>

አይ ይሄ ልጅ! [አትክልት አሰፋ]

እናት የለው አታነባ፡
ዘመድ ወዳጅ ውስጥ አይገባ፤
ምንም የለው፤ ጠያቂ አልባ፡፡
በከርቼሌ ተከርችሞ፡
ነብሱን ሰጥቶ፤ ውስጡ ታሞ፡
ህመም ቁስሉን ተሸክሞ፤
ስቃይን ሊቀበል፡
ጽናትን ሊካፈል
ባመነበት ሊኖር
ቆርጦ ሊገዳደር፤
ወስኖ ለራሱ፡
አምኖበት ከነብሱ፤
የሚኖረው ያ… ወንድሜ
መጣ ዛሬ በምናቤ፡፡
ወደኋላ ‘ንዳይጎትቱት፡
ብርታቱንም እንዳይነጥቁት፡
ሚስት ልጁን ተሰናብቶ
ሂዱ… ብሎ ተለይቶ፤
የቆረጠው ያ… ወንድሜ
ዛሬ መጣ በምናቤ፡፡
መምህር ነው ለጓዶቹ፡
ኩራት፡ ጋሻ ላጋሮቹ፤
ግምባር ቀደም ተፋላሚ፡
እውነተኛ… ተስፋ አላሚ፤
በከርቼሌ ተከርችሞ፡
ነብሱን ሰጥቶ ፤ውስጡ ታሞ፡፡
ሀገር ብሎ! ሙያ ብሎ! ህዝብ ብሎ!
ብቻውን ነው ተከልሎ
ጨለማ ውስጥ ተጥሎ፡፡

ለብርቱ ሰው (Iron man)
ሲጻፍ ኤፕሪል 2015 ቫንኩቨር (ካናዳ) ነበር

Filed in: Amharic