>

ተዘወሪ መኪና ተዘወሪ !! [እንግዳ ታደሰ፤ ኖርዌይ - ኦስሎ]

ተዘወሪ መኪና ተዘወሪ ፣ አስመራ ፥ ሸዋ ኮይኑ መዛወሪ , በለሆሳስ ትርጉም ከአንድ ወዳጄ ኤርትራዊ እንደተረዳሁት ከሆነ ከአስመራ ተነስተሽ ወደ ሸዋ ብረሪ አንቺ ተሽከርካሪ !! እንደማለት እንደሆነ ትርጉሙ አጫውቶኛል ፡፡ ይህ ዘፈን የተዘፈነበት ወቅት ኤርትራ ወደናት አገሯ በፌዴሬሽን የተቀላቀለችበት ጊዜ ነበር ፡፡ በቅርቡም በዘመኑ የሙዚቃ ቋንቋ ሪ-ሚክስ ተደርጎ ፣ርዕሶም በሚባል አንድ ኤርትራዊ አቀንቃኝ ታድሶ በአዲስ መልክ ይህ ሙዚቃ ቀርቧል፡፡ ማድመጥ የፈለገ ዩቲዩብ ላይ ሄዶ ፈልጎ ማድመጥ ይችላል ፡፡

የኢሳት ጋዜጠኞች አስመራን ጎብኝተው ከመጡ ወዲህ፣ ተዘወሪ መኪና ፊቷን ከአስመራ አባሻውል ወደ አዲስ አበባዋ ሺህ-ሰማንያ ሸዋ ኮይኑ መዛወሪ እያለች በፍቅር ልትንደረደር እንዳሰበች በግንቦት ሰባትና በአርበኞች ግንባር ደጋፊዎች እየተበሰረ ነው ፡፡ በቅርብ አስመራ ለእረፍት ሂዶ የተመለሰ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ኤርትራዊ እንደነገረኝም ከሆነ ፣ እንኳን ቡና ቤት ፣ በታክሲ ውስጥ ሳይቀር የምትሰማው ሙዚቃ ሁሉ አማርኛ ነው ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቶኛል ፡፡ ኧንደውም ጭራሽ አስመራ ካሉ ወዳጆቹ ተቀድቶ የተሰጠውን ልዩ፥ ልዩ የአማርኛ ሙዚቃዎችን አስደመጠኝ ፡፡ተዘወሪ መኪና እውነትም ዳግም አስመራና አዲስ አበባ ላይ ልትዘመር ይመስላል ፣ ከበጎ ምኞት ጋር፡፡ ምንም እንኳን የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ አማርኛ አለመናገር ቢያወዛግበንም ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኢሳት ጋዜጠኞች አስመራ ከርመው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስን ቃለ መጠይቅ ካደረጉላቸው በኋላ፣ ከቃለመጠይቁ ሰበዝ የመዘዙ ተጠራጣሪዎች ነገር ጠርጥረው ያልተዋጠላቸውን ነገር የሆላንዱ አገር ሰው ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ስላፈነዳላቸው ፣ውስጥ ውስጡን ያጉረመረመ ሁሉ በክንፉ ባትሪ አብሪነት የወጣውን ጽሁፍ በማድመቅና ፥ ክንፉን በማውገዝ ጭምር ጽሁፎች ብቅ ፥ ብቅ ማለት ጀመሩ ፡፡ ችግራችን እዚያ ላይ ነው ፡፡ ወያኔን በአፋኝነቱ እያወገዝን ፣መስማት የማንፈልገውን ነገር አንድ ሰው በጽሁፍም ሆነ በድምጽ ሲያሰማ ግን ፣ ልክ እንደ ወያኔ ሊያፍኑ የሚዳዳቸው ወገኖች አሉ ፡፡ የሚወጡ ጽሁፎችንም እንዳይወጡ ማፈን ይጀምራሉ ፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ የታሪክ-መፋለስ/ distortion ብለው ከአንደበታቸው የወጣውን ቃል ጋዜጠኞቻችን ፈርጠም ብለው ባይጠይቋቸውም ፣ቀድሞ ታፍራና ተከብራ ቀይ ባህርን በጀግንነት ከአረቦች ትጠብቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ የቀድሞ ክብሯና ዝናዋ የለም ፡፡ ይህ እንደ ታሪክ መፋለስ፣ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አንደበት ውስጥ ካለ በጸጋ መቀበል ያለብን ይመስለኛል፡፡ የለም ይህ የፖለቲካ ቋንቋ ነው ፣ የእከክልኝ ልከክልህ ጉዳይ ነው የሚል ጠርጣራም ካለ እሱንም ማድመጥ ይገባል ፡፡ በመደማመጥና በመወያየት ጭጋጉን ማጥራት ይቻላል ፡፡ ይህን የታሪክ መፋለስ ጉዳይ ደግሞ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ በጥርጣሬ ቢጠይቅ እንደ አደፍራሽ መቆጠር የለበትም ፡፡

የኤርትራ ከበሳ ተወላጆች/ ደገኛ ክርስቲያኖች/ ለሴት ልጆቻቸው ስም ሲያወጡ ፣ « ኢትዮጵያ » በማለት ነበር በኩራት የሚጠሯቸው ፡፡ ይህን ስም ኢትዮጵያ ውስጥ ከኤርትራውያኖች በበለጠ ፣ አማሮች፥ ትግራዋዮች፥ ኦሮሞዎች… ወዘተ ለሴት ልጆቻቸው ስም አያወጡላቸውም ነበር ፡፡ የቀድሞ ኤርትራውያን ግን ይህን ስም ለሴት ልጆቻቸው በኩራት ያወጡ ነበር ፡፡ እነኝህን ስሞች ዛሬ ለማረጋገጥ በኤርትራ ጋዜጦች ላይ ፣ ወይ በውርስ ሽግግር አሊያም በአርባ ቀን ተዝካር ማስታወሻ ላይ የታተሙትን ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡  ይህም በታሪክ መፋለሱ ውስጥ መታየት የሚገባው ጉዳይ ነው ፡፡

የአቶ ኢሳይያስን ቃለ መጠይቅ አስመልክቶ ፣ ያመኑም ሆነ ያላመኑም ወገኖች በሁለት ጎራ ተሰልፈው ሲወያዩም ሆነ ሲጽፉ ማየት አንፈልግም አይነቱ አካሄድ አያዋጣም፡፡ይህ ሚስጥረ ቁርባን አይደለም ፡፡የታሪክ መፋለሶች አሉ ብለው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጉዳዩን እስካነሱት ድረስ ፣ የታሪክ መፋለሱ ዳግም እንዳይፋለስና ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ቢፈልጉ በፌዴሬሽን ወይ በኮንፌዴሬሽን አሊያም በጥሩ ጉርብትና እንዲቀጥሉ ፣ የታሪክ መፋለሱ በግልጽ ወጥቶ መወያየቱ ለሁለቱም አገሮች ጠቃሚ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ ሁለቱ አገሮች ኩታ ገጠም ስለሆኑ እጣ ፈንታቸው ተደጋጋፊ ነው ፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ፣ ስለፌዴሬሽኑ መፍረስና ችግሩ ፣ ወይም በስድሳዎቹ ውስጥ በተፈጠረው ግራ ዘመም ፖለቲካና ጦሱ ፣ ገብቶ ዝርዝር ውስጥ የመግባት አባዜም አይደለም ፡፡ ወደድንም ጠላንም የሁለቱ አገሮች ጉዳይ ፣ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ብቻ ሳይሆን ፣አይንም ሲያለቅስ አፍንጫም ይናፈጣል ነው ፡፡ በታሪክ የተሠሩ ስህተቶችና ፣ ደርሰን የፈጠርናቸው ድርሳናት ፣ሁለቱም አገሮች በታሪክ እንዲያነክሱ አድርገዋቸዋል ፡፡ የአይሲስ ሊቢያ መድረስና ፥ የሰሞኑ የየመን ጦርነት መቀስቀስ ለኤርትራ እጅግ ቅርብ ናቸው ፡፡ ቁርስ ኤርትራ በልተው ምሳ አዲስ አበባ ላይ እንደሚያደርጉ መጠራጠር የለብንም ፡፡ ዛሬ የኤርትራ ባህር ኃይል ቀይ ባህርን ብቻውን መክቶ ይወጣዋል ብሎም መገመት የዋህነት ነው ፡፡ ይህም በታሪክ መፋለስ ውስጥ ሊካተት የሚገባው ጉዳይ ነው ፡፡

ዛሩ በርዶ – አዎ ዛሬ ዛሩ ወርዶ መሬት ሰፍፎ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ኤርትራ መንደርደርያ መሬት እንደሰጠችና ፣ መሳርያም እንዳስታጠቀች እንዲሁም እንደ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ቃል ፣ አንድ ትንሽ ብሄር ብቻዋን ኢትዮጵያን የመንዳቷ ፣ ሁኔታ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃን ቀንድ ስለሚያምስ ፣ ይህ ስርአት እንዲፈርስ ኤርትራ ጭምር ትተባበራለች በማለት ፕሬዝዳንቱ በግልጽ ተናግረዋል ፡፡ ኢትዮጵያ በዘር ፖለቲካ እንዳትታመስ ፕሬዝዳንቱ ከቀድሞ ጀምረው ይከራከሩ ነበር የሚል ምስክርነትም ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ጭምር ምስክርነት አግኝተዋል ፡፡ ዶክተር ጌታቸው በጋሻውና ታዋቂው ጋዜጠኛ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ጭምር አቶ ኢሳይያስን በሚደግፍ መልኩ ምስክርነት ጨምረዋል ፡፡ በቅርቡም የአመስተርዳሙ ጋዜጠኛ ደረጀ ኃብተወልድ ከቤልጀየም ፣ የግንቦት ሰባት አርበኞች፣ አቶ አሰፋ ቦጋለ እና አቶ መሃመድ ሃሰንን በግል ስለኢሳይያስ አፈወርቂ የአርበኛ ልጅ እንደነበሩና ራሳቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ስለትውልዳቸው ሁኔታ ያልነገሩንን ፣ ሁለቱ እንግዶች ስለአቶ ኢሳይያስ ተናግረውላቸዋል ፡፡ ጋዜጠኛ ደረጀም ከጠያቂነት ባሻገር ራሱ የአስተዋዋቂነትንትን ሥራ በያዘ መልኩ የሚመስል ፕሮግራም ሠርቷል ፡፡

ዛሬ የአቶ ኢሳይያስን መንግሥት የከዳ የቀድሞ የኤርትራ ሰላይ አሁን ደግሞ በጀርመን አገር የሚገኝው አቶ የማነ ተክለጊዮርጊስ፣የአቶ ኢሳይያስን መንግሥት ቢከዳም፣ አቶ ኢሳይያስ ሱማሌያ ውስጥ የሲዳማ ነጻ አውጭ ድርጅት መሪ የነበሩትን አቶ ወልደ ሚካኤል ዱባለን በማግኘት ፣  ሲዳማ ኢትዮጵያዊ እንደሆነና ሲዳማ ከኢትዮጵያ ሊገነጠል እንደማይችል አፈርጥመው ነግረዋቸው ኧንደውም ለወልደሚካኤል ዱባለ ፣ ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ አስተማሯቸው ብሎ ምስክርነት ሰጥቷል ፡፡

እንግዲህ የቱን እንመን ?  ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ለኢሳት ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ ፣ ይህን ሁሉ የታሪክ መዛባት የያዘ፣የወያኔ ጉድፍ በዶክመንት የተጠረዘ ዶሴ እንዳላቸው ደግመው ደጋግመው ተናግረዋል ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ግን ይህን ሰነድ ለምን እንደደበቁት አልነገሩንም ፡፡ ይህም ሊሆን ይችላል አቶ ክንፉን ፥ አቶ ልኡል ቀስቅስን ፥ አቶ ዩሱፍ ያሲንን እና ልጅ ተክሌን በተሟጋችነት ያመጣቸው ፡፡ በደረጀ ሃብተወልድ ቃለ መጠይቅ ላይ ፣ አቶ ኢሳይያስ ያላሳዩንን ዶክመንት የቤልጅየሙ አቶ ሃሰን  በእጃቸው ስላለ በቅርቡ ለዕይታ ለህዝብ እንደሚያሳዩ ቃል ስለገቡ ብዥታው ይጠራል የሚል እምነት አለኝ ፡፡ ከዚህ በተረፈ ፣ ኢትዮጵያን ቆርጠው ነጻ እናወጣታለን ብለው ወደ ኤርትራ በረሃ የገቡትን ፋኖዎች ምርጫ የሚጋፉ ወገኖች ፣ የራሳቸውን ምርጫ አቅርበው በመረጡት መንገድ መሄድ ሲገባቸው ጉልበታቸውን በግንቦት ሰባት አርበኞች ላይ የማጥፋቱም መንገድ አዋጭ  አይደለም ፡፡

የነክንፉን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጋፋ ኃይል እንደማይደገፍ ሁሉ ፣ የግንቦት ሰባት አርበኞችን ትግል የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው እስካልሰጡ ድረስ ማውገዙም ተደጋፊነት የለውም ፡፡ በአባ መላ ጥቀስ ሃሳቤን ልቋጭ ፡፡  « ፖለቲክስ ዳይናሚክስ » ነው እንደሚለው ትላንት የነከስነውን ጥርስ ባይሲስ ግስገሳ እና የየመን መተራመስ ብቻ ሳይሆን ከሁለቱም አገሮች ኩታ ገጠም ጥቅም አንጻር አርቀን መመልከት ያለብን ጉዳይ ነው ፡፡ የፖለቲካው አካሄድ በወግ በወጉ ቢሆን ለሁላችንም ይበጃል ፡፡የነአይሲስ ተዘወሪ ታንክ ከሚመጡብን የድሮዋን ተዘወሪ መኪና ከሪል-ቴፕ ላይ አቧራዋን አራግፈን በጋራ መዝፈኑ ሳይበጀን አይቀርም ፡፡

 

Filed in: Amharic