>

የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ የፍርድ ቤት ውሎ ''የጋዜጠኛ አስማማው ሁኔታ የችሎቱን ታዳሚ እንባ አራጭቷል'' (ኣዲስ ጉዳይ- ኣዲስ ኣበባ)

”የሥነልቡና ጫና ደርሶብኛል”

ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ

”ከሌሊቱ 8 ሰዓት እየተወሰድኩ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ወከባ ተፈጽሞብኛል”
አጥናፍ ብርሃኔ

”ለምርመራ የምጠቀምበት አንድ ኮምፒውተር ነው ያለኝ፤ ጊዜ ይሰጠኝ”
ፖሊስ

ቅዳሜ ግንቦት 9፣ 2006 በቀጠሯቸው መሠረት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት 3 ጋዜጠኞች እና 3 ብሎገሮች ነበሩ፡፡ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ጉዳዩ ከወንጀል ወደ ሽብር በማሻሻሉ እና ምርመራዬን አላጠናቀቀኩም በማለቱ የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ሦስት ሰዓት ይሰማል የተባለው ችሎት 4፡30 አካባቢ የተጀመረ ሲሆን በመዝገብ ቁጥር 118721 የተከሰሱት ሦስት ተጠርጣሪዎች ኤዶም ካሣዬ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ በመጀመሪያ ቀርበዋል፡፡ በዛሬው ችሎት ከእየአንዳንዱ ታሳሪ ሦስት የቤተሰብ አባላት ወደ ችሎት ገብተው እንዲታደሙ ተፈቅዶ ነበር፡፡ ፖሊስ ክሱን ከወንጀል ወደ ሽብር ከፍ አድርጎ ቀርቧል፡፡ ምርመራዬን ስላላጠናቀቅኩ የተጨማሪ የ28 ቀናት ጊዜ ይሰጠኝ ብሎም ለችሎቱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ግን ከዚህ ቀደም በተሰጠው ሁለት ቀጠሮዎች ውስጥ አጣራቸዋለሁ ያላቸው 6 ጉዳዮች አሁንም አልተሰሩም፤ ድርጊቱ ደንበኞቻችንን በቀጠሮ ማጉላላት ነው፣ ማስረጃ ባልተሰበሰበበት ሁኔታ ከወንጀል ወደ ሽብር የተቀየረበት መንገድም ተገቢ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ፖሊስ መተርጎም ያለባቸው ሰነዶች ወደ ትርጉም ቤት ተልከዋል፣ ግብረአበሮቻቸው አድራሻ እየለዋወጡ ሊያዙልኝ አልቻሉም፣ አቀርባለሁ ያልኳቸውን ምስክሮችም እያስፈራሩብኝ ለማቅረብ አልተቻለኝም ሲል መልሷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡

በዚህም መሠረት ጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ ቅዳሜ ሰኔ 7፣ 2006 ከጠዋቱ በ3፡30 ሰዓት እንዲቀርቡ አዟል፡፡ አጥናፍ ብርሃኔ ከሌሊቱ በስምንት ሰዓት ወደ ምርመራ ክፍሎች እየተወሰደ በመርማሪዎች ወከባ፣ ድብደባ እና ማስፈራሪያ እንደደረሰበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ባለፈው ቀጠሮ ሚያዚያ 30 ቀርበው የነበሩት በፍቃዱ ኃይሉ እና አቤል ዋበላ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡ ቀጥሎ በታየው መዝገብ 118722 ተጠርጥረው የቀረቡት አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ዘላለም ክብረት ክሳቸው ወደ ሽብር ተለውጦ በመቅረቡ እነሱም ሰኔ 7 ቀን 2006 እንዲቀርቡ ታዟል፡፡ ለችሎቱ የመናገር እድል እንዲሰጠው ጠይቆ የተፈቀደለት ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ “መርማሪው የዞን 9 አባል አለመሆኔን ቢያምንም በተደጋጋሚ ጊዜ እየተጠራሁ አንድ ዓይነት በሆነ ጥያቄ ስለዞን 9 የምታውቀው ነገር አለና ተናገር እየተባልኩ ከፍተኛ የሥነልቡና ጫና ደርሶብኛል፡፡ ጋዜጠኛ እንደሆንኩም ያውቃሉ፡፡” በማለት ቅሬታውን እንባ እየተናነቀው አሰምቷል፡፡ የአስማማው ሁኔታ የችሎቱን ታዳሚያን እንባ አራጭቷል፡፡

ጠበቆቻቸውም ፖሊስ ከዚህ ቀደም በጠየቃቸው ቀጠሮዎች የሰራው ነገር ስለሌለ የ28 ቀን ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም፤ ዋስትና ይፈቀድልን፤ ዋስትና አያሰጥም እንኳን ከተባለ ፖሊስ ከዚህ በኋላ በጠየቀው ጊዜ ምን ሊሰራ እንዳሰበ ይግለጽልን ሲሉ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መልስ የሰጡት መርማሪም በመረጃ ዴስካችን ውስጥ ያለን ኮምፒዩተር አንድ ብቻ በመሆኑ የሁሉንም ተጠርጣሪዎች ፋይል ለማጣራት ጊዜ ወስዶብናል ብለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሕቡዕ ተደራጅተዋል፤ ከእያንዳንዳቸው ኢ-ሜይል ለአመጽ የሚቀሰቅሱ ማስረጃዎች አግኝተናል እያንዳንዱን ለማስተርጎም ጊዜ ይወስዳል፤ በስማቸው ከውጭ የተላከ ገንዘብ እንዳለና ለሽብር ድርጊት ሊጠቀሙበት እንደሆነ ደርሰንበታል ያለ ቢሆንም ጠበቆቻቸው ግን ፖሊስ የጸረ-ሽብር ሕጉን አለአግባብ እየተጠቀመበት ነው፤ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ እና ተስፋለም ወልደየስ የዞን ዘጠኝ አባላት አይደሉም፡፡ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ደንበኞቻችንን ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ወንጀል አልተገኘባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የዞን 9 አባላት ከውጭ የሽብር አካላት ስልጠና አግኝተዋል የሚለው ልክ አይደለም፡፡ አርቲክል 19 እና ፍሪደም ሃውስ ሀሳብን የመግለጽ መብት እንዲከበር የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው፡፡ የትም ሀገር እና ቦታ የሽብር ተቋማት ተብለው አያውቁም፡፡ በኛም ሀገር በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው አልተወገዙም ሲሉ ጠበቆቻቸው ተናግረዋል፡፡ በመዝገብ ቁጥር 118720 የተካተቱት በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና አቤል ዋበላ እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት ይቀርባሉ፡፡ ጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሚያዚያ 18 እና 19 ቢሆንም ጠበቆቻቸው እንዲጎበኟቸው የተፈቀደው ግን ባሳለፍነው ረቡዕ ግንቦት 6 እና አርብ ግንቦት 8፣ 2006 ነው፡፡

Filed in: Amharic