>

ኢትዮጵያውያን በኦስሎ ድንቅ ምሽት ኣሳለፉ

Oslo Sep. 13Bewketu Siyum
በኪነ-ጥበብና በስነ ጥበብ ስራዎችዋ ተደናቂና ተወዳጅ የሆነችው ዓለም ጸሃይ ወዳጆ (ከኣሜሪካ)፣ በስነ ጽሁፍና የግጥም ስራዎቹ ”ጠቢቡና- ፈላስፋው”የተባለው በዕውቀቱ ስዩምና ተዋንያን ሃረገወይን ኣሰፋ (ከኣዲስ ኣበባ) እንዲሁም የኢሳት ጋዜጠኛና ተዋንያን ገሊላ መኮንን (ከኔዘርላንድ) ያሬድ የሙዚቃና የቲያትር ባንድ በኣጃቢነት (ከኦስሎ) የተገኙበት ድንቅ ምሽት በኦስሎ  ተካሂዶኣል።
Alemtsehay Wedajo in OsloHaregewoyn Asefaይህን ዝግጅት በኦስሎ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ያዘጋጀው በመሆኑ የዚህን ውብ ትዕይንት መክፈቻ የኮሚኒቲው ሊቀመንበር እንግዶቹንና ታዳሚዎቹን ”እንኩዋን ደህና መጣችሁ” በማለት የጀመሩ ሲሆን፣ በመቀጠልም በዕውቀቱ ስዩም ”ኢትዮጵያዊ ነኝ!” በተሰኘው ውብ ግጥሙ በመጀመር የተለያዩ  ኣዝናኝ፣ ኣስተማሪና ውብ ግጥሞቹንና  ኣጫጭር ጥዑም ብዕሮቹን  በኣዳራሹ ለተገኙት ተመልካቾች በማቅረብ  ታዳሚዎችን ኣስደስቶኣል።
 ኣንጋፋዋ የጥበብ ሰው ዓለም ጸሃይ ወዳጆ  ደጎስ ካለው የግጥም መድብሉዋ ”እምቢኝ ደጉ!”  የግጥም ስራዋን በመጀመር የተለያዩ ኣጫጭር ተውኔቶችንና ግጥሞችን ያቀረበች ሲሆን ”ጣይቱ” የተሰኘው ኣጭር ድራማዋ  የተመልካቹን ቀልብ የሳበና  የኣርቲስቱዋንም የጥበብ ክህሎት ያሳየ እንደነበር በስፍራው የነበረው የኢትዮ ሪፈረንስ ዘጋቢያችን  ገልጾልናል።
ይህ በያሬድ ሙዚቃ ባንድ እየታጀበ በኣርቲስት እንዳለ ጌትነት የመድረክ መሪነት ለኣራት ሰዓታት የዘለቀው ፕሮግራም  መነባንቦች፣ ግጥሞችና ጭውውቶች የቀረቡበት ሲሆን በነዚሁ ኣንጋፋ ድንቅ የጥበብ ሰዎች የቀረበው ዝግጅት በኣዳራሹ የተገኘውን የኦስሎ ነዋሪ ያዝናናና ያስደሰተ ነበር።
ዝግጅቱ ከመጠናቀቁ  በፊት የሽልማት ስነርዓትና የምስጋና መልዕከቶች የቀረቡበት ሲሆን  በዚሁም መሰረት የኦስሎ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲና በኦስሎ የሰላም የሴቶች ማህበር ለእንግዶቹ የጥበብ ሰዎች ማለትም በዕውቀቱ ስዩም፣ ዓለም ጸሃይ ወዳጆ፣ ገሊላ መኮንንና ሃረገወይን ኣሰፋ ስጦታዎችን ኣበርክተዋል።
በተለይም በኣንጋፋነቱዋና በጥበብ ስራዎችዋ ኣንቱ ለተሰኘችዋ የጥበብ ሰው ዓለም ጸሃይ ወዳጆ የኦስሎ ሰላም የሴቶች ማህበርና  የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ  ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በእቅፍ ኣበባ የገለጹላት  ሲሆን ኣርቲስቱዋም ልባዊ ምስጋናዋን  ኣቅርባለች።
Filed in: Amharic