>
5:13 pm - Monday April 18, 0411

የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በሰፊው አደባባይ !!

ከኮንሰርቱ ጎን ለጎን ያለና የነበረውን እንጨዋወት ዘንድ ….
(አሌክስ አብርሃም)

Tedros Kasahun by Alex Abrhaእነሆ የጥበብ አጋርነታችንን ልንገልፅ ከብዙ መቶ ሽዎች ወገኖቻችን ጋር ቁመናል ….የድምፃዊ ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት በፌስቡል ዛሬ ማታ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ይከበራል !! በሚሊየን የሚቆጠሩ በመላው አለም የሚገኙ የፌስቡክ የቲውተር ተርቲበኞች ባሉበት ሰፊ እጅግ በጣም ሰፊ አደባባይ ላይ … የሰራን ልናሞግስ ኪነጥበብ ከየትኛውም የሰው ልጆች ተራ ጥላቻና ተንኮል በላይ መሆኗንም ልናሳይ ዘር ሃይማኖት ቦታ ሳይለየን በአዲስ አመት ዋዜማ ይሄው ፌስቡክ ላይ ሽክ ብለን ተገኝተናል !ቴዲ አፍሮን በስራው እንወደዋለን !! ይሄው ነው …ለምን ወደድነው ግን …??? ተዲ ዘፋኝ ስለሆነ ብቻ ነው ?….አይደለም!! ቴዲ ምርጥ ገጣሚ ስለሆነ ብቻ ነው ?….አይደለም !! ቴዲ በጥረቱ ታዋቂ ስኬታማ ስለሆነ ብቻ ነው ?… አይደለም !! ቴዲና ብዙሃኑ ኢትዮጲያዊ ወዳጆቹ ከዚህም የመረረ ትስስር ከዚህም ያለፈ የነብስ ወዳጀነት እንዲኖረን ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉን ……ከሙሉ ፍቅርና አክብሮት በድክመቱ እየወቀስን ብቃቱንም እናውጃለን …..

ማነህ ቁጠርልኝ …..አንድ በል ….እኛ ደሃ ህዝቦች ነን …ለስኳር የምንሰለፍ …ለታክሲ የምንሰለፍ በሊሞንዚን የምንታለፍ … ኪነጥበብ እኛን ለማስቀናት የተፈጠረች እስኪመስለን ሙዚቃዎቻችን ውስኪ መራጫ የቆንጆ ሴትና ሃብታም ኑሮ መፈንጫ ሁነው ሆድ ሲያስብሱን ይሄ ቴዲ አፍሮ የሚባል ልጅ መጣና ድህነታችንን ዘፈነው… እኛም ዘፋኞቻችንን ዝፈኑልን ሳይሆን እኛን ራሳችንን ዝፈኑን ነበር ያልነው ቴዲ ዘፈነን !! እኛን ሁኖ እኛን መስሎ ፍቅራችንን እንዳፈቀርናት አስቀመጣት ! ደስም አለን !!

ና ወዲህ ተባብለው በደላው መድረክ ተጋብዞ ተራምዶት እኛ ደሆቹ ጋር ባዶ ሜዳ ላይ ቁሞ ከድሃ ወገኖቹ ጋር …ብሶታችንን ሆድ ብሶት ዘፍኖልናል …. !! ብትፈልጉ ‹‹አርት ፖለቲክስ›› በሉት ቢያሻችሁ ያሻችሁን በሉት …ብቻ ቴዲ መድረክ ላይ እኛ ከስር ሳይሆን ….ቴዲ መሃላችን ተገኘ …እኛን ሆነ እኛም እሱን መሰለን !! ውቡን አዳራሽ ግድግዳና ጣራውን ትቶት መጣና….‹‹እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር !!›› አዳራሽ ውስጥ ተሁኖ ‹‹ኮከብ ሰዎች…ሃብታም ሰዎች ›› እንጅ የግዜር ኮከብ አይቆጠርማ ! ይመስክር ስቴዲየም …ውጭ አድረን ኮከቡን ከነጨረቃው ከነእግዜሩ እያን ደስስስስ ብሎን አመሸና ማን ጋር ቴዲ ጋር ! ያኔ ከወደዛ ግድም ርችት ወደሰማይ ሲተኮስ ከወደስቴዲየም የሽዎች የሃሴት ፈገግታ ምድሩን አንቆጥቁጦት ነበር …ደግሞኮ አላኮረፍንም … የኑሮ ልዩነቱን ወደአንድነት ጠራውና አስጠራን እንጅ …..እንዲህ ነበራ ቅኔው
‹‹ብንኮራረፍ ጠላት ይስቃል
ያገርህ ሰርጓስ በማን ይደምቃል
አሳልፈናል ክፉ ደጉን …
ቃል ኪዳን አለን እንዳይለየን›› !

8ሁለት በልልኝ …..መሸብን …ምሽታችን ሲከፋ ቴዲ በተሰጠው መክሊት ኤሎሄ ብሎ ኤሎሄ አስባለና …. ‹አይነጋም ወይ › ሲል …ከምር ግን አይነጋም እንዴ ብለን አብረነው ጮኸናል … ኤችሁ በተለይ ለአንዳንድ ልማታዊ ዘፋኞች ጨለማ ጥሩ ነው ክለብ እንዲሰሩ ይረዳቸዋል …የክለብ መብራት ንጋት መስሎት የማይዘናጋ ከክለቡ ውጭ ያሉ ሚሊየን ህዝቦች ጨለማ ውስጥ መቆማቸውን አስቦ ‹‹አይነጋም ወይ ›› የሚል የህዝብ ልጅ ነው አልን ….እሱማ ለቀን ጉርሱ ላመት ልብሱ አልጨለመበት ስለእኛ እንጅ !! እና ወደድነው ! በቃ ወደድነዋ!

ሶስት በልልኝ ….(ቁጥር እንዳታሳስት አንተ ልጅ ) ….ዘራፍ አሉና ስለእኛ የቆሙት ከእኛ ከራሳችን ጋር አጋጩን ….እልፍ ደም ፈሰሰ ህዝብ ከህዝብ ተለያየ …ሌሎችን ሊጫን የሚዳዳው ፖለቲካችን ጉልበቱ ይሄው ነው …..እልቂትና ማለያየት ! ባለትዳሮች ተለያዩ ሚስት ከባል ባሎች ከሚስት …. ልጆች ከወላጆቻቸው እናቶች ከልጆቻቸው ….ፍቅረኞች ከፍቅረኞቻቸው ተለያዩ ግማሹ እዛ ግማሹ እዚህ መሃል ላይ የፖለቲካ ተራራ …የናፍቆት እንባ ከድንበር ወዲያና ወዲህ ….ልክ በዚህ ሰዓት ወጣቱ የኪነጥበብ ሰው ቴዲ መጣና መለያየትን በዜማ ግሬደሩ ጠራርጎ በተለያየ ህዝብ መሃል የኪነጥበብ ሃዲዱን ዘረጋው….. እናም የፍቅር ባቡሩን ሸከተፍ እያደረገ ያውም ህዝቡን ጢም አድርጎ ጭኖ ዳህላክ ላይ ዝርግፍ !ከነፍቅር ቤት መስሪያው …… ቢያንስ በመንፈስ አገናኘን …እና ….ወደድነው …ወደድነዋ !!

አራት በል ቆጣሪ ….ግን ግዴለም አረፍ እያልን …ማታ ከመቶ ሽዎች ጋር ዘና ብለን እንጨዋወታለን ….እኔ የምልህ ግና አደባባዩን ሰፋ ሰፋ እድርገው ዛሬ ማታ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ኮንሰርቱ እንደሚጀመርም ….በደንብ አሳውቅ …ቆይ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ በል…ማንንም ከማንም ሳትለይ ሁሉንም ጋብዝ …ኪነጥበብ በፍቅር ሁሉንም መሳብ እንጅ መግፋት …አንዱን ስባ ሌላውን መግፋት አይሆንላትማ ጃ ! ወደፊት !!

Filed in: Amharic