>

ኢትዮጵያ፡ እ.ኤ.አ ኖቬምብር 24/1974ን እናስታውስ፣ [ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም]

ትርጉም :- በነጻነት ለሀገሬ

ባለፈው ሳምንት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን/ት ቤተሰቦች ከዘመዶቻቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ በመጥፎ ገጽታው ሲታወስ የሚኖረውን እ.ኤ.አ ኖቬምበር 14/1974 በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን የእልቂት ሰለባዎች ለማስታወስ በአንድ ላይ ተሰባስበው የጸሎት ስርዓት አድርገዋል፡፡ በዚያ የጥላቻ ዕለት የወታደራዊው አምባገነን ስብስብ ተራ ስብሰባ በማድረግ 60 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን፣ የመንግስት ሰራተኞችን፣ አርበኞች ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸውን ወታደራዊ መኮንኖችን፣ የተማሩ ወታደራዊ ባለስልጣናትን እና የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴን ልዩ የጥበቃ አባላት ያካተተ የግድያ እልቂት ለመፈጸም ተራ እና አስደንጋጭ ውሳኔን አሳለፈ፡፡ ያ እልቂት እስከ አሁኑ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና አምባገነናዊ ፈላጭ ቆራጭነትን በሚያራምድ ስርዓት ቅርቃር ውስጥ እንድትሰገሰግ አደረጋት፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 24/1974 ኢትዮጵያ ማቆሚያ እና መመለሻ ወደሌለው በፍጥነት እየተስፋፋ ወደመጣ ያለምንም ደም በሚል የሀሰት ቃልኪዳን ተጀቡኖ አብዮት ለማካሄድ ተይዞ የነበረው ዕቅድ ከመቅጽበት እንደ እንቧይ ካብ ተንዶ በአፍሪካ የዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ተምዘግዝጋ ደም በደም በተጨማለቀ በወታደራዊ ኃይል ስርዓት ይዞታ ስር ወደቀች፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 24/1974 በኢትዮጵያ ላይ ያጠላው ጨለማ እስከ አሁንም ድረስ ምንም ዓይነት የብርሀን ጭላንጭል ሳያሳይ ድቅድቅ እንደሆነ ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር ከብቦ ይገኛል፡፡

በደም የተጨማለቀው ደምአልባው የ1974 መፈንቅለ መንግስት

እ.ኤ.አ በ1974 በኢትዮጵያ ስልጣን ወደ ወታደራዊ መንግስት የተሸጋገረበት አካሄድ ከጅምሩ ያለምንም ደም እና በጣም ቀሰስተኛ በሆነ መልኩ እያለሳለሰ እያ እየተንፏቀቀ ስልጣንን በቁጥጥሩ ስር ያደረገ መፈንቅለ መንግስት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮቸ እንደሚደረገው ሳይሆን ከድህረ አፍሪካ ቅኝ ግዛት በኋላ የተደረገው ያ ኃይል የተቀላቀለበት መፈንቅለ መንግስት በወቅቱ በነበረው የበሰበሰ ዘውዳዊ አገዛዝ እና በዚያን ወቅት ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመጣው ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ግራ በመጋባት የሚያደርግ የሚጨብጠወን አጥቶ በመንጠራወዝ ላይ በነበረው የጉልታዊ ስርዓት አመራር ላይ በተፈጠረው ክፍተት በመጠቀም የዝቅተኛ ባለማዕረግ ስልጣን የነበራቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች አድብተው እና አስልተው በመራመድ የኢትዮጵያን ህዝብ የለውጥ ማዕበል በመቀልበስ ለእራሳቸው የስልጣን መጠቀሚያ ለማድረግ ችለዋል፡፡

ያ አዝጋሚ (ፎቃቃ ) መፈንቅለ መንግስት ከተለያዩ የጦር ክፍሎች የተውጣጡ ባለዝቅተኛ ማዕረግ ወታደሮች እና አስር አለቆች ለስልጣን እንዲበቁ አደረገ፡፡ መፈክራቸውም “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” (ምንም ዓይነት ደም ሳይፈስ እና እልቂት ሳይፈጸም ኢትዮጵያ በስልጣኔ ወደፊት ትገስግስ፣ ትራመድ) የሚል ነበር፡፡ ለእራሳቸው “ደርግ” (የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሰራዊት እና የምድር ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ) የሚል ስያሜ በመስጠት እራሳቸውን በማሞካሸት ተደራጁ፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 1974 ደርግ የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴን ዙፋን በመገርሰስ የዘውዳዊውን አገዛዝ በርካታ ታላላቅ ባለስልጣናት እና ሹማምንት በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡ ደርግ በወቅቱ ስልጣን ለመያዝ እንደምክንያት ያቀረባቸው ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ሲሆኑ እነርሱም፣

1ኛ) እ.ኤ.አ በ1973 ተከስቶ በነበረው የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ሰበብ ተማሪዎች በግንባርቀደምትነት ያቀጣጠሉትን ህዝባዊ አመጽ እና አለመረጋጋት ለመቆጣጠር፣

2ኛ) በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ረኃብ ምክንያት ላለቁት እና ለተጎዱት ወገኖች ምንም ዓይነት ጥረት ሳያደርጉ እንዲያውም በድብቅ ህዝብ ሲያልቅ በግዴለሽነት ሲመለከቱ የነበሩትን ንጉሳውያን ባለስልጣኖች ተጠያቂ ለማድረግ፣ እና

3ኛ) በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ወታደሮች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ እና በውትድርናው መስክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ወታደሮች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚሉ ነበሩ፡፡

black_saturday_pix1416810697ደርግ ህዝባዊ አመጹን ባቀጣጠሉት ወገኖች እና በጠቅላላ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን እና “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” እንዲሉ ኢትዮጵያ ትቅደም (በስልጣኔ ትራመድ) የሚል መፈክር በማውጣት የህዝብ ግንኙነት ዘመቻ ጩኸቱን ተያያዘው፡፡ በቀጣይነትም ደርግ ካወጣው መፈክር ውስጥ የእራሱን ሀሳብ በማሰባሰብ የፖለቲካ መድረኮችን በማዘጋጀት በህዝቦች መካከል በተለይም በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ እኩልነት እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የፍትህ ስርዓቱ እንዲሻሻል፣ የመሬት ስሪት እንዲሻሻል እና ብሄራዊ የጤና እና የመሰረተ ትምህርት ዘመቻዎች እንዲካሄዱ የሚያግዙ ፖለቲካዊ ፕሮግራሞችን ለሕዝብ ለፈፈ፡፡ ደርግ በጦረኝነት እና በወታደራዊ የጩኸት አንደበቱ በመጠቀም የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ለማነሳሳት መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳውን ማሰራጨት ጀመረ፡፡ ከተለያዩ የጦር ክፍሎች የተውጣጡ 120 አባላትን አካትቶ የተመሰረተው ደርግ እ.ኤ.አ በ1975 መመሪያው ህብረተሰባዊነት/Socialism እና የመጨረሻ ግቡ ደግሞ ኮሙኒዝም እንደሆነ በማወጅ ለእራሱም “የኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግስት” የሚል ስያሜ ሰጠ፡፡ ደርግ ይፋ የሆነ የስያሜ ለውጥ ቢሰጥም አብዛኛው ህዝብ የወታደራዊውን አምባገነን ስብስብ “ደርግ” በማለት መጥራቱን ቀጠለበት፡፡

ደርግ ቀስ በቀስ እየዳኸ በመምጣት ላይ ያለውን መፈንቅለ መንግስት ተግባራዊ በሚያደርግበት ጊዜ የዘዊዳዊውን መንግስት ከፍተኛ የጦር እና የሲቪል ባለስልጣኖች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ጀመረ፡፡ እነዚህን የንጉሳዊ ስርዓት ታላላቅ ባለስልጣኖች በቁጥጥር ስር ማዋል በንጉሳዊው አገዛዝ እና ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት እና ችሎታ በሌለው አገዛዝ ላይ ጥላቻ በነበራቸው ወገኖች ላይ ተጨማሪ ነዳጅ በማረከፍከፍ ለወታደራዊው የጸረ ዘውድ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሌላ ጠቀሜታን አጎናጸፈው፡፡ ደርግ በንጉሳዊው አገዛዝ ሲያገልግሉ የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጣጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር በማዋል ማሰር ጀመረ፡፡ እነዚህ ባለስልጣናት በተወነጀሉባቸው መጥፎ ባህርያት፣ በሰሯቸው ስህተቶች እና ከህግ አግባብ ውጭ በዜጎች ላይ ችግር የፈጠሩ መሆን አለመሆናቸው እየተጣራ እርምጃ እንደሚወሰድ ደርግ ቃል ገባ፡፡ ይህ ቃል የተገባለት የማጣራት ስራ እ.ኤ.አ እስከ ኖቬምበር 23/1974 ምሽት ባክኖ ቀረ፡፡

እነዚህን 60 ከፍተኛ የሆኑ የዘውድ አገዛዝ ስርዓት ባለስልጣኖችን በሞት የመቅጣት ጭራቃዊ ሀሳብ የተጸነሰው እና ተግባራዊ እንዲደረግም ታላቅ ሚና የተጫወቱት ጭፍን የሆነ የስልጣን ፍላጎት በነበራቸው እና እስከ መጨረሻው የደርግ አገዛዝ ፍጻሜ ደረስ ቁንጮ ሆነው በዘለቁት መንግስቱ ኃይለማርያም በሚባሉ ወታደራዊ መኮንን ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው የመንግስቱ ዓይን ያማትር የነበረው የመጨረሻው ሽልማት በሆነው የደርግ ሊቀመንበርነት ወንበር ላይ ፊጥ ለማለት ነበር፣ ሆኖም ግን ይህንን ሀሳባቸውን ዕውን ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ኃይላቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ መንግስቱ የመሰሪነት ጉብዝናን በተቀላቀለበት ሁኔታ በደርግ የመጨረሻ የሊቀመንበርነት ወንበር ላይ ለመቀመጥ እንዲችሉ የ60 ከፍተኛ የዘውድ አገዛዝ ስርዓት ባለስልጣኖችን ግድያ አቀነባበሩ፡፡ መንግስቱ በመጀመሪያ ደረጃ የደርግ የይስሙላ ሊቀመንበር የነበሩትን ጄኔራል አማን ሚካኤልን ወነጀሉ፡፡ ጄኔራል አማን በወታደራዊው መስክ ከፍተኛ የሆነ ማዕረግ ያላቸው ወታደራዊ መሪ ብቻ አልነበሩም፣ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ጦር ኃይል ውስጥ በስፋት የሚከበሩ እና የሚወደዱ ነበሩ፡፡ በውጊያ ብቃታቸው አንቱ የተባሉ ወታደራዊ መኮንን ስለነበሩ “ኮዳ ትራሱ” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸው በጦሩ ውስጥ በዚያ ስያሜ ይታወቁ ነበር፡፡ ጄኔራል አማን በኮሪያ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያ ላዘመተችው ሰራዊት አዛዥ ሆነው አመራር ሰጥተዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ የድንበር ግጭት ጦርነት ጊዜ ታዋቂነትን የሚያጎናጽፍ ወታደራዊ ጀብዱ የሰሩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

መንግስቱ በደርግ የሚመራውን አብዮት ለመቀልበስ ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም በስውር ተንቀሳቅሰዋል በሚል የሸፍጥ ስራ የሀሰት ውንጀላ በመፈብረክ ጄኔራል አማን ከስልጣናቸው እንዲወገዱ ለማድረግ መጠነ ሰፊ የሽረባ ስራን ማካሄድ ጀመሩ፡፡ መንግስቱ ጄኔራል አማንን ከኤርትራ አማጽያን ቡድን ጋር አብረዋል ምክንያቱም ጄኔራሉ ከአማጺ ቡድኑ ጋር ያላቸውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በግላቸው ተንቀሳቅሰዋል በማለት ከሰሷቸው፣ ምክንያቱም ጄኔራል አማን በትውልድ ሀረጋቸው ከኤርትራ ስለሆኑ በማለት በዘር ሰበብ ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ስለሆነም መንግስቱ ከኤርትራዊ ዝርያ ጋር በተያያዘ መልኩ በወቅቱ የነበረውን ጥላቻ እንደመጠቀሚያ መሳሪያ በማድረግ የተንኮል ሽረባ ስራቸውን በደርግ ውስጥ አስርገው በማስገባት መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡ መንግስቱ ጄኔራል አማንን የሸፍጥ ስራ የሚሰሩ እና የአማጺያን አፈቀላጢ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ የኤርትራ አማጺ ኃይሎች በወታደራዊ ኃይል መደምሰስ አለባቸው በማለት ደርግን ለማሳመን ጥረት አደረጉ፡፡ ጄኔራል አማን በደርግ ውስጥ ከመንግስቱ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር መግባባት የማያስችሉ ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ጄኔራል አማን እንደ የደርግ ሊቀመንበርነታቸው ያላቸውን ስልጣን በመጠቀም በእስር ቤት የሚገኙ ጥቂት የዘውድ አገዛዝ ባልስልጣኖች በሞት እንዲቀጡ በሚል መንግስቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርገውባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጄኔራል አማን ኢትዮጵያ በወጣት እና ምንም ዓይነት ልምድ በሌላቸው ዝቅተኛ ወታደሮች እና ደጋፊ ሰዎች መመራት የለባትም የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ከመንግስቱ ጋር በነበራቸው ጥልቅ የሆነ አለመግባባት ምክንያት ጄኔራል አማን ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመተው ከደርግ ሊቀመንበርነት እራሳቸውን አገለሉ፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 23/1974 መንግስቱ ጄኔራል አማንን በቁጥጥር ስር አውለው ወደ ደርግ ጽ/ቤት እንዲያቀርቡ ለወታደሮች ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘ መልኩ እንወስዳለን አትወስዱኝም በሚል ግብግብ በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ጄኔራል አማን ተገደሉ፡፡ በወሬ ደረጃ እንደሚነገረው ጄኔራል አማን በሌሎች ወታደሮች ተማርከው የተገደሉ ሳይሆን እራሳቸውን እራሳቸው ናቸው ያጠፉ ይባላል፡፡ ጄኔራል አማን ኤርትራ እንድትገነጠል ከኤርትራ አማጺያን ጋር በድብቅ ስምምነት ያድርጉ አያድርጉ በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም፣ ሆኖም ግን የኤርትራ ጉዳይ በሰላም ሊፈታ ይችላል የሚለዉን ጥያቄ አንደማይመለስ ሆኖ ቀርቷል። ኤርትራ እ.ኤ.አ በ1994 ከኢትዮጵያ መገንጠሏ የሚታወስ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ኖቬምበር 23/19974 የደርግ አባላት የጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም መገደልን በህዝብ ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የ250 የዘውድ አገዛዝ ባለስልጣን እስረኞችን ስም ዝርዝር በመያዝ ይገደሉ/አይገደሉ የሚል ዉሳኔ ላይ ደረሱ። የደርግ አባላቱ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 24/1974 እጅግ በጣም አስደንጋጭ እና አሳፋሪ የሆነውን የፈሪዎች ምግባር የተንጸባረቀበትን የእልቂት መርዶ ለህዝብ ይፋ አደረጉ፡፡

ደርግ በግፍ የፈጃቸውን ባለስልጣኖች መገደል ትክክለኛ ለማስመሰል እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቶ ነበር፣

ምክር ቤቱ (ደርግ) የተለያዩ ሽረባዎችን በማድረግ አገሪቱ በደም አበላ እድትታጠብ ተደጋጋሚ መሰሪ ተግባር የፈጸሙትን የቀድሞዎቹን የሲቪል እና ወታደራዊ ባለስልጣኖች በሞት መቅጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ይህ ውሳኔ ባለፉት ጊዚያት በከፍተኛ ደረጃ ሲሰቃዩ የቆዩትን ምንም ዓይነት ወንጀል የሌለባቸውን ንጹሀን ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ሲባል የተደረገ ነው፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ (ደርግ) በመጥፎ አመራራቸው ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት፣ ፍትህ እንዲስተጓጎል ደንቃራ ሲሆኑ በቆዩት፣ የሀገሪቱን ሰነድ ሚስጥር ለውጭ ወኪሎች በሸጡ እና በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያን ታላቁን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በተሰለፉት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ሰጥቷል፡፡

ከህግ አግባብ ውጭ በግፍ የተገደሉት 60 የቀድሞው የዘውዳዊ አገዛዝ ባለስልጣኖች በኋላ አጽማቸው ተቆፍሮ በክብር እንዲያርፍ ሲደረግ በታየው ቅሬተ አጽም መረጃ መሰረት እጆቻቸውን እያጣመሩ በማሰር ገድለው በጅምላ በአንድ የመቃብር ጉድጓድ ውስጥ የቀበሯቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡ (ቅሬተ አጽማቸውን እና የ60ዎቹን የጥቃት ሰለባዎች ዳግም የክብር ቀብር በዩቱቤ ቪዲዮ ለማዬት እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)

በመንግስቱ እና በደርግ ህገ ወጥ ግድያዎች፣

ጆርጅ ኦርዌል እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “የፖለቲካ ቋንቋ…የለየላቸውን ነጭ ውሸቶች የነጠሩ እውነቶች ለማስመሰል እና ገዳዮችን ክብር ያላቸው ሰዎች ለማስመሰል እንዲሁም ንጹሁን ነፋስ የጠጣርነት ቅርጽ እንዲይዝ ለማስመሰል የሚደረግ ሽረባ ነው፡፡“ አሳዛኝ እና ጭካኔ የተሞላበትን የባለስልጣኖች ግድያ ትክክለኛነት ለማሳመን፣ ለተሰራው ጭራቃዊ የወንጀል ድርጊት የህግ ሽፋን ለመስጠት እና በሁኔታው ለተደናገጠው ህዝብ የፖለቲካ ተውኔት በመስራት ደርግ በእስር ላይ የነበሩት ባለስልጣኖች እንዲገደሉ የተደረጉት በሚከተሉት 4 ምክንያቶች እንደሆነ አድርጎ አቅርቧል፣

1ኛ) ኃይላቸዉን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም፣ 2ኛ) ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም፣3ኛ) የእርስ በእርስ ጦርነት ለማነሳሳት ደባ መፈጸም እና ታላቁን የኢትዮጵያን የአመጽ እንቅስቃሴ ለማዳፈን መሞከር፣ እና 4ኛ) የገቡትን ቃል ኪዳን ማጠፍ እና በወታደሩ መካከል ልዩነትን መፍጠር የሚሉ ነበሩ፡፡

በ60ዎቹ የቀድሞው የዘውድ አገዛዝ ባለስልጣኖች ላይ የሞት ቅጣቱ ሲወሰን በስራ ላይ የዋለው የወንጀለኛ መቅጫ ህጎች የሚገኙት በ1957 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ድነጋጌ ላይ ነበር፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ የወንጀል ድርጊቶች እንዲታቀቡ እና በሲቪል ሰዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ ሳይሆኑ በክፍል 3 ስር በወታደራዊ ኃይሎች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ጭምር የሚካተቱ እንደሆነ ያመላክታል፡፡

በ60ዎቹ የዘውድ አገዛዝ ባለስልጣኖች የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ያለው ነባራዊ እውነታ እና ጥሬ ሀቅ በማያተራጥር መንገድ የእልቂቱ ሰለባ የሆኑት ባለስልጣኖች ከህግ አግባብ ለመታዬት ዕድሉን ቢያገኙ ኖሮ አንድም ምንም ዓይነት ወንጀል አንዳልሰሩ ሰርተው ቢሆን እንኳ ኖሮ የሚያቀርቧቸው መከላከያዎች በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ወይም ደግሞ በቀላል የገንዘብ ቅጣት የሚቋጩ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ 17ቱ ከፍተኛ የዘውዱ አገዛዝ ከፍተኛ ባለስልጣኖች “ከህግ አግባብ ውጭ ኃይል በመጠቀም” በሚል ውንጀላ እንዲገደሉ ተደረገ፡፡ እውነታው ግን በእ.ኤ.አ 1957 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በየትኛውም አንቀጽ ውስጥ የተጠቀሰ ከ”ህግ አግባብ ውጭ ኃይል በመጠቀም” የሚል የለም፡፡ አራት ነጥብ! እነዚያ ባለስልጣኖች እንዲገደሉ የተደረጉት በህጉ ላይ በሌለ እና ባልተጻፈ ወንጀል ነው!

በሁለተኛ ደረጃ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም የሚለው ውንጀላ በወታደራዊ መኮንኖች የቀረበው በ1957 ወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ውስጥ የለም፡፡ ይህ ነጥብ ግፋ ቢል ሊነሳ የሚችለው ምናልባት በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ በአንቀጽ 304 (ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም) ነው፡፡ ያ አንቀጽ እንዲህ ይላል፣ “ከፍተኛ ማዕረግ ያለው ወታደራዊ ባለስልጣን ስልጣኑን መከታ በማድረግ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣኑን ተጠቅሞ ከሆነ ወይም ደግሞ ከዚህ ህግ ጋር በማይጣጣም መልኩ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣኑን ለመጠቀም ከሞከረ በዚህ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲከላክል ተደርጎ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በወታደራዊ ስርዓት ህግ መሰረት ብይን ይሰጥበታል፡፡“ በክርክር መልክ ጉዳዩን እንዬው ብለን እናስብ እና ወታደራዊ ባለስልጣኖች ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል ብለን ብናስብ እንኳ እነዚያ በሞት የተቀጡት ባለስልጣኖች በአዋጅ ለተቋቋመ ወታደራዊ ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረባቸው እንጅ እንዲሁ በጅምላ ከህግ አግባብ ውጭ መገደል አልነበረባቸውም፡፡ ሆኖም ግን እንኳንስ ሁሉንም ወታደራዊ ባለስልጣኖች በጅምላ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣናቸውን ለመጠቀማቸው ይቅር እና ማንም ወታደራዊ ባለስልጣን በተናጠል ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣኑን ለመጠቀሙ የሚያመላክት ምንም ዓይነት ማስረጃ አልነበረም፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቀስቀስ በሚል ሸፍጥ የቀረበባቸው ውንጀላም እንደዚሁ በእራሱ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ውስጥ የለም፡፡ ውንጀላው አለ አንክዋን ቢባል ባንቅፀ 252 (የመሳርያ አመፅና አርስ በርስ ጦርነት) ላይ ሊመሰረት ይችል ይሆናል። ነገር ግን ያ አንቀጽ የሚለው “በንጉሱ፣ በመንግስት ወይም በህገ መንግስቱ ባለስልጣኖች ላይ የሚደረግን አመጽ፣ የሽምቅ ውጊያ ወይም ደግሞ የተደራጀ አመጽ ያካትታል…” ከህግ አንጻር የእርስ በእርስ ጦርነት በመቀስቀስ በሚል ሸፍጥ የተገደሉት ባለስልጣኖች ለዚህ ወንጀል ጥፋተኞች ተብለው መገደል አልነበረባቸውም ምክንያቱም ደርግ እራሱ በየትኛውም የአንቀጽ 252 ትርጉም መሰረት ህጋዊ ስልጣን አልነበረውም፡፡ አንድያዉም ደርግ አራሱ የዘውድ አገዛዙ ባለስልጣኖች በተገደሉበት ጊዜ ደርግ እራሱ እና አመራሮቹ ከህግ አግባብ ውጭ የንጉሱን ዙፋን ለመገልበጥና አርስ በርስ ጦረነት ለማንሳት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በ1957 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ በሌለ ወይም ደግሞ በየትኛውም ወታደራዊ ህግ እና ደንበ ውስጥ በሌለ ህግ ሶስት የባህር ኃይል ባለስልጣናት አንዱ የኮርፖራል ሌላኛው ደግሞ የግል የሆኑ ከህግ አግባብ ውጭ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡

አራተኛ በ1957 በወጣው የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ “ቃልኪዳንን ባለመጠበቅ እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ክፍፍልን ለመፍጠር“ የሚል የተጠቀሰ ወንጀል የለም! ይልቁንም ይህ ውንጀላ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 332 (ግዴታን ባለመወጣት) እና/ወይም በአንቀጽ 344 (በጦር ኃይሉ ውስጥ የሚደረግ ወንጀልን ባለማሳወቅ እና ወታደራዊ ግዴታዎችን ባለመፈጸም) በሚል ርዕስ ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ለክርክር ያህል “ቃል ኪዳንን ባለማክበር እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ከፍፍልን የመፍጠር ሙከራ በማድረግ” በሚል በተጠቀሱት አንቀጾች መሰረት ተከሰው ቀረቡ ቢባል እንኳ ቅጣታቸው ቀላል እስራት ወይም ገንዘብ መቀጭያ ነበር፡፡

አሁንም ለክርክር ያህል እነዚያ በተገደሉት ባለስልጣኖች ላይ ህዝቡን ለማሳመን ተብሎ በደርግ የቀረቡት ውንጀላዎች በደርግ በእራሱ በቀረቡ ህጋዊ ደንቦች እና ፖሊሲዎች በጠቅላላ ትክክለኞች ናቸው ቢባለም የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 5 (2) የወንጀል ህጉ ወደ ኋላ ተመልሶ ተግባራዊ እንደማይደረግ እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፡ “ይህ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከመውጣቱ በፊት የተፈጸመ ማንኛውም ወንጀል ባዲስ ሕግ ወደኋላ በመመለስ እንዲታይ ተደርጎ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም…“

እንግዲህ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ነበር 60ዎቹ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ያለምንም ማስረጃ እና ጥፋተኝነት በመንግስቱ ኃይለማርያም እና በደርግ ግድያ የተፈጸመባቸው፡፡ እናም ያ አስፈሪ እና አሳፋሪ ድርጊት በኢትየጵያ የህግ የበላይነት ሞቶ መቀበሩን በጉልህ ያስመለከተው!

** ኃይላቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል በሚል ውንጀላ የተገደሉ ባለስልጣኖች፣

1ኛ) አክሊሉ ሀብተወልድ (ጸሐፊ ትዕዛዝ፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት ውስጥ ለ13 ዓመታት በጥቅላይ ሚኒስትርነት እና በሌሎች ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በአጠቃላይ ለ39 ዓመታት ያገለገሉ)፣

2ኛ) ልዑል አስራተ ካሳ (የዘውድ ምክር ቤት አባል፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፣ እንደራሴ እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከ34 ዓመታት በላይ ያገለገሉ)፣

3ኛ) እንዳልካቸው መኮንን (ጠቅላይ ሚኒስትር፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት ልጅ፣ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ አምባሳደር እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ23 ዓመታት ያገለገሉ)፣

4ኛ) ራስ መስፍን ስለሺ (የጦር አበጋዝ፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት እንደራሴ፣ እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ54 ዓመታት ያገለገሉ)፣

5ኛ) አቶ አበበ ረታ (ሚኒስትር፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት የቋንቋ ምሁር፣ በታሪክ እና በኃይማኖት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥልቅ እውቀት የነበራቸው ምሁር፣ እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ47 ዓመታት ያገለገሉ)፣

6ኛ) ሌተናል ኮሎኔል ታምራት ይገዙ (እንደራሴ፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት የዘውድ ምክር ቤት አባል እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ38 ዓመታት ያገለገሉ)፣

7ኛ) አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ (ሚኒስትር፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት አምባሳደር እና በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ39 ዓመታት ያገለገሉ)፣

8ኛ) ዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚ (ሚኒስትር) ሆነው ያገለገሉ፣

9ኛ) አቶ ሙላቱ ደበበ (ሚኒስትር፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ22 ዓመታት ያገለገሉ)፣

10ኛ) ደጃዝማች ሰለሞን አብርሀ (እንደራሴ፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ)፣

11ኛ) ደጃዝማች ለገሰ በዙ (እንደራሴ፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ29 ዓመታት ያገለገሉ)፣

12ኛ) ደጃዝማች ሳህሉ ድፋዬ (እንደራሴ፡ የጦር አበጋዝ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ46 ዓመታት ያገለገሉ)፣

13ኛ) ደጃዝማች ወርቅነህ ወልደአማኑኤል (ሚኒስትር፡ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል፣ እንደራሴ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ30 ዓመታት ያገለገሉ)፣

14ኛ) ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ (አምባሳደር፣ ዲፕሎማት፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል)፣

15ኛ) ደጃዝማች ወርቁ እንቁስላሴ (እንደራሴ፣ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ26 ዓመታት ያገለገሉ)፣

16ኛ) ደጃዝማች አዕምሮስላሴ አበበ (እንደራሴ፡ የመንግስት ሰራተኛ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ35 ዓመታት ያገለገሉ)፣

17ኛ) ደጃዝማች ከበደ ዓሊ ወሌ (እንደራሴ፡ የወታደራዊ ኃይል አዛዥ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ34 ዓመታት ያገለገሉ)፣

ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል በሚል ውንጀላ የተገደሉ ባለስልጣኖች፣

1ኛ) አቶ ነብይ ልዑል ክፍሌ (ሚኒስትር፡ የዘውድ ካቢኔ ልዩ አባል እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ24 ዓመታት ያገለገሉ)፣

2ኛ) ኮሎኔል ሰለሞን ከድር (የደህንነት ዋና ኃላፊ፡ ሚኒስትር እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ25 ዓመታት ያገለገሉ)፣

3ኛ) አፈንጉስ አበጀ ደባልቅ (ዳኛ፣ የዘውድ ምክር ቤት አባል፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ 44 ዓመታት ያገለገሉ)፣

4ኛ) አቶ ይልማ አቦዬ (የቤተመንግስት ሹም፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ18 ዓመታት ያገለገሉ)፣

5ኛ) አቶ ተገኝ የተሻወርቅ (ሚኒስትር፡ የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ዋና አርታኢ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ12 ዓመታት ያገለገሉ)፣

6ኛ) አቶ ሰለሞን ገብረማርያም (ሚኒስትር፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ31 ዓመታት ያገለገሉ)፣

7ኛ) አቶ ኃይሉ ተክሉ (የመንግስት ሰራተኛ)፣

8ኛ) ብላታ አድማሱ እረታ (የቤተመንግስት ሹም)፣

9ኛ) ልጅ ኃይሉ ደስታ (የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ፕሬዚዳንት እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ26 ዓመታት ያገለገሉ)፣

10ኛ) ፊታውራሪ አመዴ አበራ (የእንስሳት እርባታ ባለቤት፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ)፣

11ኛ) ፊታውራሪ ደምስ አላምረው (እንደራሴ)፣

12ኛ) ፊታውራሪ ታደሰ እንቁስላለሴ (እንደራሴ)፣

13ኛ) ሌተናል ጄኔራል አብይ አበበ (ሚኒስትር፡ አምባሳደር፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት)፣

14ኛ) ሌተናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ (ሚኒስትር፡ እንደራሴ)፣

15ኛ) ሌተናል ጄኔራል ድረሴ ዱባለ (የምድር ጦር ዋና አዛዥ)፣

16ኛ) ሌተናል ጄኔራል አበበ ገመዳ (የንጉሰ ነገስቱ ልዩ ጥበቃ ኃይል ዋና አዛዥ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ40 ዓመታት ያገለገሉ)፣

17ኛ) ሌተናል ጄኔራል ይልማ ሽበሽ (የፖሊስ ኃይል ዋና አዛዥ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ34 ዓመታት ያገለገሉ)፣

18ኛ) ሌተናል ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ (ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ መኮንን/Chief of staff እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ32 ዓመታት ያገለገሉ)፣

19ኛ) ሌተናል ጄኔራል አሰፋ አየን (ሚኒስትር፡ ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ መኮንን እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ38 ዓመታት ያገለገሉ)፣

20ኛ) ሌተናል ጄኔራል በለጠ አበበ (ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ40 ዓመታት ያገለገሉ)፣

21ኛ) ሌተናል ጄኔራል ኢሳያስ ገብረስላሴ (የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው ያገለገሉ)፣

22ኛ) ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ደምሴ (የንጉሰ ነገስቱ ዋና አማካሪ ሆነው ያገለገሉ)፣

23ኛ) ሌተናል ጄኔራል አበበ ኃይለማርያም (የጦር አዛዥ፡ የቤተመንግስት ሹም፣ የምድር ጦር ዋና አዛዥ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ33 ዓመታት ያገለገሉ)፣

24ኛ) ሜጀር ጄኔራል ስዩም ገድለጊዮርጊስ (በውትድርናው መስክ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ ወታደራዊ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ31 ዓመታት ያገለገሉ)፣

25ኛ) ሜጀር ጄኔራል ጋሻው ከበደ (በፖሊስ ሰራዊት ኃይል እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት የፖሊስ ኃይል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ33 ዓመታት ያገለገሉ)፣

26ኛ) ሜጀር ጄኔራል ታፈሰ ለማ (ወታደራዊ አታሼ፡ የቤተመንግስት ሹም እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ ወታደራዊ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ28 ዓመታት ያገለገሉ)፣

27ኛ) ምክትል አድሚራል እስክንድር ደስታ (የባህር ኃይል ዋና አዛዥ፡ የኢትዮጵያ የተሻሻለው ባህር ኃይል ኦፊሰር፣ ዲፕሎማት)፣

28ኛ) ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ ወልደዮሀንስ (የፖሊስ ሰራዊት ዋና አዛዥ እና በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ31 ዓመታት ያገለገሉ)፣

29ኛ) ብርጋዴር ጄኔራል ግርማ ዮሀንስ (በፖሊስ ሰራዊት ኃይል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ28 ዓመታት ያገለገሉ)፣

30ኛ) ኮሎኔል ያለምዘውድ ተሰማ (የአየር ወለድ ዋና አዛዥ ሆነው ያገለገሉ)፣

31ኛ) ኮሎኔል ጣሰው ሞጆ፣

32ኛ) ኮሎኔል ይገዙ ይመር፣

33ኛ) ሜጀር ብርሀኑ ሜጫ፣

34ኛ) ካፒቴን ሞላ ዋቀና፣

የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቀስቀስ በተሸረበ ደባ እና ታላቁን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት በተደረገ አሻጥር ተወንጅው የተገደሉ፣

1ኛ) ካፒቴን ደምሴ ሽፈራው፣

2ኛ) ካፒቴን በላይ ጸጋዬ (የአየር ኃይል ሄሊኮፕተር አብራሪ ፓይለት፡ በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት አየር ኃይል በእብራሪነት ሙያ ለ31 ዓመታት ያገለገሉ)፣

3ኛ) ካፒቴን ወልደዮሀንስ ዘርጋው፣

4ኛ) ላንስ ኮርፖራል ተክሉ ኃይሉ (የ18 ዓመት እድሜ እና የአርሚ መሀንዲሶች አባል የነበሩ እና የወታደራዊ መንግስትነትን ሀሳብ በመቃወማቸው የተገደሉ)፣

5ኛ) የግል ወታደር በቀለ ወልደጊዮርጊስ (በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ22 ዓመታት ያገለገሉ)፣

ለመስሪያ ቤት የተገባን ቃል ኪዳን ባለመጠበቅ እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ሙከራ ማድረግ በሚል ተወንጅለው የተገደሉ፣

1ኛ) ሌተናል ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም (የደርግ ሊቀመንበር እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፡ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ዋና አማካሪ እና አዛዥ ሆነው ያገለገሉ)፣

2ኛ) ሌቴናል ጄኔራል ተስፋዬ ታከለ (የ24 ዓመት እድሜ የአርሚ አቬሽን ፓይለት እና የደርግ አባል የነበሩ)፣

3ኛ) ዮሀንስ ፊቲዊ (መለስተኛ የአውሮፕላን ጠጋኝ እና የደርግ አባል የነበሩ)፣

መንግስቱ ኃይለማርያም፡ ሰዎች ለተገደሉበት ጥይት ዋጋ የሚጠይቁ መሪ፣

እ.ኤ.አ ከ1974 – 1991 ድረስ ለተፈጸመው ግድያ፣ እልቂት እና በመሊዮኖች ለሚሆኑ ወገኖች ህይወት መጥፋት ዋና ብቸኛ ተጠያቂ ከመንግስቱ ኃይለማርያም ውጭ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስቱ በታሪክ ከተመዘገቡት ገዳይ አምባገነኖች መካከል በ13ኛ ተራ ቁጥር ላይ ይገኛሉ፡፡ (ለግምት ያህል አዶልፍ ሂትለር 1ኛ፣ ጆሴፍ ስታሊን 3ኛ፣ ፖልፖት 8ኛ፣ የሱዳኑ ኦማር አልባሽር 9ኛ፣ ኢዲአሚን 22ኛ፣ ኪም ጆንግ- ኢል 23ኛ፣ )

መንግስቱ ኃይለማርያም እና ደርግ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የሚፈጽሙ ስለነበር በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነ ውግዘት ደርሶባቸዋል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሰረት እ.ኤ.አ ከ1977 – 1978 ድረስ መንግስቱ በቀይ ሽብር ዘመቻ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ገድለዋል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሰረት ደግሞ የመንግስቱ ቀይ ሽብር አንዱ በመንግስት ስልታዊ በሆነ መንገድ በዜጎች ላይ እስከ አሁን ድረስ ተደርጎ የማያውቅ በአፍሪካ የተፈጸመ የግድያ እና እልቂት ማስረጃ ነው ብሎታል፡፡ እ.ኤ.አ በሜይ 1977 የስዊድን ህጻናት አድን ድርጅት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ባወጡት ዘገባ እንዲህ ብለው ነበር፣ “1000 ህጻናት ተገድለው በየመንገዱ ተጥለዋል፣ እናም እሬሳቸው በጅቦች እየተበላ ነው… ከአዲስ አበባ ወጣ ብለህ በምትነዳበት ጊዜ አብዛኞቹ ከ 11 እስከ 13 ዓመት እድሜ የሚሆናቸው ህጻናት ሬሳዎች በየፉካው ተቆልለው ትመለከታለህ“ ብለዋል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ ብሏል፣ “የቀበሌዎች አመራሮች ልጆቻቸው የተገደሉባቸው ወላጆች የልጆቻቸውን እሬሳዎች ለመረከብ እና ለመቅበር ጥያቄ ሲያቀርቡ ልጆቻቸው ለተገደሉባቸው ጥይቶች ዋጋ እንዲከፍሉ እና እንዲወስዱ ይጠይቁ ነበር፡፡“ ያ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም የነበረው በመንግስቱ ኃይለማርያም ትዕዛዝ እና ሙሉ እውቅና ነበር፡፡

በመንግስቱ የሽብር አገዛዝ ጊዜ በፖለቲካ አመጽ ጉዳይ እና ለተከሰተው ረኃብ ትኩረት ሰጥቶ የዜጎችን ህይወት ለማትረፍ ጥረት ባለመደረጉ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ አልቋል፡፡ የዓይን እማኞች እንዳረጋገጡት በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ግድያ ላይ የመንግስቱ እጅ በቀጥታ እንደነበረበት ግልጽ አድርጓል፡፡ (ከ18-20 ደቂቃዋች የሚወስደውን የቪዲዮ ምስል ይመልከቱ)፡፡ መንግስቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴን ገድለው ከቢሯቸው ስር ቀበሯቸው፡፡

መንግስቱ በእያንዳንዱ ንግግራቸው መቋጫ ላይ “ሞት ለጸረ አብዮተኞች! ሞት ለኢህአፓ! ሞት ለአድህሮት ኃይሎች… ሞት ለኢምፔሪያሊዝም…ሞት ለፊውዳሎች…”ይሉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን መንግስቱ ዓይንን በጨው በታጠበ መልኩ የውጭ ቃለ መጠይቅ አድራጊ ጋዜጠኛ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ “እንኳን ሰው ትንኝ እንኳ አልገደልኩም” የሚል መልስ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ አዎ በእርግጥ ትንኝ ባይገሉም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦችን እንደ ትንኝ መግደላቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

መንግስቱ ኃይለማርያም ጠላቴ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን አሳድደው የሚገድሉ ደም የጠማቸው ገዳይ ብቻ አልነበሩም ሆኖም ግን የእርሳቸውን የቅርብ ጓደኞች፣ ተባባሪዎች እና የስራ ባልደረቦች ጭምር ዶግ አመድ የሚያደርጉ እና የሚያስደርጉ እንጅ፡፡ አሁን በቅርቡ መንግስቱ እና የእርሳቸው የድሮ አገልጋያቸው እራሳቸውን ከታሪክ ተጠያቂነት ለመደበቅ በማሰብ መጽሐፎችን ጽፈው አቅርበዋል፡፡ ሁሉንም ነገር ያደረጉት በሀገር ወዳድ አርበኝነት እና ብሄራዊ ስሜት በመገፋፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እኔ ይህ የዥዋዥዌ ጨዋታ አይገባኝም፡፡ በምን ዓይነት መለኪያ እና መስፈርት ነው ህጻናትን በአደባባይ በጅምላ በየመንገዶች በእሩምታ ተኩስ እየገደለ በየፉካው የሚጥል ጨካኝ እና ልጆቻቸው ለተገደሉባቸው ወላጆች ልጆቻቸው የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ከፍላችሁ እሬሳ ውሰዱ የሚል አረመኔ ጭራቅ አገር ወዳድ አርበኛ እና የብሄረተኛ ድርጊት ሊሆን የሚችለው? በየትኛው መለኪያ ነው ህዝቦችን ያለሀበሳቸው ማሰቃየት እና የፖለቲካ ጠላቴ ናቸው በሚል እኩይ መንፈስ ተገፋፍቶ መብቶቻቸውን የሚደፈጥጥ ጨካኝ አገር ወዳድ አርበኛ እና የብሄረተኛ ድርጊት ሊሆን የሚችለው? በምን ዓይነት መስፈርት ነው በእድሜ የጃጁትን ንጉስ አፍኖ በግፍ መግደል እና ከእራስ ቢሮ ስር መቅበር አገር ወዳድ አርበኛ እና የብሄረተኛ ድርጊት ሊሆን የሚችለው? በምን ዓይነት መለኪያ ነው የእራሳቸውን ልጆች በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ በጥይት ገድሎ ልጆቻችሁ የተገደሉበትን የጥይት ዋጋ ከፍላችሁ እሬሳችሁን ውሰዱ ማለት አገር ወዳድ አርበኛ እና ብሄረተኛ ሊሆን የሚችለው?! ሀገር ወዳድ አርበኝነት እንዴት የመርህ ደፍጣጮች፣ ደም የተጠሙ ገዳዮች እና ጉሮሮ አናቂዎች መደበቂያ ዋሻ ሊሆን ይችላል? መንግስቱ እና ደርግ አገር ወዳድ አርበኛ እና የብሄረተኛ ስሜት ስላላቸው አይደለም ያንን ሁሉ እምቡቃቅላ ህጻናት እና የኢትዮጵያን የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑትን ምሁራን በስሜታዊነት እና በእብሪተኝነት ተነሳስተው በግፍ የጨረሱት ሆኖም ግን ያንን የመሰለ ጭራቃዊ እኩይ ምግባር የፈጸሙት ከጭፍን አመለካከት እና ለስልጣን ካላቸው ጉጉት እና ምኞት አንጻር ነው፡፡

መንግስቱ እና መሰል የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ ወንጀለኞች በመለስ ዜናዊ መንግስት ቅጣት ተበይኖባቸው ነበር፡፡ ሶስት ደርዘን የሚሆኑ የደርግ አባላት ጉዳያቸው በህግ ቀርቦ በመታየት ላይ ነበር፡፡ መንግስቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በመግደል ወንጀል በሌሉበት የፍርድ ሂደታቸው ታይቷል፡፡ በመንግስቱ ላይ ለቀረበው ወንጀላ ማስረጃ ሆኖ የቀረበው ግድያ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡበት እና የፈረሙት ፊርማ፣ ግርፋት ሲፈጸም የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች እና የሰው ምስክሮችን ያካተተ ነበር፡፡

አሁን በህይወት የሌለው የመለስ ዜናዊ መንግስት የመንግስቱን እና ግብረአበሮቻቸውን የፍርድ ሂደት ለማጠናቀቅ እ.ኤ.አ እስከ 2006 ድረስ 12 ዓመታትን ወስዷል፡፡ መንግስቱ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው ነበር ሆኖም ግን ወዲያውኑ ያ ብይን ተሸሮ ወደ ሞት ቅጣት ተቀይሯል፡፡

እንዴት ያለ የሚያስገርም ነገር ነው! ትሻልን ሰድጀ ትብስን አገባሁ! ወይም ደግሞ ከድጡ ወደ ማጡ! እንዲሉ መንግስቱን እና ግብረአበሮቻቸውን ለህግ ያቀረቡ የፍትህ አስመሳይ ሰዎች ዛሬ የመንግስቱን አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ እና አዲስ ዓይነት የግድያ እና የማሰቃያ ዘዴን በመቀየስ ህዝቦችን በዘር፣ በጎሳ፣ በኃይማኖት እና በእምነታቸው ብቻ በመፍጀት እና በማተራመስ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወሮበላ አረመኔ ጎሰኛ የቡድን ስብስቦች ደርግ መለዮውን ለብሶ ሲጨፈጭፍ እና ሲፈጅ የነበረውን አካሄድ ቀየር በማድረግ እነርሱ ግን ውድ እና ዘመናዊ የሆኑ የቆዳ ጃኬቶችን በመልበስ የቆዳ ቦርሳዎችን በመያዝ የእነመንግስቱ ቡድን ሲያደርግ ከነበረው ጭፍጨፋ በበለጠ እና በረቀቀ መልኩ ህዝብን በመፍጀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱም አምባገነን እና አፋኝ ቡድኖች አንድ ዓይነት አስተሳሰብን ይጋራሉ፣ ይኸውም “የእኛ ብቻ እውነት ሌላው ፍጹም ውሸት!”፣ ወይም ደግሞ “ከእኛ ውጭ መሞከር ህይወት ለመገበር!፣ እስር ቤት በመዋል እስር ቤት ለማደር!” በሚሉ ስንኞች ይጠቃለላሉ፡፡

እንደዚሁም ሌላው አስገራሚ ነገር የመለስ ዜናዊ የወሮበላ ዘራፊ ጎሳዊ ቡድን በህዝብ ደም እጁ ተጨማልቆ እና በደም ባህር ውስጥ እየዋኘ እያለ በምን ዓይነት መለኪያ እና መስፈርት እንዲሁም የሞራል ልዕልና ነው ሌላውን የእርሱ ተመሳሳይ ወታደራዊ አምባገነን ለፍትህ ማቅረብ የሚችለው? ሌባን ለፍትህ አቅርቦ የሚዳኘው እውነተኛ ፍትህን የሚያሰፍን ንጹህ ዜጋ እንጅ ሌላው ሞላጫ ሌባ ሊሆን ይችላል እንዴ? ፍትህን ፍትህ ከሚያሰፍን እውነተኛ የህዝብ ወገን እንጅ ከበቀልተኛ እና ከዘራፊ ቡድን ፍትህ ይገኛል ብሎ መጠበቅ ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ይቆጠራል፡፡ በሰሩት ወንጀል ሁለቱም ጭራቀዊ አፋኝ ቡድኖች ደርግ እና ወያኔ ለእውነተኛው ፍትህ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ቀርበው የየስራቸውን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፣ በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ሰው የዘራውን ያጭዳልና! እስከዚያው ድረስ አይበገሬው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ይቀጥላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግስቱ በአምባገነኑ ሮበርት ሙጋቤ ፈቃድ በዚምባብዌ ርዕሰ ከተማ በሀራሬ ጥገኝነትን አግኝተው ተቀምጠዋል፡፡ ሙጋቤ ከፍተኛ የሆነ የምስጋና እዳ በመንግስቱ ላይ እንዳላቸው እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “ለነጻነታችን ስናደርግ በነበረው ትግል መንግስቱ እና እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ለእኛ ቁልፍ እና ታላቅ ሚና ተጫውተዋል“፡፡ ወደ 23 የሚሆኑ የደርግ አባላት ተበይኖባቸው የነበረው የሞት ቅጣት በሌላ ተለወጠላቸው፡፡ ሌሎቹ 16 የሚሆኑት የደርግ አባላት ደግሞ ከእስር ተለቀቁ፡፡ እንደዚሁም ሌሎች በእስር ቤት እንዳሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 መንግስቱ እራሳቸው በሰሩት እና በእርሳቸው ትዕዛዝ ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ላለመሆን ከደሙ ንጹህ ነኝ በሚል ዓላማ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አቅርበዋል፡፡ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ! ወይም ደግሞ ለማያውቅሽ ታጠኝ! ነው ነገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አቅም አጥሮት ልጆቹ ከጉያው እየተነጠቁ በአደባባይ በጥይት እየተመቱ ሲጣሉ በወቅቱ በመከላከል ደመኛ ጠላቱን አንበርክኮ ለፍትሀዊ ፍርድ ማቅረብ ሳይችል ቀረ እንጅ ሁሉንም ነገር ከደርግ በበለጠ መልኩ አንጠርጥሮ ያውቃል፡፡ የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ እንዲሉ አሁን ደግሞ በሌላ የማታለያ ዘዴ መጽሐፍ ጽፈው በማቅረብ የደርግን ሀገራዊ የተጋድሎ ታሪክ ተብሎ ቢቀርብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጠብ የሚል ነገር ሊኖር እንደማይችል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ መርፌ ወስዶ ማረሻ ቢተኩ ልብ አይሆንምና፡፡ የወደቁት እና ያለቁት ሰማዕት ወገኖቻችን በአንድ የወታደር መጽሐፍ የውሸት ዲስኩር አይመነዘሩምና፡፡

አንዳንድ ሰዎች መንግስቱን ለመበቀል ሲሉ ህግወጥ በሆነ መልኩ ገልብጠው እና መጽሀፋቸውን በድረ ገጽ መስመር ላይ እንዲለቀቅ አድርገዋል፡፡ የህትመት የባለቤትነት መብት በመጣሱ እኔ በግሌ በጣም አዝኛለሁ፡፡ እናም ይህንን ጉዳይ በማስመልከት እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 2012 “የህትመት የባለቤትነት መብት እና የቅጅ ወንጀሎች” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ዓይን ባወጣ መልኩ የሰዎችን የአዕምሮ ውጤት የሆኑትን የህትመት ስራዎች በድፍረት ቀምቶ ማውጣት ስህተት እና መቻቻልን የጣሰ መጥፎ ባህሪ ነው በሚል የድርጊቱን ህገወጥነት ማውገዜ የሚታወስ ነው፡፡ መንግስቱ በሰው ልጆች ላይ ባደረሱት የሰብአዊ መብት ረገጣ እጅግ የጠለቀ ጥላቻ እና ቅሬታ ቢኖረኝም መጽሐፍ የማሳተም እና የመሰላቸውን የመናገር መብት እንዳላቸው፣ እንዲሁም ይህ መብታቸው ለድርድር እንደሚቀርብ አጽንኦ ሰጥቼ በመናገር እና በመከላከል እኔ የመጀመሪያው ነበርኩ፡፡ በትቸተ ላይ አንደፃፍኩት:

ማንም ቢሆን በአዕምሮው ውስጥ ይዟቸው ካሉት ትውስታዎእ አንጻር መንግስቱ ባቀረቧቸው እውነታዎች ወይም ውሸቶች ጋር ጥልቅ የሆነ አለመስማማት ሊኖረው ይችላል፡፡ መጽፋቸውን ከማንበቤ አንጻር ብዙዎችን እውነታዎች መርጠው ለማቅረብ ካደረጓቸው ጥረቶች እና ምርጫዎች አንጻር ልዩ እይታ ይኖረኛል፡፡ ሆኖም ግን በዚያ ትግል ወቅት በግላቸውም ሆነ በአገዛዙ የተፈጸሙትን ጅምላ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች ኃላፊነት ላለመውሰድ በሚያደርጉት ሙከራ ላይ በፍጹም አልስማማም፡፡ ግን ሁሉም አምባገነኖች የሚያደርጉት ይህንኑ አይነት አቀራረብ ነው፡፡ ሁልጊዜ ታሪካቸውን ጀግንነት በተሞላበት መልኩ ለማቅረብ እና በአገዛዝ ዘመናቸው ወቅት የፈጸሟቸውን ወንጀሎች ሁሉ ለሀገራቸው የአርበኝነት እና የሀገር ወዳድነት ፍቅራቸውን ለመግለጽ ሲሉ እንዳደረጓቸው አድርገው ያቀርባሉ፡፡

ከመንግስቱ ጋር በብዙ እውነታዎች እና በእርሳቸው የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ባላቸው ምዝገባ ላይ የማልስማማ እና የማወግዝ ብሆንም እንዲሁም ምንም እንኳ የጻፉት በሙሉ ውሸት ቢሆንም ከእርሳቸው ጎን በመቆም መጽሐፍ በመጻፍ እና በማሳተም ሀሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ በመከራከር እና በመደገፍ የመጀመሪያው ሆኛለሁ፡፡ እውነት ለመናገር እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2012 መንግስቱን የተካው እና አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በመምጣት ንግግር ማድረግ መብቱ እንደሆነ ስከራከር እንደነበረው ሁሉ አሁንም መንግስቱ እራሳቸውን መግለጽ እንዲችሉ መብታቸው እንዲከበር እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት አምባገነኖች እራሳቸውን መግለጽ እንዳይችሉ የማንፈቅድላቸው እና የምንከለክላቸው ለምንድን ነው? የእነርሱን እውነታዎች፣ ውሸቶች፣ ሀሳቦች እና አመለካከቶች ማን ይፈራቸዋል? ህዝቡ የእነዚህን አምባገነኖች ሀሳቦች አዳምጦ የእራሱን ፍርድ የመስጠት መብት የለውምን?

ይቅርታ ለመፈለግ ያለ ኃይል እና ይቅርታ ለማድረግ ያለ ኃይል፡ የንስኃ ኃይል

እ.ኤ.አ ኖቬምበር 24/1974 በተፈጸመው እልቂት የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን 40ኛ ዓመት ለመዘከር ስለ ንስኃ አስፈላጊነት ትንሽ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት በደርግ አገዛዝ ጊዜ በዚያች የጥላቻ ምሽት በተፈጸሙት ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች አሁንም ቢሆን የጠለቀ ሀዘን፣ የልብ ስብራት፣ ብስጭት እና ጥላቻ እንዳሉ ናቸው፡፡ በመንግስቱ እና በደርግ ከተፈጸሙ አሰቃቂ የእልቂት ወንጀሎች በታምር ተርፈው አሁን በህይወት በሚኖሩ ወገኖች እና በጥቃት ሰለባው ቤተሰቦች አዕምሮ ውስጥ ያ የደርግ ባለስልጣኖችን የፈጀው እልቂት አዲስ ሆኖ ይኖራል፡፡ ያ አሰቃቂ ወንጀል ከእነዚያ አሰቃቂ እልቂቶች በህይወት ተርፈው ላሉት እና ለግፍ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ወገኖች የልብ ቁስል ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ በነበረው ሰቆቃ እና ሀዘን በኋላ ለዚህን ያህል ጊዜ ቁስሉ ክፍት ሆኖ እንዳይድን እና እንዲያመረቅዝ ተደርጎ የቆየበትን ሁኔታ በማስወገድ ይህንን ያልዳነ እና እያመረቀዘ ያለ ቁስል እንዲጠግግ እና እንዲድን ለማደረግ እንዲቻል አሁን ያለውን ስቃይ እና መከራ ማስወገድ የሚጀመርበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ቁስሉ እስከ አሁን ድረስ ሳይድን ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ያደረጉት ወገኖች የመጀመሪያ ደረጃ የሆነውን እርምጃ ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው መንግስቱን እና አሁን በህይወት ተርፈው ያሉትን የደርግ አባላት ለዚያ አሰቃቂ ድርጊት እና ወንጀል ኃላፊነት ወስደው ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቁ ያለኝን ጠንካራ ተስፋ እያራመድሁ ያለሁት፡፡ ለዚህም ነው በመንግስቱ እና በደርግ የጥቃት ወንጀል የተፈጸመባቸው የጥቃቱ ሰለባዎች እና ቤተሰቦች ልቦቻቸውን ለይቅርባይነት እንዲያዘጋጁ ተማጽእኖዬን እያቀረብሁ ያለሁት፡፡

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን እና ጥቃት ፈጻሚዎችን አጽንኦ ሰጥቸ ልማጸናቸው የምፈልገው ነገር ለእራሳችሁ ብቻ ብላችሁ ሳይሆን ገና ላልተወለዱት እና ወደዚህ ዓለም ለሚመጣው ትውልድም ስትሉ ጎራዴዎቻችሁን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ቅበሯቸው፡፡ በእርግጥ እንደዚህ ያለ ጥያቄ ለማቅረብ የሞራል ስልጣን እንደሌለኝ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን የሞራል ስልጣኑ ያላቸው የኃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግዎች እና ሁሉም ምሰሶ የሆኑት የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች በሙሉ ለ40 ዓመታት የዘለቀውን ያልዳነ ቁስል ለመፈወስ የመሪነት ቦታውን ሲይዙ አይስተዋልም፡፡ ስለሆነም የደርግ ሰለባ በሆኑት ወገኖች እና በደርግ የሰለባ ፈጻሚዎች መካከል የእርቀሰላም ጥያቄ መምጣት እና ንስሀ መግባት አስፈላጊ እንደሆነ ለመናገር ወስኛለሁ፡፡

መንግስቱ እና ሌሎች የተረፉት አሁን በህይወት ያሉት የደርግ አባላት የመሪነቱን ቦታ በመያዝ ለሰሯቸው ወንጀሎች ጥፋት መሆናቸውን አምነው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ይህንንም ለማድረግ ለ60ዎቹ ንጹሀን የጥቃቱ ሰለባዎች ቤተሰቦች እና ፍትሀዊ ባልሆነ እስራት፣ ስቃይ እና ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ሰውን መግደል ሰለባ ለሆኑት ወገኖች ይቅርታ በማድረግ መጀመር ይቻላል፡፡ የእነርሱን የጥቃት ሰለባዎች ይቅርታ በመጠየቅ መንግስቱ እና የደርግ አባላት በመጨረሻ ለአራት አስርት ዓመታት ሲቆጠቁጣቸው የቆየውን መጥፎ ስሜት በማስወገድ ውስጣዊ ሰላም ያገኛሉ፡፡ ከጥፋተኛ ህሊና ጋር መኖር ገሀነም እንደመግባት ነው (እኔ መንግሥቱና የደርግ ሰዎች ህሊና የላቸውም ከሚለው አባባል ጋር አልስማማም)፣ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የጥቃት ሰለባው ሙትመንፈስ ብቅ እያለ እጁን እየቀሰረባቸው እያዩ መኖር ከህሊና ጋር መኖር አይደለም፡፡ ነብስን ከመሰቃየት ሊፈውስ የሚችለው ብቸኛው መንገድ አንድ ሰው የሰራውን ስህተት አምኖ መቀበል እና ይቅርታን በመጠየቅ ዕርቀሰላም በማውረድ ንስሀ መግባት ነው፡፡

ንስሀ ማለት የአንድ ጊዜ ድርጊት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ካሳ ለመካስ፣ ቁስልን ለመፈወስ እና ዕርቀሰላም ለማውረድ በአንድ ላይ ተሰባስሰቦ የሚደረግ ተጨባጭ ድርጊት ማለት ነው፡፡ ንስሀ በመግባት በርካታ ደግ ነገሮችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህን በማድረጉ አንድ ሰው የእራሱን አዕምሮ እና ልብ ከጥፋተኝነት እዳ ብቻ አይደለም ነጻ የሚያወጣው ሆኖም ግን እራሷን ነብስን ያድናል፡፡ ንስሀ በመግባት የዕርቀሰላም ሂደት ጥላቻ በፍቅር ይተካል፡፡ ባለፈው ጊዜ በተሰራ ስህተት አንድ ሰው ልቡን በዚያ ሰው ላይ አስሮ ከመኖር በመላቀቅ ንስሀ በመግባት ለአዲስ ቀን ለአዲስ ህይወት እንዲያስብ ያደርጋል፣ ዕርቀሰላም በማውረድ ንስሀ የመግባት ሂደት የቆሰለውን እና ተሰበረውን ልብ ይጠግናል፡፡

ዕርቀሰላም በማውረድ እያንዳንዱ ሰው ማድረግ ያለበት በርካታ ካሳዎችን ያገኛል፡፡ የጥቃት ሰለባ የሆኑት የ60ዎቹ ሟች ባለስልጣናት ቤተሶቦች የሚወዷቸውን ሰዎች በማጣታቸው ብቻ አይደለም ታላቅ ስቃይ ውስጥ የሚገቡት ሆኖም ግን ላጧቸው የጥቃት ሰለባዎች የቤተሰብ አባላት እና ዘመዶችም በመሆናቸው ጭምር እንጅ፡፡ የጥቃት ሰለባው በህይወት ያለው ቀሪ ዘመዱ እንዴት ያለ ውርደት፣ ከማህበራዊ ህይወት የመገለል፣ እና የሰው ልጅ ሊቋቋመው ከሚችለው ወሰን በላይ ጭካኔ የተሞላበት የማግለል ግፍ ይደርስበት እንደነበር እያንዳንዱ ሰው ያውቃል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን በክብራቸው ላይ ስቃይ ይደርስባቸው ነበር፣ የቆሸሸ ስም ይሰጣቸው ነበር፣ ምንም ወንጀል ሳይኖርባቸው እና ሳይረጋገጥ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ የተገደሉት የጥቃት ሰለባዎቹ የቤተሰብ አባላት በመሆናቸው ብቻ እንዲዋረዱ ይደረግ ነበር፣ በንቀት ምራቅ ይተፋባቸው ነበር፣ እንደማንኛውም ተራ ሰው ለመኖር እንዳይችሉ መብቶቻቸው ይገደቡ ነበር፡፡ መንግስቱ እና የእርሳቸው የደርግ አገዛዝ አባላት እነዚህን ከሰለባ የተረፉ ሰዎች ቀርበው ማናገር ይኖርባቸዋል፣ እናም ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡

መንግስቱ እና የእርሳቸው የደርግ አገዛዝ አባላት በቀይ ሽብር ዘመቻ ጊዜ ለሰሯቸው ወንጀሎች እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ለእናቶች፣ አባቶች፣ አያቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶች፣ አጎቶች እና በስልጣን ዘመናቸው ሁሉ በግፍ ለገደሏቸው የጥቃት ሰለባዎች ወጣት ቤተሰቦች ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የእነዚያ ወጣት የጥቃት ሰለባዎች እናቶች እና አባቶች ልብ ወስጥ በደርግ የተተወው ክፍተት መሞላት እና መደፈን እንዲሁም መጣበቅ ይኖርበታል፡፡

መንግስቱ እና የእርሳቸው የደርግ አገዛዝ አባላት እ.ኤ.አ በ1984-85 ተከስቶ በነበረው ታላቅ ረኃብ ሰለባ ሆኖ ለነበረው ህዝብ በቸልተኝነት እርዳታ እንዳይቀርብለት በማድረግ እና ከዚያም በተጨማሪ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የመጣውን እርዳታ እንኳ አማጺያንን ለማጥቃት በሚል ለወታደራዊ ስልት ዕርዳታ እንዳይደርስ ከልክለው አያሌ ወገኖቻችን ላለቁበት ወንጀል ተጠያቂዎች በመሆናቸው ለዚህም ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነትን ተቀብለው በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡

ለእኔ ተቀራርቦ መነጋገር እና ለእርቀሰላም ዝግጁ ሆኖ መገኘት ሂደት ሲሆን ይቅርታ ማድረግ ደግሞ ወሳኝ ድርጊት ነው፡፡ ለተፈጸሙ ስህተቶች ጸጸትን ማሳየት እንደ መንታ መንገድ ይቆጠራል፣ ይኸውም ይቅርታ ለመጠየቅ የሚፈልጉ እና ይቅርታውን ለመስጠት የተዘጋጁ ሰዎች በጥሩ ህሊና እና በንጹህ ልቦና በፈቃደኝነት የሚገኛኙበት ቦታ ነው፡፡ በዚያ መንታ መንገድ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚፈልጉ በግልጽ በዚያን ወቅት ስህተት መስራታቸውን አምነው መቀበል ይኖርባቸውል፡፡ እንደዚሁም በሌላው በኩል ይቅርታ የሚሰጡት ለበርካታ ዓመታት በንዴት እና በጥላቻ የቆዩት የጥቃት ሰለባ ቤተሰቦች እና ዘመዶች ናቸው፡፡ በእኔ አመለካከት የዕርቀሰላም ይቅርባይነት ውጤቱ የሚወሰነው በጥቃቱ ሰለባዎች ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና በጥቃት ፋጻሚዎች የአመለካከት እና አስተሳሰብ የለውጥ ደረጃ ነው፡፡ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ያለ ጥላቻ መርዛማነት እንዲወገድ ሆኖ አንድ ሰው እድለኛ ከሆነ ወደ ፍቅር ይለወጣል፡፡ ጥላቻ እና ፍቅር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ያችን ሳንቲም እንዴት ወደ ላይ እንደምናጉናት ባለው ሂደት ላይ ይወሰናል፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የምናጉናት ከሆነ መግባባትን እና ዕርቀሰላምን ማምጣት እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን በተለያየ አቅጣጫ የምናጉናት ከሆነ አለመግባባት እና ጥላቻን እናተርፋለን፡፡ ይቅርታ ለጥላቻ፣ ለሀዘን፣ ለተስፋቢስነት፣ ለጥልቅ ጥላቻ፣ ለምሬት እና ለበቀል መነሳሳት ፈዋሽ መድኃኒት ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የዕውነት እና ዕርቀሰላም ኮሚሽን (ዕዕኮ) “ደቡብ አፍሪካውያን/ት የሞራል ተቀባይነት ባለው መንገድ እና ዕርቀሰላምን በማውረድ ወደፊት ለመገስገስ እንዲቻል ስላለፉት ድርጊቶች ተቀራርበው መወያየት እንዲችሉ” ነበር የተመሰረተው፡፡ ግዙፍ የሰብአዊ መብትን የደፈጠጡ ደባ ፈጻሚዎች ይዘውት በነበረው የፖለቲካ አመለካከታቸው መሰረት ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ሙሉ እና እውነተኛ የሆነ ምስክርነታቸውን በመስጠት ከዚህ በኋላ ግን በእንደዚህ ያሉ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ፍጹም በሆነ መልክ ላልሳተፍ ቃል እገባለሁ በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡ ዕዕኮ እንደየሰው አመለካከት በስኬት የተጠናቀቀ ወይም ደግሞ በውድቀት ታጅቦ የቀረ ሊባል ይችላል፣ ሆኖም ግን በእኔ አመለካከት በስኬት ጉዞ የተጠናቀቀ ነው ምክንያቱም ሊፋቅ በማይችል ቀለም እና ታማኝነትን ባረጋገጠ መልኩ ኔልሰን ማንዴላ በህዝብ ተመርጠው ስልጣን ለመያዝ ባደረጉት የበዓሉ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “በፍጹም፣ በፍጹም እናም በፍጹም ይህች እጅግ የተዋበች ምድር እንደገና ተመልሳ አንዱ ሌላውን የሚጨቁንባት ልትሆን አትችልም“፡፡ ያ ለእኔ እንደዚህ ያለ ዕርቀሰላም በማውረድ ለቀጣዩ ትውልድ በአረብ ብረት ላይ የተጻፈ ቃልኪዳን በመግባት እንዲህ የሚል ክቡር የሆነ ቃልኪዳን ማሰር ያስፈልጋል፣ “ከእንግዲህ ወዲያ እጅግ በጣም በተዋበችው በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንደገና ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ዜጎች የሚገደሉባት፣ ስቃይ እና ሌሎች መጠነሰፊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች የሚደፈጠጡባት በፍጹም፣ በፍጹም እናም በፍጹም አትሆንም”፡፡ የሚለው የዕርቀሰላም ውጤት ነው።

እርግጥ ነው ወደ ዕርቀሰላም ሊያመጣ የሚችል የመጸጸት ውይይት በመንግስቱ፣ በእርሳቸው የደርግ አባላት እና በእነርሱ የጥቃት ሰለባ ወገኖች መካከል ማዘጋጀት እና ማከናወን እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነገር እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወንዶች እራሴን ጨምሮ በሀሰት ኩራት እና በባዶ ጉራ የተጀቦንን ነን፡፡ ሰው እንደ ሰው ሆኖ ለሰው አስቦ እና ሰውን አክብሮ ከመኖር ይልቅ ከእውነታው ውጭ ከዚህ በተጻረረ መልኩ በእብሪት በመወጠር ወንድ ኃይለኛ፣ አይበገሬ፣ ለጥቃት የማይንበረከክ፣ እርሱ ሁልጊዜ ይቅርታ እንዲደረግለት የመጠየቅ እንጅ ይቅርታ ለማድረግ ልቦናው የማይቀበል አድርገን እንስላለን፡፡ ይኸ በእውነት ሊወገድ የሚገባው የስልጣኔ ወይም የጉብዝና ምልክት ሳይሆን የነውረኛና የሀሳበ ግትርነት መለያ ባህሪ ነው፡፡ ይህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ በፍጹም ሊወገድ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ስህተቶቻችንን አምነን በመቀበል ለሰራናቸው ጥፋቶች ይቅርታ መድረግን የምንሸሽ ይመስላል፡፡ ምናልባትም ይህ ሁኔታ የባህል ተጽእኖ ያመጣው ጥቅል የባህሪ ችግር ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ እኔ በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር ቢኖር “በእውነት አዝናለሁ፣ ይቅርታ አድርግልኝ/አድርጊልኝ፣ ከተቻለ ስህተቴን አርምልኝ/አርሚልኝ፣ ወይም ደግሞ ቀጥል“ ከማለታችን በፊት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለሰዓታት ያህል ሀሳቦችን አሳማኝ በሆነ መልኩ ሆኖም ግን እውነታውን ብቻ መሰረት በማድረግ መወያዬቱ እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ኃላፊነትን አምኖ ከመቀበል እና ነገሮች እንዲሻሻሉ ጥረት ከማድረግ ይልቅ መጸሐፍ በመጻፍ ይቅርታ ለማድረግ ሺህ ምክንያቶችን በመደርደር የሰራናቸውን ስህተቶች እናድበሰብሳለን፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የሰው የመጨረሻው ድክመት እና የባህሪ ንቅዘት እንደሆነ አድርገን ልንመለከት እንሞክራለን፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የመሸነፍ፣ የሀፍረት፣ እና የመጨረሻ ስብዕናን የማጣት ምልክት እንደሆነ አድርገንም እንቆጥራለን፡፡

ይኸ ሁሉ ነገር መቀየር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ መጥፎ ባህሎችን ባለመማር እና ባለመውሰድ ይልቁንም አዲሶችን እና ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑትን በመውሰድ እራሳችንን ከእራሳችን ልንጠብቅ እንችላለን፡፡ ተቀራርበን ስለዕርቅ ልንወያይ እንችላለን፣ ይኸ መቀጠል ያለበት ጥሩ ልምድ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1974 ለተካሄደው አሰቃቂ እልቂት 40ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ሆነን ወደኋላ መለስ ብለን ስናየው ቀደም ሲል ስልጣን ይዘው ለነበሩት እና አሁንም በህይወት ለሚገኙት፣ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ስልጣንን ጨብጠው ላሉት ለህይወት ዘመን የሚዘልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡ መለስ ለሰራቸው ወንጀሎች ሁሉ ምንም ዓይነት ይቅርታ ሳይጠይቅ አለፈ፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው በቀጠፋቸው ህይወቶች እና ከሞተም በኋላ እስከ አሁን ድረስ በየሳምንቱ እንደበግ እየነዱ ወደ እስር ቤት በሚያጉሩት የወያኔ ወንጀለኞች ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ከእዚህ ዲርጊታቸው እንዲታቀቡ በግልም ሆነ በቡድን የሚጠይቅ የለም፡፡ ከሞተ በኋላ መለስ አሁን በህይወት ለሌሉት እና እርሱ ለቀጠፋቸው እንዲሁም ከመሞቱ በፊት እና በአሁኑ ጊዜም በመላ ሀገሪቱ ህይወታቸው በእስር ቤት እንዲያልፍ በየእስርቤቶቹ አጉሯቸው ለሚገኙት ወገኖቻችን በሰራው ወንጀል ምክንያት በሰማይ ቤት በሚያገኘው ዘላለማዊ ፍርድ ካልሆነ በስተቀር በዓለማዊው የወያኔ ፍርድ ቤት ሳይሆን ለህዝብ ፍርድ ቤት ይቅርታ ሊጠይቅ አይችልም፡፡ ይቅርታ ሳይጠይቅ በማለፉ ምክንያት ትክክለኛውን ውሳኔ ከታሪክ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

የሚገርመው ነገር ግን በመለስ የተተካው ታምራት ላይኔ ከ12 ዓመታት የእስራት ህይወት በኋላ ለእድሜ ልኩ የሚሆን የማያዳግም ትምህርትን ቀስሟል፡፡ ያ ትምህርት እራሱን ከእራሱ እንዲጠብቅ፣ ኃይለኞች ከሆኑት ከእራሱ ጓደኞች እራሱን እንዲጠብቅ፣ ጓደኛው ከሆነ ወንድ እና ሴት እንዲሁም ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን አውቆም ሆነ ሳያውቅ ለሰራቸው ስህተቶች ሁሉ በቢሮ እና በአደባባይ ይቅርታ ጠይቆ የደረሰበትን መከራ እና ስቃይ ተሸክሞ ከእስር ቤት ሊወጣ ችሏል፡፡

ከእስር ቤት በተለቀቀ ጊዜ በሰጠው መግለጫ የመጀመሪያ ነገር የሚያደርገው ነገር ቢኖር ከመለስ ፊት ቀርቦ ይቅርታ እንዲያደርግለት መጠይቅ ነው ብሎ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር ስልጣን ካላቸው ሰዎች ጋር እኩል ያደረጉትን እንዳደረገ እና እርሱ የተለየ ነገር እንዳላደረግ ግልጽ አድርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ በቢሮ ላይ በነበረበት ጊዜ ቀደም ሲል ለሰራቸው ስህተቶች ይቅርታን ጠይቆ የሚያምንበትን ለመስበክ እና የእራሱንም እምነታዊ ታሪክ ለማስተማር እንዲሁም ለሰራቸው ስህተቶች ሁሉ ይቅርታ ለመጠየቅ ተንቀሳቅሷል፡፡ ይቅርታ እንዲደረግለት ህዝቡን ጠይቋል ሆኖም ግን ይቅርታውን መቀበል አለመቀበል የህዝቡ ፋንታ ይሆናል፡፡

እንደ አንድ መሪ እና እንደ አንድ ሰብአዊ ፍጡር ታምራት ላይኔ ለሁሉም በእራሱ ግለሰባዊ እና ሙያዊ ውድቀቶች እና ስኬቶች በእራሱ ምክንያቶች የእራሱን ተነሳሽነት ወስዶ በቢሮ በነበረበት ጊዜ ለሰራቸው ስህተቶች እና ግድፈቶች ሁሉ ይቅርታ በመጠየቅ ሙሉ ኃላፊነትንም እንደሚወስድ ግልጽ አድርጓል፡፡ በተፈጥሮ በአብዛኛው እውን ሆኖ እንደሚታዬው አንድ ሰው በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ መከራ እና ፍዳውን እንዲያይ ያደረጉትን ሰዎች ለመበቀል ጥረት እንደሚያደርግ ነው ሰው የሚገምተው፡፡ ሆኖም ግን ብዙ ሰው ያልተጓዘበትን መንገድ መረጠ፡፡ እናም ይቅርታ እንዲደረግለት ጠየቀ እና ይኸ ነው እንግዲህ እንዲህ የሚለውን የሮበርት ፍሮስት ስንኞች በመውሰድ ይህንን ልዩነት ያመጣው፣ “የእኔ ምኞት በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉትን ለረዥም ጊዜ ከስልጣናቸው የተገለሉትን እናም ስልጣንን ለማግኘት ጥረት የሚያድርጉትን ሰዎች ማየት እና ለስልጣን ምንም ደንታ የሌላቸውን በጣም ጥቂቶች የተጓዙበትን ለመጨረሻው ፍቅር የሚያደርሰውን የይቅርታ እና የዕርቅ መንገድ መከተል ነው“፡፡

እናንተ እና እኔ ኞቬምበር 24ን ለምን እንደምናስታውሰው፣ መማርም ያለብን

ታሪክን አስመልክቶ እንዲህ የሚባል አባባል አለ፣ “የታሪክን ትምህርት የሚረሱ ያንኑ መልሰው ይደግሙታል“፡፡ እናንተ እና እኔ ኖቬምበር 24/1974ን ማስታወስ አለብን ምክንያቱም ከዚህ የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች እና ለቀጣዩ ትውልድም የምናስተላልፋቸው ጠቃሚ መልዕክቶች አሉ፡፡

ትምህርት ቁጥር 1. ኢትዮጵያ በህግ የበላይነት ፍትሀዊ የሆነ የህግ ስርዓት በመዘርጋት መተዳደር አለባት እንጅ በዘፈቀደ እና በስሜታዊነት ውሳኔ በሚሰጡ ወታደራዊ አዛዦች፣ አማጺያን መሪዎች እና እና በሌሎች መንገዶች ስልጣንን በሚይዙ ወይም ደግሞ በኃይል በሚቆጣጠሩ ሰዎች አትመራም፡፡ የህግ የበላይነት መርህ በመሰረቱ ስለህግ እና ህገመንግስታዊ ተጠያቂነት ነው፡፡ ማንም ወንድ ይሁን ሴት ከህግ በላይ የለም፡፡ ነጻ እና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ ከተደረገ በኋላ በህዝብ ተመርጦ ካልተወከለ በስተቀር ማንም ተነስቶ የስልጣን ፈረስን በመያዝ የሚጋልብበት አካሄድ መኖር የለበትም፡፡ ያለምንም ስጋት ጠንቃቃ ሆነን ለዘላለሙ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እና በስልጣን ላይ ባሉ ወይም ስልጣን በሌላቸው ሰዎች መጠነሰፊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች በምናይበት ጊዜ ማስረጃ በመያዝ ማጋለጥ እና መከላከል አለብን፡፡

ትምህርት ቁጥር 2. ከህግ አግባብ ውጨ ማንም ኢትዮጵያዊ/ት ህይወቱን/ቷን፣ ነጻነቷን፣ እና ንብረቱን/ቷን ሊያጣ/ልታጣ አይገባም፡፡ ይህም ማለት ማንም ሰው ቢሆን ወዲያውኑ አይገደልም ወይም ደግሞ በይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የችሎት ሂደት/Kangaroo trial ወደ ማጎሪያ እስር ቤት አይወረወርም፡፡ በወንጀል ተጠርጥሮ ክስ የተመሰረተበት ማንኛውም ሰው ትክክለኛ የሆነ የክሱ ዝረዝር ተጽፎ ሊሰጠው እና በቂ ማስረጃ ማቅረብ እንዲችል በቂ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንደዚሁም መከላከያ እና የቀረበበትን ክስም ለማስተባበል በተጨባጭ የመከራከር፣ የሚቀርቡ ክሶች ነጻ ለሆነ ችሎት ቀርበው መወሰን ይኖርባቸዋል (የፖለቲካ ጣልቃገብነት ሳይኖር በህጉ እና በህጉ ብቻ ብይን የሚሰጡ ነጻ ዳኞች፣ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች የሌሉበት)፣ የእራሱ የህግ አማካሪ የመያዝ፣ አማካሪ ለመያዝ አቅም የሚገድብ ከሆነም መንግስት እንዲመድብለት ማድረግ፣ ስምን ጥላሸት ከመቀባት እንዲታቀብ የማድረግ፣ (ምንም ዓይነት የማሰቃየት ስራ እንዳይተገበር ወይም ደግሞ በሀሰት እንዲያምኑ ለማድረግ ተብሎ ምንም ዓይነት የማስገደድ ድርጊት እንዳይፈጸም) እና ቅሬታን ለማቅረብ መብት ያለ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ መሰረታዊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ህግ አጠባበቅ ዙሪያ እራሳችንን ማስተማር እና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን መብት ለማስከበር ሳያወላውሉ መስራት ይጠበቃል፡፡

ትምህርት ቁጥር 3. የማንም ኢትዮጵያዊ/ት መብት ሲደፈር ስናይ በምንም ዓይነት መልኩ ዝም ማለት የለብንም፡፡ ጭራቃዊነት መሰረቱን የሚተክለው በዝምታ እና በፍርሀት ነው፡፡ አምባገነንነት እና ጭቆና የሚኖሩት በተጨቋኖቹ ዝምታ ነው፡፡ በዱሮ ጊዜ የአሜሪካ የባሪያ ፈንጋይ የነበሩት እና በኋላ አመለካከታቸውን ቀይረው በመገልበጥ ጸረ ባሪያ እንቅስቃሴዎችን ሲያራምዱ የነበሩት ፍሬድሪክ ዳግላስ እንዲህ ብለው ነበር፣ “የጨቋኞች የመጨረሻ የመጨቆን የወሰን ጣሪያ እነርሱ በሚጨቁኗቸው ተጨቋኞች የመጨቆን ጽናት የሚወሰን ነው“፡፡ በጣም ጭካኔ የተሞላባቸው ውሸቶች ሁልጊዜ በዝምታ ይታለፋሉ፡፡ በጣም ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ሁልጊዜ በንቀት ዓይን ታይተው ይታለፋሉ፡፡ ከጭራቃዊነት ጋር መታገል የማንኛውም ሰው የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ኤድመንድ ቡርኬ የተባሉ ሰው እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሁሉም ጨቋኞች ለእኩይ ምግባራቸው የመሰረት ድንጋይ ሆኖ እንዲያገለግላቸው የሚፈልጉት ነገር ቢኖር ጥሩ ህሊና ያላቸው ሰዎች ዝምተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነው…ጭራቃዊነት በድል አድራጊነት ተንሰራፍቶ የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ወንዶች እና ሴቶች ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ብቻ ነው“፡፡ ዝምታ ወርቅ ሊሆን ይችላል ሆኖም ግን በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ዝም ማለት ከጭቃዊነት ጋር እንደመተባበር ያህል ነው፡፡

ስለሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የመናገር አስፋላጊነት ምክንያት ቀላል እና ግላዊ ነው፡፡ ይኸውም በቀጣዩ የሰብዊ ድፍጠጣ ዝርዝር ውስጥ አንተ ልትሆን ስለምትችል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የጀርመን ፕሮቴስታንት የሆኑት እና በናዚ ስቅይት የተፈጸመባቸውን የፍሬደሪክ ጂ.ኢ.ኤም ኒሞለርን እንዲህ የሚሉትን ጠንካራ ቃላት እንከተል፣ “መጀመሪያ በአይሁዶች ላይ መጡባቸው እና ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም አይሁድ አልነበርኩምና፣ ቀጥሎ በኮሚኒስቶች መጡባቸው እና ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም ኮሙኒስት አልነበርከምና፣ ከዚያም በመቀጠል በሰራተኞች ማህበር አባላት ላይ መጡባቸው እና ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም የሰራተኛ ማህበር አባል አልነበርኩምና፣ በመጨረሻም በእራሴ ላይ መጡብኝ እናም ለእኔ የሚጮህልኝ ምንም ሰው አልተገኘም“

ደርግ በአዳሀሪያን፣ በጸረ አብዮተኞች፣ በስርዓተ አልበኞች፣ በተማሪዎች እና በወጣቶች ላይ ተራ በተራ በመጣባቸው ጊዜ ሌሎቻችን በጸጥታ ዝም አልን፡፡ ለእኛ እስካልቆሙልን ድረስ ስለእነርሱ ጉዳይ ደንታ የለንም፡፡ የእኛ ጎረቤት ልጆች በቀበሌ አመራሮች፣ የጎረቤት ሰላይ ቡድኖች እና በወሮበላ ዘራፊ ሚሊሻዎች እየተያዙ እየተወሰዱ እንደአበደ ውሻ በጥይት እየተገደሉ በየመንገድ ሲጣሉ እኛ በፍርሀት ቆፈን ተውጠን እና እራስን ለማዳን በስሜት ሽባ በመሆን በዝምታ ተቀምጠን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ደርግ የቀይ ሽብር ዘመቻን መተግበር በጀመረ ጊዜ በእያንዳንዱ ቤት ማንኳኳቱን ቀጠለ፡፡ በፖለቲካ ጦርነት አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ እንደቡዳ እርስ በእርሱ መበላላት ጀመረ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ህወሀት በአማራ ህዝብ ላይ በመጣበት ጊዜ ዝም ብለን መመልከት የለብንም፡፡ ወያኔ በአማራ ላይ በሚመጣበት ጊዜ እና ስማቸውን በማጥፋት በእራሳቸው ሀገር “ሰፋሪ” (መሬት የሚቀራመቱ ወንጀለኞች) እየተባሉ በሀገራቸው ውርደት ሲያደርሱባቸው ድምጻችንን ከፍ አድርገን በመጮህ መቃወም አለብን፡፡ ወያኔዎች በኦሮሞዎች ላይ ሲመጡባቸው፣ ሲይዟቸው እና በየእስር ቤቱ ሲያጉሯቸው እንዲሁም ስቃይ ሲፈጽሙባቸው ዝም ብለን መመልከት የለብንም፡፡

** ደርግ በህገ ወጥ መንገድ የገደላቸው የመንግስት ሹማምንት የሰራ አገልገሎቶች አንድ አንድ መረጃዎች የተወሰዱት ከአቶ አሉላ ዋሴ መፅሐፍ “ይህም ያልፋል” ከሚለው ነው።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም

Filed in: Amharic