>

ኑ ባንስማማም እንደማመጥ - እንተማመን! [ዮናታን ተስፋዬ - ሰማያዊ ፓርቲ]

(POWER TO THE PEOPLE)

Power-To-The-People - Yonatan Tesfayeላለፉት ሀምሳ እና አርባ ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ትግል እንዲከሽፍ ካደረጉት ዋና ነገሮች ውስጥ ጥርጣሬ እና አለመደማመጥ ግምባር ቀደሞች ናቸው፡፡ በኔ እምነት ብዙዎች የተለያዬ ርዕዮተዓለሞችን ለመተግበር ጥረዋል፤ ብዙዎች የሀገራችን ችግር ይህ ነው ያሉትን (የመደብም ይሁን ‘የብሔር’ ጭቆና) ለመቅረፍ የተላያዩ መላዎችን ዘይደው ደምተዋል ቆስለዋል ብዙም ዋጋ ከፍለዋል፡፡

የዚህን ያህል ዋጋ ተከፍሎም ከክሽፈት አዙሪት ያለመውጣታችን እውነታ ግን አንደኛው ቡድን ሌለኛውን ለማዳመጥ ፍላጎት አላማሳየቱ እና በሞቲቭ ትንተና በተበላሸው የሴራ ባህላችን በመጠለፍ ጭንቅላታችንን የተቆጣጠረው አብዝቶ የመጠራጠር መንፈስ ነው፡፡
አንዲህ ያለው ክፉ ልማድ ደግሞ መነሻው ለህዝቡ እኔ አውቅለታለሁ የሚል መታበይ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም ድርጅት ራሱን እወክለዋለሁ ለሚለው ማህበረሰብ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማየት ሲጀምር ነው ነገሩ የሚበላሸው፡፡ ጥራጣሬውም ሆነ አለመደማመጡም የሚመነጨው ከዚሁ የመታበይ እና ‘ከኔ ወዲያ’ ከሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ ያላቸውን ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ከማድመጥ፣ ከመቻቻል እና የሚበጀውን ተቀራርቦ መላ ከመዘየድ ይልቅ አብዝቶ መጠራጠር እና ለማዳመጥ ዝግ መሆን ለራስ ካለመጥቀሙም ሌላ እንወክለዋለን ለሚባለው ማህበረሰብ የነፃነት ትግል ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡

አሁን ባለንበት የአገዛዝ ስርዓት – በዚህ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል ውስጥ ያለፉ በርካቶች ዘመናችንን በልካችን ለሀገራችን እና ለህዝባችን መልካሙን እንዳናደርግ ያረጀ እና ያልበጀ ተጠራጣሪነታቸውና ሌላውን ለማድመጥ ዝግ የመሆን አባዜያቸውን እየጫኑብን እና እያዋረሱን ይገኛሉ፡፡ ይህ አካሄድ ግን ለነሱም ሆነ ለህዝብ ለኛም ትውልድ እንዳልበጀ ቆም ብሎ የማሰብ እንኳን ጊዜ የላቸውም፡፡
ይባስ ብሎ ይህ ክፉ ልማድ የተጠናወታቸው ወጣት ፖለቲከኞችና የመብት ተፋላሚዎች በየፊናቸው ከትመው በዛው አዙሪት መቆራቆዙን ሙያዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡

እኔም እመክራለሁ – እባካችሁ ስለዉዲቷ ሀገራችን፣ ስለምንቆረቆርለት ህዝብ ስንል ያለፈውን የክሽፈት መንገድ ቆም ብለን መርምረን በቀናው ጎዳና እንጓዝ፡፡ እውነት ለሀገርና ለህዝብ የምናስብ ከሆነ የምናራምደውን ሀሳብ ይዘን ህዝብ ዘንድ የምንቀርብበት እና ዳኝነቱን ህዝቡ የሚሰጥበት ስርዓት ለመዘርጋት እንታገል፡፡ ቢያንስ ቢዘህ ተማምነን በጋራ ስርዓቱን እንታገል፡፡ ቢያንስ በዚህ ተደማምጠን ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንዋደቅ፡፡ ለኔ ከዚህ ውጪ አማራጭ ያለን አይመስለኝም! ካለም ያው መሳሪያውን የያዘ ባለተራ በትረመንግስቱን ጨብጦ መከራውን ማብዛት ነው፡፡

እያንዳንዳችን ስለሁላችን ሁለንተናዊ እድገት ስንል ለሀገር እና ህዝብ የሚበጀውን በማድረግ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጠጠራችንን እንጣል! ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ እንስጥ! ህዝብ የሰልጣን ባለቤት ካልሆነ የትኛውም አማራጭ መንገድ ከመንገድነት ባለፈ ልንጓዝበት አይቻለንምና!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Filed in: Amharic