>

ደላሎች ለሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ እንዳያከራዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

‹‹ለአሸባሪ ፓርቲ ቢሮ ብታከራዩ ተጠያቂነቱን ትወስዳላችሁ›› የቂ/ክ/ከ ወረዳ 8 ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ

ነገረ ኢትዮጵያ

የቤት ደላሎች ለሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ እንዳያከራዩ ከቀበሌ ባለስልጣናት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ተደራጅተው በመስራት ላይ የሚገኙት ደላሎች የቂ/ክ/ከ ወረዳ 8 ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ከበደ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አሸባሪ ፓርቲ ነው፡፡ ለአሸባሪ ፓርቲ ቢሮ ብታከራዩ ተጠያቂነቱን ራሳችሁ ትወስዳላችሁ›› ብለው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ለማከራየት ተስማምተው የነበሩ አንድ ግለሰብ በቀበሌ ካድሬዎች ትዕዛዝ ቤቱን እንዳያከራዩ ተደርገዋል፡፡ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ደላሎች ግለሰቧን ‹‹መጀመሪያ ቀበሌ ሄደሽ ለሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ልታከራይ መሆኑን አሳውቂ›› ብለው በመከሯቸው መሰረት ቀበሌ ሄደው ‹‹ለሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ላከራይ ነበር፡፡ ምን ችግር ይኖረዋል?›› ብለው ሲጠይቁ የቀበሌ ካድሬዎች ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ህገ ወጥና አሸባሪ ፓርቲ ነው፡፡ ለእሱ ቢሮ ማከራየት በህግ ያስጠይቅሻል›› ብለው ስላስፈራሯቸው ለማራየት ሳይደፍሩ ቀርተዋል፡፡

የየካ ክፍለ ከተማና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በጋራ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ እንዳይከራይ ደላሎቹና አከራዮችን እያስጠነቀቁ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ ካሳንቺስ የሚገኘው ጽ/ቤቱን እንዲለቅ በቤቱ ባለቤቶች ላይ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ አከራዮቹ በቀበሌ ባለስልጣናትና በደህንነቶች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ፓርቲው ቤታቸውን እንዲለቅላቸው፣ ካልለቀቀም አሁን ከሚከፍለው 3 እጥፍ ገንዘብ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል፡፡

Filed in: Amharic