>

ሰማያዊ ከምርጫ ማግስት እየተወሰደ ያለው እስርና ግድያ እንዲቆም ጠየቀ

Negere Ethiopia - News of blueparty

ነገረ ኢትዮጵያ

ሰማያዊ ፓርቲ ከ2007 ሀገራዊ ‹‹የውሸት ምርጫ›› ማግስት በገዥው አካል እየተወሰደ የሚገኘው ግድያ፣ እስር፣ ከስራ ማፈናቀል፣ ማሸማቀቅና ድብደባ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ፡፡

ፓርቲው ዛሬ ሐምሌ 7/2007 ዓ.ም ‹‹የወለደውን የረሳ ብሶት የወለደው ስርዓት! የዘመቻ እስርና ግድያ ተጠናክሮ ቀጥሏል!›› በሚል በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እዳመለከተው፣ ምርጫው ከተጠናቀቀበት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ማግስት በምርጫው በንቃት ይሳተፉ የነበሩና በአስተሳሰባቸው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች በማንአለብኝነት መደብደብ፣ ከሰራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና መግደል የአገዛዙ ዋና መገለጫ ሆኗል፡፡
ሰማያዊ በመግለጫው ‹‹በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማዊ፣ የመኢአድ፣ የቀድሞው አንድነት፣ የመድረክና የሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በተለዬ ኢላማ ተጠምደው እየተሳደዱ፣ እየተደበደቡና በጅምላ እየታሰሩ አለፍ ሲልም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ይገኛሉ›› ሲል ገልጾአል፡፡
አሁን በገዥው አካል እየተወሰደ ያለው ድርጊት ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን የሚለውን አስተሳሰባቸውን የሚያጨልምና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞችን አንገት የሚያስደፋ ይዋል ይደር እንጅ መዘዙም ለማንም ወገን በተለይም ለገዥው መደብ የማይጠቅም መሆኑንም ፓርቲው በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡
‹‹የአፈናው ስርዓት ብዙ ዓይነት አስተሳሰብና ልዩነት ባለባት ኢትዮጵያ ምርጫን መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ ቢልም ሃቁ ግን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግብዓተ መሬት እየተቃረበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ገዥው ቡድንም የማይክደው መሆኑን በምርጫው ማግስት ጀምሮ የተዘፈቀበት ህዝብን እንደጦር የመፍራት አባዜው ገሃድ አድርጎታል›› በሏል ፓርቲው በመግለጫው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ገዥው አካል ከሚፈፅማቸው ህገ ወጥና የማን አለብኝነት ተግባሩ እንዲቆጠብ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ደጋግሞ መጠየቁን አስታውሶ፣ አሁንም ይህ አይነቱ ህገ-ወጥና የማንአለብኝነት ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እንደተናገሩት አሁን ያለው ትግል ‹‹ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ የነጻነት ትግል›› ነው፡፡
በመጨረሻም ፓርቲው ሕዝብ የስልጣን ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ በሚያደርገው ትግል ሁሉ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Filed in: Amharic