>
5:14 pm - Wednesday April 20, 0489

ድንቄም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ? ማስተር ፕላኑማ የዘ-ህወሀት ነው!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የጸሐፊው ማስታወሻ፡ መለያ ምልክት ምንድን ነው? ደህና፣ “በስም ውስጥ ያለው ምንድን ነው? ያ ጽጌረዳ እያልን የምንጠራው/በሌላ በማንኛውም ስም ቢጠራም ያው ጣፋጭ ሽታው መሽተቱ አይቀርም…“ ብሎ ነበር ሸክስፒር:: “ካራቱሪ እና የሕንድ ኃያልነት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባቀረብኩት ጽሑፍ በካራቱሪ ዓለም አቀፍ ከኢትዮጵያ በተነጠቀው መሬት ላይ የበቀሉት ጽጌረዳዎች በእርግጥ ጽጌረዳዎች አይደሉም የሚለው እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የመሬት ነጠቃ እና ዘረፋ እያካሄድኩት ያለው ጽሑፍ ለሶስተኛው ጊዜ ያዘጋጀሁት ትችቴ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ዘ-ህወሀት በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር መሬት ከነጠቀ፣ ከዘረፈ እና ለውጭ ሸፍጠኛ ኢንቨስተሮች እና ለጎረቤት ሀገሮች ካደለ በኃላ ለኢትዮጵያውያን ምን የተረፈ ሀገር ይኖራል የሚል ጥያቄ በማንሳት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ትችቴ ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እየተባለ የሚጠራው ፕላን ለዘ-ህወሀት ማስተር ፕላን የመሬት ዘረፋ በብልጣብልጥነት ተሸፍኖ የቀረበ የህዝብ ግንኙነት የተንኮል ስራ ስለመሆኑ ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡

“የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን” ከዚህ በኋላ ሊኖር ይችላልን?

Master Plan 40ከጥቂት ሳምንታት በፊት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የዘራፊ ቡድን (ዘ-ህወሀት) ስብስብ ከህዝብ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ካጋጠመው በኋላ መናገሻ ከተማዋን ወደ አካባቢው የእርሻ መሬት የማስፋፋት ድርጊቱን የሚያቆም መሆኑ ታውጆ ነበር፡፡ “የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን” የማዘጋጃ ቤቶችን እና በመናገሻ ከተማይቱ ያልታቀፉ አካባቢዎችን ስልታዊ በሆነ መልኩ በማካተት ፈጣን የሆነ ግዙፍ የምጣኔ ሀብት የያዘ ከተማ ለመገንባት ነው የሚል ስልትን መርህ አድርጎ የተነሳ ነበር፡፡

ሆኖም ግን ዘ-ህወሀት ከአካባቢው ኗሪዎች ከባድ ተቃውሞ የደረሰበት በመሆኑ ተቃውሞውን ለመጨፍለቅ እና ሁኔታውን ለመቆጣጠር ሲል ተቃውሞው በተነሳባቸው አካባቢዎች የግድያ እና የአፈና ዕኩይ ድርጊቱን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ ከህዳር 2015 አጋማሽ ጀምሮ በዘ-ህወሀት የተካሄደውን እልቂት በማስመልከት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “የደህንነት ኃይሎች በምዕራብ አዲስ አበባ በሚገኙት በሸዋ እና በወለጋ ዞኖች እንዲሁም በወሊሶ ከተማ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት የንጹሀን ዜጎች እሬሳዎች በአደባባይ በመንገዶች ላይ እንዲዘረሩ አድርገዋል፡፡“

ዛር እንደሰፈረበት የአዕምሮ ህመምተኛ የሚለፈልፈው እና የዘ-ህወሀት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆነው አዞው ጌታቸው ረዳ እውነተኛ የማስተር ፕላን እንደሌለ አሳፋሪ በሆነ መልኩ በመካድ እንዲሁም ፕላኑን ምንም የሚረባ ነገር እደሌለው በመግለጽ እውነተኛ ፕላን ቢኖር ኖሮ ሁከት ፈጣሪዎች ይቃወሙት እንደነበር እንደህ በማለት ተናግሯል፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መደረጉን ተከትሎ የተዘጋጀ እውነተኛ ፕላን አልነበረም፡፡ የመጨረሻ የፖለቲካ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ሙያዊ በሆነ መልኩ የተነደፈ ወይም ደግሞ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ፕላን አልነበረም፡፡” ብሎ ነበር በገሃድ ሲሸፍጥ::

ረዳ በዘ-ህወሀት እልቂት የተፈጸመባቸውን የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች እና የጥቃት ሰለባዎች ሁከት ፈጣሪ ወሮበሎች በማለት እንዲህ ፈርጇቸዋል፡ “የተፈጠረውን አለመግባባት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ሁከት ፈጣሪዎች በአሁኑ ጊዜ ወደለየለት በትጥቅ ወደተደራጀ ወሮበላነት ከፍ በማለት የግለሰቦችን ህንጻዎች በተደጋጋሚ ማቃጠል እና የመንግስትን መሰረተ ልማት ማውደሙን ቀጥለውበታል፡፡“ አይን ያወጣ ዘራፊ ሌባ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁትን ዜጎች ወሮበላ ብሎ ይጠራል!)

የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እየተባለ በሚጠራው ፕላን ላይ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ በዘ-ህወሀት ስልጣን ላይ አስደንጋጭ ማዕበልን የፈጠረ ሲሆን የዘ-ህወሀት አለቆችን ጭራ እየተከተሉ ያሉ ጥገኛ ምሁር ተብየዎች ቁጥሩ እየጨመረ ከመጣው መሬት አልባ፣ ተስፋ የለሽ፣ ድምጽ አልባ እና ኃይል የለሽ ደኃ ገበሬዎች ላይ መሬት እና ሀብትን ያግበሰብሳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በመሬት ነጠቃ ቅርምቱ የዘ-ህወሀትን ዙፋን የነቀነቀው ሌላ ምንም ሳይሆን እናንተ እንደምትገምቱት ምህረት የለሽ የሆነ የገንዘብ ቀያሪ ወሮበላው የዓለም ባንክ እና እኔ በግልጽ “የድህነት አቃጣሪ” እያልኩ የምጠራው እና ለበርካታ ዓመታት ሳጋልጠው የቆየሁት ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ እ.ኤ.አ ህዳር 2015 “ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ውሸቶች እና ተራ አሀዛዊ ቅጥፈቶች“ በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ፡፡)

እውነት ለመናገር የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በከፍተኛ ደረጃ እንደ አዲስ አበባ ባለ ትልቅ ከተማ እያደገ የመጣውን የመሬት ነጠቃ፣ ደኃውን ህዝብ በኃይል ማባረር እና ማፈናቀል ለመሸፈን ሲባል በዓለም ባንክ የተፈበረከ ትረካ ነው፡፡ የዓለም ባንክ የወደፊት የከተሞች እድገት እንደ አዲስ አበባ ያሉት ከፍተኛ የሆነ መልክዓ ምድራዊ እና የቦታ መስፋፋት ምክንያት ከያዙት የከተማ ድንበር አልፈው ወደ ጎረቤት ማዘጋጃ ቤቶች እና አካባቢዎች የመስፋፋት አስፈላጊነትን በማቅረብ ይሞግታል፡፡ የመስፋፋቱ ሁኔታ ባካባቢው ላሉት ተጠቃሚዎች ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ እና የከተሞች ቀጣይነት ባለው መልኩ በመተግበር የከተማውን አካባቢ ማስፋፋት ነው፡፡

ግልጽ በሆነ መልኩ ለማስቀመጥ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ደኃ አርሶ አደሮችን ከይዞታቸው በማፈናቀል ለዘ-ህወሀት፣ ለስርዓቱ ተጣቃሚዎች እና  ለጥገኛ ምሁር ተብዬ ነቀዞች የግል ይዞታ ለማድረግ በዓለም ባንክ/ዘ-ህወሀት የተቀየሰ ደባ እና ሽረባ ነው፡፡

በእርግጥ የዓለም ባንክ ከዘ-ህወሀት ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን በልማት ስም የአካባቢውን ህዝብ ሲያፈናቅል መቆየቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ባንኩ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት እየተባለ የሚጠራውን አካሄድ ዘ-ህወሀት እንዲጠቀምበት በማድረግ በመንደር በማሰባሰብ (ደህና የሚመስል እና ዜጎችን የሚያፈናቅል፣ ጠራርጎ የሚያባርር፣ ከይዞታቸው የሚነቅል እና ለዘላለም ነባር ኗሪ ህዝቦችን ከኖሩበት ቦታ የሚያፈናቅል) በምዕራብ ኢትዮጵያ የጋምቤላ ህዝቦችን (እና ሌላ አካባቢዎችን) ህዝቦች መሬት በመንጠቅ ለኢንቨስተሮች በመስጠት በመጨረሻም እነዚህ ነጣቂዎች ዋና ሸፍጠኞች በመሆን መሬቱን ነጥቀው ወስደዋል፡፡ (“በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የሞራል ኪሳራ“ በሚል ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ፡፡)

እ.ኤ.አ ግንቦት 2014 የዓለም ባንክ እንዲህ በማለት ይፋ አድርጓል፣ “ከተሞች በፍጥነት በሚያድጉበት ጊዜ ቀልጣፋ እና ዘላቂነት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እንዲቻል በከፍተኛ ደረጃ የተዘጋጀ ስልታዊ ዕቅድ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡“

እ.ኤ.አ የካቲት 2015 ከዓለም ባንክ የተዋቀረ የባሉሙያዎች ቡድን ከመንግስት ባለስልጣኖች፣ ከባለሙያዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅድሚያ መሰራት ያለባቸውን እና የከተማዋን ችግሮችን የመቋቋም አቅም ለማጎልበት እና የከተማ ፕላንን ለመተግበር በአዲስ አበባ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ ያልተጠበቀውን የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠን አዲስ የተቀናጀ የከተማ ፕላን በማዘጋጀት በፍጥነት ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 የዓለም ባንክ “አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፡ የከተሞችን ችግር የመቋቋም አቅም ማጎልበት“ በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አውጥቷል፡፡ ያ ዘገባ አዲስ አበባ ችግርን መጋፈጥ የምትችል ከተማ መሆን አለባት የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቧል፡፡ እናም የከተማዋ የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት ሁለገብ፣ የብዙሀን ዘርፎች እና ለከተማ ዕድገት ተለዋዋጭ መንገድን መከተል አስፈላጊ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንዴት ነው አደጋን የበለጠ መቋቋም የምትችለው? ዘገባው የተቀናጀ የልማት ዕቅድ እና ተዛማጅነት ያላቸውን ህጎች እንዲሁም በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ከተማዋ የመጀመሪያ እና ቀዳሚ ዓላማ አድርጋ መውሰድ ይኖርባታል የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡

የተቀናጀ የልማት ዕቅድ ማለት ህዝብን በፍጥነት እያደጉ ከመጡት ክልሎች ጋር ማገናኘት እና ትናንሽ ከተሞችን እና ክልሎችን በትራንስፖርት እና በኤሌክትሪክ መረብ በማገናኘት በጣም ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ፋብሪካ ማቋቋም ውድ ስለሆነ ትናንሽ ከተሞች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ይችላሉ፡፡

በቀላል አባባል ለማስቀመጥ የተቀናጀ ልማት ማለት በከተማዋ አቅራቢያ ያለውን መሬት እያግበሰበሱ ለኪስ ማድለቢያ በማዋል በከተማው ውስጥ ስርዓት የለሽ ሁኔታ እንዲፈጠር እና የላሸቀ ሞራል እንዲፋጠን ማድረግ ነው፡፡

በአዲስ አበባ አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ በማካተት በዘ-ህወሀት የሙስና አገዛዝ የተቀናጀ የልማት ዕቅድ ለማምጣት እንዲያው ከቅንነት አኳያ በህልወት ደረጃ እንኳ ተግባራዊ ሊሆን ይችላልን?

ደህና፣ እንግዲህ ይህ ይሆናል ብለን የምናስብ ከሆነ በገሀነም በረዶ ላይ ሰይጣን ሸርተቴ ይጫወታል እንደ ማለት ነው?

የዚህ መልስ “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ የዓለም ባንክ ባዘጋጀው ሰነድ ከገጽ 285 – 326 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚያ ዘገባ ላይ እ.ኤ.አ በ2013 በርካታ ትችቶችን ያዘጋጀሁ ሲሆን almariam.com በሚለው ድረ ገጽ ላይ ይገኛል፡፡

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የመሬት ሙስና ጥናት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአካባቢው ህዝብ ላይ አሉታዊ የሆነ እንደምታ ሊያስከትል እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ያ ጥናት እንዲህ በማለት ደምድሟል፣ “መከፋፈል የሌለበት መሬት በመከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ቀርቷል፣ እናም አብዛኞቹ አረንጓዴ አካባቢዎች እና በማስተር ፕላኑ ላይ የነበሩት መንገዶች ለግል ጥቅም እንዲውሉ ተደርጓል፡፡“ (ገጽ 303፡፡)

ሆኖም ግን ሰላማዊ አመጽ በማድረግ እና የማስተር ፕላኑ ለጊዜው እንዲቆም የደፋሮቹ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ባይታከልበት ኖሮ ኦሮሚያ ተጨማሪ 36 ትናንሽ እና ትላልቅ ከተሞችን ታጣ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ታስቦ የነበረው ዕቅድ የአዲስ አበባን ወሰን ወደ 1.1 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ እንዲል ያደርገው ነበር፡፡ ይህም አሁን ካለበት ስፋት ሀያ ጊዜ እጥፍ እንዲበልጥ ያደርገው ነበር፡፡

በቀላል አገላለጽ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች እና ኗሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከዚህም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች በኃይል እንዲባረሩ እና እንዲፈናቀሉ ይደረጉ ነበር፡፡

የዘ-ህወሀት የመሬት ነጠቃ ዕቅድ፣

የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እየተባለ የሚጠራው የሚያስከትለውን እንደምታ በውል በመገንዘብ በኢትዮጵያ የመሬት የባቤትነት መብት ባህሪ ምን እንደሚመስል መገንዘብ ይቻላል፡፡

እ.ኤ.አ በ1995 ዘ-ህወሀት ያዘጋጀው ህገ መንግስት እንዲህ በማለት ያውጃል፣ “የገጠር እና የከተማ መሬት የባለቤትነት መብት እንዲሁም ሁሉም የተፈጥሮ ሀብት በብቸኝነት የመንግስት እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ነው፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሶበች እና ህዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ እናም አይሸጥም ወይም ደግሞ በማንኛውም መንገድ አይለወጥም፡፡“ (አንቀጽ 40 (30)፡፡)

መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የገጠር እና የከተማን መሬት በብቸኝነት የባለቤትነት መብት ቢኖረው ኖሮ ግልጽ የሆነው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡ “በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በብቸኝነት እና በአጠቃላይ የመንግስት ባለቤትነት ያለው ማን ነው? ባለፉት 25 ዓመታት የመንግስት መዋቅሩን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ መንግስቱን ሲዘውረው የቆየው ማን ነው?“ መልሱ ከዚህ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው: እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 የተካሄደውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በ100 ፐርሰንት ያሸነፈው ማን ነው?

በኢትዮጵያ ሁሉም መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር የመዋሉ ጉዳይ ለመሬት ሙስና ዋና ምንጭ ለመሆን በቅቷል፡፡

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የሙስና ዘገባ እንዲህ በማለት ይገልጻል፣ “በኢትዮጵያ የመሬቱ ዘርፍ በተለየ መልኩ ለሙስና እና ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ ነው፡፡ ይህም ማለት ምንም ዓይነት አዲስ ሀብት ሳይፈጠር የነበረውን ሀብት በማህበራዊ ወይም በፖለቲካ ተቋማት አማካይነት ለተለያዩ የህብረተሰብ ቡድኖች ማከፋፈል ነው፡፡“

ሀብታሞቹ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ የዘ-ህወሀት ግለሰቦች፣ ዝምድና ያላቸው ቡድኖች እና ሆድ አምላኩ ጥገኛ ምሁራን ተብየዎች የድሆችን መሬት በመያዝ በግዳጅ በማፈናቀል ሆኖም ግን በህጋዊ መንገድ ማስወገድ እና የማየቀረውን ድርጊት በመፈጸም ዜጎች እንዲገለሉ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት እና በዓለም አቀፍ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ሸፍጠኞች ሲካሄድ የነበረውን ደባ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ለአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ስራዎች ምስጋና ይግባና ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ትኩረት እንዲያገኝ እና እንዲጋለጥ ተደርጓል፡፡ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የሙስና ሰነድ እንዲህ በማለት ጠቁሟል፣ “በርካታ የሆነ የተወሰደው መሬት የግል ፍላጎት ላላቸው ሰዎች እንዲዛወር ተደርጓል፣ ሆኖም ግን አነስተኛ ይዞታ ላላቸው ዜጎች አይደለም፡፡“

አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ማፈናቀል እና ወደ አዲስ ቦታ እንዲሰፍሩ ማድረግ ጠቀሜታው ሰፋፊ የንግድ እርሻ ለሚያካሂዱ የአበባ እርሻዎችን፣ ባዮ ፊዩል እና ሌሎችን ሸቀጦች ለሚያመርቱ ሰዎች ነው፡፡

በዘ-ህወሀት እየተካሄደ ያለው የውስጥ የመሬት ዘረፋ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ሆኖም ግን ከፍተኛ የሆነ ውድመትን እያስከተለ ነው፡፡

በቀረበው የሙስና ዘገባ መሰረት የውስጥ የመሬት ዘረፋው ሂደት ትንሽ ቁራጭ መሬትን ለይቶ በማውጣት ይጀምርና ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር የሊዝ ስምምነት ማድረግ ይጀመራል፡፡ ለዘ-ህወሀት ምቹ እንዲሆን ምንም ዓይነት መመሪያዎች የሉም፡፡ ይህም በመሆኑ በዘገባው ገጽ 302 ላይ እንዲህ ይላል፡

“በርካታ ሙስና አለ…መሬት ለማግኘት ያሉት ህጎች ግልጽ አይደሉም፣ እናም ጥቂት ሰዎች በአብዛኛው ባላቸው ግንኙነት ወይም ደግሞ ጉቦ በመክፈል ከሌሎች የተሻለ መሬት የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡ የግሉ ዘርፍ በዚህ አይተማመንም ወይም ደግሞ ሊዙን ይጠባበቃል ወይም የጨረታ ሂደቱን ይከታተላል፡፡ ስለሆነም ሁልጊዜ ሌሎች አማራጮችን ይመለከታል፡፡ የማዘጋጃ ቤቱን መሬት ህገወጥ በሆነ መልኩ አሳልፎ ለሌላ ለመስጠት የሚጠቀሙበት ቁልፍ መንገድ በአልሚዎች ቁጥጥር ስር ላሉት የቤት ስራ ማህበራት በመደልደል ከዚያ በኋላ በህገወጥ መልክ መሬቱን ይሸጡታል፡፡ መሬቱን የሚገዙት ሰዎች ስለመሬቱ የህጋዊነት ሁኔታ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡“

እንግዲህ መልሱ ከዚህ ላይ ይገኛል፡፡ የመንግስቱን ስልጣን የያዙት ሰዎች የመሬት ባለቤትነቱንም ይይዛሉ፡፡ የመሬት ባለቤትነቱን የያዙት እና መንግስት እስከ አጥንታቸው ድረስ በሙስና የበከቱ ናቸው፡፡ የዓለም ባንክ ይህንን ዓይነት ድርጊት ፈጽሟል አላልኩም!

በመሬት ላይ እየተካሄደ ያለ ሙስና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሁሉም ሙስናዎች ሁሉ ዋና ስር ነው! ታላቁ የመሬት ሙስና በከፍተኛው የስልጣን እርካብ ላይ ካሉት ቡድኖች እና ከግሉ ዘርፍ የሚመነጭ ነው፡፡ ኃይለኞቹ የዘ-ህወሀት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ልሂቃን ህገወጥ አሰራርን፣ የዘፈቀደ አካሄድን፣ ሚስጥራዊ አያያዝን፣ ተጠያቂ ያለመሆንን እና የአስተዳደር ስርዓቱን ግራ በማጋባት ሽባ እንዲሆን በማድረግ የእራሳቸውን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት መረባቸውን ይዘረጋሉ፡፡

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የሙስና ዘገባ መሰረት በመሬት ዘርፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ውስብስብ የሆኑ በርካታ የሙስና መንገዶች እንደሚፈጸሙ ግልጽ ያደርጋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ልሂቃን እና ከፍተኛ ባለስልጣኖች በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ተፈላጊ የሆነ መሬት ለእራሳቸው ነጥቀው ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ የዘ-ህወሀት ወፍራም ድመቶች በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ደካማ ፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ እንዲሁም ያሉትን ፖሊሲዎች እና ህጎች ደካማ አፈጻጸም ለእራሳቸው ጥቅም እንዲውሉ ያደርጓቸዋል፡፡ በሁሉም የከተማ እና የገጠር አካባቢዎች፣ ከቤት ስራ ማህበራት እና ከከተማ አካባቢ አልሚዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሙስና ስራ በመስራት መሬቱን ለእነርሱ እንዲመደብ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና በጥብቅ የተሳሰሩ ግለሰቦች ያሉትን ሕጎች እና ደንቦች በመጣስ ለእነርሱ መሬት እንዲመድቡ ያደርጋሉ፡፡

ሌላው የመሬት ሙስና ቁልፍ ዘዴ የማዘጋጃ ቤትን መሬት ህገወጥ በሆነ መንገድ በአልሚዎች ቁጥጥር ስር ለተያዙት የቤት ስራ ማህበራት እንዲሰጡ በማድረግ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እንዲሸጥ ያደርጋል፡፡ ሁልጊዜ መሬት የገዙ ሰዎች የተሸጠላቸውን መሬት ህጋዊነት አያውቁትም:: በመጨረሻም እነዚህ ገዥዎች በሙስና ከተዘፈቁት ባለስልጣኖች አጋሮች ጋር ከፍትህ አካል ፊት ይቆማሉ፡፡

ሌላው ቁልፍ የመሬት ሙስና ቁልፍ መንገድ ባለስልጣኖች የሀሰት ሰነዶችን በማዘጋጀት ሙስና የሚሰሩበት መንገድ ነው፡

“ትክክለኛውን ነገር ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ውስንነት በተለይም በከተማ አካባቢዎች እና ውስን ምልከታ በመኖሩ ምንክያት ባለስልጣኖች የሀሰት ሰነዶችን ለማዘጋጀት በርካታ የሆኑ ዕድሎች አሏቸው፡፡ አንድ ቁራጭ መሬት ለበርካታ ሰዎች የመስጠቱ ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ከዚህም ሂደት ባለስልጣኖች እና አቀባዮቻቸው በርካታ የልውውጥ እና የአግልግሎት ክፍያዎችን ይሰበስባሉ፡፡“

የሊዝ የጨረታ አወጣጥ ሂደቱን በሚያዩት በቦርድ አባላት መካከል ያለ ዓይን ያወጣ የፍላጎት ግጭት፣ ለሊዝ አሰጣጡ እና አከፋፈል የክትትል ስርዓት ያለመኖር እና የመሬት አጠቃቀም ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን ሙስና እንዲፋጠን አድርጎታል፡፡

የሀገሪቱ መናገሻ ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ ለከተማው አስተዳደር ባለስልጣኖች ጉቦ ሳይሰጥ ቁራጭ መሬት ማግኘት ፈጽሞ የሚቻል ጉዳይ አይደለም፡፡ እነዚህ ባለስልጣኖች ግዙፍ የሆነ ጉቦ ብቻ አይደለም የሚጠይቁት ሆኖም ግን ከዚህም በተጨማሪ ለግዙፍ የመሬት ቅርምት እንዲመቻቸው ከመሬት ዋጋ ተንባዮች ጋር እና የህገ ወጥ የሸፍጥ ስራውን ከሚያቀላጥፉላቸው የቤት ስራ ማህበራት ጋርም ደባ ይሰራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ 15,000 የተጭበረበሩ ስያሜዎች እንደታተሙ ይገመታል፡፡

ይህንን ነው እንግዲህ የዓለም ባንክ በእርግጠኝነት የተናገረው!

ስለሆነም የትኞቹ የመንግስት ባለስልጣኖች ናቸው ግዙፍ የሆነ ጉቦ የሚጠይቁት? ደህና፣ እነማን ናቸው የመንግስትነት ስልጣኑን የያዙት ባለስልጣኖች?

በተመሳሳይ መልኩ የገጠር መሬት አስተዳደርም በዘ-ህወሀት ሙስና ጥልቅ በሆነ መልኩ ተበክሏል፡፡ በገጠር አካባቢዎች ባለስልጣኖች የሕዝብ መሬትን ትርጉም የመንግስት መሬት በማለት አዛብተው ያቀርቡታል፡፡ ባለስልጣኖች ሕዝብን ለማፈናቀል ሲፈልጉ እና በመጨረሻም ለመሬት የለሽነት ለሚዳርገው ተግባር ለህዝብ ጥቅም ዓላማ የሚል ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለስልጣኖች ለሌሎች ብዙም እርባና በሌለው ተግባር ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ ባለስልጣኖች መሬት ነጥቀው በመስጠት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን ይህ ድርጊት በወረዳ ደረጃ ላይ የሚፈጸም ሲሆን ይህም ድርጊት በተመሳሳይ መልኩ በቀበሌ ደረጃ በተመረጡ የኮሚቴ አባላት ደረጃ እንዳለ ተቀድቶ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ እንደ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የሙስና ዘገባ ከሆነ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከመሬት ጋር በተያያዘ ሁሉም የልውውጥ ስራዎች ሁልጊዜ ሙስናን ያካትታል፣ ምክንያቱም መሬትን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ፖሊሲ ወይም ደግሞ ግልጽ የሆነ ሕግ የለም፡፡

ቀላል በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ የህዝብ የሚባል መሬት የለም፡፡ ያለው የመንግስት መሬት ብቻ ነው፡፡ ደህና፣ ማን ነው የመንግስት ስልጣንን እና መሬትን የያዘው?

ዘ-ህወሀት በጣም ተራ የሆነውን የመሬት አስተዳደር ስርዓት በስራ ላይ ያላዋለ መሆኑን ከዓለም ባንክ ዘገባ መማር በጣም አስደናቂ ነገር ነው፡፡ የዓለም ባንክ ዘገባ እንዲህ ይላል፡

“የገጠር አካባቢዎች የተመዘገበ የመሬት ይዞታ ካርታ የላቸውም…በከተማ አካባቢዎች ጥቂት የተመዘገቡ ንብረቶች ካርታ አለ፡፡ ዕዳዎች እና ክልከላዎች በመመዝገቢያ ሰነዱ ላይ አይመዘገቡም፡፡ ሆኖም ግን ዕዳዎች የሚመዘገቡ ከሆነም እራሱን በቻለ በሌላ ሰነድ ላይ ነው የሚመዘገቡት፡፡ የመሬት አጠቃቀም ክልከላዎች በመመዝገቢያ ሰነዱ ላይ አይመዘገቡም፡፡ የህዝብ መሬት ቆጠራ የለም፡፡ ይህም ደካማ የሆነ የህዝብ መሬት አስተዳደር ህገወጥ በሆነ መልኩ የህዝብን መሬት ለግል ቡድኖች እና ግለሰቦች መሬት የማግኘት ዕድልን ይፈጥራል፡፡“

በአሁኑ ጊዜ ያሉት ተ ቋማት እና ሕጎች የተሸረሸሩ፣ የተተው እና ለግል ጥቅም ሲባል የሚፐወዙ በመሆናቸው ምክንያት የመሬት አስተዳደር ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ውድቀት ደርሶበታል፡፡ ይህም በመሆኑ በስልጣን ላይ ያሉት ባለስልጣኖች እየፈጸሟቸው ላሉት የሙስና ተግባራት  ተጠያቂ መሆን አልቻሉም፡፡

ሆኖም ግን ይህ ቀውስ የበዛበት የመሬት አስተዳደር ስርዓት ሆን ተብሎ የዘ-ህወሀትን የመሬት ነጠቃ አዳኝነት ተሞክሮ ለማሳደግ እና ለማፋጠን ተብሎ ነውን?

መሬት መዝረፍ ወይም የግል ሀብት መንጠቅ፣

የዘ-ህወሀት ህገ መንግስት “ለህዝብ ጥቅም ሲባል የግል ሀብት በሚወሰድበት ጊዜ አስቀድሞ በቂ የሆነ የካሳ ክፍያ በመክፈል ይሆናል“ በማለት ለዘ-ህወሀት ስልጣን ይሰጣል፡፡ (አንቀጽ 40፡1)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘ-ህወሀት ለሕዝብ ጥቅም በሚል ሰበብ መሬትን ለመዝረፍ እንዲችል አዋጅ ቁጥር 455/2005ን አውጥቷል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ በመሬት ይዞታ ላይ ያለን ሀብት ለመውረስ በሚፈለግበት ጊዜ የካሳ ክፍያ ለመክፈል በሚል የይስሙላ አካሄድ የካሳ ክፍያ እና የምኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 135/2007ን አውጥተቷል፡፡

እነዚህ ሁሉ ሕጎች በእውነት ጥርስ አላቸውን? ወይስ መሳቂያ ናቸው? ወይም ደግሞ ዘ-ህወሀትን በገንዘብ የሚያንበሸብሹት እና የመሬት ዘረፋው እንዲካሄድ የሚያግዙትን ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎችን ደስ ለማሰኘት ሲባል ዝም ብለው ለቃላት ፍጆታ (እንደ ዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት) በወረቀት ላይ የተጻፉ ናቸው?

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያደረገው የሙስና እና ሌሎች ጥናቶች በግልጽ እንደሚያመላክቱት እደዚህ ያሉ ሕጎች ከተማን ከመስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ዞኖችን እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ከማመላከት አንጻር የአካባቢ ማዘጋጃ ቤቶች በቂ የካሳ ከፍያ ገንዘብ የሌላቸው በመሆናቸው ፋይዳ የሌላቸው ትርጉመ ቢስ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማ መስፋፋት ሂደት ባብዛኛው ያለምንም የካሳ ክፍያ ወይም ደግሞ በቂ ያልሆነ የካሳ ክፍያ በመስጠት ወይም የመሬት ባለይዞታዎችን ያለምንም ማቅማማት ከይዞታቸው ኃይልን በመጠቀም ያለምንም የሕግ የይግባኝ አቤቱታ ማባረር  ነው፡፡ ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የዘ-ህወሀት የመሬት ዘረፋ ማሰተር ፕላን ነው! 

ዘ-ህወሀት መንግስትን ከመሬት ባለቤትነት ለማስወገድ ወይም ደግሞ መሬት በግሉ ዘርፍ በግል ሀብትነት እንዲያዝ ዕቅዱም ፍላጎቱም የለውም፡፡ የገንዘብ ማካበቻ እና ማግበስበሻ ምንጫቸውን በፈቃደኝነት ለምን ብለው ይለቃሉ?

ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያ ፊውዳል ታሪክ ከኋላ ቀሩ ባህላዊ የመሬት ይዞታ ስሪት ጋር በመቀላቀል ጠፍተው የነበሩት የመሬት ከበርቴዎች እንደገና ተመልሰው ይቆጣጠሩታል፣ እናም መሬት የሌላቸውን ህዝቦች ይበዘብዛሉ፣ ወዘተ በማለት ይሰብካሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዘ-ህወሀት የመሬት አስተዳደሩን በተሻለ ሁኔታ መያዝ እንደሚችል ይናገራል፡፡ እኮ ለማን ነው የተሻለ የሚያደርገው?

በእርግጥ ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያን መሬት ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እንዲያስተዳድረው መጠበቅ ማለት ቀበሮ የዶሮዎችን ማደሪያ ቤት ወይም ደግሞ ተኩላ የበግ ለምድ በመልበስ የበጎችን ጋጥ ማስተዳደር እና መጠበቅ እንዲችሉ መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ይህ ምንም እርባና የሌለው ፋይዳቢስ ጉዳይ ነው!

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመንግስት የመሬት ባለቤትነት ማለት በተጨባጭ የዘ-ህወሀት የመሬት ባለቤትነት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዘ-ህወሀት በብቸኝነት የመንግስት መዋቅርን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ ለዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነት መብትን መልቀቅ ማለት የመንግስት ስልጣንን የመልቀቀቅ ያህል ከባድ ነገር ነው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን መሬት በብቸኝነት በይዞታ ከመያዝ ውጭ ዘ-ህወሀት ምንም ዓይነት ምርጫ የለውም፡፡

ለዘ-ህወሀት የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረውን የእያንዳንዱን 100 ሚሊዮን ህዝብ ህልውና መቆጣጠር ማለት ነው፡፡

መሬት ለዘ-ህወሀት ጉቦ እየተባለ የሚጠራው ስጦታ መስጠት ማለት ነው፡፡

መሬትን መቆጣጠር ማለት የገጠሩን ህዝብ ድምጽ መያዝ ማለት ነው (ድምጽ መስረቅ ማለት ነው)፡፡

ለዘ-ህወሀት መሬት የመጨረሻ የሆነውን ፍጹም ስልጣን የመያዝ ምንጭ ነው፡፡ ስልጣን ያባልጋል የሚለው እውነት ከሆነ በመሬት ላይ የሚፈጸም ሙስና በስልጣን መባለግን ያስከትላል፡፡

ዘህወሀት ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት እስከሚጣል ድረስ ከእያንዳንዷ ቁራጭ መሬት ጋር እንደ መዥገር ተጣብቆ ይቆያል፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ዘ-ህወሀት የህዝብን ድምጽ መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ የህዝብ ተወካዮች እየተባለ የሚጠራውን ይስሙላውን ፓርላማ ተብዬ መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡

ዘ-ህወሀት በሀገሪቱ ውስጥ መሬትን መቶ በመቶ ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡

እንግዲህ ይኸ ሁሉ ሁኔታ ዘ-ህወሀት በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊት ኢትዮጵያ አዲስ ምስለኔ፣ ገዥ እና አድራጊ ፈጣሪ መኳንንት ሆኖ ይገኛል፡፡

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለው የጎሳ ፌዴራሊዝም በመካከለኛው  ክፍለ ዘመን እንደነበረው ዓይነት ስያሜ ሊኖረው አይችልምን?

የመካከለኛው ክፍለ ዘመን የፊውዳል ንጉስ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኘውን ሁሉንም መሬት ይቆጣጠራል፣ እናም የሚፈልገው ብቻ መጠቀም እንዲችል ይፈቅዳል፡፡ ሁልጊዜ በሚባል መልኩ ንጉሱ መሬቱን ለሚያምናቸው እና ለእርሱ በቃለ መሀላ ታማኝ ለሆኑ ሎሌዎቹ ብቻ ይሰጣል፡፡ የንጉሱ ሰዎች ባሮን እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን ለንጉሳቸው ይዋጉ ነበር፡፡ ባሮኖች በጣም ሀብታሞች፣ ኃይለኞች እና ከንጉሱ ላይ በሊዝ በያዙት መሬት ላይ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጣሪ ሆኑ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በክልል መንግስታት እየተካሄደ ያለው ይኸ አይደለምን ወይም ደግሞ በትክክለኛው ስማቸው የማዘጋጃ ቤት ኃላፊዎች ብለን ልንጠራቸው አንችልምን?

ለዘ-ህወሀት ሌቦች (አለቆች ማለቴ ነው) ጽናቱን ይስጣቸው፡፡

የዘላለማዊ ቁጥጥር አስፈላጊነት፣

ዘ-ህወሀትን አሻፈረኝ ብለው ከባድ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ያባረሩት እና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዜሮ እንዲሆን ያስገደዱት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ በሆነ የደስታ ስሜት ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ እና የአይበገሬ የአሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ዘ-ህወሀትን ሙሉ በሙሉ ድል እንዳደረጉት ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡

እንደዚህ ያሉ ስሜቶች ዝም ብለው የየዋህነት ስሜቶች ብቻ አይደሉም ሆኖም ግን ለመጨረሻ ጊዜ የተሳሳቱትን ስሌቶች በተጨባጭ ስህተት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ እንጅ፡፡

ጸሐይ ነገ ትወጣለች ከሚለው እርግጠኝነት አኳያ የዘ-ህወሀት የመሬት ተቀራማች ዘራፊዎች በፍርሀት በመዋጥ ጥንብ አንስተው እንደሚበሩ አሞራዎች (ጆቢራዎች) እንደገና ተመልሰው ይመጣሉ፡፡ በእርግጥ የተነሳውን እና የቦነነውን አቧራ ለማረጋጋት ሲሉ ጸጥ በማለት ካሰለፉ በኋላ በከፍተኛ የበቀልተኝነት ስሜት ታጅበው እንደገና ብቅ ይላሉ!

በእርግጥ የዘ-ህወሀት አለቆች በኃይል ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ በመደረጋቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡ ከስርዓቱ አፈቀላጤ ከጌታቸው ረዳ የሚወጡ የቅጥፈት ቃላት ዘ-ህወሀት እንደ ድሮው ሁሉ እንደፈለገው መሬት እየዘረፈ ሊኖር እንደማይችል እና የዘ-ህወሀት አለቆች ምን ያህል እንደተደናገጡ እና ይይዙት ይጨብጡት እንዳጡ የሚያመላክት ነገር ነው፡፡ (የዘ-ህወሀት አለቆች ተመልሰው ወደ ላይ ከፍ እንደማይሉ እና በሰሩት ነገር ላይ ምንም ዓይነት ገለጻ ማድረግ እንደማይችሉ ፍጹም ፍጹም በሆነ መልኩ እና ሊሆን በማይችልበት ደረጃ እርግጠኛ ሆኘ መናገር እችላለሁ፡፡ ወያኔዎች ሁልጊዜ እንደ ጌታቸው ረዳ ወይም ደግሞ እንደ ሬድዋን ሁሴን ያሉ ለእራሳቸው ብቻ ንግግር ከሚያደርጉት የወደቁ ሙትቻ የስርዓቱ አፈቀላጤዎች ጀርባ ይቆማሉ፡፡) ኃይለማርያም ደሳለኝስ እንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመላቸው አይደለምን?)

ዘ-ህወሀት እንደገና በአንድ ወቅት ይመለስ እና ይህንኑ መሬት ሊዘርፍ ይችላል፡፡

ይህ ጉዳይ የዱሮውን አስቸጋሪ የቃላት ድርደራ ስርዓት ሊያስታውስ አይችልምን? እንጨት ቆርጣሚ ዓይጥ እንጨት መቆርጠም የሚችል ከሆነ ምን ያህል እንጨት ሊቆረጥም ይችላል?

ደህና፣ የዘ-ህወሀት መሬት ዘራፊዎች መሬት መዝረፍ የሚችሉ ከሆነ ምን ያህል መሬት ሊዘርፉ ይችላሉ?

ሊካድ የማይችለው ዋናው ነገር የዘ-ህወሀት አለቆች እና ወፍራም ድመቶች በአዲስ አበባ አካባቢ የሚገኘውን መሬት ለመቀራመት እና ለመዝረፍ ምራቆቻቸውን ከምላሶቻቸው ላይ በማንጠባጠብ ላይ የሚገኙ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለማግኘት ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ፡፡ ጊዜ ተበድረው ቢሆን ይሰራሉ፡፡

ዘ-ህወሀት በሚቀጥለው ጊዜ የበለጠ ውስብስብ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ በማስተር ፕላኑ ላየ ዘ-ህወሀት ተከታታይነት ክርክር ወይም ደግሞ የህዝብ ትችት እና ተቃውሞ እንዲሰማ አያደርግም፡፡ መሬትን ለመዝረፍ በዝረራ አይሸነፉም፣ ድርጊቱን በማዘግት ለመፋለም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሁሉንም ነገር በሚስጥር፣ ስልታዊ በሆነ መንገድ እና በውል ሊታይ በማይችል መልኩ ይሰራሉ፡፡

ዘ-ህወሀት ማስተር ፕላኑን እንደተውት የሚመስል ግንዛቤ በህዝቡ ላይ በማሳደር እያንዳንዱን ሰው ጸጥ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል፡፡ ለውጤቱ የበለጠ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራሉ፡፡ እስከ አሁን ሲኖር የነበረው ማስተር ፕላን ሞቶ ተቀብሯል ብለው ያስወራሉ፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ ሌላ የማህበረሰብ ፕሮጀክት (ዕቅድ ሳይሆን) በማዘጋጀት ከህዝቡ ጋር አብረው ለመስራት ቃል ይገባሉ፡፡ (ከዚህ በኋላ ዘ-ህወሀት “ማስተር” የሚለውን ቃል በማንኛውም ለህዝብ በሚያቀርቡት ዕቅድ ውስጥ በፍጹም አይጠቀሙም በማለት በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡)

ዘ-ህወሀት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ ጠባቂዎች እስኪወድቁ ድረስ ጊዜ በመሸመት ዝም ብሎ ይመለከታል፡፡

“በሚፈላ ውኃ ውስጥ ያለ እንቁራሪት“ የሚለውን አሮጌ ስልት ይጠቀማሉ፡፡ እንቁራሪትን በፈላ ውኃ ውስጥ ብትጨምራት ወዲያውኑ ከመቅጽበት ዘላ ትወጣለች፡፡ ሆኖም ግን እንቁራሪትን በቀዘቀዘ ውኃ ማሰሮ ውስጥ ብትጥላት እና ቀስ በቀስ ሙቀት በመስጠት በዝግታ እየፈላ እንዲሄድ ብታደርግ እንቁራሪቷ እዚያው ተቀቅላ እስክትሞ ድረስ ልትቆይ ትችላለች፡፡

ዘ-ህወሀት በአንድ ጊዜ ሁሉንም መሬት ለመዝረፍ ሙከራ አደረገ፣ እናም ህዝቡ በአንድ ጊዜ ገንፍሎ ወጣ እና ተቃውሞውን አሰማ፡፡

ሆኖም ግን የመሬት ቅርምት ዝርፊያው ቀስ በቀስ የሚከናወን ቢሆን ኖሮ ህዝቡ ዓይኑን ርግብ አያደርግም ነበር፡፡ ችግሩ ተከስቶባቸው በነበሩት አካባቢዎች ህዝቡ የአመጹን አስተባባሪዎች አጋልጦ ይሰጣል ብዬ እሰጋለሁ፡፡

እስከዚያው ድረስ ግን ዘ-ህወሀት እጆቹን አጣምሮ ዝም ብሎ አይቀመጥም፡፡ ማስተር ፕላን ቢን (ማስተር ፕላን እንዳላቸው ባታውቁም እንኳ) ወይም ደግሞ የመሬት ዘረፋቸውን በመቃወም የሚያኮላሹባቸውን ስልታዊ እና ዘዴ በተመላበት መልኩ ከጥቅም ውጭ በማድረግ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡

ዘ-ህወሀት የማስተር ፕላኑን ተግባራዊነት የሚቃወሙትን በማስወገድ ማስተር ፕላን ቢን ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሉት ዘዴዎች አሉት፡

1ኛ) የሚቃወሙትን ሰዎች በገንዘብ መግዛት፣

2ኛ) የሚቃወሙትን ሰዎች ጸጥ በማድረግ፣

3ኛ) የሚቃወሙትን ሰዎች በማስፈራራት እና በማሸበር ከድርጊቱ እንዲወጡ በማድረግ፣

4ኛ) የሚቃወሙትን ሰዎች በማሰር እና በማሰቃየት፣ እና

5ኛ) የሚቃወሙትን ሰዎች በመግደል (በመፍጀት) ነው፡፡

ይኸ አካሄድ ዘ-ህወሀት ሲጠቀምበት የቆየው እና ትክክለኛው የአካሄድ ስርዓት ነው በማለት የሚተገብረው ዘዴ ነው፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ዘ-ህወሀት ጅራቱን በእግሮቹ መካከል በጉያው ወትፎ ተመልሷል ብለው ለአንዲት አፍታም ቢሆን የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ብልሀት የሌለው ድፍረትን እያካሄዱ ነው፡፡

የዘ-ህወሀት የጥፋት ሰለባዎች ዘ-ህወሀት አጭበርባሪ፣ ሚስጥራዊ፣አታላይ፣ ደባ ሰሪ፣ ዲያብሎስ፣ ህገ ወጥ፣ ኃይለኛ፣ ሰይጣናዊ፣ በጣም መጥፎ፣ ድብቅ እና ማቻቬሌናዊ አካሄድን የሚከተሉ የዕኩይ ምግባር አራማጅ የፖለቲካ መሰሪዎችን የሚያራምድ አንደነሱ አንደሌለ መረሳት የለበትም፡፡

እነዚህ ሰዎች ከመሬት ቅርምት ዘረፋው እና ከማይነጥፈው የገንዘብ ማግበስበሻ ምንጫቸው በቀላሉ የሚሄዱ አይደሉም፡፡ በአዲስ አበባ አካባቢ ያለውን መሬት በአንድ ጊዜ አግበስብሰው ለመውሰድ የማይችሉ ከሆነ ቀስ በማለት አንድ በአንድ እያሉ መውሰድ ይችላሉ፡፡ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡ የዘ-ህወሀት መሪዎች ደኃ ገበሬዎችን በአንድ ጊዜ ከይዞታ መሬታቸው ላይ በአካል በማባረር መሬታቸውን ካልዘረፉ ጋህነም በማታለል እና በማጭበርበር ከመሬታቸው ላይ የሚያስወግዳቸው መስሎ ይታያቸዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ማንኛውንም መንገድ የአካባቢ ግንባር ቀደም ሰዎችን እና ገንዘብ ሰብሳቢዎችን ጨምሮ በኋላ እንዲያስተላልፉላቸው በማሰብ መሬት እንዲገዙ የሚያደርጉ ለመሆናቸው ምንም ዓይነት ጥርጥር የለኝም፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመሆን ከግል አልሚዎች ጋር ሽርክና በመፍጠር ለማስመሰል ይሞክራሉ፡፡ ቁርጥራጭ መሬት በተናጠል ለማግኘት እንዲመቻቸው እዩልኝ እመኑኝ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ያቀርባሉ፡፡ ማስተር ፕላኑን በሌላ ጣፋጭ በሚመስል የአካባቢ ስም ስያሜ በመስጠት ድብቅ አድርገው ይይዛሉ፡፡ መሬቱን ለመዝረፍ ያለ የሌለ ጥረታቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ፕላናቸው የሚሰራ ከሆነ በአዲስ አበባ አካባቢ የሚገኙትን 36 ትናንሽ እና ትላልቅ ከተሞች እንዳለ ይውጣሉ፡፡ ይኸ እንግዲህ በርካታ የሆነ የመኖሪያ ቦታ ነው!

ዘ-ህወሀት የዘረፈውን መሬት በመያዝ ምላሱን አውጥቶ በማሾፍ ይጓዛል፡፡ ይህም ማለት የዘረፉትን ጥንብ በመያዝ እንደሚበሩት አሞራዎች ዓይነት ማለት ነው፡፡

“የነጻነት ዋጋ ዘላለማዊ ምልከታ ነው“ ይባላል፡፡ የአንድን ሰው መሬት የመጠበቅ ዋጋም ዘላለማዊ ምልከታ ነው እላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ዘላለማዊ ምልከታ ማድረግ እና በአካባቢው የሚደረጉ ማንኛቸውንም ዓይነት ግብይይቶች በንቃት የመጠበቅ ዕድሎቻቸውን በመጠቀም መሬቶቻቻው ከነጣቂዎች በመጠበቅ የወደፊቱን የልጆቻቸውን ዕድል ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡

በቅድመ ፕላን እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ችግሮችን በማስወገድ የከተማ ልማትን ማምጣት መቃወሜ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላንን አንብቤዋለሁ እናም በጥንቃቄ አጥንቸዋለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ከ2006 – 2030 ድረስ የሚዘልቅ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ አካባቢ ልዩ ዞኖች በሚል የተዘጋጀ ማስመሰያ ነው፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት የተዘጋጀ የማስመሰያ የሸፍጥ ሰነድ ነው፡፡ ዕቅዱ በተቀናጀ ልማት የአዲስ አበባን ችግሮች መቋቋም በማስመልከት በበርካታ የዓለም ባንክ ዘገባዎች እና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ የተነሱ ጉዳዮችን በመያዝ በጥልቀት እና በዝርዝር ያቀርባል፡፡ ስለመሰረተ ልማት፣ ስለትራንስፖርት፣ ስለአገልግሎቶች፣ ስለኢንዱስትሪ ዞኖች፣ ስለስነምህዳር ክብካቤ፣ ስለአረንጓዴ ልማት ቦታዎች፣ ስለመስኖ እና ስለሌሎች ነገሮች  ይናገራል፡፡ የወደፊት የፓርኮችን፣ የአየር ማረፊያዎችን፣ የክልል ልማት ቦታዎችን በካርታው ላይ ያመላክታል፡፡ እንደ የቴክኒክ ሰነድ ዕቅዱ ልዩ በሆነ መልኩ ዝርዝር ጉዳዮችን በማከተት በዓለም ባንክ የከተማ ፕላን አወቃቀር ተቃኝቷል፡፡

የማስተር ፕላኑ ፍጹም በሆነ መልኩ የተወው ነገር ቢኖር በፕላኑ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው ዜጎች ግብዓት ምን ሊሆን እንደሚችል ያለመነካቱ ብቻ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከተለጠጠ እና የእርሻ እና የግጦሽ መሬቶቻቸውን ሁሉ ከወሰደባቸው በኋላ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ የጉዳት ሰለባዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዴት ነው ሊረዱ የመችሉት? እነዚህ ዜጎች ለዘ-ህወሀት ትርፍ ዜጎች እና በክልል ታዛዥ አጋሮቻቸው እንደፈለጉ የሚጣሉ ዜጎች ናቸው ማለት ነው?

የጀርመን ብሄራዊ ሶሻሊስት የሰራተኞች ፓርቲ በመኖሪያ ቦታ ላይ አውዳሚ የሆነ ደርጊት በመፈጸም እና የኃይል ግዛት የማስፋፋት ዕቅዱን ለመተግበር ህዝብን በመጨረስ፣ በማፈናቀል፣ እና እንደ አርአያኖች ዝርያ ያልሆኑትን በአንተርሜንስቸን ህዝቦች የተያዙትን ህዝቦች በማፈናቀል በጎረቤት ሀገሮች ላይ ጭምር የመስፋፋት ዕቅዳቸውን አካሂደው ነበር፡፡ ብሄራዊ ሶሻሊስቶች ሁለት ቀዳሚ ዓላማዊች ነበሯቸው፡፡ እነርሱም፡

1ኛ) የመኖሪያ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥሮ መያዝ፣

2ኛ) አይሁዶችን ዘላለማዊ በሆነ መልኩ ማጥፋት ነበር፡፡

በመጨረሻም ብሄራዊ ሶሻሊስቶች ተሸነፉ፡፡

ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያን ለመቅበር የጎሳ ፌዴራሊዝምን ጉድጓድ ቆፈረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጎሳ ፌዴራሊዝም እራሱን ዘ-ህወሀትን ለመቅበር በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

በኦሮሚያ ላይ እንደተደረገው ሁሉ እያንዳንዱ በዘ-ህወሀት የተፈጠረ ክልል ወደ ኋላ የሚገፋ ከሆነ ከዘ-ህወሀት የሚተርፈው ምንድን ነው?

“ጉድጓድ የሚቆፍር ሁሉ እራሱ ይገባበታል፣ እንደዚሁም ሁሉ ድንጋዩን ማንከባለል የሚጀምር ሁሉ እራሱ ድንጋዩ በእራሱ ላይ ይጫነዋል“ ተብሎ ተጽፏል፡፡

ይህ እውነተኛ አምላካዊ ቃል ነው፡፡ ከዚህ ጋር ስምምነት አድርጉ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!         

ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም

Filed in: Amharic