>
5:13 pm - Saturday April 19, 2031

በቀልድ የታጀበው ምስክሮችን የመስማት ውሎ

– በዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች ላይ

photo by zone 9ers

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የማስረጃ መስማት ውሎ ዛሬ ምስክሮችን በማስማት ተጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ጉዳዬን ያስረዱልኛል ያላቸውን 17 ምስክሮች ያስመዘገበ ሲሆን 15ቱ በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ አቃቤ ህግ ችሎቱ በዝግ ችሎት አንዲሆን የጠየቀ ሲሆን ምስክሮቼ እና የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ችሎቱ በዝግ ሊሆን ይገባል የሚለውን አቤቱታውን ጠበቆች በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመውታል፡፡ ምስክሮቹ የጭብጥ ምስክሮች ሳይሆኑ ፍተሻን የታዘቡ የደረጃ ምስክሮች በመሆናቸው እና ስማቸውም በግልጽ ተከሳሾች ጋር ስለደረሰ ምንም አይነት የደህንነተ ስጋት የለባቸውም ከሚለው የጠበቆች ክርክር በኋላ ፍርድ ቤቱ በጉዳዬ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን ረፍት ወስዷል፡፡ በዚህም መሰረት የአቃቤህግን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ችሎቱ በግልጽ ሆኖ መስክሮች ምስክርነታቸውን እነዲያሰሙ ታዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች አነማን ላይ አንደሚመሰክሩ እና ምን አንደሚመሰክሩ በተጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱም በጠበቆቹ ስለተነሱት ነጥቦች የአቃቤ ህግን ምላሽ ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግም በዛሬው ዕለት የቀረቡት ምስክሮች በ2ኛ፣ በ3ኛ፣ በ5ኛ፣ በ6ኛ፣ በ7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ( በስድስቱ የዞን9 ጦማርያን ላይ እና በጋዜጠኛ አስማማው ላይ ) ላይ እንደሚመሰክሩ ገልጾ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቡድን በብርበራ ያገኛቸው ማስረጃዎች ከተከሳሾች የተገኙ ስለመሆናቸው ያስረዱልኛል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በምላሹም መሰረት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡ ምስክርነታቸው ሲሰጡ በነበረበት ወቅት የተከሳሾችን ስም አለማወቅ አንዲሁም የተከሳሾችን መልክ አለመለየት የመሳሰሉት ጉዳዬች የተስተዋሉ ሲሆን ምስክርነታቸውን የሰጡት ሰዎች ስም ዝርዝር እና የምስክርነታቸው ጭብጥ በአጭሩ አንደሚከተለው ነው ፡፡

1.ሙሉጌታ መዝገቡ ለማ – ናዝሬት ነዋሪ ነኝ መአከላዊ ምርመራ ለግል ጉዳይ ሄጄ ፓሊስ ታዛቢ ምስክር አንድሆን ጠይቆኝ በዚያ መሰረት ምስክር ሆኜ ተገኝቻለሁ፡፡ ከአቤል ከኮምፒውተሩ ላይ ጽሁፍ ሲወጣ እና ሲፈርም አይቼ እኔም ፈርሜያለሁ ፡፡ የጽሁፉን ይዘት አላነበብኩም አንዳንድ ቦታ አፍሪካ ሪቪው ኬንያ የሚል ቃል አይቻለሁ የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

2.በለጡ አበበ ዮሴፍ ይባላሉ፡፡ እድሜያቸው 32 ሲሆን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የካ ምድብ ሰራተኛ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ በማን ላይ ለመመስከር እንደመጡ ሲጠየቁ በስም እንደማያስታውሱት ገልጸው በአካል ግን ለይተው አሳይተዋል፡፡ መስካሪዋ በ6ኛ ተከሳሽ ዘላለም ክብረት ላይ የሚመሰክሩ ሲሆን በተለየ ስም ሲጠሩት ተስተውለዋል
“የሽብርተኝነት ጉዳይ የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ ወደ 70 ገጽ አማርኛና 10 ገጽ እንግሊዝኛ ጽሁፍ ተገኝቷል፡፡ ያየሁትን አይቼ ፈርሜያለሁ፡፡” ካሉ በኋላ ተከሳሹስ ፈርሟል ተብለው ሲጠየቁ መጀመሪያ አላስታውስም ቢሉም እንደገና ሲጠየቁ ግን አዎ ፈርሟል ብለዋል፡፡

3.እታፈራሁ ጌታቸው ወልዴ የሚባሉ ሲሆን እድሜያቸው 36 ነው፡፡ በመንግስት ት/ቤት በአስተዳደር ሰራተኛነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ማን ላይ እንደሚመሰክሩ ሲጠየቁ ፍቃዱ እና…..(ስሙ ጠፍቶባቸው ቆይተው) እ…አጥናፉ ብለዋል፡፡ በአካል ደግሞ በፍቃዱን አሳዩ ሲባሉ አጥናፍን አሳይተዋል፡፡ የምስክርነት ቃላቸውም ማእከላዊ ምርመራ ለግል ጉዳይ ሄደው ጽሁፎች ሲታተሙ ማየታቸውንና በፍቃዱ በፍቃደኛነት ሲፈርም ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለጽሁፎቹ ሲጠየቁ “የአማርኛ ጽሑፎች ናቸው፡፡ 60 ገጽ የሚሆን ‹ወያኔ ይውደም› ምናምን የሚል ጽሑፍ አይቻለሁ፡፡ እንግሊዝኛም አለው 10 ገጽ ይሆናል፡፡ በምስል ከውጭ ሰው ጋር ሆነው የሚነጋገሩትም አይቻለሁ፡፡ ይዘቱ ግን ግር ይለኛል፡፡” ብለዋል፡፡ አጥናፍን አስመልክቶ ደግሞ ‹‹የእሱንም በዚያው መልኩ ነው ያየነው፡፡ ዕለቱም ግንቦት 16/2006 ነው፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ የነበሩትን ጽሁፎች እዚያ ለነበሩት ሲያሳይ ነበር፡፡ ጽሑፎችን አይቻቸዋለሁ….‹የጨለማው ቀን….የጨለማው ንጉስ› የሚል አይቻለሁ፡፡ ‹ኢትዮጵያ አንድ ናት› የሚልም አይቻለሁ፡፡ ወደ 30 ገጽ ይሆናል፡፡ ሁሉም ፕሪንት ተደርጎ ሁላችንም ፈርመንበታል፡፡››ብለዋል

ሶስቱ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ጠበቆች በሂደቱ ላይ አስተያየት አለን በማለት፣ ዶክመንቶቹ ፕብሊክ ዶክመንት ናቸው በአደባባይ የተጻፉ ጽሁፎቻቸው እና በማንኛውም ቦታ የሚገኙ ስለሆኑ ዶክመንቶቹን ክደን አልተከራከርንም የእኛ ክርክር ዶክመንቶቹ ለወንጀል ስራ የሚበቁ አይደሉም ነውና በዚህ ጭብጥ ዙሪያ ምስክር መስማቱ ያብቃልን የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡አቃቤ ህግ በበኩሉ ሁሉም ምስክሮች አንዲሰሙልኝ እፈልጋለሁ በማለቱ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያስረዱልኛል ካለ ይቀጥል በማለቱ ምስክሮቹ ቀጥለዋል፡፡ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጠይቁ ተከታዬቹ ምስክሮች መሰማታቸው ቀጥሏል፡፡

4.አራተኛው ምስክር አፈወርቅ ካሳ ይባላሉ፡፡ የግል ሰራተኛ ሲሆኑ እድሜያቸው 46 ነው፡፡‹‹ቀኑ ሚያዝያ 18/2006 ነው፡፡ የተከሳሹ አስማማው ቤት ጠዋት 3፡00 አካባቢ ሲፈተሸ ታዛቢ ነበርኩ፡፡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ፓስፖርት…ብዙ ወረቀቶች ላይ ‹‹አዎ የእኔ ናቸው›› እያለ ሲፈርም አይቻለሁ፡፡ እኔም ፈርሜያለሁ፡፡ ቤተሰቦቹም ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ አብዛኛው ያየሁት የግል መጽሄቶችን ነው፡፡ ማህተምም አይቻለሁ፡፡ ደሞ ቢሮው ሄደን ላፕቶፕ፣ ፍላሽ፣ ሲዲ፣ መጽሔቶች አይቻለሁ፡፡ ፖሊስ የሚፈልገውን እየለየ ፈርመናል፡፡ ወደቢሮው የሄድነው በመኪና ነበር፡፡ ከዛ ደግሞ አድራሻችንን ይዘው ስለነበር ሰኔ 4….አይ 14/2006 ነው መሰለኝ ከማዕከላዊ ተጠርተን ላፕቶፕ ላይ የነበረውን ስዕሎችና የእንግሊዝኛ ንግግሮች ሲወጡ አይቻለሁ፡፡ የእኔ ነው ብሎ ሲፈርም እኛ ታዛቢዎችም ፈርመናል፡፡›› ብለው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

5.አምስተኛ ምስክር አጌና አንከና ይባላሉ፡፡ እድሜያቸው 48 ሲሆን ነዋሪነታቸው አ.አ ነው፡፡ የሚመሰክሩት ደግሞ በ3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ላይ ነው፡፡ የምስክርነት ቃላቸው፣ ‹‹ሰኔ 17/2006 ለግል ጉዳይ ማዕከላዊ ነበርኩ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ታዛቢ ሁነኝ ብሎ ፖሊስ ጠይቆኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ላፕቶፑ ላይ አማርኛ ጽሑፎች አይቻለሁ፡፡ ጽሑፎቹ የተከሳሹ ስለመሆናቸው አምኖ ሲፈርምባቸው ታዛቢዎችም ፈርመናል፡፡ ይዘቱን ግን አላነበብኩትም፤ አልተረዳሁትም፡፡ የገጹን ብዛትም አላስታውስም፡፡›› የሚል የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

6.ስድስተኛ ምስክር ገብረጨርቆስ ገብረመስቀል ይባላሉ፡፡ የ50 ዓመት የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ ምስክሩ በአስማማው ላይ ለመመስከር እንደመጡ ቢናገሩም በአካል ግን ለይተው አላወቁትም፡፡ እንዲያውም አስማማውን አሳዩ ሲባሉ አቤልን አሳይተዋል፡፡

ከፍርድ ቤቱ ውሎ በኋላ አስተያየታቸው የሰጡት የተከሳሾች ጠበቆች አቃቤ ሀግ ያቀረባቸው ምስክሮች ወረቀት ሲፈረም አየን ከማለት ውጪ ምንም አይነት ለሂደቱ ቁም ነገር ያለው ምስክርነት የሚሰጡ አይደሉም ፡፡ ተከሳሾች ተገኘባቸው የተባለው ጽሁፍ የአደባባይ ዶክመንት ከመሆኑም በላይ አልተገኘብንም ብለን ክደን አልተከራከርንም በይዘቱ ላይ ክርክር ስላልተደረገ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብም ብዙ አልጨነቅንም ብለዋል፡፡አቃቤ ሀግ የወንጀሉን የመጀመሪያ ደረጃ ጭብጥ የሚያሳዬ ምስክሮችን ያቅርብ አይቅርብ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የማስረጃ ማሰማት ሂደቱ ነገ ይቀጥላል፡፡

በተቃራኒው ምሳቸውን ችሎት ውስጥ የተመገቡት ሁሉም እስረኞች በጠንካራ መንፈስ ሆነው ሲጨዋወቱ እና ሲነጋገሩ ተስተውለዋል፡፡ የችሎቱ ተሳታፌዎች በምስክሮች መደናበር እየሳቁ ነበረ ሲሆን የዞን9 ወዳጆች አጋሮች ቤተሰብና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡

የዞን 9 ማስታወሻ

የዛሬውን አስቂኝ የፍርድ ቤት ውሎ ባልተካደ ነገር ላይ ወርቃማውን የተከሳሾች ሰአትም ሆነ የፍርድ ቤቱን የስራ ሰአት ማባከኑ የሚገርም ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ችሎቱ በግልጽ አንዲካሄድ መፍቀዱን በበጉ መልኩ ተመልክተነዋል፡፡ አቃቤ ህግ ለምስክሮቹ ደህንነት ሳይሆን የራሱን መዋረድ ለመቀነስ ሲል ችሎቱን በዝግ ለማድረግ መሞከሩ ተከትሎ የመጣውም የምስክሮች መወዛገብ ግልጽ የሚያደርገው ነው ፡፡ የዞን9 ጦማርያን አና ጋዜጠኞች ላይ የቀረበባቸው ማስረጃ በተለያየ ቦታ የጻፏቸው የራሳቸው እና የሎሎች የአደባባይ ምሁራን ጽሁፎች በመሆናቸው ጽሁፉ የእኛ መሆኑ ምስክር አያሻውም ፡፡ በተደጋጋሚ እንዳልነው ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው የታሰሩት ወጣቶች ክስ የጸፉት ጽሁፍ ይዘት ላይ ነው፡፡ የታሰሩ ወዳጆቻችንን ለመፍታት አሁንም አልረፈደም ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ፍርድ ቤት ተገኝተው አጋርነታቸውን ለሚያሳዬ የዞን9 ወዳጆች ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ-መንግስታዊ መብት ይከበር ፡፡

ዞን9

Filed in: Amharic