>

በእስር ቆይታዬ ወቅት ከጎኔ ለነበራችሁ ሁሉ [ርዕዮት አለሙ]

Reyot Alemu 3የፕሬስ ነፃነትን በማፈንና የሰብአዊ መብትን በመርገጥ የሚታወቀው የኢህአዴግ መንግስት የፈፀመብኝን እስር በመቃወምና በማውገዝ
እንዲሁም ያለቅድመ ሁኔታ እፈታ ዘንድ በመጠየቅ ከጎኔ ለነበራችሁ በሙሉ ምስጋናዬን የማቀርበው በታላቅ ትህትናና አድናቆት ነው፡፡
በነዚያ የጨለማ ቀናት አብሮነታችሁ ያልተለየኝ አለምአቀፍና ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡

ዩኔስኮ፣ አለምአቀፍ የሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን፣ ሚዲያ ሌጋል ዲፈንስ ኢንሼቲቭ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስዎች፣
ሲፒጄ፣ ፔን ኢንተርናሽናል፣ ዶሀ ፍሪደም ሴንተር፣ አርቲክል 19ንና ሌሎች ያልጠቀስኳችሁ በርካታ አለምአቀፍ ድርጅቶች ለጉዳዬ
የሰጣችሁት ትኩረት በኢትዮጵያ ያለውን አምባገነን ስርዓት በማጋለጥ በኩል ትልቁን ድርሻ ተጫውቷልና ከፍ ያለ ምስጋናዬን
አቀርብላችኋለሁ፡፡

መፈታቴን እንደራሳቸው ጉዳይ ቆጥረው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እንደ ማርቲን ሽቢዬ፣ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም፣ አና ጎሜዝ፣ ናኒ ጃንሰን፣ ክርስቲያን አማንፑርና ሌሎች ዘርዝሬ መጨረስ የማልችላቸው በርካታ ግለሰቦች ለጉዳዩ የነበራቸውን ጠንካራ መሰጠት አብዝቼ አደንቃለሁ፡፡

ምንም እንኳን በአስከፋ ሁኔታ ተገልዬ የቆየሁባቸውና ጤናዬ ተቃውሶ የነበረባቸው መጥፎ ጊዜያትን ያሳለፍኩ ቢሆንም ከእስር የወጣሁት ግን ሁኔታዎቹ ሞራሌን ሳይሰብሩትና ይልቁንም ለዲሞክራሲ በተለይ ደግሞ ለፕሬስ ነፃነት መከበር የምችለውን ሁሉ ለማድረግ የበለጠ ቁርጠኝነት ኖሮኝ ነው፡፡

በመሆኑም ለዲሞክራሲ ስለታገሉና ሀሳባቸውን ስለገለፁ ብቻ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ካለምንም ጥፋታቸው ታስረው የሚሰቃዩ በጣም
ብዙ አርበኞችና ጓዶች ከሀሳቤ አይለዩም ፡፡ ኢፍትሀዊነትን አምርራችሁ የምትጠሉ ኢትዮጵያዊያንም ሆናችሁ የሌላ ሀገራት ዜጎች ለነዚህ ሰዎች መፈታት ያላሳለሰ ጥረት ታደርጉ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡

በድጋሚ አመሰግናለሁ
ርዕዮት አለሙ

Filed in: Amharic