>

የኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ 60ኛ ዓመት የልደት በዓል በኦስሎ ኖርዌይ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

”የኣቶ ኣንዳርጋቸው 60ኛው ዓመት የልደት በዓል ላይ በመገኘቴ ደስተኝ ነኝ”
Alemu Adugna Ferede & Tigst Tadesse from Stavanger on Andargachew Tsige 60BD- photo Abebe Demekeይህንን ያሉን የ 7 ሰዓት የባቡር ጉዞ ተጉዘው ከ አስታቫንገር ኦስሎ የደረሱት (ፎቶ) ኣቶ ኣለሙ ኣዱኛ ፈረደና ወ/ሪት ትእግስት ታደሰ ናቸው። በኖርዌይ ኦስሎ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ የወጣቶች ክፍል ባዘጋጀው የኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ 60ኛ ዓመት የልደት በዓል  ላይ ለመገኘት ከፍተኛ  የመጓጓዣ ወጪ በመክፈል ለመታደም የመጡትን ኣነጋግረናቸው ነበር።
”ኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌን መስከረም 28/2013  በኖርዌይ – ኦስሎ ባደረጉት ዝግጅት ላይ ለመካፈል እድሉን ኣግኝቼ ነበር። ያን ጊዜም ዝግጅቱን ለመታደም የመጣሁት ከስታቫንገር ነበር።  ያን ጊዜ እሳቸውን በቅርብ ለማወቅ ዕድሉን ኣግኝቻለሁ ማለት እችላለሁ። ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ኣስተውያለሁ። የሰላሙ በር እስኪዘጋባቸው ድረስ የቻሉትን ሁሉ የሞከሩ ሰው ናቸው።ኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ ወያኔ/ኢህኣዲግን በሁሉም ነገር ኣሸንፈውታል። እኛን ሁሉ ያፈሩት ኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ ናቸው። ዛሬ ሁላችንም ኣንዳርጋቸው ጽጌ ነን።
60ኛው የልደት በዓላቸውን ሁሉም ነገር ተለውጦ ኣንዳርጋቸው የሚመኙዋት ኢትዮጵያን ኣይተን የምናከብረው ልደት ቢሆን ደስታዬ ይበልጥ ነበር። ኣሁንም ለዚያ የሚያስፈልገውን ጠጠር ሁላችንም በኣቅማችን መወርወር ከቻልን ኣንዳርጋቸው ጽጌ የዘረጋልን የትግል መንፈስና በጣለልን መሰረት መጨረሻው መድረሱ የማይቀር መሆኑን እረዳለሁ።” በማለት የገለጸችልን ትዕግስት ታደሰ ስትሆን፣ ኣቶ ዓለሙ ኣዱኛ ፈረደም በበኩላቸው:- ኦስሎ በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት  ትራንስፖርት ቲኬት ኣጥተው በውድ እንደገዙ ነግረውን፤  በኣቶ ኣንዳርጋቸው መታሰቢያ ዕለት መገኘታቸውን የገለጹልን እንዲህ በማለት ነበር።
B- Oslo Andargachew Tsige 60 BD- photo Abebe Demeke”ኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌን ካንዴም ሁለቴ ኣግኝቸዋለሁ። እዚሁ ኖርዌይ ውስጥ። ኣቶ ኣንዳርጋቸው ልዩ ሰው ነው። ከማናችንም ይለያል። ከሞቀ ቤቱ ወጥቶ ትግል የገባ ሰው ነው። ሁልጊዜ በፍቅርና በወኔ የማነሳው ሰው!… የኢትዮጵያችን ማንዳላ ኣንዳርጋቸው ጽጌን 60ኛ የልደት በዓል ለማክበር የተገኘሁት በፍላጎቴ ነው። ለሃገሩና ለወገኑ ትልቅ መስዋዕትነት ለከፈለው ጀግና ይሄ የኔ መገኘት ሲያንስ ነው። የተፈለገውን መስዋዕትነትም ለመክፈል የተዘጋጀሁ ነኝ – በግሌ። በሃገር ቤት ውስጥ በኣረመኔውና ወንበዴው ስርዓት ለሚሰቃዩ ወገኖቻችን ኣንዳርጋቸው የከፈለው መስዋዕትነት ልዩ ነው።ምሳሌነቱም ለሁላችንም ነው።ለዚያም ነው የተገኘሁት። ኣዎ ሁላችንም ኣንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን።” ብለውናል።
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ኖርዌይ  ኦስሎ በ”ኣንቲ-ራሲስት ሴንተር” በተያዘው ኣዳራሽ ውስጥ ከኖርዌይ ከተለያዩ ከተሞች ስታቫንገር፣ በርገን፣ ኦስሎና ኣካባቢዋ የሚገኙ የድርጅቱ ኣባላቶችና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያኖች በተገኙበት በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት የኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ 60ኛ ዓመት የልደት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል።(ኢትዮ- ሪፈረንስ)

 

Filed in: Amharic