>

ከዋሺንግተን ስንብት [መስፍን ወልደ ማርያም]

ኅዳር 1/2008

profeser Mesfen Weldemariam Quateroወደ አሜሪካ ከመጣሁ ሁለት ወሮችን እያስቆጠርሁ ነው፤ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ወደ አሜሪካ የመጣሁት ደስ እያለኝ አልነበረም፤ ምክንያቱም አሜሪካን ወይም ሕዝቡን ጠልቼ ሳይሆን፣ ከ1965 ወዲህ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ላይ የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው ጉዳት በጣም ስለተሰማኝ ነበር፤ ነገር ግን በአገር ቤትም በአሜሪካም ያሉ ወዳጆች ያሳደሩብኝ ጫና አሸንፎኝ ወደአሜሪካ ሄድሁ፡፡
አሜሪካን የማውቀው ከስድሳ ዓመታት በፊት ጀምሮ ነው፤ የአሜሪካንን ሕዝብ አከብረዋለሁ፤ እወደዋለሁም፤ ርኅሩኅና ቸር ሕዝብ ነው፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለሕጋዊ ሥርዓት ያለውን ጠንካራ አቅዋም አከብራለሁ፤ ነጻነትን እኩልነትንና ሕጋዊ ሥርዓትን ለኢትዮጵያም እመኛለሁ፡፡
ወደአሜሪካ እንድመጣ አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ ችለው፣ ስመጣም በታላላቅ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ ልዩ አቀባበል ተደረገልኝ፤ በዋሺንግተንዲሲ የተደረገልኝ አቀባበልና መስተንግዶ በሄደሁባቸው ሌሎች ከተማዎች ሁሉ ተደጋገመ፤ ይህ ሁሉ በጭራሽ ያልጠበቅሁት ነበር፡፡
ይህንን ያቀባበልና የመስተንግዶ በጎ ተግባር ያሳዩኝ ሰዎች ሁሉ የራሳቸው በጎ ፈቃድ ፈንቅሏቸው ነው እንጂ እኔ ለበጎ ተግባራቸው ብቃት ኖሮኝ አይመስለኝም፡፡
ብዙ ሰዎች ስለኔ ከሚናገሩት ስነሣ ምናልባት እኔን ከብዙዎቹ ሌሎች የእኔ ትውልድ ጓደኞቼ የሚለዩኝ ሁለት የሕይወት መመሪያዎችን ያዘለ ገና የሃያ አንድ ዓመት ጎረምሳ በነበርሁበት ጊዜ ለራሴ የገባሁት ቃል ኪዳን ይሆናል፤ መንገዳገድ ባይቀርም እነዚህን መመሪያዎች በተቻለኝ መጠን ልከተላቸው ሞክሬአለሁ፡፡
አንደኛው መመሪያ ሁሌም ነገን እያሰብሁ መኖር ነው፣ ቃሌም ሆነ ተግባሬ ነገ የሚያስከትለውን ኮተት በቅድሚያ ዛሬ ማየት ልማዴ አደረግሁ፤ ዛሬ የምናገረውም ሆነ የማደርገው ሚዛን ላይ የሚወጣው ነገ መሆኑን አውቃለሁና ሁሌም አስበዋለሁ፡፡
ሁለተኛው መመሪያዬ የሙያና የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት በተግባር ለማሳየት ለራሴ የገባሁት ቃል ኪዳን ነው፤ በየወሩ ለማገኘው ደመወዝ ራሴን ብቁ ለማድረግ መሞከርን ግዴታዬ አድርጌ ተቀበልሁት፤ ምናልባትም የዚህ ቃል ኪዳን ማረጋገጫ ዶክተር ለመባል ከሁለት እስከሦስት ዓመታት አለማጥፋቴ ይሆናል፤ ብዙ ሰዎች ባያውቁትም (Rural Vulnerability to Famine in Ethiopia: 1958-1977) በሚለው መጽሐፌ ዶክተርነትን ከዚያው ከተማርሁበት የታወቀ ዩኒቨርሲቲ በሥራዬ አግኝቼዋለሁ፤ ለጌጥ ብዬ ስላላገኘሁት ለጌጥ አልጠቀምበትም፤ ደመወዝ እየተከፈለኝ በሥራዬ ያገኘሁት ነው፡፡
ስለዚህም ለሠራሁበት ሁሉ ተከፍሎኛል ብዬ ወደማመኑ አዘነብላለሁ፤ ነገር ግን የተከፈለኝን ያህል ሠርቻለሁ ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር ያዳግተኛል፡፡
ሁሌም የማስባቸው ፊደል አስቆጥረው ዳዊት ያስደገሙኝን አለቃ ታምራት የሚባሉ የጎንደር ሊቅን ነው፤ ቀይ ሣንቲም ሲከፈላቸው አላየሁም፤ ጊዜና ተለዋዋጭ የኑሮ ሁኔታ የአለቃ ታምራት ተማሪዎችን ቢበታትነንም እንደማውቀው ከፈለኝ ይብዛ የሚባል ጄኔራል፣ እሙን የሚባል የቅኔ ሊቅና ጠበቃ አፍርቷል፡፡
አለቃ ታምራትና በሺዎች የሚቆጠሩ እንደሳቸው ያሉ አስተማሪዎች በኢትዮጵያ በሙሉ የከፈቱትን የብርሃን መንገድ ያለክፍያና ያለምስጋና ለደለደሉት ሰዎች የእኔን ዕድል ሳያገኙና ውለታቸው ሳይታወቅ ለቀሩ ሁሉ ያለኝን ክብርና ውለታ ከልቤ እገልጻለሁ፡፡
በበጎ መንፈስ ተነሣስተው እኔ ወደአሜሪካ እንድመጣ የለሌሎችን በጎ ፈቃድ ቀስቅሰውና አስተባብረው ወደአሜሪካ እንድመጣና ከዋሺንግተንዲሲ ሌላ አራት ሌሎች ከተማዎችን እንድጎበኝ ያደረጉት የሚከተሉት ናቸው፡—
ታማኝ በየነ
ጌታሁን ካሳሁን
ባንታምላክ ካሳሁን
ቸርነት ሀብተ ጊዮርጊስ
ክባዱ በላቸው
አንተነህ ማስረሻ

በየሄድሁባቸው ከተማዎች እየተቀበሉ የተንከባከቡኝ የሚከተሉት ናቸው፡–

በአትላንታ፡– ዓለሙ ያይኔ፣ መርዕድ በቀለ፣ ቸሩ ተረፈ፣ ጌታቸው ለገሰ
በዳላስ፡– ድጅኔ አሳየ፣ ሚሚ ክፋለ
በላስ ቬጋስ፡– ጌታድጉ ወልደ ማርያም፣ ኢትዮ-ቪዥን ላስ ቬጋስ ኮሚቴ
ቦስተን፡– ሰሎሞን ለማ፣ ለዓለም ዘነበ

ለእነዚህና ለተባበሯቸው ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናዬን እያቀረብሁ እነሱም ሁሌም አሳቢ እንዲያገኙ እመኝላቸዋለሁ፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ለዜጎችዋ ሁሉ የምትመኝ አገር ሆና እነሱም በወዳጅ-ዘመድ መሀል በአገራቸው የሚኖሩበት ጊዜ ለማየት ዕድሜውን እንዲሰጣቸው ከልቤ እመኛለሁ፡፡

Filed in: Amharic