>
5:13 pm - Friday April 19, 5326

ጋዜጠኞችና ጦማርያኑ ለጥር 26 ቀጠሮ ተሰጠባቸው

∙ፍርድ ቤቱ ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ ብይን ሰጥቷል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

photo by zone 9ersየዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ዛሬ ጥር 20 ቀን 2007 ዓ.ም ለ16ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ ተሻሻለ የተባለውን ክስ አይቶ ብይን ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ከአራቱ ነጥቦች መካከል አንዱን ብቻ ውድቅ ሲያደርግ ሦስቱን እንደተሻሻሉ ቆጥሮ በክሱ ውስጥ እንደተካተቱ እንዲቀጥሉ በብይኑ አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግ የክስ ማሻሻያ ላይ የሰጠውን ብይን በንባብ አሰምቷል፡፡ በዚህ መሰረት የፌደራል አቃቤ ህግ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ ከአንዱ ነጥብ በስተቀር ቀሪዎቹ ሦስት ነጥቦች ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አቃቤ ህግ አሻሽሏል በሚል ፍርድ ቤቱ በቀበሉን በብይኑ አመልክቷል፡፡
ስለሆነም በክሱ ላይ የተጠቀሰው የተከሳሾች የስራ ክፍፍል አለ በሚል የቀረበው ነጥብ ብቻ በአቃቤ ህግ እንዳልተሻሻለ በመውሰድ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ሲያደርገው ሌሎቹ ነጥቦች፣ ማለትም ‹ቡድን› በሚል የተጠቀሰው፣ የ48000 ብሩን ጉዳይ እንዲሁም ተከሳሾቹ ስልጠና መውሰዳቸውን የሚገልጸው ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ እንደተሻሻሉ ቆጥሮ ተሻሻለ በተባለው ክስ ውስጥ እንዲካተቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
በክሱ ላይ ‹ቡድን› በሚል የተጠቀሰው ነጥብ ተከሳሾቹ በህቡ ያቋቋሙት ቡድን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቧል ያለው ችሎቱ፣ የቡድኑ አጠቃላይ ሁኔታ በቀጣዩ በክርክር ወቅት በማስረጃ የሚረጋገጥ አልያም ውድቅ ሊሆን የሚችል ስለሆነ በክሱ ላይ መካተቱ ተገቢነቱን ተቀብሎታል፡፡
ስልጠና መውሰድን በተመለከተም ‹‹ተከሳሾች ከ2004 ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በግንቦት 7 አመቻችነት ስልጠና መውሰዳቸውን የተሻሻለው ክስ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም ጊዜውና በማን የሚለው ስለተጠቀሰ ክሱ መሻሻሉን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎታል›› በሚል ነጥቡ በክሱ ላይ እንዲካተት በይኗል፡፡ የ48 000 ብሩን በተመለከተ ደግሞ ‹‹ብሩን ውጭ ሀገር ከሚገኙ የቡድኑ አባላት መቀበላቸውን የተሻሻለው ክስ ስለሚጠቅስ›› በሚል እንደተሻሻለ አድርጎ ፍርድ ቤቱ መቀበሉን በብይኑ አመልክቷል፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎ ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው በክሱ ላይ ‹‹የእምነት ክህደት ቃል ይሰጡ ከሆነ›› ውሳኔያቸውን እንዲያሳውቁ አጭር ቀጠሮ በመፍቀድ በቀጣዩ ማክሰኞ (ጥር 26/2007 ዓ.ም) ችሎት እንዲቀርቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

Filed in: Amharic