>
5:13 pm - Saturday April 20, 4272

ምን አይነት ሰላማዊ ሰልፍ? [ተክሉ አባተ - ዶ/ር]

ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፍኩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ግቢ ተማሪ እያለሁ ነበር:: በአራት ዓመት የትምህርት ቆይታዬ በርከት ያሉ ሰልፎች ተካሂደዋል:: አንዳንዴ የምግብ ጥራት ማሽቆልቆሉን በመቃወም ሌላ ጊዜ ነጻነትን ፍትህንና ዴሞክራሲን እንዲሁም የመሬት ክፍፍልን በመቃወም:: ምግብን በተመለከተ የተቀናጁ ሰልፎች አጀማመራቸው ምግብ-ነክ ይሁን እንጅ መደምደሚያቸው ፖለቲካ ነበር:: ድንገት ከሰልፉ መካከል አንዱ ተነስቶ “ፍትህና መብት ይከበር” ካለ ተሜ ወዲያው ተቀብሎ  ያስተጋባዋል:: አንዳንዶች ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀድሞ የተዘጋጀ የጽሁፍ መፈክር ብቅ ያደርጋሉ:: በአቅራቢያቸው ያለ ተሜ እያነበበ ያስተጋባዋል:: ሌላው ይቀበለዋል:: የአንገት ስር እስኪወደር ድረስ ይፎከራል:: ስሜት እየጋለ ይሄዳል:: የተሰላፊው ቁጥር የሚጨምረው ሰልፉ ከተጀመረ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ነው:: መጀመሪያ ላይ ፈራ ተባ እያሉ ከዳር ሆነው የሚመለከቱ  ይበዛሉ.: በኋላ ድንገት ሰልፉን የሚቀላቀሉ ይበዛሉ:: ሰልፉ ዋናውን በር የሚወጣው በሦስትና አራት ረድፍ ባለው ረጅም መስመር ነው::

Addis_Abeba_Universityየሚገርመው ሰልፉ ሰላማዊ ተብሎ ቢጀመርም ሰይፋዊ ሆኖ ይጠቃለላል:: ካድሬ ሰላይ ፖሊስና ወታደር ሙያቸውን የሚያስመሰክሩበት ልዩ  አጋጣሚ እስኪመስል ድረስ አካባቢውን ያጥለቀልቁታል:: ከጥቂት ማስፈራራት በኋላ ወደ ርምጃ ይሸጋገራሉ:: ተሜም እድሉን የሚለካበት ጊዜ ይገጥመዋል:: ግርግርና ዱላ በጥበቃ አካላት ይጀመራል:: ጥጋቸውን ይዘው በሚጠባበቁ አይፋ በሚባሉ ወታደራዊ መኪናዎች ተሜ ወደ ማሰቃያ ጣቢያዎች ይወሰዳል:: በደንብ የሚደበደቡ: የሚታሰሩ: ከትምህርታቸው የሚባረሩ: ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው ብዙ ናቸው:: ጀርባቸው እስኪላጥ እግራቸው እስኪጠቁር በፖሊስ የሚሰቃዩ ሞልተዋል:: በተለይ ሸጎሌ ተብሎ ከሚጠራው መጠርነፊያ ጣቢያ የተወሰዱት ያጋጠማቸው ስቃይ ‘ታሪካዊ’ ነበር:: በባዶ እግራቸው እንደጦር በቆመ አሸዋ ላይ ያሴዷቸው ነበር:: በካድሬዎች ወከባ የተነሳ ትምህርት ያቋረጥንባቸው ጊዜያትም ነበሩ::የበለጠ የሚገርመው ደግሞ ለቀናት ከሚዘልቀው አካላዊ ስቃይ ይልቅ ተማሪዎች የሚደርስባቸው ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ነበር::ተማሪዎች ከእስርና ከስቃይ ለመውጣት ከፈለጉ መንግስትን ይቅርታ እንዲጠይቁ ይገደዳሉ:: ከዚያም በማናቸውም ተመሳሳይ ሰልፎች ወይም ዝግጆቶች ላይ ወደፊት እንደማይሳተፉ በሚገልጠው ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ይደረጋሉ:: በመሆኑም ከእስራታቸው በኋላ ትንፍሽ እንኳን የማይሉ እየተበራከቱ መጥተው ነበር:: እስካሁንም ድረስ ያንን  የገቡትን ‘ቃል ኪዳን’ ታሳቢ በማድረግ በመሳቀቅ የሚኖሩ አሉ::ውጤታቸው ምንም ይሁን ምን የተደረጉ ሰልፎች መደረግ የነበረባቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ:: ውጤት ያመጡ ሰልፎች ነበሩ:: እነወይዘሮ  ገነት ዘውዴ እና እነ ዶክተር ዱሪ ላባቸው እስኪመጣ ድረስ በተሜ ተፋጠዋል:: ቀላል የማይባሉ ለውጦችም ወዲያውኑ ተደርገዋል:: እነዚያ ሰልፎች የተማሪን ህይወት ያማከሉ ቢመስሉም (አንዳንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች ተሜ ለዳቦ ጥራት እንጅ ለሃገሩ እድገት አይሰለፍም እያሉ ቢሳለቁም) ከብሄራዊ የዜግነት ግዴታዎችና መብቶች ጋር የተያያዙ ናቸው:: ነጻነት ፍትህ እኩልነት የተጠየቀባቸው ሰልፎች ነበሩና::

የሰልፍ ሁሉ መጀመሪያ

ከላይ ያለውን ታሪክ ያነሳሁት እንደመግቢያ እንዲያገለግለኝ ነው:: ዋናው ነጥቤ በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ ሰልፍን አስፈላጊነት ለማመላከት ነው:: የዜግነት መብት እስካልተከበረ ድረስ ሰልፍ ይካሄዳል:: ለመብትና ለአገር ክብር የሚደረግ ሰልፍ ሰው የመሆን አንዱ መገለጫ ነው:: ሰልፉ ግን መጀመር ያለበት ከግል ህይወት ነው:: በማይጠቅሙ ሃሳቦች የተሞላ አእምሮ  ያለው ሰው በራሱ ላይ ሰልፍ መውጣት አለበት:: መብቱ በጓደኛው ወይም በሥራ ባልደረባው የሚጣስበት ካለ በዚያ ላይ ሰልፍ መውጣት አለበት:: አባል የሆነበት ድርጅት መብቱን የሚጥስበት ከሆነ ሰልፍ መውጣት አለበት:: ሰልፍ መውጣትም በአካል ወደአደባባይ መንጎድን ብቻ አይመለከትም:: ፍርሃትንና ይሉኝታን አስወግዶ ሃሰተኞች ወይም መብት እረጋጮች የሚሰሩትን ግፍ ፊትለፊት መናገርንም ያጠቃልላል:: በአደባባይ ሰልፍ ተገኝቶ በጓዳ መብቱንና ጥቅሙን የሚያስነካ ሰው ራሱን ያታልላል:: በውስጥም በውጭም በአካልም በሥነ-ልቦናም በግልም በቡድንም በደልን መቃወም ማጋለጥም ያስፈልጋል:: “መብቴ ተጣሰ” ብሎ ሰልፍ የሚወጣ የሌላውን ሰው መብት መጠበቅም ሊኖርበት ነው::  እያንዳንዳችን ለራሳችን መብት ሳናቋርጥ ሰልፍ መውጣት አለብን:: ይህ ከሆነ ነው የቡድን ሰልፎች የሚያምርባቸውና ውጤታማ የሚሆኑት:: ብዙ ሰዎች አብዝተው የሚጨነቁት ግን በቡድን ስለሚደረግ ሰልፍ ነውና ለጊዜው እሱን እንመልከት::
ውጤታማ ሰልፍ
psychአጠቃላይ ሲታይ የትም ቦታ በማናቸውም ጊዜ የሚደረጉ ህግን መሠረት ያደረጉ የቡድን ሰላማዊ ሰልፎች ሁሉ ልዩ ባህርይ አላቸው:: ዳሩ ግን አንድ ሰልፍ ግልጽ ዓላማዎችና የአፈጻጸም ስልቶች ሊኖሩት ይገባል:: ይህ ደግሞ በጊዜና በቦታ ሊወሰን ይችላል.: ያም ሆኖ አንድን ሰልፍ ውጤታማ ነው ብሎ ለመፈረጅ በርካታ መለኪያዎችን ማሟላት ይኖርበታል:: ለእኔ የተሳካ ሰልፍ ማለት ቀጥለው የተዘረዘሩትን የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜያት አብዛኞችን መስፈርቶ ች ያሟላል::
  • ሰልፉን ተከትሎ  ተሰላፊዎች በራስ የመተማመንና የእርካታ ስሜት ማግኘት አለባቸው
  • ተሰላፊዎች በቋሚነት የራሳቸውንና የወገናቸውን መብቶች ለማስጠበቅ ጽኑ አቋም ይይዛሉ
  • ሰልፍ ህግን በማያከብረው በመንግስት ላይ ስጋትና ፍርሃትን ማስፈን አለበት
  • መንግስት ለጊዜው በይፋ ለውጦችን ለማድረግ ቃል ባይገባም ወደዚያው የሚያደርሱ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ ማስገደድ አለበት
  • መንግስት ተረጋግቶ ጭቆናውን እንዳይቀጥል ያደርገዋል
  • የመንግስትን  ጨቋኝነት የሌሎች ሃገራት መሪዎችና ተቋማት በደንብ እንዲያውቁት ያደርጋል
  • አንዱ ሰልፍ ሌላ ሰልፍ ይወልዳል
  • በሰልፉ ምክንያት የሚታሰር የሚደበደብ የሚሰደድ ወዘተ ካለ ስለእሱም ፍትህ ይጠይቃል ሌላ ሰልፍ በተሻለ ሁኔታ ይደረጋል
  • መንግስት በሚያደርጋቸው ጥቂት የማስታገሻ ማሻሻያዎች አይታለልም
  • በመጨረሻም የሚፈለገው ለውጥ በመጠንና በዓይነት ይገኛል
  • የውጤታማ ሰልፍ ባህርያት
  • ከላይ የተዘረዘሩትን እንዲሁም ሌሎችን ውጤቶች ለማሳካት አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ማሟላት ያለበት ባህርያት ይኖራሉ:: ጥቂቶችን እንዲህ ዘርዝያለሁ::power
    • በደንብ የተደራጀና የተመራ ሰልፍ የተሰላፊውን ቀልብ ከመሳብ በተጨማሪ ያልተሰለፉ ሰዎችም ወደፊት እንዲሰለፉ ይጋብዛል
    • ለረጅም ጊዜ ወይም በተከታታይ የሚደረግ ሰልፍ እጅግ አመርቂ ውጤት ያመጣል
    • ሰልፍ በሚደረጉ መጥፎ ሥራዎች ላይ ያለን ተቃውሞ  ለማሰማት ብቻ ሳይሆን ለውጥ እንዲደረግ የሚያስገድድ መሆን አለበት
    • ሰልፍ መንግስት መመለስ ያለበት ግልጽ ጥያቄዎችን ማቅረብ አለበት
    • እንደ ጉዳዮች ትልቅነትና አሳሳቢነት እየታየ መንግስት መልስ የሚሰጥበት ጊዜም መገለጽ አለበት
    • በተሰጠው ጊዜ መንግስት አጥጋቢ መልስ ካልሰጠ በአይነቱና በመጠኑ ልዩ የሆነ የተቀነባበረ ሰልፍና ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚደረግ ማሳወቅ አለበት
    • ሰልፍ አስተባባሪዎች ሊታሰሩ ወይም ሊሰው ስለሚችሉ በርካታ መሪዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል
    • ህዝቡ መብቱን በሚገባ እንዲያውቅና ትግሉን በቀጣይነት እንዲመራ ማድረግ ወሳኝነት አለው
    • ህዝቡ ኃይልንና ስሜትን ተቆጣጥሮ ከሰልፉ ዓላማ ላይ ትኩረትን ማድረግ  እንዳለበት መነገር አለበት
    • ህዝቡ በአቋሙ ከጸና ጨቋኝ መሪዎች እንደሚሸነፉ ማስተማርና ሥልጣን የህዝብ እንደሆነ ማሳሰብ ያስፈልጋል
    • ፖሊስና ወታደር በሚመጣበት ጊዜ ከመሮጥ ይልቅ ሁሉም ተረጋግቶ ባለበት እንዲጸና ማድረግ ያስፈልጋል

      ማጠቃለያ

      የኢትዮጵያ ህዝብ የግልም ሆነ የቡድን መብቱ ተረግጧል:: ኑሮ ከአቅሙ በላይ ሆኗል:: ይህ አላንስ ብሎ ያሰበውን እንዳይናገር አንደበቱ ተዘግቷል:: በተጨማሪም መንግስት አንዱ ህዝብ በሌላው ላይ እንዲነሳ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው:: በመሆኑም እውነተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አማራጭ የሌለው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኗል.: አገር ቤት ሆነው የሚታገሉት ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድነት መድረክ በመፍጠር ሰላማዊ ሰልፍ ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ/ም ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ:: ይህ በዓይነቱ የተለዬ ሰልፍ  በሁሉም ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል:: በአካል በሞራል በሃሳብና በገንዘብ መደገፍ ይኖርብናል::
      የሰልፉ አስተባባሪዎችም እጅግ ጥበብ የተሞላበት እቅድ ነድፈው ህዝቡን ደረጃ በደረጃ መምራት አለባቸው:: መንግስት ሊያሟላቸው የሚገቡ ጉዳዮች በቁጥር ተለይተው እስከነ ጊዜ ገደባቸው መቅረብ አለባቸው:: ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ ቀጣይነት ወዳለው ህዝባዊ ተቃውሞ ማሸጋገር ያስፈልጋል:: መስቀል አደባባይን እንደ ዋና ቢሮ አድርጎ በመላ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ማድረግ ወሳኝነት አለው:: ሰልፉ በመጠንና በቦታ ባደገ ቁጥር የመንግስት ጫና እየላላ ይሄዳል:: በመጨረሻም የህዝብ መብት ተከብሮ ሥልጣን ለህዝብ ይሆናል:: ከዚያም ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸውን እያጣጣሙ ሃገራቸውን እንደገና በኅብረት ይገነቧታል:: አላስፈላጊው ስደትና ስቃይ ታሪክ ሆኖ ይቀራል::
Filed in: Amharic