>

ኢትዮጵያና አሜሪካ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም]

ዱሮ ዱሮ ምዕራባውያን የሶቭየት ኅብረትን ኮሚዩኒዝም መስፋፋት ለመቋቋም ከእሥራኤል ሌላ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ አገሮችን ሲያስሱ፣ ኢትዮጵያ፣ ቱርክና ፋርስ እየታጩ ነበር፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የተወዳጀበትና በአስመራ ቃኘው ጣቢያን የተከለበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፤ የፋርስ ጉዳይ ከንጉሠ ነገሥቱ መፈንቅለ መንግሥትና ሞት ጋር አበቃ፤ ቱርክ እያንገራገረም ቢሆን የሰሜን አትላንቲክ አገሮች ማኅበር ውስጥ አለበት፤ እሥራኤል በአረቦች አካል ላይ እሾህ እንደሆነች ጥጋበኛ የአሜሪካ ቅምጥል ሆናለች።

የፋርሱ ጉዳይ ከፋርሱ ንጉሠ ነገሥት ጋር እንደተያያዘው ሁሉ የኢትዮጵያም ጉዳይ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ጋር የተያያዘ ነበር፤ የእውቀት ጥበብ (ቴክኖሎጂ) እያደገ ሲሄድ የቃኘው ጣቢያ ለአሜሪካ አማራጭ የሌለው መሆኑ ቀረ፤ አሜሪካ ኮተቱን ይዞ ወደህንድ ውቅያኖስ ሲሄድ ኢትዮጵያን ችላ ማለት ተጀመረ፤ መቃቃሩ እየበረታ ሲሄድ የአሜሪካ እብሪትና የኢትዮጵያ ኩራት ተጋጩ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ የአሜሪካኑን አምባሳደር አስከማስወጣት ደረሱ፤ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ያኔ ተጀመረ፤ የፋርሱ ንጉሠ ነገሥት ሲገለበጥ ቀጣዩ አገዛዝ ከአሜሪካ ጋር ጠላት እንደሆነው የአጼ ኃይለ ሥላሴም አገዛዝ ሲገለበጥ ቀጣዩ አገዛዝ ከአሜሪካ ጋር ጠላት ሆነ።
አሜሪካ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው ግፍ የጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው፤ የደርግ አገዛዝ ኮሚዩኒስት መሆኑን አወጀ፤ የደርግ አገዛዝ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ማኅበርተኛ መሆኑን አወጀ፤ የደርግ አገዛዝ የአሜሪካ መንግሥት ዓለም-አቀፍ ቄሣራዊነትን የሚያራምድ መሆኑን እየደሰኮረ የአሜሪካ ባላጋራ መሆኑን አስታወቀ፤ ይህ ሁሉ እውነት ነው፤ ነገር ግን አንዱም የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈቃድ ያዘለ አይደለም፤ አንዱም ኢትዮጵያን እንደአገር የሚያስጠይቅ አይደለም።
ከላይ ለተጠቀሱት የደርግ ‹አዋጆች› የአሜሪካ መንግሥት መልስ የሰጠው ለደርግ መንግሥት ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነበር፤ መልሱ ይህ ነበር፤ አንደኛ ኢትዮጵያን የወረረችውን ሶማልያን ረዳ፤ ሁለተኛ ሻቢያንና ወያኔን የሚረዳውን የኑሜሪን ሱዳንን ረዳ፤ ሦስተኛ ሻቢያንና ወያኔን ረዳ፤ አራተኛ የኤርትራን መገንጠል ደገፈ፤ አምስተኛ የወያነን አምባ-ገነን አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ ተክሎ አቅፎታል፤ እነዚህ የአሜሪካ መልሶች ደርግ ወንበሩን አስረክቦ ቃሊቲ ከገባ በኋለም መቀጠላቸው የአሜሪካ ጠብ ከደርግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም ጋር የሆነ ያስመስላል።
በኢትዮጵያውያን ድካምና በአሜሪካ ጫና ኢትዮጵያ ዛሬ ሁለት ሆናለች፤ በአንዱ ክፍያ ላይ አሜሪካ እግሩን ዘርግቶ አድራጊ ፈጣሪ ቢሆንም በሌላው ክፍያ ላይ እግሩን ማስገቢያ አላገኘም፤ ብዙ ሰው ያልተረዳውና የሚያስደንቀው የአሜሪካ ዶላርና የአሜሪካ ጫና ኤርትራን ማንበርከክ አለመቻሉን ነው፤ ሎሌ ሆኖ ጌታ ከመምሰል ደሀ ሆኖ መከበር ይሻላል፤ ይህ የቀድሞው የኢትዮጵያዊነት አልበገርም-ባይነት፣ የክብርና የኩራት ምልክት ነው፤ አልጠፋም!

በአለፉት ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በኢራቅ ምን አደረገ? ማንን ጠቀመ? ማንን ጎዳ? በአፍጋኒስታንስ? በፓኪስታንስ? በሶርያና በየመን የሚካሄደውስ ብጥብጥ የት ድረስ ይሄዳል? የትስ ይቆማል? ቀደም ሲል በኮሪያ (ኢትዮጵያን አስከትሎ) ምን ፋይዳ ሠራ? ሁለት ኮሪያዎችን ፈጠረ፤ በቭየትናም ሕዝብ ጀግንነት ቭየትናም አንድነቱን ይዞ በድል ወጣ፤ መከፈል ለሱዳንም ደረሰው፤ መከፋፈል ሲጀምርም የማይቆም መሆኑን በሱዳን እያየን ነው።

ነገ በኬንያ ምን ይሆናል? ዛሬ ኬንያውያን ሳይገባቸው አገራቸው ውስጥ እሳት እየተቀጣጠለ ነው፤ እሳቱ ወዴት እንደሚዘምትና ማንን እንደሚያጠፋ ወደፊት እናያለን፤ በየመን በኩል የሚቀጣጠለው እሳትም በጂቡቲና በሶማልያ በኩል ባሕር የሚገባ አይመስለኝም።
ኢትዮጵያን የማላነሣው ረስቼ አይደለም፤ አንዴት ብዬ! አንዱ የወያኔ ጮሌ ‹ምሁር› በፌስቡክ ላይ መቀሌ አይባልም፤ መቐሌ ተብሎ መጻፍ አለበት ብሎ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር ነበር፤ እንደሚመስለኝ አሸነፈ መሰለኝ! አዋቂነት መሆኑ ነው! ነገ ደግሞ አንዱ ተነሥቶ ባቄላ አይደለም፤ ባኤላ ነው፤ ቢል ማን እንደሚያሸንፍ አላውቅም፤ እንደፕሮፌሰር ዓለሜ እሸቴ (ነፍሱን ይማረውና)፣ እንደፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽና እንደፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ያሉ የታሪክ አዋቂዎች ስድስት ሺህ ዓመታት ሲቆጥሩ ገና ፊደል የቆጠሩት የዘመኑ ደርሶ አዋቂዎች ደግሞ ዳዴ ሊያስኬዱን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም ገና የእውቀትን መስፈሪያና የታሪክን ማበጠሪያ አላረጋገጥንም፤ ከግራም ሆነ ከቀኝ ለሚመጣብን አደጋ በአሜሪካ ላይ የምንተማማን ከመሰለን የደቡብ አሜሪካን፣ የምሥራቅ እስያንና የመሀከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን ታሪክ እናጥና።

አሁን ደግሞ የጦርነት ዓይነት በጣም እየተለወጠ ነው፤ በሰልፍ የጦር ሜዳውን የሚሞለው ወታደር የለም፤ የመሣሪያው ዓይነትና ብዛት እምብዛም ዋጋ የለውም፤ ጥቂት ሰዎች በጥቂት ፈንጂዎች ከባድ ጥፋትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ አሸባሪ ቡድኖቹ ለሰው ሕይወት ዋጋ የላቸውም፤ ለሀብትም ሆነ ለባህላዊ ቅርስ ግድ የላቸውም፤ የራሳቸውን ሕይወት ወደመሣሪያነት ለውጠውታል፤ አንድ ቦታ አይቆዩም፤ ይዘዋወራሉ፤ ጥላቻ እንጂ ፍቅር አያውቁም፤ ሞት እንጂ ሕይወት አያውቁም፤ ጥፋት እንጂ ልማት ዓላማቸው አይደለም፤ አቃጥሎ መቃጠልን እንደመጨረሻ ዓላማ የሚከተሉ ናቸው፤ የሚያከብሩት ሕግ፣ የሚፈሩት ኃይል የለም፤ ከነዚህ ጋር ጦርነት መግጠም የማይበርድ እሳት ውስጥ መግባት ነው፤ ታላቁ አሜሪካ ከማያልቀው ሀብቱና ወደር ከሌለው የጦር ኃይሉ ጋር ለለፉት ስድሳ ዓመታት ከደቡብ አሜሪካ ጀምሮ እስከእስያ፣ ከብይሩት እስከቭየትናም ጥረቱ ሁሉ ከሽፏል፤ ውድና ክቡር የአሜሪካ ሕይወት በአረመኔዎች እንዳይቀጠፍ ከደሀ አገሮች የእሳት እራት የሚሆኑ ወታደሮችን ይከራያል፡፡

Filed in: Amharic