>

“ተወይኖብኛል … በዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ተልእኮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባርሬአለኹ” [ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ]

Dr Dagnachew Assefa facebook picዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት (sabbatical leave) ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

አዲስ አድማስ – በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በእርስዎ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ጋር በኹለት ጥያቄዎች ዙሪያ የማይታረቅ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው÷ አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ ኾኖም ግን ዩኒቨርስቲው ‹‹የጡረታ ሥርዓተ – ሒደቱን አላሟላኽም›› በሚል በሕጉ ፊት የማይጸና ሰበብ ፈጥረው ይገባኻል ብለው ከፈቀዱልኝ በኋላ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ለማንኛውም መምህር ሥርዓተ ሒደቱን የማስፈጸም ሓላፊነት የሰው ሀብት አስተዳደሩ ድርሻ ኾኖ ሳለ፣ እኔን ተጠያቂ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል::
በነገራችን ላይ የጥናት ዕረፍት ፈቃዴን የጠየቅኹት ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስድሳ ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡ በየሰበቡ ሲጓተት ስለቆየ ወደ ስድሳ ዓመቱ ገደብ ደረስኹ፡፡ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ከመሔዱ አስቀድሞ ውስጣዊ ተቋማዊ መፍትሔ ለማበጀት ወደ ዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ቀርቦ ምላሽ ስጠባበቅ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡
የሥራ ውሌን በተመለከተ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን የአገልግሎት ቆይታ እንደሚፈልግና በተለይም በቅርቡ ለሚጀምረው የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተሳትፎዬ እንደሚጠቅም በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ በመወሰኑ ውሌ እንዲራዘም ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን ጽፎልኝ ነበር፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሓላፊዎች በተሰበሰቡበት፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ከተወያየበት በኋላ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉን ጥያቄ ዳግመኛ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶበት፣ ውሳኔው በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በፕ/ር ወልደ አምላክ በዕውቀት በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይኹንታቸውን እንዲሰጡበት(እንዲያጸድቁት) ተጠይቆ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከአራት ወራት ያኽል ቸልተኝነት በኋላ ‹‹ወረቀቱ ይመጣለታል›› በሚል ለተከታዩ ሴሚስተር እንዳልደለደል በአዲሱ ዲን በኩል ለትምህርት ክፍሉ ሊቀ መንበር መመሪያ አስተላለፉ፡፡ መመሪያው የእኔን መሰል ጥያቄ ባቀረቡ ሌሎች መምህራን ላይም የተላለፈ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በላይ ደመወዜን ይዘው መክፈል ከአቆሙ በኋላ ‹‹ለሚመጣው ሴሚስተር አትመድቡት›› ማለት በአካዳሚያ ቋንቋ ግለሰቡ ተሰናብቷል ማለት ነው፡፡

በመሠረቱ፣ የትምህርት ክፍሌና አካዳሚክ ኮሚሽኑ የሥራ ውሌን መራዘም ተስማምተው ላቀረቡት ጥያቄ ሲኾን እንደወጉ ማጽደቅ አልያም በአስቸኳይ ውሳኔን ማሳወቅ ሲገባ ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ወራት በላይ ማቆየታቸው ኢ-ሕጋዊ ነው፤ ሕጉን ጠብቆ በወጉ ለቀረበ ጥያቄ ከሦስት ወራት በላይ ምላሽ አለመስጠት እብሪት፣ ትዕቢትና ማናለብኝነት እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም፤ በተመሳሳይ ወቅት አንድ ዐይነት ጥያቄ በደብዳቤ ከአቀረብነው መምህራን መካከል፣ ለምሳሌ ከኛው ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማ በሥራው እንዲቀጥል በቃል ትእዛዝ ፈቅደው፣ ለእኔ በአግባቡ ውሳኔ ሳይሰጡ ‹በሚቀጥለው ሴሚስተር እንዳትመድቡት ማለት የአድልዎ አቀራረብ ብቻ ሳይኾን በዘፈቀደና በግፊት የሚካሔድ አመራር መኾኑን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አድማሱ ዩኒቨርስቲውን ለመምራት ያላቸውን ብቃት ከዝህ ቀደም በአደባባይ ስለጠየቅኹ በቂም በቀልና ኹን ብለው እኔን ለመጉዳት የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡

የጥናትና ምርምር ዕረፍት(sabbatical leave) በተመለከተ በጊዜው የካሌጁ ዲን የነበሩት ዶ/ር ገብሬ ይንቴሶ የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ተከትለው ከላይ እንደጠቀስኹት የሰጡኝን ፈቃድ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከማምራቴ በፊት፣ የፕሬዝዳንቱን ምላሽ ከወዲኹ ባውቀውም አቤቱታዬን የግድ ለእርሳቸው ማቅረብ ነበረብኝ፡፡

በኮሌጁ የቀድሞ ዲን ውሳኔ ላይ ከዐሥር ገጽ ያላነሰ አባሪ ሰነዶች አያይዤ ጠዋት ላቀረብኹት አቤቱታ፣ ከቀትር በኋላ ‹‹በጥልቅ መርምረን›› በሚል በአንድ መሥመር የኮሌጁ ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ ፌዝና የቀልድ ምላሽ ነው የተሰጠኝ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራን ከበሬታ የሌላቸውና አመራራቸውም ከሞራላዊነት የተራቆተ መኾኑን ነው፡፡ እኔ ግን ታዋቂው አርበኛ አበበ አረጋይ በአንድ ወቅት በፋሽስት ጣልያንና በባንዳ ለተከቡበት የተራቡ ጭፍሮቻቸው ‹‹ሞተን አንጠብቃቸውም፤ ተረጋግታችኹ ብሉ›› እንዳሉት፣ ከማባረር ያልተናነሰ የዘገየ አንድ ብጣሽ ወረቀት ገና ለገና ይመጣል ብዬ ሞቼ አልጠብቃቸውም፡፡

አዲስ አድማስ – የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ ለማራዘም የተፈቀደላቸው መምህራን አሉ ወይ? ማለትም በዩኒቨርስቲው አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ መምህራን ውላቸውን ማራዘም ይችላሉ ወይ?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ- በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ፡፡ በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው፡፡

አዲስ አድማስ-የዚኽ ኹሉ መነሻ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ- ከኹሉ በፊት የእኔ መከልከልና መሰናበት ከፖሊቲካ እይታ አኳያ የመነጨ መኾኑ ማንም አይስተውም፡፡
ማለት…
በዩኒቨርስቲው በማስተማር ሥራ በቆየኹባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች የማደርጋቸው የዐደባባይ አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች አልተወደደዱም፡፡ እንዲያውም ለሹመኞች ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝ፣ ‹‹ዳኛቸው፣ ዩኒቨርስቲውን እንደ ደጀንና ገዥ መሬት ተጠቅሞ መድፍ ሲተኩስብን ቆይቷል›› ተብዬአለኹ፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ አቋም ከተወሰደ በኋላ በሥራ ገበታዬ እንድቀጥል አለመደረጉ አይገርመኝም፡፡

አዲስ አድማስ -ለሰባት ዓመት ካስተማሩበት ዩኒቨርስቲ በዚኽ መልኩ ሲሰናበቱ ምን ተሰማዎ?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ- እንደ እውነቱ ከኾነ የተደበላለቀ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ነገር ከሰባት ዓመት በኋላ መኾኑ አስደስቶኛል፡፡ ይኸውም የመጣኹበትን የማስተማር ዓላማ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመኾን ለመስኩ ተተኪና ምሉዕ የኾኑ ተማሪዎች ለማፍራት በመብቃታችን አስደስቶኛል፡፡ ይህ ክልከላና ስንብት በቂ ምሩቃን ባላፈራንበት ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ቢከሠት ኖሮ አዝን ነበር፡፡
በኹለተኛ ደረጃ፣ ‹የዓመት ዕረፍት(ሳባቲካል) አይሰጥኽም፤ ከእንግዲኽ ማስተማርም አትችልም› ስባል ለራሴ በጥልቀት ተሰምቶኝ ያልኹት፣ ‹‹አኹን ገና ኢትዮጵያዊ ኾንኩ፤ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚኽ ሰባት ዓመት ቆይታዬ ከአሜሪካ ሳልፈታ ይዠው የመጣኹት የነፃነትና የመብት አቅዋም፣ ከአገራችን ፖሊቲካዊ ነባራዊ ዕቀባ በተፃራሪው እንደ ልቤ እንድተችና ያለገደብ እንድናገር አስችሎኝ ነበር፡፡ አኹን ግን ሥርዓቱ ‹ይኼ አሜሪካ አይደለም፤ እንደ ጎረቤትኽ ሳይኾን እንደቤትኽ እደር› ተብዬአለኹ፡፡

ይህን ስል ግን፣ እኔ በዕድሜዬ የምወልዳቸው ልጆች በኾነ ባልኾነ ክሥ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ባሉበት ኹኔታ ከሥራ አባረሩኝ ብዬ የማለቅስ ሰው አይደለኹም፡፡ በእኒኽ ብሩህ ተስፋ ባላቸው ወጣቶች ላይ ከደረሰው አንጻር ሲታይ መብቴ መረገጡ እውነት ቢኾንም፣ የአገራችን ተረት ‹‹እናቱ ውኃ ልትቀዳ የወረደች ልጅና እናቱ የሞተችበት ልጅ አንድ ጋር ቆመው ያለቅሳሉ›› እንደሚባለው ይመስልብኛል፡፡
በመጨረሻም በአንድ በኩል፣ በውጭ ለብዙ ዓመት ቆይቼ ስመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የት ከረምክ ሳይለኝ ችሎታዬ በሚፈቅድልኝ ቦታ ሥራ ሰጠኝ፡፡ ለዚኽ ትልቅ ምስጋና ነው የማቀርበው፡፡ ኾኖም በሌላ በኩል የውስጥ አስተዳደሩና የውጭ የፖሊቲካ ኃይሎች በመተባበር መክረው ከሕዝብ ባገኘኹት ቸርነት ላይ ወይነውብኛል!

አዲስ አድማስ – ከዚኽ በኋላስ ምን ዓይነት ሥራ ላይ ለማተኮር ያስባሉ?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ-ይህን ጥያቄ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ብትጠይቀኝ ኖሮ፣ ጉዳዩ በራሴ የሚወሰን በመኾኑ አኹኑኑ እመልስልኽ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ቤትኽ እደር ተብዬአለኹና የጥያቄው ምላሽ በእኔ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥያቄው በአንድ ወቅት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሉ የተባለውን ያስታውሰኛል፡፡ አንድ ሹም ጃንሆይ ፊት ቀርበው የንጉሡ ትችትና ተግሣጽ ሲገጥማቸው፣ ‹‹እንዲያውም ግርማዊ ሆይ፣ የሰጡኝ ሹመት ይቅርብኝ፤ የአባቴን ርስት እያረስኩ እኖራለኹ›› አላቸው፡፡ ጃንሆይም ወዲያው ‹‹እርሱንም እኛ ስንፈቅድ ነው…›› ብለው አሉ ይባላል፡፡ እኔም እንደ አቅሜ ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም በቀጣይ ምን መሥራት እንደምችልና እንደማልችል ብያኔው በመሠረቱ ከእኔ ውጭ ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን በአለችኝ ቀሪ ዕድሜ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ በዚኹ አጋጣሚ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበትን ተቋማዊ ኹኔታ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ እንደማስነብብ ከወዲኹ ለማሳወቅ እወዳለኹ፡፡

ምንጭ፡ አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic