>

በሃሰት በ''ሽብርተኝነት'' ክስ ከታሰሩት ኣንዱ - ናትናኤል መኮንን

የአንዲት ትሁት ኢትዮጵያዊት ባላቤትና የልጅ አባት ነዉ

ግርማ ካሳ

Natinael Mekonen የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ወጣት አመራር አባል ነዉ። በፓርቲዉ ዉስጥ፣ በዉጤት ላይ የተመሰረተ፣ የሰለጠነ ሰላማዊ ፖለቲካ የሚያራምደዉ፣ የአንድነት ፓርቲ አደራጅ ነዉ። በሐሰት የሽብርተኝነት ክስ ይከሰሳል። ምንም እንኳን በአገራችን የሕግ ስርዓት እንደሌለ ቢታወቅም፣ የአገዛዙን ሕገ-አራዊነትን ለማጋለጥ ሲል፣ ራሱን ለመከላከል ሞከረ። ሕግን በማመዛዘን ሳይሆን ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮ በተሰጠ የፖለቲካ መመሪያ መሰረት፣ ከሌሎች የትግል አጋሮቹ ከነአንዱዋለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ ከመሳሰሉት ጋር፣ ጥቁር ካባ በለበሱ ዳኛ ተብዬ ካድሬዎች በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ። የ18 አመታት እስራት ተበየነበት። ይህ ወጣት ናትናኤል መኮንን ይባላል።

የተከሰሰበት ችሎት ይሰማ በነበረ ወቅት፣ ናትናኤል መኮንን በፍርድ ቤት ከተናገራቸው የተወሰኑትን፣ አንባቢያን ምን ያህል የተከበረ፣ ትልቅ እና አስተዋይ መሪ ፣ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዉያን እንዳለን ይረዱ ዘንድ፣ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡

«ክቡር ፍ/ቤት፡- እኔ እንኳን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ስለመግደል ላሴርና የህዝብ ሀብት፣ የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ስለማውደም ላቅድ ቀርቶ አፈናን፣ ጭቆናንና ግፍን በሰላማዊ መንገድ ከመታገልና ከመቃወም ውጭ የገዥውን ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንኳን በጥላቻ ዓይን ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም አልመለከታቸውም፡፡ ነገር ግን በፅናት አምርሬ እታገላቸዋለሁ፡፡ አፈናቸውን እንዲያቆሙ ከቁልቁለት ጉዟቸው እንዲመለሱ፤
ክቡር ፍ/ቤት፡- ሽብር የእኔ መገለጫ አይደለም፡፡ አገዛዙ እንዳለው እኔ ባለስልጣናትን ለመግደልና የህዝብ ሀብት የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ለማውደም ያሴርኩ፣ ያቀድኩና በሽብር የተፈረጀ ድርጅት አባል ያልሆንኩና ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ሁኔታ ላይ ካለው የሻዕቢያ መንግስት ጋርም የተባበርኩ ሳልሆን በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ መስራችና የም/ቤት አባል ለአንድነት አላማዎች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት የምታገል፣ እንኳን ከሻዕቢያ ጋር ልተባበር፡- ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ሀገሬን የባህር በር ያሳጣትን ወያኔን የምታገል ለሀገር አንድነትና ክብር የምታገል፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ።

ክቡር ፍ/ቤት፡- አሁን በአገዛዙ እየተወሰዱ ያሉት የእስር እርምጃዎች ዋነኛ ምክንያት ሽብር ስለተሞከረ፣ ወይም ስለታቀደ፣ ወይም ደግሞ የሻዕቢያ ተላላኪ ስለተገኘ ሳይሆን ዜጐች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያቀርቧቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ማዳፈን ነው፡፡ እስሩ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ባለች ሀገራችን ለምን ራበን /ለምን ኑሮ ተወደደ/ ትላላችሁ ነው፡፡ ለምን የነፃነት ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእስሩ ምክንያት ለምን እኔ የምላችሁን ብቻ አትቀበሉም ነው፡፡ ለምን የለውጥ ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእሥሩ ምክንያት በአረብ አገራት የለውጥና የነፃነት ንፋስ ወደ አቶ መለስ አገዛዝም እንዳይመጣ የተወሰደ የመከላከል እርምጃ ነው።»

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፈተኞች በተባለ ጊዜ ናትናኤል ከተናገረዉ የሚከተለዉ ይገኝበታል፡

«እኔ አቶ ናትናኤል መኮንን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ቤት አባልና መስራች፣ የወረዳ 2 እና 14 ሰብሳቢ /አደራጅ/፣ በሰላማዊ ትግል የማምን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲራብ ተርቤ፣ ሲጠማ ተጠምቼ፣ ሲገረፍ ተገርፌ፣ እስሩንም መከራውንም ከህዝቤ ጋር እየተቀበልኩ ለዴሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ከሌሎች ሰላማዊ ታጋዮች ጋር በመሆን በፅናት እያካሄድኩ ያለሁ፣ ከችግሩ ባለቤት ከኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍና አጋርነት በስተቀር የማንንም ድጋፍ የማልፈልግና የማንንም ፍላጐት የማላስፈፅም፣ የሀገሬን ጥቅም በምንም ሁኔታ አሳልፌ የማልሰጥ፣ ኃላፊነት የሚሰማኝ፣ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል ነኝ፡፡ አዎ እኔ የግንቦት ሰባት አባል ሳልሆን የአቶ መለስ ረጅም አገዛዝና ጭቆና በቃኝ ያልኩ የሻዕቢያ ተላላኪ ሳልሆን ለነፃነቴ መታገል የምችል፣ ነፃነቴን እስከ ሞት ድረስ የወደድኩ ኩሩ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል እንጅ ሽብርተኛ፣ የሻዕቢያ ተላላኪና የግንቦት ሰባት አባል አይደለሁም፡፡ አያቶቼ እንዳስተማሩኝ ኢትዮጵያዊነት የርህራሔ፣ የኩራትና የነፃነት ምልክት እንጅ የጭካኔ፣ የባርነትና የውርደት ምልክት አይደለም፡፡ ስለዚህ የጭካኔ ምልክት የሆነው ሽብር ፈፃሚም አስፈፃሚም አይደለሁም፡፡ ወደፊትም አልሆንም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ከድርጅቴ ከአንድነት ጋር በመሆን በፅናት የትም፣ መቼም፣ በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እቀጥላለሁ»

ሕወሃት/ኢሃዴጎች፣ እነርሱ፣ ናትናኤልን «ሽብርተኛ» ይሉታል። እኛ ግን ይህንን አንጋፋ ጀግና ኢትዮጵያዊ “ጀግና ወንድማችን” የሚል ስያሜ ሰጥተነዋል። እነርሱ ዜጎችን ማዋረድ፣ ማሰር፣ ማሰቃየትና ማሸበር ያስደስታቸዋል። እኛ ግን ድምጻቸውን ማሰማት ለማይችሉ ፣ በግፍ ለታሰሩ፣ ለነ ናትናኤል መኮንን እንቆማለን። እነርሱ ያሸነፉ ይመስላቸዋል። ነገር ግን፣ እስረኞችን ለመፍታትና ሌሎችን ላለማሰር ባልወሰኑ ቁጥር፣ ተቀባይነታቸው እየወደቀ፣ የበለጠ ጠላቶች እያፈሩ፣ የዲፕሎማቲክም ሆነ የአገር ዉስጥ ፖለቲካ ኪሳራ እያጋጠማቸው፣ ወደ ዉድቀት እያመሩና እየተዋረዱ ያሉት፣ እነርሱ እራሳቸው መሆናቸውን እንነግራቸዋለን።

በአንጻሩ ግን፣ በአካል ከጥቂት ሜትሮች አልፈው መንቀሳቀስ ባይችሉም፣ እነ ናትናኤል መኮንን እያሸነፉ ናቸው። ፖለቲካቸው እያሸነፈ ነዉ። በነርሱ ላይ የተሰነዘረዉ ክስ መሳቂያ መሆኑ በገሃድ እየታወቀ ነዉ። በአለም አቀፍ ደረጃ የሕሊና እስረኞች በየመድረኮቹ ስማቸው እየተጠራ ነዉ። ፎቶግራፎቻቸው፣ በየሰልፉ፣ በየፌስቡኮችና ድህረ ገጾች፣ በአክብሮትና በፍቅር እየወጡ ነዉ። መልካም ተግባራቶቻቸውና አገር ወዳድነታቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናትናኤሎችን እያፈራ ነዉ።

ናትናኤል የሚለው ቃል የእብራይስጥ ቃል ነዉ። ትርጓሜዉም የእግዚአብሄር ስጦታ ማለት ነዉ። በርግጥ፣ እንደ ናትናኤል መኮንን፣ አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ፣ ርዮት አለሙ፣ ዉብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ ወገኖቻችን፣ በዘመናችን ለአገራችን ኢትዮጵያ የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው። ከግላቸዉ ጥቅም ይልቅ የአገርን እና የሕዝብን ጥቅም ያስቀደሙ፣ ለፍርሃት ያልተንበረከኩ፣ ሰላምን እና ፍቅርን የሚሰብኩ፣ ለፍትህና ለእኩልነት የቆሙ፣ የአደርባይነት የፖለቲካ ባህሪ የማይታይባቸው ጨዋ ኢትዮጵያዉያን !!!!!!!

መድሃኔ አለም እርሱ፣ በቸርነቱ ባሉበት ቦታ በረከቱን ያብዛላቸው። ቤተሰቦቻቸውን ሁሉ ይባርክ። የወህኒዉም መዝጊያ ተሰብሮ ፣ እንደ ደራርቱ ቱሉ፣ የአገራችንን ንጹህ ኮከብ የለሽ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ለብሰው፣ በክብር በአገራችን ነጻ መንገዶች የሚጓዙበትን ቀን ያፍጥንልን !
ለተቀረነው ኢትዮጵያዉያንም ከዝምታ ወጥተን ለፍትህ ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ በግፍና በጭካኔ ለታሰሩ፣ ለተገፉ የምንቆመብት፣ ከራስ ወዳድነት አልፈን ለሌሎች የምናስበት፣ ከተስፋ መቁረጥና ከፍርሃት ተላቀን የድርሻችንን ለማበርከት የምንነሳበት ጊዜ አሁን ነው።

Filed in: Amharic