን ምክንያቶች እየጠቀስኩ አወራንና ተማመንን፡፡ ይሄንኑ ጉዳይም ለባልደረባው እንዲነግረውና እንዲታረም እንዲያደርገውም አደራ ብየው ተለያየን፡፡ ነገር ግን ቀልቤ ሊያርፍልኝ ስላልቻለ እኔው እራሴ ልነግረው በማሰብ ያንን ሰሞን ስልኩን ብቀጠቅጥም ሊያነሣልኝ ሳይችል ቀረ፡፡
አሁን ደግሞ ከስንት ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት ጥቅምት 2008ዓ.ም. ላይ ሌላኛው ባልደረባቸው በአንድ የመጽሐፍ መገምገሚያ መድረክ ላይ “ባይተዋሩ ንጉሥ” በሚል ርእስ የተተረጎመውን የዐፄ ኃይለሥላሴ ወጥ ቤት ሠራተኛና ኃላፊ የነበረ ኸርበርት ፎክ የተባለ አውሮፓዊ መጽሐፍ እንዲሔስ (እንዲሔስ ማለት እንኳን ይከብዳል) የመወያያ ሐሳብ እንዲያቀርብና እኛም ተወያዮችም የየራሳችንን ዕይታ እንድናወራ በተደረገበት መድረክ ላይ ያለ አንዳች መሸማቀቅ ኢትዮጵያ ቅኝ እንደተገዛች አድርጎ አውርቶ ቁጭ አይልም መሰላቹህ!
ቦግ አለብኝ በጣም ተበሳጨሁ እንደምንም ዕድሉ እስኪሰጠኝ ድረስ ታግሸ ቆየሁ፡፡ ዕድሉ ሲሰጠኝ የተሻለ የንባብ ልምድና በሳል ዕይታ ያለው ይመስለኝ እንደነበር፣ ይሄ ሳይሆን በመቅረቱና ይሄንን የተሳሳተ አባባል በመናገሩ ማዘኔን ገልጨ ሀገራችን በፍጹም በፍጹም ቅኝ እንዳልተገዛችና የነበረው ነገር ከወረራ ሁኔታ አልፎ ወደ ቅኝ ግዛት ደረጃ እንዳልተሸጋገረ የመሸጋገር አቅምም እንዳልነበረው ቅኝ ተገዝተናል ሊባል ይችል የነበረው አንድ ሁለት ሦስት ብየ በመጥቀስ እነኝህ ነጥቦች ተሟልተው ቢሆን እንደነበር ጠቅሸ መሳሳቱን ተናገርኩ፡፡
እሱም ምላሽ እንዲሰጥ ዕድሉ ሲሰጠው መሳሳቱን እንደተገነዘበ ገልጾ ስሕተቱ የተፈጠረውም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ስላልነበረው እንደሆነ ተናገረ፡፡ እኔ መስሎኝ የተበረው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው የራሱ ጠንካራ የመከራከሪያ ሐሳቦች ቢኖሩት ነውና እንሟገታለን ብየ ጠብቄ ይሄ ሳይሆን በመቅረቱና ይሄንን በሚያህል ብሔራዊ ጉዳይ ላይ የሀገርንና የሕዝቧን ክብር ሊያዋርድ በሚችል መልኩ ያልሆነ ነገር በግምት ለመናገር በመድፈሩ ይባስኑ አናደደኝ፡፡
አሁን ይንን ጉዳይ እንድጽፍበት ያስገደደኝም ከሱ በኋላ በአዋጅ “በሉ” እንደተባሉ ሁሉ ሲጠየቁ ምን እንደሚመልሱ የማያውቁ ይሄንን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ግለሰቦች በተለያየ ቦታ በገፍ ስላጋጠሙኝና ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ነው፡፡
የአምስት ዓመቱን ፋሽስት ጣሊያን ቆይታ ወረራ እንጅ የቅኝ ግዛት እንዳልነበረ የሚያረጋግጡ ነጥቦች ምን ምን ናቸው?
1. ሀገሪቱ የራሷ የሆነው መንግሥታዊ አስተዳደር ተወግዶ ጠፍቶ ፈርሶ ተደምስሶ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ቅኝ ለመግዛት በመጣው ኃይል አገዛዝ ወይም አሥተዳደር ቁጥጥር ስር የነበረች ብትሆን ኖሮ፡፡
2. ሠራዊቱ እንዲሁም ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ እጅ ሰጥቶ ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቶ ባርነትን አምኖ የተቀበለ ቢሆን ኖሮ፡፡
3. ወራሪው ኃይል ሕዝቡን ሴት ከወንድ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል በጅምላና በገፍ ያለምንም ክፍያ በግዳጅ ሥራዎች ላይ ማሠራት ቢችል ኖሮ፡፡
4. ወራሪው ኃይል ያለ ከልካይ የሀገሪቱን የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ሀብት እንደፈለገ ማጋዝ መበዝበዝ የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፡፡ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
እነኝህ ጉዳዮች ቢፈጸሙ ኖሮ በርግጥም ሀገሪቱ በቅኝ ግዛት ስር ነበረች ማለች ይቻል ነበር፡፡ ማንም እንደሚያውቀው ሁሉ እነኝህ ሁኔታዎች ተፈጻሚ አልሆኑም አልተደረጉም፡፡ ስላልተፈጸሙም ነው ዓለም ሀገራችን ኢትዮጵያን “በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ነጻ አፍሪካዊት ሀገር” ሲል ዕውቅና ሰጥቶ የሽዎች ዓመታት የነጻነት ታሪክ ያላት ሀገር በመሆኗ የምትታወቀው፡፡
Amsalu Gebrekidan Articleከአፍሪካ ብቸኛዋ ስል መጥራቴ ብዙዎች በስሕተት እንደሚሉት ላይቤሪያ ነጻ ሀገር ስላልሆነች ነው፡፡ ሀገሪቱን የመሠረቷት ከሰሜን አሜሪካና ከካሪቢያን ሀገራት ከባርነት የተመለሱና ከእነሱ ቢወለዱም በኋላ በአሜሪካ በወጣው ሕግ መሠረት ልጆቻቸው ባሪያ ሳይሆኑ ነጻ ናቸው የተባሉት ልጆቻቸው በቅኝ ገዥነት ነው እንደ እ.ኤ.አ. በ1822ዓ.ም. የመሠረቷት፡፡ ሀገሪቱ በአሜሪካ መንግሥት ጥበቃና ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ ይሄ በመሆኑ አውሮፓውያን ላይቤሪያን የአሜሪካ ይዞታ እንደሆነች በመቀበላቸው በቅኝ በመዳፋቸው እንዳትወድቅ አድርጓታል፡፡ በ1847 ከባርነት ነጻ ከሆኑ ጥቁር ቅኝ ገዥዎች ነጻ ወጣች ተብሎ ነጻነቷ ቢታወጅም እስከ 1980 እ.ኤ.አ. ድረስ ከእነዚህ አናሳ ከባርነት ነጻ ከሆኑ ጥቁር ቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ስር ነጻ አልሆነችም ነበር፡፡ በመሆኑም ላይቤሪያ እንደነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር መቁጠር አይቻልም ማለት ነው፡፡
እናም ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ባልተፈጸሙበት ሁኔታ ነገራችን በቅኝ ተገዝታለች ማለት በጣም ስሕተት ነው፡፡ እያንዳንዳቸውን ነጥቦች ዕንይ ካልን እርግጥ ነው አዎ የሀገሪቱ መንግሥት በመቀመጫው አዲስ አበባ ላይ አልበረም፡፡ መሪዋና ሌሎች ባለሥልጣናት ለአቤቱታ ወደ አውሮፓ ቢሔዱም በወረራው ምክንያት የሀገሪቱ መንግሥት መቀመጫውን ከአዲስ አበባ ወደ ጎሬ አዛወረ እንጅ አልፈረሰም አልጠፋም፡፡
ወደ ሁለተኛው ነጥብ ስንሻገር እርግጥ ነው ሠራዊቱ ፈርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ሠራዊቱ በመፍረሱ ምክንያት መደበኛ ጦርነት ማድረግ ባይችልም በየቦታው በጎበዝ አለቃው እየተመራ ኢመደበኛ ውጊያ በማድረግ ለወራሪው ኃይል ይበልጥ አስቸጋሪና አደገኛ ሆኖ የወጣበት ከዚህም የተነሣ ወራሪው በከተሞች ብቻ ለመወሰን የተገደደበት ገጠሩና ሰፊው የሀገራችን ክፍል ግን በአርበኞች ቁጥጥር ስር የነበረበት ሁኔታ ተፈጠረ እንጅ ፋሽስት መላ ሀገሪቱን በቁጥጥሩ ስር እንዲያደርግ አላስቻለው፡፡
ሦስተኛው ነጥብ፡- ፋሽስት ጣሊያን በነበረው ቆይታ ሕዝቡን ሴት ከወንድ ሕፃን ሽማግሌ ሳይል በጅምላና በገፍ ያለምንም ክፍያ በግዳጅ ሥራዎች ላይ ለማሠራት (ለመግዛት) የሚችልበትን ሁኔታና አቅም መፍጠር አልቻለም ነበር፡፡ አንዳንድ ሥራዎችን በሚያሠራበት ጊዜም በደሞዝና በክፍያ ያሠራ ነበር እንጅ በባርነት እንደተያዘ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝብ በብላሽ ያለ ክፍያ አስገድዶ እንዲሠራ አላደረገም ነበር፡፡ ሕዝቡም ለዚህ ዝግጁ አልነበረም፡፡ እንኳንና ሕዝቡ አሜን ብሎ ሊገዛለት ቀርቶ ወዶ ገብቶልኛል ብሎ የሚያስባቸው እንኳን በውስጥ አርበኝነት ቁም ስቅሉን ስላሳዩት ሕዝቡ አሜን ብሎ የሚገዛለት አለመሆኑን በመረዳቱና ተስፋ በመቁረጡ ግራዚያኒ ለጌታው ሞሶሎኒ “ከኢትዮጵያዊያን ጭምር ካልሆነም ያለኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ያንተ ትሆናለች!” ብሎ እስከመናገር ደርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በአራተኛነት ላነሣነው ነጥብ፡- ወራሪው ኃይል በነበረው ቆይታ ያለ ከልካይ የሀገሪቱን የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ሀብት እንደፈለገ ማጋዝ መበዝበዝ አልቻለም ነበር፡፡ በእርግጥ ይሄንን ለማድረግ በማሰብ ወራሪው ኃይል ወደ ወደብ የሚያመሩ አውራ መንገዶችን ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመነሣት የነበረውን በማሻሻልና ተጨማሪ አዳዲስ መስመሮችንም በብዙ አሳርና መከራ ገንብቶ ነበር፡፡ ይሁንና የቆይታው ጊዜ አጭር ስለነበር መንገዶቹን አጠናቆ ገንብቶ የሀገራችንን አንጡራ ሀብት ወደ ሀገሩ በማጋዝ ላሰበው ዓላማ ማዋል ሳይችል ቀርቷል፡፡
እንኳንና የሀገሪቱን የገጸምድርና የከርሰ ምድር ሀብት ሊቦጠቡጥ ቀርቶ ለቀለቡ ስንዴ ለማምረቻነት ያሰባቸውን ወገራን (የሰሜን ጎንደር ክፍል) እና ባሌን እንኳን አርበኞቹ በሚያደርሱበት አደጋ መጠቀም ስላልቻለ ተባሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ቀለቡን እንኳን የሚያመጣው ከሀገሩና ቅኝ ከያዛቸው ሌሎች ሀገሮች ነበር፡፡ እንግዲህ ወራሪው ኃይል እንኳንና ቅኝ ሊገዛ ቀርቶ ወረራውን እንኳን እራሱ በብቃት መፈጸም ያልቻለበት በአርበኞች ተቀፍድዶ የተያዘበት ሁኔታ ነበር እንጅ የነበረው ጭራሽ ቅኝ ግዛት ሊባል በሚችል ደረጃ ምንም ነገር መፈጸም የቻለበት ሁኔታ አልነበረም፡፡
በእርግጥ ወራሪው ኃይል በቆይታው ጊዜ በርካታ ዘግናኝና አረመኔያዊ ግፎችን ፈጽሟል፣ ለደኅንነቱ በመሥጋት ለጸጥታ ጥበቃ ሲል ብቻም ሳይሆን ባለበት የዘር ጥላቻ ምክንያትም ጭምር ልክ በቅኝ ግዛት ስር እንደነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ሐበሾች የገዛ ሀገራቸው ሆኖ ሳለ አምስቱንም ዓመት ወራሪው ኃይል ባለባቸውና በገነባቸው ከተሞች መግባት አይፈቀድላቸውም ነበረ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ፋሽስት ጣሊያን ቆይታውን ከወረራ ወደ ቅኝ ግዛት መለወጥ የቻለ ስላልነበረና እነኝህ ሁኔታዎች ሳይፈጸሙ “ቅኝ ግዛት ነው የነበረው” ብሎ ማለት ስለማይቻል ሀገራችን በፍጹም በፍጹም ተወራ ነበር እንጅ ቅኝ አልተገዛችም ነበረ፡፡
እናም ዓላማው ምን እንደሆነ በደንብ ግልጽ ባይሆንልኝም ሀገራችን ቅኝ ግዛት ተገዝታ እንደነበር በዘመቻ እያወሩ ያሉ ሰዎች ሲያጋጥሟቹህ እነኝህ ነጥቦችን ዓለማቀፋዊ መስፈርቶችን በማንሣት ሀገራችን በጭራሽ ቅኝ እንዳልተገዛች በማረጋገጥ እንድታሳፍሩ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ስለ የነጻነት በዓል ስንናገር ወይም ነጻ ስለመውጣታችን ስንናገር አያይዘን ነጻ የወጣነው ከወረራ መሆኑን መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲህ ማድረጋችን ምንም ወይም ብዙ የማያውቁ ወገኖችን ከመሳሳት ወይም ከመደናገር እንታደጋለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

 
Filed in: Amharic