>

አምስተኛው ዙር የድምጽ ዘረፋ... [ክንፉ አሰፋ]

የ”ምርጫው” ድራማ እየተተወነ ሳለ፤ የቦርዱ ሊቀመንበር ዶ/ር መርጋ በቃና እና ምክትል ሊቀመንበሩ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ለአቦይ ስብሃት ስልክ ደወሉ።

“ሃሎ?”

“ሃሎ፣ አቦይ ስብሃት ኖት?”

“ነኝ፣ ምን ፈለግክ?”

“ዶ/ር መርጋ በቃና እና ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ነን።”

“ችግር መስማት አልፈልግም። የታዘዛችሁትን አደረጋችሁ?”

“99.8% ህዝብ አልመረጠንም። ግን በታዘዝነው መሰረት ውጤቱን ገልብጠነዋል!”

“0.2% ብቻ ነው የመረጠን ማለት ነው?”

“አዎን ጌታዬ። ሌላ ምን እንታዘዝ?”

“99.8% ህዝብ የስም ዝርዝሩን አንብብልኝ።” አሉ አቦይ ስብሃት እየተባለ ይወራል።

አንድ ወዳጄ ስለ አቦይ ስብሃት የነገረኝ ታወሰኝ። ሰውዬው ከግመል እንኳን የማይሻል እንስሳ ብጤ ነው። ግመል ሳትጠጣ ለቀናት ትሰራለች አቦይ ስብሃት ደግሞ ሳይሰራ ቀኑን ሙሉ ይጠጣል። አብዛኞቹ የህወሃት አባላት እድሜያቸው እንደ አስተሳሰባቸው ስላረጀ ጨዋታቸው ከውሃ ጋር ነው። ከውድ ውሃ ጋር!  ድንጋይን ውሀ ያስጮኸዋል!

ሜዳው የኢህአዴግ፣ ዳኛው ኢህአዴግ፣ ታዛቢው ኢህአዴግ፣ ድምጽ ቆጣሪው ኢህአዴግ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀው “ምርጫ” እነሆ ተጠናቀቀ። በአፈና የታጀበው ምርጫ ጸጥእረጭ ባለ ድባብ ተጠናቅቋል። ልክ አስገድደው እንደሚደፍሩ ወሮበሎች፤ በሃይል ጠልፈው ያላቻ ትዳር እንደሚመሰርቱ ጉልበተኞች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፍቃዱ እንደገና የአምስት አመት የትዳር ቁርኝት ውስጥ ገብቷል።  ሌላ አምስት አመት። ሌላ የህወሀት ዘመን። ሌላ የጥርነፋ ዘመን!  ሌላ የቁምራ ዘመን! ሌላ የመፈናቀል ዘመን! ሌላ የመሬት ነጠቃ ዘመን! ሌላ የስደት ዘመን!…

የህወሃት ሰዎች አሁን የጭንቀቱ ምእራፍ ሁለት ላይ ናቸው። በዛሬው እና በትላንቱ እለት የህወሃት ባለስልጣናት ተሰባስበው በፐርሰንቱ ምደባ ላይ ውይይት ይዘዋል። ዘረፋው ላይ ሁሉም በ 100% ይስማማሉ። ምደባው ላይ ግን ችግር አለ።  አንዳንዶቹ ይህ ጉዳይ ተአማኝነት እንዲኖረው ለተቃዋሚዎቹ ትንሽ መልቀቅ ይኖርብናል ሲሉ ለሎች ደግሞ ይህንን ሃሳብ ይቃወማሉ። ጥቂት ተቃዋሚዎችን ፓርላማ እንዲገቡ መፍቀድ አለብን የሚሉ ተከራካሪዎች “ሌባ ከሰረቀው ጥቂቱን ቢሰጥ” እንደማይጎዳው ይናገራሉ።  ይህንን የማይቀበሉት ግን የተቃዋሚዎች በፓርላማ መግባት ራስ ምታት እንደሚሆንባቸው በስፋት መክረዋል። 547 መቀመጫ የነበረው የቀድሞው ፓርላማ ውስጥ እውነትን የያዘ አንድ ተቃዋሚ ብቻ ጭንቅላታቸውን በጥብጦት እንደነበር ሁሉም አይዘነጉትም። ይህንን በድጋሚ መፍቀድ አልያም ውግዘቱን በመቀበል መሃል ባለ አጣብቂኝ ውስጥ ከርመዋል። ውጤቱን ከሰሞኑ ይፋ ያደርገዋል ዶ/ር መርጋ።

የዘንድሮው ዝርፍያ ጤናማ አይደለም።  ልክ እንደ ቦራት ዘ-ዲክታተር ፊልም ተወዳዳሪዎችን እግር እግራቸውን እየመቱ ለብቻ ሮጦ፤ በራስ ዳኛ የድል ዋንጫ መረከብ? ይህ በእውነት በዚህ በ21ኛው ዘመን እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው። ተቃዋሚ ሃይሎችበምርጫው ክርክር እና በትውልድ ስፍራቸው ላይ የነበራቸው የሕዝብ ድጋፍ ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ በታየበት ሁኔታ ህወሃቶች 100% አሸንፈናል ሲሉ ከሌብነታቸው ይልቅ ንቀታቸው ጥርስ የሚያስነክስ መሆኑን ለአፍታ እንኳ አላስተዋሉትም። እጅግ ትንሽ ጭል ብላ የነበረችውን ዲሞክራሲ በምድረ ኢትዮጵያ ገድለው፣ ከፍነው ቀበሩት። አዲዮስ ዲሞክራሲ…

ፈረንጆች የሚሉት አባባል አለ። “ለነብሰ-ገዳዮች ትክክለኛ ዲሞክራሲ ማለት ፍጹም አንባገነን መሆን ነው።”

“በ100% ድምጽ ተመርጠናል!” አሉ።  የመረጣቸው ህዝብ የቱ ይሆን? በአዲስ አበባ በነቂስ ወጥቶ “ወያኔ በቃን! መንግስቱ ይግደለን” ያለው ህዝብ ነው ወይንስ ለም መሬቱን ተነጥቆ ለባእድ የተሰጠበት የገጠር ህዝብ? በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል፣ በሁመራ…ወዘተ የተፈናቀለው ህዝብ ነው የመረጣቸው? ወይንስ  አምቦ – ጉደርን እንደ ሱናሚ ያጥለቀለቀው ህዝብ ? የቱ ነው ወያኔን የመረጠው?  ከስርአቱ ጋር ሆድና ጀርባ የሆነው ሙስሊሙ እምነት ተከታይ ነው ወይንስ በእምነቱ ጣልቃ እየገቡ ካድሬ ጳጳስ የሚሾሙለት ክርስቲያኑ ህብረተሰብ?  ማን ነው ህወሃትን የመረጠው? እንደ ምጽዓት ለስደት እያኮበኮበ ያለው ስራ-አጥ ወጣት ነው ወይንስ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅቶ ድንጋይ የሚፈልጠው ወጣት ምሁር?  መብራት እና ውሃ በፈረቃ ያደረጉበት ህዝብ ነው የመረጣቸው?…  ለመሆኑ ስንት አመት ነው ህዝቡ ላይ እንዲህ የሚቀልዱት?

እነሱ ልባቸው በትእቢት ስለተወጠረ፤ ሌላው ህዝብ የማይመለከትና የማይሰማ ይመስላቸው ይሆናል። ትእቢት ደግሞ የውድቀት ምልክት ናት።  በመጀመርያ የውጭ ታዛቢዎች እንዳይገቡ ተደረገ። ዝም!  በምርጫው ወቅት ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎችን አሰሯቸው። አሁንም ዝም ተባለ።  ከዚያ ኮሮጆ እየተሞላ ቀረበና በቁም ያሰሯቸው ታዛቢዎችን ምሽት ላይ ፈትተው እንዲፈርሙ አዘዝዋቸው። የተያያዙት አስገድዶ መድፈር ነውና አንዳንዱን አስገድደው በተሰረቀ የድምጽ ሳጥን ላይ አስፈረሟቸው።   ምርጫ 2007 በዚህሁኔታ “ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፤ ዲሞክራሲያዊና የህዝብ ተዓማኒነትን አግኝቶ” ተጠናቅቋል ሲሉ ፕ/ር መርጋ በቃና አበሰሩ። እኚህ ፕሮፌሰር ግን ህሊና ይኖራቸው ይሆን? ካላቸው በምን ለወጡት? በገንዘብ? ህሊና ስንት ያወጣል?

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከምርጫው በኋላ ስላለው ነገር ብዙም አላሉም።  ማን እንደሚያሸንፍ እና በምን ያህል ድምጽ እንደሚያሸንፍ አስቀድመው ዘግበው ስለነበር ውጤቱን መድገም የፈለጉ አይመስልም።  አስቀድሞ ውጤቱ የታወቀበት ምርጫ መሆኑን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሱ የምርጫው ቦርድ በድረ-ገጹ ላይ በግልጽ አስቀምጦት ነበር። የምርጫው ቦርድ በድረ-ገጹ  እንዳስቀመጠው የኢሕአዴግ 501 ተወዳዳሪዎች የተመዘገበለት ሲሆን መድረክ 270፣  የሰማያዊ ፓርቲ 139 እጩዎች ብቻ እንዲኖራቸው ተደረገ። የሰማያዊ ፓርቲ 200 እጩዎች በምርጫ ቦርዱ ተሰርዘውበታል።  108 እጩዎች አስመዝግቦ የነበረው አንድነት ፓርቲም ስልታዊ በሆነ ዘዴ በቦርዱ እንዳይሳተፍ ታግዷል። ይህ እንግዲህ በሎተሪ ሰበብ የተገለሉትን ሳይጨምር ነው።

መቼም ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትምና ቀኑ እስኪደርስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልፈለገው ሊገዛ፤ ባላመነበት ሊዳኝ፣ ባልመረጠው ሊተዳደር ነው። አሁንም ዝምታን መርጧል።  ዝምታ ራሱን የቻለ መልስ ነው። በዝምታ የተዋጠች እያንዳንድዋ ሰከንድ ቁርሾ ይዛ ማለፍዋም ግልጽ ነው። ማሰብ ላልተሳነው ሁሉ ዝምታ ያስፈራል።  ምጥና ውሃ ሙላት በድንገት እንዲሉ ዝም ያለ ወራጅ ሲወስድ አይታወቅም። ጽዋም ሲሞላ ይፈስሳል…

አለም-አቀፉ ህብረተሰብም ዝርፊያውን ስለለመደው ችላ ብሎታል። የእንግሊዙ “ዘ ጋርዲያን” ጋዜጣ “ምርጫውን ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ክስተትም አይቆጥረውም።” ሲል፣  ሂዉማን ራይትስ ዎች፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፍሪደም ሃውስ፣ ሲፒጄ፣ የመሳሰሉት አለም አቀፍ የመብት ተከራካሪ ተቋማት አፈና የሰፈነበት እና ነጻ ሜድያ በሌለበት ሁኔታ የሚካሄደው ይህ ምርጫው ፍሱም ኢ-ፍትሃዊ እንደነ ገልጸዋል። አልጃዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ ታላላቅ ሜድያ ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ ምርጫ ሲሉ ሂደቱን  በክፉ ኮንነውል።

ነገሩ ግልጽ ነው። ነጻ ሜድያ በሌለበት፣ ገለልተኛ ታዛቢዎች ባልተፈቀዱበት፣  ነጻ ዳኛ በልተመደበበት  ነጻ ምርጫ አይታሰብ። የዘንድሮው ክስተት ህወሃት የዘረፋ ደረጃውን ያወረደበት ምርጫ ነው። ከረቀቀ የዘረፋ ስልት ወደ ግልጽ የውንብድና ተግባር።

የጀርመን ድምጽ እንግሊዝኛው ክፍል ከምርጫው በኋላ ምንጮችን ጠቅሶ ሲዘግብ “ታዛቢዎ የቁም እስር ላይ ስለነበሩ ወደ ውጭ ወጥተው ምርጫውን መታዘብ አልቻሉም” ብሏል።  የሰራዊት እና የሚሊሽያ አባላት በየምርጫ ጣብያው እየተገኙ መራጮችን እያስፈራሩ የተካሄደ ምርጫ በአለም ላይ ይህ ብቻ ነው። የምርጫ ዘመቻም በታጠቁ ሃይሎች ወታደራዊ ትእይንት የተካሄደው በኢትዮጵያ ብቻ ነው።

30 አመት ሙሉ ያል ህዝብ ፍቃድ በስልጣን መቆየት ይሰለቻል። እነዚህ ሰዎች የምእተ አመቱን አንድ አራተኛ የሃገሪትዋን ሃብት ብቻ ሳይሆን የህዝብን ድምጽም እየዘረፉ ተቀመጡ።  ባለፉት 24 አመታት በአሜሪካ አምስት ግዜ መንግስት ተቀይሯል። በሆላንድ 7 ግዜ መንግስት ወርዶ በህዝብ ድምጽ ሲቀየር አይተናል። አፍሪካዊቷ ጋና አምስት ግዜ ፕሬዝዳንታዊ  ምርጫ ፣ ሶስት ግዜ ፓርላሜንታዊ ምርጫ አድርጋለች።…  ያልታደልን ወይንም ያልታገልን እኛ ግን ለ30 አመታት በአንድ አንባገነን ተይዘናል።

ህወሃቶች በሩን ሁሉ ዘግተው ህዝቡን ወደማይፈለገው አመጽ እየገፉት ነው። ያልተረዱት ቢኖር አንደኛው በር ሲዘጋ ሌላኛው በር መከፈት መቻሉን ነው። የ90 ሚሊዮን ህዝብን ድምጽ ሰርቀው፣ አንደበቱን ለጉመው ምን ያህል እንደሚዘልቁ የምናየው ይሆናል። መቶ አመት የዘለቀ አንባገነን በታሪክ አልተከሰተም።

ከዚህ ቀደም ባስነበብኳችሁ ቀልድ ጽሁፌን ልቋጭ። አንድ የህንድ ኢንቨስተር አዲስ አበባ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያንን የቀብር ስፍራ አይቶ በሊዝ ሊገዛ ፈለገ። የአዲስ አበባ ባለስልጣናትን ጠርቶ እንዲሸጡለት ጠየቀ። ባለስልጣናቱም መልሰው ሌሎች ቦታዎች ሳያልቁ የቀብር ስፍራ ለግዜው እንደማይሸጡለት ነገሩት። ህንዱ መለሰና መከራቸው። “እኛ አገር ሰው ሲሞት እናቃጥላለን እንጂ አንቀብርም። ለምን ይህን ለም ቦታ ታባክናላችሁ?” አላቸው።  ባለስልጣናቱም መለሱ፣ “እኛ አገር ደግሞ ሰውን በቁሙ እንጂ ሲሞት አናቃጥልም!”

Filed in: Amharic