>

እስረኞቹን ብቻ ሳይሆን የራሳችሁንም ችግር ፍቱልን [አሣዬ ደርቤ]

  • Zone 9 blogers picዛሬ የዞን ዘጠኞችን መፈታት ስሰማ የተሰማኝ ደስታ ልዩ ነበር፡፡ ግን ይሄ ደስታ አብሮኝ አልቆየም፡፡ እንዲያውም ሲታሰሩ ከተሰማኝ የበለጠ መከፋት ነው የተሰማኝ፡፡
    መቶ ፐርሰንት ስልጣንን ሸክፎ ይዞ ኮሽ ባለ ቁጥር እራሳቸው በላኩት ኢሜይል ትንሽ የነቀፋቸውን ሁሉ እየለዩ አሸባሪ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ሰበብ አመታትን ከሕይወት ላይ እየቀሙ የደህንነት ስሜት በተሰማቸው ሰዓት ደግሞ ‹‹ብርድ ልብስህን ይዘህ ውጣ›› የሚል አካል የማፍያ ስብስብ እንጂ በህዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግስት ነው ሊባል አይችልም፡፡
    በጣም ያበሳጫል፡፡ እስካሁን ከተካሄዱት ውሳኔዎች ላይ በመነሳት ‹‹እዚህ ሀገር ላይ ተሸባሪ መንግስት እንጂ አሸባሪ ዜጋ የለም›› ብለን እንድንደመድም እያደረጉን ነው፡፡
  • ሁሌም ቢሆን ይሄ መንግስት ለኔ ዋስትናዬ ሳይሆን ስጋቴ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ነገረ ስራቸው ሁሉ ይሸክከኛል፡፡ ወፈፍ ያደረጋቸው ቀን ‹‹‹ያንን ልጅ እስከ ፌስቡክ ጓደኞቹ ጉፍፍ አድርጋችሁ ወህኒ ቤት ክተቱልኝ›› ብለው ቃለ-ጉባኤ ላይ የሚወስኑ ሁሉ ይመስለኛል፡፡
    ዝም ብለህ ስታየው የሀገራችን ህግ ከግለሰብ ጥቃት እንጂ ከመንግስት ውንጀላ የማዳን ጉልበት የለውም፡፡
ሌላው ደግሞ ከልማት በፊት መታመን ያስፈልጋል፡፡ የማይታመን መንግስት ስራዎቹን የሚያደንቅለት አያገኝም፡፡ የማይታመን መንግስት ያን ሁሉ ሀዲድ ዘርግቶ በፊደል ግድፈት ሲዘረጠጥ ይውላል፡፡ ምክንቱም ስራውን ለመውደድ መጀመሪያ ሰሪውን ልታምንበት ይገባል፡፡ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ሰው ልብ ውስጥ መግባት አይቻልም፡፡ በዚያ መልኩማ ህዝብን ማሸነፍ ቢቻል ጣሊያን እስካሁን ድረስ ይገዛን ነበር፡፡ ወደ ልማት ከመሮጣችሁ በፊት መጀመሪያ እኛ ጋር ተግባቡ፡፡ ‹‹መንግስቴ›› ብሎ የሚያወራላችሁ ዜጋ ፍጠሩ፡፡ እቃቃውን ትታችሁ ወደ እውነተኛ ምርጫ ተሸጋገሩ፡፡ ከዛ በኋላ ልማታችሁን ማድነቅ፣ ልማታችሁን ማገዝ እንጀምራለን፡፡ አሁንም ቢሆን ወህኒ ቤት ውስጥ የቀሩት ንፁሃን ልትፈቱ ይገባል፡፡
ህዝቡ ነፃነት የሚሰማው ከአገሩ ሲወጣ መሆን የለበትም፡፡ መስማት አለመስማት የናንተ ፋንታ ነው፡፡ እኛን ግን እንዳንናገር ዱዳ ማድረግ አይቻልም፡፡ የአፋችን ዋናው ጥቅሙ አንድም መብላት ነው፣ አንድም ማውራት ነው፡፡ ምግቡን ለናንተ ትተናል፡፡ ባባዶ ሆድ ማውራቱን ግን ፍቀዱልን፡፡

እውነት ለመናገር የመንፈስ ጭንቀት እንዳለባችሁ ተረድተናል፡፡ ስለዚህ ሆዳችሁ በተሸበረ ቁጥር፣ ስጋት ስጋት ባላችሁ ቁጥር ‹‹ይሄ ሰው አይነውሃው አላማረኝም›› እያላችሁ ሰውን ወህኒ ቤት ውስጥ ከምታበሰብሱ ጭንቀታችሁን የምትቀርፉበት ሌላ አማራጭ ማዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡
ለምሳሌ፡- ጭንቀት ላይ ሱስ ሲጨመር ጥሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሱስ ካለባችሁ ጋብ አድርጉት፡፡
በተጨማሪም ደግሞ ኢቲቪ ስቴድዮ ዉስጥ የሚቀናበሩ አሸባሪ ዶክመንታሪዎችን መመልከታችሁን ትታችሁ ‹‹ጭንቀትንና ሽብርን ለማስወገድ የሚረዱ አስራ ሰባቱ የሳይኮሎጅ ምክሮች›› የሚሉ መጽሃፎችን ከነ ዶፍተር እየተዋሳችሁ በማንበብ የሽብር ስሜታችሁን ብትፈቱ መልካም ነው፡፡
መልካም ምሽት።
መልካም ሰንበት፡፡
Filed in: Amharic