>
5:13 pm - Thursday April 18, 1376

ጨለማው ሳምንት [ክንፉ አሰፋ]

እየሩሳሌም አስፋው እንደወትሮው ቴሌቭዥን ከፍታ እየተመለከተች ነው። ብርቱካንማ ቱታ የለበሱና፣  እጆቻቸው የፍጢኝ የታሰሩ ወጣቶች በአሸባሪዎች ታጅበው ሲጓዙ ያሳያል ቴሌቭዥኑ። ለእርድ ከተሰለፉት ወገኖች ፊት ለፊት ላይ ያለው የእየሩሳሌም ወንድም ነበር። ሌላኛው ወንድሟም ከበስተኋላ ተሰልፏል። እያሱ ይኩኑዓምላክ እና ባልቻ በለጠ፤  ሁለቱም በዚያች ቅጽበት ክቡር ነብሳቸውን በግፈኞች ተነጠቁ። ከሁሉም የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ወዳጅ ዘመዶች የነዚህን ወገኖች አስከሬን አግኝተው ለመቅበር እድል እንኳን ባለማግኘታቸው ነው። የሁሉንም ልብ የሚሰብር ክስተት!

“ወንድሞቼ ያልፍልኛል ብለው ከቤት እንደወጡ እዚያው በበረሃ ቀሩ።” ትላለች እየሩሳሌም።  እትብታቸው የተቀበረባትን ሃገር ለቀው ሲወጡ ጣሊያን ለመግባት ነበር ዕቅዳቸው።  አውሮፓን አልመው ቀዬአቸውን ለቅቀው የወጡ እነዚህ ወጣቶች ህልማቸው እውን ሊሆን አልቻለም። ከሌሎች 28 ወገኖቻችንን ጋር ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ህይወታቸው አለፈች።  ‎ISIS የተባሉ ጨካኞች ሲያርዷቸው በቪደዮ አሳዩን።

የሳምንቱ ሃዘን እጥፍ ድርብ ነው። ኢትዮጵያዊ ላይ ያነጣጠረ እስከሚመስል ድረስ ነው እየተካሄደ ያለው። ብሔራዊ መንግስት ስለሌለን ብሄራዊ ውርደታችን አላቆመም።  ከ 700 በላይ ስደተኞችን ይዛ ወደ አውሮፓ ትጓዝ የነበረች ጀልባም በዚህ ሳምንት ነበር በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የሰመጠችው። ቁጥሩን ለማረጋገጥ ባይቻልም፣  ከሞቱት ገሚሱ ኢትዮጵያውን እንደሆኑ ከወደ ጣልያን የሚመጣው መረጃ ይጠቁማል።

በደቡብ አፍሪካ ዉስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በቁም ሲቃጠሉ እና ሲገደሉ እያየን ነው። በተለይ ደርባን ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  እስካሁንዋ ደቂቃ በፍርሃት ቤታቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል።

የመን ያሉ ወገኖቻችንም ምጥ ላይ ናቸው። የመን ያሉ ኢትዮጵታውያን ቁጥር ከምናስበው በላይ መሆኑ እጅግ ይረብሻል።  አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ.ኦ..ኤም  እንደሚለው ከሆነ በየመን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር አንድ ሚልዮን ይጠጋል። ሁሉም በጭንቅ ላይ ናቸው። ያለመታደል ሆኖ የሚቆረቆርላቸው መንግስት ግን አላገኙም። ልብ በሉ ከአንድ ሚሊዮን ዜጋ፤  በስልጣን ላይ ያለው መንግስታችን 30 ዜጎቼን በጅቡቲ አድርጌ  ወደ ሀገር ቤት አስገባሁ ሲል አብስሮልናል። በእርግጥ ይህ ጉዳይ በሊቢያው ክስተት ከሰጡት ምላሽ አይብስም።  የ ISIS  አሸባሪዎች ኢዮጵያውያንን አረድን ባሉ ግዜ “ጉዳዩን እናጣራለን” ሲሉ ነበር የቀልዱብንል። ከዚህ ድርጊት የባሰ ምን ሊመጣ ይችል ይሆን? በበረሃ የወደቀን ወገን፣ የትና በምን አግኝተው ነው የሚመረምሩት። አለሁ ባይ አካል ስለሌለን የተረሳን እና የተዋረድን ህዝቦች ነን።

እንደሌሎች ሀገሮች በአለማቀፍ መድረክ የሚከራከርልን አካል ስለሌለን የጥቃት ሰለባ እንድንሆን ተደርጓል።  ሃገራችንም ጥርስ የገባች ሃገር ሆናለች።

ይህንን ስረዓት እየሸሹ እየሄዱ አውሬ የሚበላቸውና በረሃ ወድቀው የሚቀሩትን ወገኖች ቤቱ ይቁጠረው።  በሳውዲ ጀምሮ የመን ተከትሎ ከዚያም በደቡብ አፍሪካ እና በሊቢያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በተለያዩ አረብ ሃገሮች በቃላት መግለጽ የማይቻል ድርጊት እየተፈጸመብን ነውና ሁላችንንም እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ሰው ወድዶ አይሰደድም። ተስፋ የቆረጠ ህዝብ ይሰደዳል፣  የተገፋ ህዝብ ይሰደዳል፣ ፍትህ ያጣ ህዝብ ይሰደዳል፣  የተራበ ህዝብ ይሰደዳል። ስደት እስካለ መከራውም ይኖራል።

የሃዘን ቀን ቢታወጅልንም፣ ባይታወጅልንም ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም። በዚህ ጨለማ ሳምንትም ሆነ ከዚያ በፊት በሆነው ነገር ሁሉ ልባችን ተነክቷል። ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጠለቀ የሃዘን ስሜት ውስጥ ነን።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አሜሪካዊትዋ ባለስልጣን፣ ዌንዲ ሼርማን መንግስታችን ስኬትን እያስመዘገበ እንደሆነ በዚሁ ሳምንት ነበር ያበሰረችን። ዜጋው ሁሉ ተስፋ ቆርጦ እየተሰደደ በየበረሃው መውደቁን ይሆን ዌንዲ እንደ ስኬት የቆጠረችው?

የማያልፍ የለምና ይህም ጊዜ ያልፋል። እስከዚያው ግን ወዳጅ ዘመዳቸውን ያጡ ሁሉ ፈጣሪ ብርታቱን ይስጣቸው።  መፍትሄው ታድያ ፍትሃዊ ስርዓትን እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው። ይህ ሲሆን የስደት ምንጩ ይደርቃል።

Filed in: Amharic