>

ሃይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው) ከ 12 ዓመት በፊት ከኢትኦጵ መጽሔት ጋር ያደረጉት ቆይታ

Gemoraw 2ታላቁ ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቃኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ባለፈው እሁድ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ/ም – ኖቨምበር 9/2014 በስደት በሚኖሩባት ስዊድን – ስቶክሆልም  ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል ።የእኚህ ታላቅ ሰው የቀብር ስርዓትም በርካታዎቹን የስደት ዓመታት በኖሩባት በስዊድን እንደሚፈፀም ታውቋል። ደራሲና ባለቅኔ ሃይሉ ገብረዮሃንስ ከ 12 ዓመት በፊት በነጻው ፕሬስ ውስጥ ገናና በነበረችው ኢት ኦ ጵ መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ ኣድርገው ነበር።ያደረጉትን ቆይታ ከቀድሞው ኢት ኦ ጵ ኤዲቶሪያል ጋዜጠኛ ዳን ኤል ድርሻ ኣግኝተነዋል።እንዲያነቡት እንጋብዛለን።  

ኢት፡- በፅሁፎችዎ የስደትን አስከፊነት ደጋግመው ጠቅሰዋል፣ ሆኖም የስደትን አስከፊነት እየገለፁ እንደምን የስደተኝነትን ህይወት መረጡ?

ኃይሉ/ገሞራው፡- ከአራቱም ማዕዘናተ ዓለም በተሰበሰበ ጥያቄ፤ የኔን ጊዚያዊ ሁኔታ ለማወቅ፣ ብዙሃን ወገኖች በመጠየቃቸው፣ አንዳንድ መጣጥፍ ለምሰጣቸው መፅሔትና ጋዜጦች የተደጋገመ ጥሪ አቅርበው፤ በበኩሌ ጥሪውን ለመቀበል በተለያዩ ግላዊ ምክንያቶች አዘገይቼው ነበር፡፡ አሁን ጥያቄው ገፍቶ በመምጣቱ ተከታዩን መለስተኛ መግለጫ፤ ለጊዜው መስጠት አስፈልጎኛል፡፡ ይህም መግለጫዬ ወደፊት በክርክር ለማቀርበው “ዝክረ-ኩነቴ” እንደመንደርደሪያ ሁኖ እንዲያገለግለኝ የቀየስኩት ነው፡፡
ዛሬ ለቀረበው “ቃለ መጠይቅ” እንደመንደርደሪያ ሐሳብ እንዲሆነኝ፣ ከዚህም ከዚያም አንዳንድ ጠቃሚ አስተያየቶችን “ብልጭ ብልጭ” ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ከእነዚህ የአስተያየት ብልጭታዎች በቃለ መጠይቅ ላይ የቀረበውን ነባር ሃሳብ ለማጎልበት የተቀየዱ ናቸው፡፡…..ወዘተ
.ከሃገሬ ከወጣሁ ጀምሮ ለሩብ ምዕተ ዓመት እዚህና እዚያ ስንከራተት የኖርኩበትን ፀሊም ህይወት በማስመልከት የፃፍኳት ‹ሞቼም እኖራለሁ› የምትል ትንግርተኛ ግጥም አለችኝ፡፡ ግጥሚቱን የፃፍኳት እዚህ ያለሁበት ሃገር ውስጥ፤ ሀገሬንና ወገኔን በመታደግ የምፅፋቸውን ምግታራውያን ፅሁፎች መነሻ በማድረግ፤ ባልፈፀምኩት አንዳች ወንጀል፤ ከታላቁ የፍትህ አደባባይ ላይ የፊጥኝ አስረው አቅርበው ‹እብድ ነህ› የሚል መንግስታዊ ውሳኔ በተሰጠበት ማግስት ነው፡፡ እነሱ በሃገሬ የውስጥ ጉዳይ ባይገቡ ኖሮ ባልተነቸፉ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህይወቴ ቀልቡን እንዳጣ ይገኛል፡፡ ሁኔታዎችን ከኔ አንፃር ሳያቸው ‹ደግ አድርገዋል – ይበለኝ!› የምልበት ጊዜ አለ፡፡ ወትሮውንስ ቢሆን እንደኔ ያለ ሰው የመጣው ቢመጣ ከሃገሩ መውጣት አልነበረበትም፡፡ ይኼ ኋላ መጥ አስተያየቴ፣ ዛሬ ዛሬ ካለሁበት ኹነቴ ውስጥ፣ የደረሰብኝን ፍዳና መከራ በጥሞና ሳስታውሰው ነው፡፡ ግን እኮ ከገዛ ሃገሬም ውስጥ የነበረኝ እድል ስስ ነበርኮ፡፡ እስቲ አንዱን ለምሳሌ ይሆነኝ ዘንድ ልጥቀስ፡፡
እኔን በቅርብ የሚያውቁኝ ወገኛች ሁሉ እንደሚስታውሱት በንጉሰ ነገስት የዘውድ ግዛት ዘመን፣ ነፍሴ ለጥቂት ዳነች እንጂ (በሆነ ልዩ ተዓምር) እንደተንፈራጋጭ እምቦሳ ጥጃ በየወሩ ስታሰርና እንደእንቦሳም ስቀጠቀጥ ነበር ለምለሙን የወጣትነት ዘመን ያሳለፍኩት፡፡ ከለውጥ በኋላ የተሻለ ይመጣል ብዬ ስመኝ፣ ተከታዩ ድርጊት ተፈፀመብኝ፡፡ ከምፃፅፈው የግል ታሪካዊ ሁነቴ ውስጥ፣ አንድ ታሪከኛ ትንግርት ይኸውላችሁ፡፡
….አንድ ሳምንት ያህል ፔኪንግ እንደቆየሁ፣ ትቼው ከሄድኩበት ሃገር አንድ ትንግርተኛ በብዳቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ደረሰኝ፡፡ “….እግዜር በክንፈ ምህረቱ ከልሎ እንደሚጠብቅህም፤ ዘንድሮ በገቢር አረጋገጥኩ፤ ይኸውም ….” የሚል መነሻ ርዕስ አለው፡፡ ይኸንን ያስባለው ምን ነገር ቢገኝ ነው ብዬ ደብዳቤውን በጥሞና ማንበብ ጀመርኩ፡፡ እንዲህ ይላል “…አንተ ሃገሩን ለቀህ በሄድክ ማግስት፣ ሁለት ባለ ቋሚ ተጠሪ ጂፖችና ቁጥራቸው ከአስር በላይ የሆኑ ክላሺንኮቭ ያነገቡ ታጣቂ ወታደሮች፣ ከለሊቱ 11 ሰዓት ላይ ከቤታችን መጥተው በመውረር ‹ኃይሉን ለመውሰድ ከባለ ሥልጣን ታዘን ነው የመጣነው፤ እዚህ ከሌለ ያለበትን ንገሩን፤ ኃይሉን ካልወለዳችሁ…› እያሉ፤ ቀኑን ሙሉ ከግቢያችን የገባ እንዳይወጣ የገባውም እንዳይወጣ አግረው አግረው፣ ሲያስቸግሩ ውለው፣ ማምሻው ላይ ተመለሱ፡፡” የሚል የትንቅንቅ ሪፖርታዥ ነው፡፡ ለእኔ ድርጊቶ አልደነቀኝም፡፡ ወደ ቼይና ለመሄድ መዘጋጀቴን የሰሙ የቅርብ ጓደኞቼና ተማሪዎቼ የነበሩ የኢትዮጵያ ሹሞችና ሰራተኞች “የመሰናበቻ ፕሮግራም ማዘጋጀት አለብን፤ እንዴት እንዲሁ ዝም ብለህ ትመርሻለህ?” ይሉና፤ የአንድ ሰዓት ፕሮግራም በማዘጋጀት ረዥም ቃለመጠይቅና እንዲሁም ‹ጎጆዬ ጠላችኝ› በስዕል የታጀበች መዝማዥ ግጥም ይዘጋጃል፡፡ የሚተላለፍበትን ቀን እኔው እንድወስን ቃል አስገባኋቸውና፤ እኔ ሃገር ምድሩን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ መሆን እንዳለበት ተስማማን፡፡ ምክንያቱም የቋሚ ተጠሪው ትንግርት አሰቀድሞ ሸቶኝ ነበርና፤ በዚያም ስምምነት መሰረት፤ ዝግጅቱ እኔ በሄድኩ በማምሻው ላይ ይቀርባል፡፡ እነዚያ የአንድ ወቅት ከዋክብቶቻችን ፀጉራቸው ይቆምና ሲነጋጋ ሰራዊታቸውን ይልካሉ፡፡ ያ የጦዘበት አዝማሪም (ይርጋ ድባለ) “የፍየል ወጠጤውን” ለማንባረቅ አቆብቁቦ እንዳለ፤ ኃይሉ የለምና ኩም ብሎ አፉን እንደከፈተ ቀረ፡፡ “ነፍሰ ዝንብ” የሆነው የደርግ መጋዣ መንጋም እንደለመደው “ለምሳ ያሰባቸውን ለቁርስ ያደረገው” እኔንም ባልበላ አንጀቴ ስሰቃይ የኖርኩት አንሶኝ፤ ለማታ እራቱ ሊያደርገኝ አስቦ ሲሰናዳ በለስ ቀንቶኝ ሃገር ምድሩን ለቅቄ መሄዴ ሲነገረው እርር ኩምትር አለ፡፡ በዚያን ዕለት አረጋዊ አባቴን እየጨቀጨቁ “ልጅዎን ይውለዱ” ሲሏቸው “ትናንት ሄዶ፤ በምድርና በየብስ ሳይሆን፣ በሰማይ ላይ ደመና ሰነጣጥቆ፣ እንደቅዱሳኖች እንደነ እዝራና እንደነኤልያስ! …..እናንተው አይደላችሁም እንዴ የፈቀዳችሁለት? እዚህ ያለነው እኛ ነን፤ እኛን እንደብጤታችሁ ማድረግ ትችላላችሁ፤ ሌላም መሄጃ የለንም፤ እሱ ግን ሲሰቃይ ኖሮ ዘንድሮ አዶናይ ረድቶት እጁን አውጥቷል፤ አዶኒስ ይቀደስ!….” እያሉ ሲያበግኑአቸው ዋሉ አሉ ወታደሮቹን፡፡ ድርጊታዊ ትንግርቱ አንድ ቀን ሙሉ ሲያስቀኝ ዋለ፡፡ አዎ እያንዳንዱ ሰው በዕለተ ልደቱ ቁጥር መጠን፣ ትንንሸ ሞት አሉበት ይባላል፡፡ እኔም በ16ቱ የልደት ቀኔ መጠን፣ የዚያን ቀኑ ትንሽ ሞቴ 7ኛው መሆኑን አስባለሁ፡፡ እዚያ ቻይና እያለሁም በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከምኖርበት 4ኛ ፎቅ ስዘል፣ 8ኛ ሞቴ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እዚሁ ስዊድን ደግሞ፣ ያለወንጀሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤታቸው አቅርበው “እብድ ነው” ብለው ሲፈርዱብኝ 9ኛው ትንሹ ሞቴን መሆኑን ቆጥሬአለሁ፡፡ የሚቀሩኝን ትንንሽ ሞቴን እናንተው ልታሰሏቸው ትችላላችሁ፡፡…… ቂቂቂቂቂ (ሳቄ መሆኑ ነው)

ኢት፡- በነጮች ሃገር እየኖሩም ዛሬም ለነጮች ያለዎትን ጥላቻ ሲገልፁ ይታያሉ፡፡ ይህ ባዕዳንን ማለትም ነጮችን የመጥላቱ ጉዳይ እንዴት ተከሰተ? ወይንም እንደምን “ለከፈዎት”?
ኃይሉ/ገሞራው፡- “ገነተ ምድር” የተባላት ሃገረ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ባደላት ልዩ ውበቷና ማህፀኗ አርግዞት ባለው የተፈጥሮ ሃብቷ፣ ከባህር ማዶ የመጣ ጋኔልም በሉት ጭራቅ አልያም ጋንጩራ ተነድፋ፤ “ቡዳ በልቷታል” እንደሚባለው ብሂል፤ ተነድፋና ተነጅሻ ስትማቅቅ ወደ አራት ምዕተ ዓመታት ሆኗታል፡፡ ያንን ደባና ግፍ በዓይኖቹ እያየ አስችሎት ዝም የሚል ቢኖር፣ የታመመ ደዌኛ አሊያም ጅላጅል መሆን አለበት፡፡ በተለይም፤ ከማሕፀኗ ተፈልቅቀው የወጡ በምንም ተፅዕኖ ቢሆን ማረመም አይኖርባቸውም፡፡ ከ400 ዓመታት የትግል ሙከራ በኋላ የነጭሌው ያላቋረጠ ትግል፣ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሊያገለግሉት የሚችሉ የውስጥ በቀል (ውሻ) ከሃዲያን ባንዳዎች በማገኘቱ፣ ሲያደባ የኖረበት ዕቀዱ ተሳክቶለት፣ ዛሬ በነዚሁ ወኪሎቹ አማካኝነት በፕሮክሲ (በቀላጤ) በሉት በዲፋክቶ (በምሳሌ) እናት ሃገራችንን እየገዛና እየመጠመጠ ነው፡፡ እኔ ይህ ብሄራዊ ደባ፤ ገና በወጣትነት ዘመኔ አደገኝነቱ ታውቆኝ ስለነበረ፤ እተወለድኩበት መንደሬ ግንባር ላይ የአፍሪካ አዳራሽ ከተመሰረተ ጀምሮ፣ ያፍሪቃ መሪዎች ለስብሰባ በመጡ ቁጥር በፓምፍሌት መልክ ግጥሞችና ቅኔዎች አበረክት ነበር፡፡ የግጥሞቼም መልዕክት “ከጭራቆቹ ሃገር አስፋፊ ጃውሳዎችና” (Gaint Imperialist) ከጆፌዎቹ ቀኝ ግዛት አስፋፊዎች (colonial voltures) ተጠንቀቁ፤ እናት ሃገራችሁን አፍሪቃን ጠብቋት የሚል ነበር፡፡ እኔም ነጭሌው የለከፈኝ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በስተመሃሉም ላይ፤ በአማርኛ ግጥሞቼ ውስጥ ተልዕኮዬን ይፋ አድርጌ፡-
“…… ባንድ አንሆንም ብለው አንድነት እንዲያጡ፣
አንዳንድ ወስላቶችን፣ በጎሳ ወረንጦ ስታቆናጥጡ፣
ከሾህ ህሊና ላይ፣ የጠመቃችሁት፣ ጥንስሳችሁ ፈልቶ – በኃይል ሲቆመጥጥ፣
ዝቃጨ አተላ፣ ገምቶ ሲከረፋ – ያ የእናንተው ብጥብጥ፣
ትግል ቅጥ እንዲያጣ – ተውሳክ የሆናችሁ፣
ኢምፔሪያሊስቶች- ደቂቀ ቹቹሊ ፋሽስቶች ሁላችሁ!
የኑክለር ነፋሪት፣ አንድዶ አቃጥሎ – ቀቅሎ ይፍጃችሁ!!!”
(በረከተ መርገም ገጽ 62 – 1957)
በአደባባይ በማውገዜ፣ የውጭም የውስጥም የኢትዮጵያ ጠላቶች እስከዚች ጊዜ ድረስ እንደወቀጡኝና እንደቀጠቀጡኝ አሉ፡፡ የቻይና ትምህርቴን ጨርሼ፣ በሶቪየት ኃይል ቁጥጥር ስር ወደ ነበረችዋ ሃገሬ (በዚያን ወቅት) ለመመለስ እንደማልችል ገልጬ፣ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ጥገኝነት ብጠይቅ፣ የተሰጠኝ መልስ “እኛን ከሃገርህ ለማስወጣት በግንባር ስትቃወም ኖረህ፤ዛሬ ከኛ ሃገር ጥገኝነት ትጠይቃለህ?” የሚል ነበር፡፡ እዚህ አለሁበት ሃገር ጭምር ባልፈፀምኩት ወንጀል ከፍትህ አደባባይ አቅርበው “እብዱ ነህ” የሚል ውሣኔ በመስጠት ሕይወቴ መቅኖ እንዲያጣ የተደረገው ዋና መንስዔአዊው ሰበብ፣ ያው ዱሮ የተለከፍኩበት የሃገሬ ጉዳይ ነው፡፡ ወዘተ
የእርግማን ውርጅብኝ ሰለባም የሆንኩ የሚመሰለኝ ጊዜ አለ፡፡ ሃገራችን በአሁኑ ጊዜ ታጋይ ልጆች ሳታጣ፣ በየስርቻውና በየጓዳው ተልፈስፍሰውና ተሽመድምደው የቀሩት የቀደሙት አባቶች ባወረዱብን የእርግማን ዶፍ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ከባለ 3.000.000 ውስጥ የወጡ የዘረኞች ደባና ተንኮል፤ የቀረውን 57.000.000 ብዙሃን ኢትዮጵያውያን ሕዝብ ላለፉት አስር አመታት ሊነዳው ባልቻለ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት አቅርቤው የነበረውን መጣጥፍ አንድ አንቀፅ እጠቅሳለሁ፡፡ (እኔ የነበርኩበት የነጋሲ ዘርፍ፤ በስተመጨረሻ እድሜያቸው ላይ ረግመው ነበርና ይመለከተኛልና ነው)
“…..አበው እንደጡኝ ምላሽ ከሆነ ‹የማይፋቅ መርገምት አለብን› የሚል ነው፡፡ የወረደብንን መርገምት ምንነት ሲያብራሩ፣ ከትናንትናው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ምዕራፍ ዘመን ላይ ይጀምራሉ፡፡ ከነገሥታቱ የአፄ ቴዎድሮስ እርግማን፣ የአፀ ዮሐንስ፣ የነ አፅ ሚኒልክ፣ የነአጼ ኃይለሥላሴ፤ ከሕዝባውያኑ ደግሞ የነ አቡነ ጴጥሮስ፣ የነበላይ ዘለቀ፣ የነ መንግስቱ ንዋይ …ይጠቀሳሉ፡፡ ቴዎድሮስ ሃገር አንድ ላድርግ ብሎ ቢነሳ ካህናት ሳይቀሩ በመስዋዕት ውስጥ የእባብ ጭንቅላት አድርገው ሊገድሉት እንደሞከሩና፣ በተለይ ለመንገስ ሲሉ፣ የራሱ ሃገር ሰው የሆኑትን አፄ ዮሐንስ፣ የጠላት ጦር (እንግሊዞችን) መቀደላ ድረስ እየመሩ አምጥተው ሊያስገድሏቸው ሲዘጋጁ በማወቃቸው “ይቺን የኢትዮጵያ ኩሩ ነፍስ የውጭ ጠላት አይገድላትም” ብለው ራሳቸውን በሽጉጣቸው ሊገድሉ ሲሉ “ኢትዮጵያን ወንድ አይብቀልብሽ1 ብለው ረግመዋታል፡፡ ቀጥሎም ኢትዮጵያን ከተንባላት ወረራ ለማዳን ከደርቡሽ ጋር አፄ ዮሃንስ በተፋጠጡ ጊዜ፣ የሸዋው አፄ ዮሐንስና የጎጃሙ ንጉስ ተክለኃይማኖት ለእርዳታ እንዲደርሱላቸው ጠይቀው ባለመምጣታቸው ከጦርነቱ አውድ ገብተው አንገታቸው ተቆርጦ ከመሞቱ በፊት “ኢትዮጵያ ዘር አይብቀልብሽ” ብለው ረግመዋል፡፡ ከዚያም አፄ ሚኒሊክ እንደልጃቸው ያዩት የነበረውን የልጅ ልጃቸውን አቤቶ ኢያሱን ለማንገስ ፈልገው “ልጄን ተቃውሞ ለዙፋኔ የማያበቃ ቢኖር ጥቁር ውሻ ይውለድ” ብለው በመረገማቸው፣ ያው እንዳየነው ንጉስ ተፈሪ ኢያሱን ገድለው ዙፋኑን ቢወርሱ፣ያን ፋደት የደርግ ጥቁር ውሻ ወልደው አንድ ንፁህ ትውልድ አስበሉ፡፡ ራሳዋው ንጉስ ኃይለሥላሴም በተራቸው ከሞቀ ዙፋናቸው ወርደው 4ኛ ክፍለጦር ታስረው ሳሉ፣ ምግብ ተመግበው ከጨረሱ በኋላ እጃዠውን ታጥበው ከጨረሱ በኋላ፣ ፎጣ ለማድረቂያ ሲሰጣቸው እምቢ ብለው ጣቶቻቸውን ወደታች አድርገው የታጠቡበትን ውሃ እያንጠባጠቡ “ይኼን አስተምሬው የከዳኝን ትውልድ ደሙን እንዲህ አንጠባጥብልኝ” እያሉ መርገማቸውን ያየ የሰፈሬ ሰው በደብዳቤ ገልጾልኛል፡፡ እንዲሁም አባት ጴጥሮስ “ለጠላት ጣሊያን የሚገዛ ውጉዝ ይሁን፤ መሬቲቱም እሾህ አሜዜላ ታብቅል” ብለው ሊረሸኑ አቅራቢያ ረግመዋል፡፡ በላይ ዘለቀም መሰቀያው አጠገብ እንዳለ “አንቺ ሃገር ወንድ አይውጣብሽ” ብሎ ተራግሟል፡፡ ጄኔራል መንግስቱም ከተሰቀለበት የተክለኃይማኖት አደባባይ ላይ ሕዝብ እየሰማው “አንቺ ሃገር …” ብሎ በማማረር ተራግሞ አልፏል፡፡ ወዘተ
እንግዲህ እኛ የዛሬዎቹ፤ ይህ ሁሉ የግፍና የደይን፣ የፍዳና የመከራ፣ የመቅሰፍትና የመአት ማዕበል ናዳ የሚወርድብን፣ ያን ሁሉ እርግማን ቆጥሮብን ይሆን? እንዲህ በኤይድስ (በሚሊዮን)፣ በረሃብ (8 ሚሊዮን)፣ በጦርነት (በሚሊዮን)፣ በስደት (በ3 ሚሊዮን) ….በአጠቃላይ አብዛኛው ሕዝባችን በጨለማ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ገብቶ የሚጨማለቀው? የሃገራችንም ምድር የድርቅ መጋኛ ተጠናውቷት እንዲህ የስቃይ አፈጠቋን የምትበላው ….በዚህ አይነት መርገምቶች የተነሳ የምንከፍለው ዕዳ ሆኖብን ነውን? እንደ ደርግ እና ባንዳ ወያኔ ያለውንስ ነፍሰ በላ ጭራቅ ጥሎብን ስንሰቃይ የኖርነውና ያለነው በዚህ ፍዳችን ይሆን? ይህንን ጥያቄ ሁላተንም በማሕበር የምንመልሰው ይሆናል፡፡….”
ኢት፡- ወደ ፖለቲካው ትግልና ወደ አመፅ እንቅስቃሴ መቼና እንዴት ሊሳቡ ቻሉ?
ኃይሉ/ገሞራው፡- “ምስጢረ አመፅ” ምንድር ነው? በተፍፃሜተ ዘመነ ነገስት ወቅት፣ እኔ የተሰለፍኩበት የብዕር ትግል እጅግ ጎልብቶ ነበር፡፡ የእኔም ብዕር እንዲህ ከመዳከሙ በፊት ብልት እየመረጠ ይጠዘጥዝ ነበር፡፡ ከታህሳሱ መፈንቅለ መንግስት ሳኒታ ላይ ‹ሲኦል› የምትል ግጥም በዩኒቨርስቲው መድረክ ላይ ይዤ ብቅ ብል ‹ገነቲቱን ሃገረ ኢትዮጵያ ሲኦል አላት› ብለው ጅራፍ አለንጋቸውን ይዘው መግረፍ ጀመሩ፡፡ ከዩኒቨርስቲም አባረሩኝ፡፡ ያለትምህርት ያለስራ ብዙ ወራት አሳለፍኩ፡፡ ከዛ እንደገና ወደዩኒቨርስቲ ስመለስ ይግረማችሁ ብዬ ‹በረከተ መርገም›ን ይዤ ቀረብኩ፡፡ አበዱ፡፡ የህቡዕ ወረቀት ሳሰራጭ በማውቃቸው ሰዎች ጠቋሚነት ተይዤ ተቀጠቀጥኩ፡፡ በሃገሪቱ ሚዲያ ‹መርዘኛው ብዕረኛ› Poison Pen Writer የሚል አዋጅ ታወጀብኝ፡፡ ቤተ “ወፌ ይላላም ሰቀላ በመግረፍ የተግባር ግዳጇን ተወጣች፡፡ ያ ሁሉ የብዕር አመፅ የፈጠረው ዋጋ ነበር፡፡ ……

 ኢትዮ ሪፈረንስ :- ለኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን፣ ለኣንጋፋውም ገነትን ያወርስልን ዘንድ እንመኛለን።  

Filed in: Amharic