>

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም በወታደሮች ተደበደበ

በዳዊት ሰለሞን

በዝዋይ ወህኒ ቤት የሚገኘውን ወንድሙን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ ትናንት ማለዳ ወህኒ ቤቱ በራፍ ላይ የደረሰው ታሪኩ ደሳለኝ በወህኒ ቤቱ ሀላፊና ስምንት በሚደርሱ ወታደሮች ድብደባ እንደደረሰበት በፌስ ቡክ ገጹ ታሪኩ አስታውቋል፡፡ለተመስገን ይዞ የመጣውን ምግብ ወታደሮቹ መሬት ላይ ከመድፋታቸውም በላይ በኪሱ የያዘውን ገንዘብ ወስደውበታል፡፡ታሪኩ ከደረሰበት ድብደባ በላይ ወንድሙን ሳይጠይቅና የሚገኝበትን ሁኔታ ሳያጣራ መመለሱ ህመም እንደፈጠረበት አስታውቋል፡፡የታሪኩ ስለ ሁኔታው የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር፡፡
Tariku Desalegnስምንት አንድን ሰው በደም እስኪታጠብ ድረስ በርግጫ፣ በጥፊና በሰደፍ መደብደብ፣ በእጁ ላይ የሚገኝውን ብርና መፃሀፍ መንጠቅ፣ ስልኩን መስበር…. ይህ ድርጊት በሌሊት አንድ ሰው ላይ በሌቦች የተፈፀመ ሳይሆን ትላንት ከረፋዱ በ 5 ሰዓት ላይ በዝዋይ እስር ቤት ግቢ ውስጥ በኔ ላይ የተፈፀመ ነው፤
ነገሩ እነዲህ ነው የሆነው፣ እንደልማዴ ዝዋይ የደረስኩት በማለዳ ነው፡፡ የያዝኩትን ስንቅ አስፈትሼ እንደጨረስኩ የሬዲዬ መገናኛ የያዘ መቶ አለቃ እንደሆነ የሚገልፅ ማዕረግ ያለው ወታደር እየገላመጠኝ “ለምን መጣህ?” አለኝ፤ “እዚህ የታሰረ ወንድም አለኝ እሱን ለመጠየቅ ነው” ስል መለስኩ፡፡ ቀጥ ብለህ ወጣ ተከተለ “አንተ ወንድምህን መጠየቅ አትችለም” ሲለኝ “ምክኒያቱ ይነገረኝ” ብዬ ብናገር ከጉዳይም አልቆጠረኝም “እሺ እኔ ባልገባ እንኳን ያመጣሁት ምግብን አድርሱልኝ” ብል ስሚ አጣሁ፡፡ አንገቴን ደፍቼ ልወጣ ስል መቶ አለቃው በሬዲዬ እያወራ አንድቆም በእጁ ምልክት ሲሰጠኝ ልገባ ነው ብዬ ደሰ አለኝ፡፡ መቶ አለቃው በፍጥነት ወደኔ በመምጣት ያዙት አለ፡፡ በዙሬያዬ ወደ ስምንት የሚጠጉ ወታደሮች ከበቡኝ፡፡ የመቶ አለቃው “የተመስገን ታናሽ ወንድም ታሪኩ ነህ?” አለኝ፡፡ የተመስገን ወንድም መሆኔን በአንገቴም በአፌም “አዎ ነኝ” ከማለቴ ጥፊ ጆሮዬ ላይ ጮኽ፡፡ ከዛም አንደኛው በከስክስ ጫማ ሌላኛው በሰደፍ ተቀባበሉኝ፡፡ ደምቼ መሬት እስክወድቅ ድረስ ደበደቡኝ….ደበደቡኝ፤ ወደኩኝ፡፡ ከነደሜ አነሱኝ የያዝኩትን ብርና መጽሐፍ ነጠቁኝ ያመጣሁትን ምግብ መሬት ላይ ደፉተው እየገፈታተሩ ከግቢው አስወጡኝ፡፡ እስር ቤቱ ፊት ለፊት አቧራው ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ ተሜን በዓይን ርቀት ያህል ብቀርበውም መጠየቅ ባለመቻሌ አለቀስኩኝ፤ ደሜን አፍስሼ ወንድሜን ሳላይ ተመልሻለሁ … ተሜ ለኔ አንተን አለማየት የማይቻል ሽክም ነው፡፡ ይሄንንስ እንዴት ልንገርህ?

Filed in: Amharic