>

መንግስታዊ ሽብር የህዝብን ቁጣ ያባብሳል እንጂ መፍትሔ አይሆንም! [ሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ]

Blue party 2ዛሬ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም የተወካዮች ም/ቤት የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን እንደሚደግፍ እና ደጋፊዎቹና አባላቱ በሰልፉ ላይ እንዲገኙ በትናንትናው እለት ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ሊገኙ የሄዱ የፓርቲው አመራሮች እና አባላት ገና ወደ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት እየታደኑ የታሰሩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ሰልፉን ለመሳተፍ በቦታው ተገኝተው ነበር፡፡

ሰልፉ በርካታ ዜጎች በቁጭት እና በሃዘን የተገኙበት መሆኑንም ሁሉም ሰው የሚገነዘበው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ የሰልፉ ተካፋዮች ተቃውሟቸውን ንግግር በሚያደርጉ ሰዎች ላይ በማሰማት ገለፁ፡፡ ይህን ተከትሎም ፕሮግራሙን በችኮላ ያጠናቀቀው መንግስት ሰልፈኛው እንዲበተን መልዕክት በማስተላለፉ የተቆጡ ዜጎች ጋር ግጭት ፈጠረ፡፡

ለህዝብ ቁጣ እና ተቃውሞ ክብር እና ተገቢውን መልስ የማይሰጠው መንግስት በዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በእጅጉ የሚያሳዝን እና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባ ነው፡፡ በእርግጥ ስርዓቱ ለዚህ መሰሉ የሀይል እና የጭካኔ እርምጃ አዲስ ባይሆንም የአሁኑ ግን የተለየ የሚያደርገው ማንም ሰው ሊጠብቀው እና ሊያስበው በማይችለው መልኩ በወገኖቻችን ሞት እና በመንግስት ቸልተኝነት ልቡ ያዘነውን እና ተቃውሞ በማሰማት ላይ የነበረውን ህዝብ “ሰልፍ አልቋል ተበተኑ” በሚል ሰበብ የወሰደው እርምጃ በሀዘናችን ላይ ሀዘን መደረቡ ነው፡፡

በእለቱ ከተፈፀሙት አስከፊ ሁኔታዎች የባሰው ግን መንግሰት የወሰደውን እርምጃ ለመካድ እና በህዝብ የደረሰበትን ከፍተኛ ተቃውሞ ለመደበቅ የህዝብን ቁጣና ሀዘን የሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ እንደሆነ አድርጎ በኮምኒኬሽን ፅህፈት ቤት በኩል የወጣው መግለጫ ይዘት ነው፡፡ በዚህ መግለጫ እንደተገለፀው በመስቀል አደባባይ የተገኙ ዜጎች ማሰብ የማይችሉና በነሲብ እንደሚነዱ ሁሉ “ሰማያዊ ፓርቲ ለአመፅ አነሳሳቸው” ማለት ሀዘን የገባውን እና የተቆጣን ህዝብ መሳደብ ነው፡፡ ህዝብን መናቅ ነው፡፡ ከአንድ መንግስት ነኝ የሚል አካል የሚጠበቀውን ኃላፊነት ከመውሰድ እና ተቃውሞዎችን በአግባቡ ከመፍታት ጋር የማይተዋወቀው የኢህአዴግ ስርዓት ቁጣቸውን በገለፁ እና መንግስት በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚያሳየውን ቸልተኝነት በተቃወሙ ዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ ሳያንስ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር አዛምዶ ተቃውሟቸውን ማጠልሸት በፍፁም ተቀባይነት የሌለው አፀያፊ ተግባር ነው፡፡ መንግስት ነኝ ከሚል አካል በፍፁም የማይጠበቅ ስህተት ነው፡፡ አዲስ አለመሆኑ እና መደጋገሙ ደግሞ እጅግ እንድናዝን ያስገድደናል፡፡

ከራሱ ታሪክ እና ተሞክሮ መማር ያልቻለው የኢህአዴግ ስርዓት በተደጋጋሚ የሚፈፅማቸው የመብት ጥሰቶች እና ተቃውሞን በሀይል ለመፍታት የሚወስደው እርምጃም ችግርን፣ ቁጣን ከማባባስ በስተቀር መፍትሔ ካለመሆኑም በላይ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ እና የአመፅና የጦርነት አዙሪት እንዲከስም ጭቆናን ተቋቁመን የምናደርገውን ትግል ለማኮላሸት መሞከሩ የከፋ አደጋ እንዳለው ለማስገንዘብ እንወዳለን! የህዝብን ጥያቄ ያለፍርሃት በማንሳት እና ተቃውሞ በማሰማታችን እየደረስብን ያለውን አፈና ችለን በምናደርገው ትግል ውስጥ እንዲህ መሰሉ የስም ማጥፋት ዘመቻና የፈጠራ ክስ ይበልጥ ትግሉን እንደሚያጠናክረውም እናስገነዝባለን!

በተያያዘም ዛሬ በተጠራው ሰልፍ ለመካፈል ሲሄዱ የታሰሩ፤ መንግስት በወሰደው የሀይል እርምጃ የታሰሩ እና የታሰሩትን ለመጠየቅ እስር ቤት ሄደው በዛው የታሰሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው (እነዚህ እስካሁን በእርግጠኝነት ማጣራት የቻልነው ብቻ መሆኑ ይታወቅ)፡-

1- ወይንሸት ሞላ – የድርጅት ጉዳይ አባል (ወደ ሰልፉ በመሄድ ላይ ሳለች ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስጢፋኖስ አካባቢ ተይዛ ታስራለች)
2- ጠና ይታየው – የ2007 ሀገራዊ ምርጫ የተ/ም/ቤት ተወዳዳሪ (በሀይል እርምጃው ወቅት ተደብድቦ የታሰረ)
3- ኤርምያስ ስዩም – የፓርቲው አባል (በሀይል እርምጃው ወቅት ተደብድቦ የታሰረ)
4- ማስተዋል ፈቃዱ – የፓርቲው የቂርቆስ ክ/ከተማ አስተባባሪ (በሀይል እርምጃው ወቅት ተደብድቦ የታሰረ)
5- ዳንኤል ተስፋዬ – የፓርቲው የጉለሌ ክ/ከተማ አስተባባሪ (በሀይል እርምጃው ወቅት ተደብድቦ የታሰረ)
6- ቴዎድሮስ አስፋው – የአዲስ አበባ ምርጫ ጉዳይ ኮሚቴ ህ/ግንኙነት (በሀይል እርምጃው ወቅት ተደብድቦ የታሰረ)
7- እስክንድር ጥላሁን – የ2007 ሀገራዊ ምርጫ የተ/ም/ቤት ተወዳዳሪ (የታሰሩትን ለመጠየቅ ምግብ ይዞ በሄደበት የታሰረ)
8- ይድነቃቸው አዲስ – የ2007 ሀገራዊ ምርጫ የተ/ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ (የታሰሩትን ለመጠየቅ ምግብ ይዞ በሄደበት የታሰረ)

በሌላ በኩል እነዚህ አባላቶቻችን በታሰሩበት እስር ቤቶች በርካታ ወጣቶች ታስረው ይገኛሉ፡፡ በስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ – ካሳንቺዝ፣ አምቼ ፖሊስ ጣቢያ – ቦሌ፣ በአድዋ የካ ንዑስ ፖሊስ ጣቢያ – አዋሬ፣ በየካ ፖሊስ መምሪያ – ኮተቤ፣ ኮልፌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ፣ ላንቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ – ቂርቆስ እና በሌሎች ፖሊስ ጣቢያዎች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውንም ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

በመሆኑም መንግስት ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ በነቂስ ወጥተው ተቃውሟቸውን በገለፁ ዜጎች ላይ የወሰደውን የጭካኔ እርምጃ አጥብቀን እያወገዝን የታሰሩት ዜጎችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
በሰልፈኞች ላይ እንግልት፣ እስርና አሰቃቂ ድብደባ የፈፀሙ እና ትእዛዝ ያስተላለፉ በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጥይቃለን! የመንግስት ጽ/ቤት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ባወጣው የፓርቲያችንን ስም የሚያጠፋ እና የሚወነጅል ብሎም የህዝብን ሀዘንና እና ቁጭት የሚያባብስ መግለጫም በእጅጉ ያስቆጣን መሆኑን እያሳወቅን ይህን በፓርቲያችን ላይ የተቃጣ ህገወጥ ውንጀላና የህዝብን ብሶት እና ተቃውሞ ያቃለለ ድርጊት በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሚያዝያ 14 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Filed in: Amharic