>

ኢሳት ሙሉ የ24 ሰአት ዝግጅቱን ጀመረ

ESAT 1ሐምሌ ፺፻ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በገዢው መንግስት ከፍተኛ አፈና የሚደርስበት የኢሳት የቴሌቪዝን ስርጭት ከሳምንታት ሙከራ በሁዋላ ዛሬ ሙሉ ስርችቱን በ ኤም 44 ሳተላይት ጀምሯል።

አዲሱ ሳተላይት ጠንካራ ሲግናል ያለው ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ በሙከራው ወቅት ስርጭቱን ለማፈን ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን የኩባንያው ኢንጂነሮች ገልጸዋል። ተመልካቾች አልፎ አልፎ የድምጽ ወይም የምስል መዛባት ቢያጋጥማቸው ስርጭቱን ለማፈን ከሚደረግ ሙከራ የመጣ መሆኑን እንዲያውቁት ኢንጂነሮች መክረዋል።

ኢሳት በዚህ ሳተላይት ለርጅም ጊዜ የሚያቆየውን ስምምነት ፈርሟል። ሌሎች ተጨማሪ ሳተላይቶችን ለመከራየት በድርድር ላይ ሲሆን፣ እንደተሳካለት ለህዝብ ያስታውቃል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሳትን ለማፈንና የኢሳት ጋዜጠኞችን ኮምፒዩተሮች ለመሰለለል ብዙ ሚሊዮኖችን እያወጣ ሲሆን፣ ለአንድ አመት ብቻ 1 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ሀኪንግ ቲም ለተባለ ድርጅት መክፈሉ ሰሞኑን የአለም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። ስለላውን ተከትሎ አንድ አሜሪካ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የከፈተው ክስ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ተከሳሹ ለኢሳት ተናግሯል። ለደህንነት ሲባል ስሙ እንዳይገለጽ የተፈለገው ከሳሽ ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በሰሞኑ ችሎት ላይ አለመገኘታቸውን ይሁን እንጅ በጠበቆቻቸው አማካኝነት መልስ መስጠታቸውን ገልጿል። ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው የቀጠሩዋቸው ጠበቆች ጠንካራና ታዋቂ ቢሆንም፣ በከሳሽ በኩል የቀረቡት የህግ ባለሙያዎች ለእውነት የቆሙ በመሆናቸው ያሸንፋሉ ብሎ እንደሚገምት ገልጿል። ፍርድ ቤቱ የኢህአዴግን መንግስት ጥፋተኛ ብሎ ከወሰነ ውሳኔው በአለም ላይ ስለላን በተመለከተ አዲስ የህግ አካሄድ እንደሚፈጥር ገልጿል። ውሳኔው በአሜሪካ የስለላ ድርጅት ላይ ሳይቀር ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥቷል።

Filed in: Amharic