>

በትግሉ መንገድ ላይ [ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዝዋይ እስር ቤት ]

(ለኢሳት የተላከ ፁሑፍ)

Journalist Temesgen Desalegn‹‹እነሆ በረከት›› እንዲል ስብሐት ገ/እግዚአብሔር (‹‹ከስብሐት ነጋ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም›› እንዲሉ ፕሮፍ) ይህች መጣጥፍ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ‹‹እነሆ በረከት›› ተባለች፡፡ መቼም ወያኔ ኢሳትን መዝጋት እንደ ጋዜጣ መዝጋት አልቀለለውምና፤ በብርቱ እየተፈተነበት መሆኑን መስማቱ በራሱ ልብ የሚያሞቅ ደስታን ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ለግፉአን ከሚቆረቆር አዋጅ ነጋሪ ተርታ መሰለፍ ታላቅ መሰጠት ነውና ‹ምስሌክሙ› ብለን መርቀን ወደ ርዕሰ-ጉዳያችን  እንለፍ፡፡
ከሁለት አስርት በላይ ያስቆጠረው የፀረ-ወያኔ ትግል ዛሬ ድል በራፍ ላይ መድረሱ በግላጭ የሚታይ እውነታ ሆኗል፡፡ ተወዳጁ የአንጎላውያን የነፃነት መዝሙርም፡- ‹‹ትግሉ ቀጥሏል ድሉ አይቀሬ ነው (A Luta continua A Vitoria é Certa)›› …. ከሑመራ እስከ ባሌ፣ ከሽሬ እስከ ጎዴ መናፈሱ… ረዥሙ የእስር ቤት ግንብ ውጦ ያላስቀረው ብስራት ሆኗል፡፡ ወቅቱም አንድም በትግሉ መንገድ ላይ የተሰነደሩ ግብረ-ይሁዳ በጥንቃቄ
የሚመነጠሩበት፤ ሁለትም ስለአዲስቷ ኢትዮጵያ በብሔራዊ መግባባት የሚነጋገሩበት ሰዓት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሊያ በአያሌ ወንድም-እህቶች
መስዋዕትነት እየተመዘገበ ያለው አኩሪ ድል በክላሽ የሚቀለበስበት ሳልሳይ የታሪክ ምፀት ሊከሰት ይችላል፡፡
(ከመሬት ለአራሹ-አብዮት መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ከወያኔ አመፅ-መለስ ዜናዊ መሰረፃቸውን ከቶም ሊዘነጋ አይገባም)፡፡ በግልባጩ ‹‹ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፤ የኢኮኖሚ ዕድገታችንን አድንቆ፣ ልማታዊ መንግሥታችንን አወድሶ፣ በናኒ ህንፃ ተመስጦ፣ በባቡር ሀዲዳችን ተከይፎ ሄደ…….››የሚለው ዳንኪራ፣ ለአሰቃቂ ችጋርና ድርቅ ቦታውን ለቋል፡፡ ይህም ሆኖ በሕዝብ ላይ መቀለድ የአስተዳደር ዘይቤ ሆኗልና ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹‹….ካሊፎርኒያም ድርቅ ገብቷል፤ አውስትራሊያም ተጠቅቷል….›› እያለ የመሬት ቅርምት ያንጋጋቸውን ዲያስፖራዎች
ሲያስጨበጭብ ካመሸ በኋላ፣ መልሶ እነዚሁ ሀገራት ስንዴ እንዲረጥቡት ደጅ መጥናቱ በዋና ዜናነት በኢቲቪ እየተላለፈ ነው፡፡ ሌላኛው ቧልት ደግሞ ድርቁ እንደበሰለ ሾላ እያረገፋቸው ወዳሉ ወገኖቻችን ዘንድ ሄዶ፣ ‹‹እንወያይበት›› ሲል መሰማቱ ነው፡፡ (ይሄን ጊዜ ነው፡-
‹‹ለጠገበው ጥይት፣ ለራበው እንጀራ
የጀግኖቹ ሀገር እንደምነሽ ቋራ›› ማለት)

በትግሉ መንገድ ላይ ፩ 

በበርካታ ሀገራት የተካሄዱ አብዮቶች ታሪክ የሚነግረን፣ የውስጥ አደናቃፊ ኃይሎች ከዋነኛ ጠላት የማይተናነስ ችግር ፈጣሪና አውዳሚ ሆነው የመገኘታቸው አጋጣሚ መብዛቱን ነው፡፡ የዘመነ-ኢህአዴጓ ኢትዮጵያም ለዚህ ዓይነቱ አደጋ በቀላሉ ተጋላጭ ተደርጋ ተበጅታለች፡፡

በተለይም የብሔር ልዩነትን አጋንኖ ማራገብ፣ ታሪክን ፖለቲካ አስመስሎ የማቅረቡ ረብ-የለሽ ‹‹ትንተና››፣አንዱን ጎሳ በፖለቲካ-ኢኮኖሚ  ጠቃሚነት የመውቀሱ አባዜ፣ በያ ትውልድ አብዮት አስከፊ መስዋዕትነት የተከፈለበት ለድርጅት የበላይነት መተጋገል፣ የለውጡን መንፈስ ወደ መንበረ-መንግሥት አብዮትነት ለማውረድ ያሰፈሰፉ ልሂቃን ቁጥር የትየለሌነት፣ እንደ ወያኔ መሪዎች በትግሉ ማግስት የቢሊዮን ረብጣ እና የሠማይ ጠቀስ ህንፃ ጌትነትን ለመሸመት የቋመጡ በተቃውሞ ስብስብ ውስጥ ማድፈጣቸው ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ እናም ከወዲሁ መፍትሔ ካልተፈለገለት አራት
ኪሎን በቅርብ ርቀት እየተመለከቱ የጭቆናውን ዕድሜ እንደ ጨቋኞቹ ምኞት ለቀጣዮቹ አርባና ሀምሳ ዓመታት መራዘሙ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ነፃነትን ለማወጅ የተጋረጡ እንቅፋቶችን ነቅሶ ማውጣትን፤ የአገዛዙን ስስ-ብልት (የአኪለስ- ተረከዝ) ፈትሾ ማተኮር፤ የጭቆና  መሣሪያዎችን ማዳከም ጨምሮ የትግሉን በጎ ጎን አጎልብቶ ድክመትን አርሞ መጓዝ ሳይዘነጋ የሚተገበር ግዴታ ነው፡፡

በትግሉ መንገድ ላይ ፪
ሌላኛው በዚህ አውድ የሚነሳው ከለወጡ በኋላ (በድህረ-ኢህአዲጓ ኢትዮጵያ) የሚነብረው አስተዳደር ይዘትና ቅርፅ ጉዳይ ነው፡፡ አቴናዊው ፈላስፋ አርስቶትል ‹‹አሮጌው አምባ-ገነን በአዲስ አምባ-ገነን የሚተካበት ዕድል ሰፊ ነው›› እንዲል፤ በሽግግሩ ከወያኔ ወደ ወያኔ ሆኖ የጠገበው ወርዶ የራበው እንዳይተካ በትግሉ መንገድ ላይ ቆም ብሎ መገምገሙና የተሻለውን መቀመሩ ቀዳሚ-ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ (በመጨረሻዋ ሰዓት ታሪክ ራሷን መድገሟን ለማስታወስ የአፄውንየተንበሸበሸ ሰማንያ ምናምነኛ የልደት ክብረ-በዓል እና የ66ቱን አስከፊ ረሀብ፤ የአስረኛውን የደርግ የኢሠፓ
ምሥረታ በዓል ቅጥ ያጣ ድግስ እና የ77ቱን ችጋር፤ የኢህአዴግን 10ኛ ጉባኤ ቸበርቻቻ እና የወቅቱን ዘግናኝ ድርቅ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡)
በአናቱም ከቀድሞ የወያኔ መሪዎች አንዱ ገብሩ አስራት ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚለው መፅሀፉ ላይ እንዲህ ሲል የገለፀው ተጨማሪ አስረጅ  ነው፡-
‹‹ኢህአዴጎች ደርግን ተክተን ሥልጣን ስንይዝ ማድረግ የነበረብን ሌላው ሥር-ነቀል ለውጥ የደርግን ዐፋኝ መዋቅሮች ማፍረስና በአዲስ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መዘርጋት ነበር፡፡ ሆኖም እንከተለው ከነበረው ቅይጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተነሳ ሥር-ነቀል ለውጥ ማካሄድ ካለመቻላችን ባሻገር፤ ደርግ አምባገነናዊ   ሥርዓቱን ለማስፈን ይጠቀምባቸው የነበሩትን ተቋማት ከበርሀ የሽምቅ ውጊያ አስተሳሰቦቻችንና ተቋሞቻችን ጋር አዳቅለን ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብትን የሚያፍኑ መዋቅሮችን ተክለን ነበር፡፡ ነፃ ፍርድ ቤቶችና የፍትሕ አካላትን ገለልተኛና አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠር ሕግ አስፈፃሚ፣ ከሕግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ሕግ አውጪ ተቋማትን፣ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን፣ ፍፁም ነፃና ገለልተኛ ሠራዊትን፣ ነፃና ገለልተኛ ፖሊስና ደህንነትን፣ ነፃ ሲቪል ማሕበረሰብንና ነፃ ፕሬስን ልናደራጅ አልቻልንም ነበር፡፡ መሠረታዊ የአስተሳሰብና
ተቋማዊ ለውጥ ሳይደረግ ባቋቋማቸውና ባስቀጠላቸው ተቋማት ማዕቀፍ አገርን የሚመራ ማንኛውም ግለሰብ፣ቡድን ወይም ፓርቲ ዞሮ ዞሮ አምባገነን ከመሆነ አያመልጥም፡፡›› (ገፅ 149)
በጥቅሉ መንጌ ‹‹በአንድ እጃችን እየተዋጋን፣ በአንድ እጃችን እናመርታለን›› እንዳለችው፤ ከትግሉ ጎን ለጎን አንድም በአገዛዙ ላይ እየበረቱ ያሉ ውጥረቶችን በመረዳት፤ ሁለትም ከዳይሌክቲካል ሕግ (ቲዎሪ) አኳያ ግንባሩ ዕድገቱን ጨርሶ ወደሚከስምበት ጠርዝ መጠጋቱን ማስተዋል፣ ከለውጡ በኋላ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች፣ የነፃ ሚዲያ ልዕልና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ማሕበራዊ ፍትሕ እና ሌሎች
ተያይዘው መመለስ የሚገባቸው ወሳኝ ጥያቄዎችን በብስለት ከወዲሁ መፍታቱ ለውጡን ከመፈንቅለ- መንግሥት፣ ከአዲስ አምባገነን ሥርዓት፣ ከብጥብጥ እና መሰል ክሽፈቶች ከመታደጉም ባሻገር፤ ዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መደላደል ይፈጥራል፡፡ ይህን ማድረጉ ካልተሳካ ግን ታሪክ አብዮቱን ለመጭው ትውልድ በአንዲት ዐረፍተ-ነገር ብቻ እንዲህ ሲል ማስተላለፉ አይቀሬ ይሆናል፡-‹‹ቀድሞውንም ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም!››
እንደማጠቃለያ
የሕዳሴውን አብዮት በተሟላ አንፀባራቂ ድል ለማጀብ ከላይ በጨረፍታ ያነሳኋቸው ሁለት ጉዳዮች ዋነኞቹ ቢሆኑም፤ ያልተጠናቀቀ የቤት ሥራም አለ፡፡ ከአፋፍ ቆሞ አንዱን የትግል ስልት ባርኮ፣ ሌላውን መርገሙ ከወያኔ በቀር ማንንም አለመጥቀሙን የሚመለከት፡፡ ፈረንጅናው ‹‹በመጨረሻው ሰዓት ከጠጣሩ እውነታ ጋር መላተሙ ግድ ነው›› እንዲል፤ በስመ-አብዮተኛ የጭቆናው ደቀ-መዝሙርት ሆነው የገዛ ጓዶቻቸውን
በ11ኛዋ ሰዓት ላይ የሚከዱትን እንደ ገለባ አበጥሮ ማንገዋለሉ የትግሉ አካል ነው፡፡ (በቅርቡ ከደምሒት የኮበለለውን ሞላ አስገዶምን የእስር ቤት ጓደኞቼ ‹‹ሞላ አስክዶ›› የሚል የዳቦ ስም አውጥተውለታል፡፡ያው ‹በባሌ ስንጠብቀው በቦሌ መጣ› ለማለትይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ይህን መሰል ንቅናቄ ከባድ ፈተናዎች የሚጋረጡት ገና ሲመሰረት የትም አይደርስም በሚል ቀቢፀ-ተስፋ ታክተው በሚያፈገፍጉ፣አሊያም በኃይል ደርጅቶ በቤተ-መንግሥት ቅርብ ርቀት ላይ ሲቆም ሥልጣን አነሰን በማለት አኩርፈው በሚነጠሉ የአመራር አባላቱ መሆኑን ተንታኞች ያስረግጣሉ)

የሆነው ሆኖ ጥንት በአፄ ዮሐንስ ዘመን፡-

‹‹ወገራ አሰላፊ፣ ደንቢያ እንጀራ ጣይ፣
ተበላህ ጎንደሬ አትነሳም ወይ?›› ተብሎ መቀኘቱን ሰምተን ነበር (ጥያቄ አንድ – በዚህ አውድ ጎንደር ምንን ይወክላል? ጥያቄ ሁለት – ጎንደር ምን አዲስ ወሬ አለ?) ….. ይህችን አጭር መጣጥፍ ለመቋጨት ሳስብ ድንገት ደርሳ በአእምሮዬ የተመላለሰችውን ብስራት አልቦ ስንኝ ማስፈር ወደድኩ፡-
‹የባሰ አታምጣ› ብሎ መታገስ፣
ጭቆናን መምረጥ ነው ሰርክ ለማልቀስ!!
ድል ለሠፊው ሕዝብ!!!

Filed in: Amharic