>

ስለደፈራ፤ ደፈር ብለን ስናወራ[ በእውቀቱ ስዩም]

ኣስገደዶ መድፈር በእንስሳት በኣሶች እንዲሁም በነፍሳት ኣለም ውስጥም ይስተዋላል፡፡ይልቁንም ለሰው እሩብ ጉዳይ በሆኑ ዝንጀሮዎች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ተፈጥሮ በደፋሪነት ያጨቻቸው ባብዛኛው ወንዶችን ቢሆንም ሞገደኛ እንስቶችም ኣልጠፉም፡፡ለምሳሌ ወንዱ ንብ ከሴቷ ጋር ሲሳረር ሴቲቱ በዚያ ነገር ቆልፋ ትይዝበታለች፡፡በጦዘ ስሜት ውስጥ ሆና ኣልመዝምዛ ትቆርጥበታለች፡፡ወይም በጅንኖች ኣባቶቻችን ኣነጋገር ትሰልበዋለች፡፡ኮርማው ንብ በጀንደረባነት የመቀጠል እድል የለውም፡፡ በደረሰበት ጥቃት ያልጋ ቁራኛ ማለቴ የቀፎ ቁራኛ ሆኖ ይሞታል፡፡ሰራተኛ ንቦች ኣስከሬኑን ከቀፎው ጠርገው ወደ ውጭ ይጥሉታል፡፡

ኣብሬሽ ኣድሬ ሲነጋ ልሙት
ላፈር ኣይደለም ወይ የተፈጠርኩት
የሚለው የሙሉቀን መለሰ ዘፈን የኮርማ ንቦችን ህይወት በደንብ ይገልጣል፡፡

ኣስገደዶ መድፈር ባገራችን ትልቅ ጣጣ ሆኖ ይቆያል፡፡ምክንያቱም ወደ ጣጣው የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች ኣሉ፡፡ ሲጀምር መናጢ ደሃ ነን። ሀብትና ስልጣኔ ባላቸው ሃገሮች የሴት ልጅን ዳሌ ላመል ያክል ነካ ካደረግህ ኣዳርህ ዘብጥያ ነው፡፡ኣገራችን ኢትዮጵያ ግን ቺስታ ናት ፡፡ያንድን ልጃገረድ መቀመጫ የሚጠብቅ የፖሊስ ግብረሃይል ማሰማራት የሚያስችል ሃቅም የላትም፡፡ሃቅም እንኳ ቢኖራት ባህሉ የላትም፡፡ የቤተመንግስቱን በር እንጂ ያንድን ሴት ገላ መጠበቅን እንደ ብሄራዊ ግዴታ የሚቆጥር ፖሊስ የለም፡፡
ባገራችን በዋናነት የሃብት ምንጭ ጉልበትና ህገወጥነት ነው፡፡ይባስ ብሎ፡ ባገሪቱ ውስጥ ያለው ሀብት ባብዛኛው በገልቱ ወንዶች እጅ ነው፡፡እኒህ ዲታ ወንዶች ድሃ ሴቶች ላይ ያሻቸውን ለማድረግ ኣቅም ኣላቸው፡፡ከሳሾችን ጸጥ የማሰኘት ጉልበት ኣላቸው፡፡የሀና ገዳዮች የተጋለጡት ወንጀላቸውን የሚሸሽጉበት ሃቅም ስለሌላቸው እንጅ እመቤት ፍትህ ፈጥኖ ደራሽ ስለሆነች ኣይደለም፡፡ተጠቅተው ያለ ኣለኝታ የቀሩትን ምኝታ ቤት ይቁጠራቸው፡፡
ሲቀጥል፤የትምርት ስርኣታችን ወንድ ኣንግስ ነው፡፡ሴት ልጅ የራሷ ነጻ ፍቃድ ያላት ፍጡር መሆኗን እያስረዳ የሚያንጽ የትምርት ስርአት የለንም፡፡ውጤቱ በእለት ተእለት ኣስተሳሰባችን ውስጥ ይታያል፡፡ብዙዎቻችን ሴቶችን” ሚስት እናት ገረድ” ከተባሉት መደቦች ባሻገር አናስባቸውም፡፡ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ሴቶች ለሚይዟቸው መኪናዎች የሚሰጡ ስሞችን ኣስታውስ፡፡ኣንዷ መኪና” በእምሴ” ትባላለች፡፡ሴት በላቧ፤ጥራ ቆጥባ እቁብ ጥላ መኪና ልትገዛ ኣትችልም ከሚል ኣስተሳሰብ የመነጨ ስያሜን ነው፡፡
ኣንድ እውንተኛ ታሪክ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡

ባገራችን መሚገኙ ከተሞች ባንዱ ውስጥ(ካርበኞች ጋር ኣላስፈላጊ ሙግት ውስጥ ላለመግባት የቦታውን ስም ዘልየዋለሁ)ኣንዲት ልጃገረድ በሰባት ጎረምሶች በፈረቃ ተደፈረች፡፡ይግረማችሁና ተኣምር በሚያሰኝ መንገድ ተረፈች፡፡ከህመሟ ኣገግማ መንቀሳቀስ ስትጀምር ግን ነዋሪዉ ኣለኝታነቱን ነፈጋት፡ኣንድ ቀን ከተማሪ ቤት ስትመለስ” ሰባት ጎራሽ” የሚል ስም ተወረወረባት፡፡ኣዲሱ ስሟ ከደፋሪዎች ይልቅ ተደፋሪዋን ባለጌ ኣድርጎ የሚያሳይ ነበር፡፡ቀስ በቀስ” ሰባት ጎራሽ” የሚለው ስም እንደ ተስቦ ተዛመተ፡፡ልጂቱ የሰባቱን ወንዶች ደፈራ መቋቋም ችላ ነበር፡፡ህብረተሰብ ተረባርቦ ሲደፍራት ግን ብርክ ያዛት፡፡ከእለታት ባንዱቀን ኣገር ለቅቃ ተሰደደች፡፡

አስገድዶ መድፈር ዋና መንስኤ የብልግና ፊልሞች መስፋፋት መሆኑን ገልጸው በፊልሞች ስርጭት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚሰብኩ ኣሉ፡፡ይህን ምክር መቀበል አለመቀበል ስለሰው ተፈጥሮ ባለን አመለካከት ላይ የተመሰረተ ይመስለኛል፡፡ ሲመስለኝ፤ሰው ምናብ የሚባል ነገር ይዞ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የብልግና ስእል ይፈጥራል፡፡የሆሊውድ ጠረን ከማይደርስበት እልም ያለ ገጠር ውስጥ ልጆች እንካስላንትያ ሲጫወቱ የሚያወጡት ብልግና እግዚኦ የሚያሰኝ ነው፡፡እኔና ኣብሮ ኣደጎቼ በልጅነታችን ሁለት ብልት ስላለው የቆሎ ተማሪ የሰማነው ተረት ከ ፕሌይ ቦይ መጽሄት የተቀዳ ኣልነበረም፡፡
በጥንታዊ የውትድርና ስርኣት ውስጥ ከመደበኛው ወታደር የተለየ፡ ሳይታዘዝ የሚዘምት የሰራዊት ዘርፍ ነበር፡፡ፋኖ ይባላል፡፡ዲሲፒሊን የማያውቅ ሀላፊነት የማይሰማው ከየት መጀመርና የት ላይ ማቆም እንዳለበት የማያውቅ ስድ ነው፡፡የሰው ኣእምሮም እንዲሁ ፋኖ ሀሳብ ያዘምታል፡፡ፋንታሲ ይሉታል ሳይኮሊጂስቶች፡፡ የብልግና ፊልሞችን ድርሰቶች የፋኖ ሀሳባችን ነጸብራቅ ናቸው፡፡ወደድንም ጠላንም ሰው የሚባለው ጣጠኛ ፍጡር እስካለ ድረስ ይኖራሉ፡፡ስለዚህ ሰዎች የሚያስቡትን ሁሉ ለማደረግ እንዳይሞክሩ ማሰልጠን እንጂ ሀሳባቸውን እንድያስወግዱ ማድረግ የሚቻል ኣይመስለኝም፡፡
ባንድ ወቅት በኣምስተርዳም ከማስረሻ ማሞ ጋር ስዞር የሰው ሰራሽ- ብልት መሸጫ ሱቅ ተመለከትሁ፡፡የመጀመርያው ስሜቴ ጉደኛው እግሬ ምን ኣይነት ቅሌታም ኣገር ላይ ጣለኝ የሚል ነበር፡፡ እየቆየሁ ሳስበው ሃሳቤን ለወጥሁ፡፡ባንድ ኣገር ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ የሩካቤ ስሜት ኣላቸው፡፡ግን ሁሉም ወንድ ሴት የመጥበስ እድል የለውም፡፡ሁሏም ሴት በወንድ ደረት ላይ የመተኛት እድል ላይገጥማት ይችላል፡፡ዋናው እስኪገኝ ድረስ ባምሳሉ ከማዝገም ውጭ ምን ኣማራጭ ኣለ፡፡የተጠሙ ሰዎች እምቢባዮችን ኣስገደደው ለመርካት እንዳይነሳሱ ማገጃ ዘዴ ይሆን?

ባገራችን ብቸኛው የስነምግባር ምንጭ ሃይማኖት ነው፡፡የእምነትን በጎ ገጽ ግለሰቦችን ለመግራት ኣስፈላጊ ነው፡፡ያም ሆኖ ለእምነት ሃይሎች ያለን የተጋነነ ኣመኔታ የማታ የማታ ዋጋ የሚያስከፍለን ይመስለኛል፡፡ለምን? ምክንያቱ ግልጥ ነው፡፡የሃይማኖት ኣባቶች የመኖራቸውን ያክል የሃይማኖት እበቶችም በየቦታው ኣሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ኣንድ ሁለት ተምሳሌቶችን ጠቅሼ ዞር ልበል፡፡

የመከራ ቀንበሩን ያቅልለትና ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ቆይታዎቹ ባንዱ ከሁለት ሽሜ እስረኞች ጋር ተገጣጥሞ ነበር፣ የመጀመርያው ስድስት ኣመት ህጻን የደፈሩ ሼህ ሲሆኑ፡ ሁለተኛው ብልታቸውን ማር በመቀባት ህጻናትን ሲያጠቡ የተገኙ መርጌታ ናቸው፡፡የመርጌታን ስልት የፈረንሳዩ ወፈፌ ማርኬስ ደ ሳድ እንኳ የደረሰበት አልመሰለኝም፡፡
ኣዲስ ጉዳይ መጽሄት ባንድ ወቅት በወንጀል ኣምዱ ኣንድ ታሪክ ኣስነብቦ ነበር፡፡ታሪኩን ኣሳጥሬ ስተርከው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ሰውየው ፓሰተር ነኝ ብሎ ካንድ ቤተሰብ ጋር ይተዋወቃል፡፡ጥቂት ሳይቆይ ከመላው ቤተሰብ መካከል ልጃገረዶቹን መርጦ ጸለየላቸው፡፡ ከዚያም ሶፍት ዌር ይመስል እጄን ካልጫንኩባችሁ ኣላቸው፡፡ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የሰራ ኣከላቱን ጫነባቸው፡፡ፖሊስ ጫኝና ኣውራጁን ፓስተር በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ከተደፈሩት ሴቶች መካከል ኣንዷ ራሷን ሰቅላ ነበር፡፡

በመጨረሻም
በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ምክር የማያለዝባቸው፣ ትምርት የማይቀይራቸው ጉዶች ይኖራሉ፡፡የተሻለው መንገድ ልጆቻችንን የኒህ ጉዶች ሙርጥ የማይደርስበት ቦታ ላይ መቀመጣቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ወላጅ የማያንቀላፋ የልጆቹ እረኛ መሆን ግዴታው ነው፡፡

Filed in: Amharic