>
5:13 pm - Friday April 19, 0763

እነ አብርሃ ደስታ ለሦስተኛ ጊዜ ችሎት ‹ደፈሩ›

ነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ Abrha Desta (photo by Kuru Hagere FB)የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ለሦስተኛ ጊዜ ችሎት መድፈራቸው ታውቋል፡፡

በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ዛሬ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ፍ/ቤት የቀረቡት አመራሮቹ መጋቢት 1/2007 ዓ.ም በነበረው ችሎት ወቅት ችሎት ደፍራችኋል በሚል አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ እያንዳንዳቸው በ7 ወር እስር እንዲቀጡ ሲበየንባቸው ብይኑን በመቃወም ማጨብጨባቸውና ሳይፈቀድላቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በዕለቱም ድርጊታቸው ችሎት መድፈር ነው በሚል ጥፋተኛ ተብለው ነበር፡፡

በዛሬው ውሎው የቅጣት ውሳኔ የሰጠው ችሎቱ ለሦስተኛ ጊዜ በሦስቱ አመራሮች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቶ የሺዋስ አሰፋ እና አቶ ዳንኤል ሺበሽን ‹ብይኑን በመቃወም አጨብጭባችኋል› በሚል እያንዳንዳቸውን በ7 ወር እስራት፣ እንዲሁም ከማጨብጨብ በተጨማሪ ችሎቱን ‹አሻንጉሊት› ብሎ ሰድቧል የተባለው አብርሃ ደስታ ደግሞ በ9 ወር እስራት በድጋሜ ተቀጥተዋል፡፡

አመራሮቹ ዛሬም ለሦስተኛ ጊዜ ብይኑ ተሰምቶ እንዳለቀ በተቃውሞ በማጨብጨብ ለሦስተኛ ጊዜ ችሎቱን ‹ደፍረዋል›፡፡ ፍርድ ቤቱም አመራሮቹ አሁንም ጥፋት መፈጸማቸውን ገልጾ፣ ነገር ግን በይቅርታ እንዳለፋቸው በመግለጽ ድርጊታቸውን እንዲያስቡበት አስገንዝቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ አቃቤ ህግ በ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ላይ አሻሽሎ እንዳቀረበው የተነገረለትን ክስ ተቀብሏል፡፡ ተከሳሾች መጋቢት 10/2007 ዓ.ም የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

Filed in: Amharic