>
5:13 pm - Friday April 20, 9263

ዘውዴ ረታ - የታሪኩ ቀንድ ስብራት (1927 – 2008)

ሔኖክ ያሬድ

Ambassador Zewde Reta‹‹… ዘውዴ! ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ከሆነው ትውልድ መካከል እንደ አንተ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት አመራር በቅርብ የማየትና የመረዳት ዕድል ያገኘ ብዙ ሰው የለም፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ያየውንና የተረዳውን፣ ጣዕም ባለው ጽሑፍ አብራርቶ ለመግለጽ ተሰጥኦ ያለው እንደ አንተ የመሰለ ጸሐፊ ብዙ የለም፡፡ ስለዚህ በእኔ አመለካከት ሁለት የተጣመሩ ዕድሎች በአንተ እጅ ተይዘው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ታሪኩን የማወቅና የጽሕፈት ችሎታህ ናቸው፡፡ ስለዚህ እኔ አጥብቄ አደራ የምልህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ጉዳይ አንተ ዕድል አጋጥሞህ ያየኸውንና ከአዋቂዎች ዘንድ ቀርበህ ያጠናኸውን እውነተኛውን ታሪክ ገልጠህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጻፍለት፡፡ ለዚህ ሕዝብ ከአንተ በኩል ከዚህ የበለጠ የምታደርግለት ሊኖር አይችልም፡፡ አንተም አስበህ የጀመርከውን ለመፈጸም እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡ … እኛም ወዳጆችህ፣ ዕድሜና ጤና አግኝተን የምትደክምበትን ለማንበብ ያብቃን…››

ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አመራርን በቅርቡ የማወቅ ዕድል ለነበራቸው፣ ከእልፍኝ እስከ አደባባይ ከንጉሠ ነገሥቱ ያልተለዩትን ዘውዴ ረታን እውነተኛው ታሪክ ገልጠህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጻፍለት ብለው የተማፀኗቸው፡፡

ይህን የማበረታቻ ምክር መቼም ያልረሱት ዘውዴ ረታ አምና እጅግ ግዙፍ የሆነውን ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› አንደኛ መጽሐፍ ከነገሡበት 1923 እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ የሚሸፍነውን ታሪክ ለንባብ አደባባይ ያዋሉት፡፡

የአዲሱ መጽሐፋቸውንም የተለየ ፋይዳም እንዲህ አስቀምጠውታል፡፡ ‹‹እንግዲህ ማንም ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ኢትዮጵያ የነፃነት ችግር ያጋጠማት በሁለት ኮሎኒያሊስት በሆኑ አገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው የፋሽስቱ የሙሶሊኒ የግፍ ወረራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ነፃ አውጪዎች ነን ብለው በመጡት ወዳጆቻችን በምንላቸው በእንግሊዞች ወታደራዊ የሞግዚት አስተዳደር የተፈጸመብን በደል ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱም ኮሎኒያሊስቶች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የደረሰበት መከራና ፈተና በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ በተለይ አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው ስለሚያስፈልግ፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ታሪኩ በተቻለ መጠን ተዘርዝሮ ቀርቦለታል፡፡››

ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማትና ስመጥር የታሪክ ጸሐፊ (ሦስት ዓይና) የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዕረፍት በኋላ የነበረውን የልጅ ኢያሱን፣ የንግሥት ዘውዲቱ፣ ብሎም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታሪክ ትክክለኛውን ሒደት የዘመኑም ሆነ መጪው ትውልድ ማወቅ ያስፈልጋል በሚል ነበር የታሪክ መጽሐፋቸውን ‹‹ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ›› ለኅትመት ያበቁት፡፡ ‹‹በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኤርትራ ጉዳይ 1941-1963›› ሌላው በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ታሪካዊ መጽሐፍንም እነሆ ብለዋል፡፡

የኤርትራን ጉዳይ የተመለከተው መጽሐፋቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው በዶ/ር ኃይሉ ሃብቱ አማካይነት “THE ERITREAN QUESTION” በሚል ተተርጉሞ ለሕትመት ዝግጁ መሆኑም ይነገራል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለበት ከ1948 ዓ.ም. በኋላ የነበረውን በለውጥ የታጀበው ዓቢይ ዘመን የሚያወሳውን መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፡፡ በተለይ በለንደን (እንግሊዝ)፣ ፓሪስ (ፈረንሣይ) እና ሮም (ኢጣሊያ) ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ስለ ዘመነ ኃይለ ሥላሴ የሚያወሱ ሚስጥራዊ ሰነዶች በቅርቡ ክፍት መሆናቸውን ተከትሎ፣ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ነበር መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ባሕር ማዶ ያቀኑት፡፡ ያለሙት የዘመናት ሕልም እውን ሳያደርጉት ተቀጨ እንጂ፡፡ ሞት ቀደማቸው፡፡ የጥናታቸው ቀዳሚ መነሻ ባደረጉት ለንደን ከተማ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በድንገት አርፈዋል፡፡

በኢጣሊያና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ዘውዴ ረት የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1927 ዓ.ም. ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በፊት ደጃዝማች ገብረ ማርያም የአርበኞች ትምህርት ቤት በሚባለው፣ ከዚያም ሊሴ ገብረ ማርያም በተባለው ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አንባቢነትና በቤተ መንግሥት ዜና አቅራቢነት ተቀጥረው ያገለገሉ ሲሆን፣ በፈረንሣይም በጋዜጠኝነት ተመርቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ድምፅ ዕለታዊ ጋዜጣና ወርኃዊው መነን መጽሔት ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የፓን አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት፣ የማስታወቂያ ረዳት ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርም ነበሩ፡፡ በዘመነ ደርግ የስደት ዘመናቸውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ የመንግሥታት ግንኙነትና የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው ለ13 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ሦስት ዓይናው ዘውዴ ረታ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ለሃያ ሁለት ዓመት በላይ ላበረከቱት ውጤታማ ተግባር ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የምኒልክ የመኰንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኰንን ኒሻን ተሸልመዋል፡፡ ከተለያዩ አገሮችም ኒሻኖችን የተሸለሙ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በባሕር ማዶና በአገር ውስጥም ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡

ከ49 ዓመት በፊት ከወይዘሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ጋብቻ መሥርተው ሦስት ልጆች ያፈሩት አምባሳደር ዘውዴ አስከሬን፣ በሳምንቱ መገባደጃ ከእንግሊዝ መጥቶ ሥርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Filed in: Amharic