>

ስደት የፍርሃት ውጤት ነው [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroከሁለት ቀኖች በፊት ስለበእውቀቱ ሥዩም አድናቆታቸውን በፌስቡክ ላይ የገለጹ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ለበእውቀቱ ያላቸውን አድናቆት እኔም እጋራቸዋለሁ፤ ነገር ግን የእነዚህ ሰዎች አድናቆት በእውቀቱ ራሱንና ማንነቱን እንዲከዳ ይቃጣቸዋል፤ አንዱን አውቀዋለሁ፤ ከፖሊቲካና ከትጥቅ ትግል ወደስደት ‹‹ነጻነት›› የተሸጋገረ ያሬድ ጥበቡ የሚል የሚያኮራ ስም ይዞ የስደት መምህር የሆነ ነው፤ ሁለተኛው ሚስተር ቴዲ ገብርኤል ይባላል፤ እነዚህ ሁለት ስደተኞች በእውቀቱ ሥዩምን በጣም ስለሚወድዱትና ስለሚያከብሩት በአሜሪካ ስደተኛ ሆኖ እንዲቀርላቸው ይፈልጋሉ፤ በዚህ ብቻ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ስሜት መገመት በጣም የሚያሳዝን ነው፤ ወደዝርዝር አልገባም፡፡
በዚያው እነሱ አስተያየታቸውን በጻፉበት ገጽ ላይ የራሴን አስተያየት ለጥፌ ነበረ፤ በበነጋታው ባየው የሁላችንም አስተያየቶ ድራሻቸው ጠፍቷል፤ አንድ ቀን ሙሉ ፈልጌ አጣኋቸው፤ ያሬድ ጥበቡና ቴዲ ልዩ ዘዴ እንዳላቸው አላውቅም፤ ሌላም ሰው ያንን ጽሑፍ ለማጥፋት ምን ምክንያት እንዳገኘ አላወቅሁም፤ ለማናቸውም ያንን ሀሳቤን እንዲያውም አስፋፍቼ ለማቅረብ ዕድል አገኘሁ፡፡
ያሬድ ጥበቡና ቴዲ በእውቀቱን በአሜሪካ ለማስቀረት የሚፈልጉበት ምክንያት ምንድን ነው? ምክንያቱን በትክክል እንኳን እኔ እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም፤ ግምቴን ግን ላቅርብና አይደለም ካሉ እንሟገትበት፤ አንደኛ ሊክዱት በማይችሉት ሐቅ ልጀምርና ሁለቱም ሰዎች በጣም ፈሪዎች ናቸው፤ ስለዚህም ፍርሃታቸውን ወደበእውቀቱ አዛምተው ጨለማን ተጋፍጦ በነጻነት ከቆመበት የማይመችና የማይደላ የእናቱና የአባቱ ዓለም ወደአሜሪካ የምቾትና የስድነት ባዕድ ዓለም ከእነሱ ጋር እንዲደባለቅ ይፈልጋሉ፤ ለምን እንዲደባለቃቸው ይፈልጋሉ? ትልቁ ጥያቄ ይሄ ነው፤ መልሱም እኔ እንደምገምተው እሱ እነሱን ሲሆን፣ እነሱ አሱን የሆኑ ስለሚመስላቸው ነው፤ ትንሽ ቢያስቡበት (ፍርሃት ለማሰብ ጊዜ አይሰጥም እንጂ!) በእውቀቱ እነሱን ሲሆን አሁን ያለውን ለነጻነት የመቆም ዋጋ እንደሚያጣና እንደሚያንስ መገንዘብ ጊዜ አይፈጅባቸውም ነበር፤ ቴዲም ሆነ ያሬድ ለበአውቀቱ ‹‹የቸሩት›› ፍርሃታቸውን ነው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ወኔ የሌላቸው የሚሆኑት እንደዚህ ያሉ የፍርሃት ጠቢባን በሰላ ዘዴ እየነደፏቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹አርቲስት›› እያለ ከሚጠራቸው ሰዎች ውስጥ በአንድ እጅ ጣቶች የሚቆጠሩ መኖራቸው አጠራጣሪ ነው፤ እኔ እርግጠኛ ሆኜ የማውቀው ቴዎድሮስ ካሣሁንን ነው፤ አሁን ደግሞ በእውቀቱ ብቅ ቢል በመንፈስ ከከሰሩት ከአላሙዲን ስብስብ ውስጥ ሊያስገቡት ይጥራሉ፡፡ (አላሙዲን በገንዘቡ ወርቅም ይግዛበት ወይም ሰው ገበያው ከፈቀደለት (በጎንደርኛ አማርኛ ወርቅ ባሪያ ማለት ይሆናል ሲባል ሰምቻለሁ፤) በብሩም ሆነ በወርቁ ላይ ባለመብት ነው፡፡
ፍርሃት የግል ነውና በፍርሃት ተገንዞ መኖርን አልቃወምም፤ አጥብቄ የምቃወመው ግን ፍርሃትን (ሕመምን) ወደሌላ ሰው ማስታለፍን ነው፤ ፍርሃት እንደማናቸውም ተላላፊ ሕመም በንክኪም ሆነ በንግግር ይተላለፋል፤ አጥብቄ የምቃወመው ወኔ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በፍርሃት ቆፈን እየተጠፈረ ስደተኛ እንዲሆን መገፋፋትን ነው፤ አጥብቄ የምቃወመው ለመብቱና ለነጻነቱ ግፉን እየተቀበለ የግፈኞቹን አረመኔነት በመንፈሳዊ ወኔው የሚጋፈጠውን ከምድረ ኢትዮጵያ እንዲጠፋ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ነው፤ እኔ አጥብቄ የምቃወመው ኢትዮጵያን በሀብት ደሀ የሆነች አገር ብቻ ሳትሆን በሰውም፣ በአእምሮም፣ በመንፈስም ደሀ የሆነች አገር እንድትሆን በማወቅም ባለማወቅም የሚደረገውን ጥረት ነው፤ የፈረንጅ አገር ኑሮ እንደሚደላና እንደሚጥም እያየን ነው፤ በፈረንጅ አገሮች ላይ የሚውለው የኢትዮጵያ አካል፣ አእምሮና መንፈስ በኢትዮጵያ ላይ ቢውል ኢትዮጵያም የምትደላና የምትጥም አገር ልትሆን ትችል ነበር፤ ጠፍሮ የያዘንን ሰንሰለት በጣጥሰን ችሎታችንን ሁሉ በግንባታ ላይ እንዳናውለው ባንድ በኩል ፍርሃት በሌላ በኩል የሥልጣን ፉክክር አደንዝዞናል፡፡
ቴዲ ገብርኤል በእውቀቱ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በመፈጠሩ አኮራለሁ›› ይልን ወዲያውኑ ያንን በኢትዮጵያ ውስጥ በመፈጠሩ የኮራበትን በእውቀቱን ለስደተኛነት ያጨዋል፤ በእውቀቱ በአሜሪካ ስደተኛ ሆኖ ቢቀር በቁሙ ሞቶ ኢትዮጵያ አላጣችውም?አያድርግበትና በእውቀቱ አገሩ ገብተ ወያኔ ቢገድለው ወይም ቢያስረው በወያኔ አረመኔነት በእውቀቱ ሕያው አይሆንም?
ሌላው ያልታሰበው ጉዳይ በሚስተር ቴዲ አስተሳሰብ ‹‹የሚያኮሩ›› ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከአገር ከወጡ አገሩ በሙሉ የነሚስተር ቴዲ መሆኑ አይደለም እንዴ! እግዚአብሔር ያውጣን! በእውቀቱንም በደህና ይመልሰውና በአገሩ በሰላም ያኑረው!
ለቀልድ የተባለነው ማለት ‹‹ቢያዩኝ እስቃለሁ፤ ባያዩን እሰርቃለሁ›› የሚለውን ዘዴ መከተል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በተለይ በደርግና በወያኔ የአገዛዝ ዘመናት በብዛት ለስደት መደረጋቸውን ማንም የሚያውቀው ነው፤ የስደቱ ምክንያት ብዙ ነው፤ ስደተኛው ሁሉ አይወቀስም፤ ነገር ግን የሚወቀሱ ሞልተዋል፤ ምናልባትም የኢትዮጵያን ስደተኞች ልዩ የሚያደርገው ስደተኛውና አሳዳጁ በአንድ አገር ስደተኞች ሆነው፣በአገራቸው ተከባብረው መኖር ያቃታቸው ሰዎች በሰው አገር በግዳቸው ተከባብረው መኖራቸው ነው፤ መቻቻል ማለት እንዲህ ነው!

Filed in: Amharic