>

ይድረስ ለአዲስ አበባ ልጆች በያላችሁበት፤ በተለይም ለካዛንችስና አራት ኪሎ ዙርያ አራዶች!! [ከእንግዳ ታደሰ]

የአዱ ገነት ልጆች ድሮ ተበልጠው ሲገኙ ፣ ”አራዳ ሁላ ወረዳ ሆነ” ይሉ ነበር ሲተርቱ ፡፡ የአራዳነት ብኩርናችሁን የህወሃት ሰዎች የሆኑት እነ ባህታዊው ተስፋ ማርያም ፥ ሞንጆሪኖና ፥ ፍስሃ መአሲ በቀላሉ ከተረከቧችሁ በኋላ ካዛንችስ ላይና አራት ኪሎ ላይ ምኩራባቸውን ገንብተው እናንት ያሰለጠናችኋትን ከተማ እነርሱ ደግሞ አሳለጡባት አሉ ፡፡

ብዙዎች ምነው እንዲህ በቀላሉ የመዲናይቷን የወርቅ ቁልፍ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ለሚለጥጡት ወሮ- በላዎች አስረከቧት እያሉም ያሟችኋል ፡፡ ድሮ ‘ወሮበላ’ ሲባል ትርጉሙ ግር ያሰኝ ነበር ፡፡ ለካስ ወሮ- መብላት ማለት ነው ፡፡

የጥንት አራዶቹ እነ-ኢዳውንና ሁጄን ቃላት በዘመነ ግሎባላይዜሽን ሳትለውጡ፣ አሜሪካን ፥ አውሮፓ እንዲሁም አውስትራሊያ በስደት ተበትናችሁ በቁጭት ስትብሰለሰሉ የአሁኑ ጊዜ አራዶች ደግሞ ወሬው የ”ጀለሲዎች” ነው ከተማይቱን በአነስተኛና ጥቃቅን ባለቤትነት አደራጅተናትና ፥ተረክበናት የብላኔ እየመራናት ነው ይሏችኋል ፡፡ መሬቱን ገለባ ያድርግለትና ያ!…የአዋሬው ጃርሶ ይህን ቢሰማ ኖሮ ሁሌ እንደሚለው ”የተናቀ ከተማ በሃሬ ይወረራል” ይል ነበር፡፡ ቤተ መንግሥቱን ሽቅብ እያየ !!

ኧረ ለመሆኑ ! ያ የአራት ኪሎው ጋንጊስተር ቡድን መሪ አቡጃ በአፀደ ሥጋ ይኖር ይሆን ? ግርም የሚለው ናይጄርያኖች የመዲናቸውን መጠርያ ስም ከአቡጃ ላይ ነጥቀው መውሰዳቸው ነው የጥንቶቹን አራዶች የሚያበግናቸው፡፡ የአራዳ ልጆች ምን ያልተነጠቃችሁት ነገር አለ ? እንኳን የናይጄርያ ማፍያ እነ ፍስሃ መአሲ ፋራው ውቧን አዲስ አበባ ሸልቅቀዋችሁ የለ? ሲኒማ አድዋ ያያችሁት የነቦናንዛ ፊልም እና የነ- ጄምስ ቦንድ ፊልም ለካስ ፊልም ቤቱ ሲፈርስ አብሮ ከናንተም ልብ ውስጥ ፈርሷል ፡፡

መቸም ያቺ የጄምስ ቦንድ ቀበቶ ወገባችሁ ላይ ሸብ የምታረጓት አትረሳችሁም ፡፡ 007 የምትለው ፡፡ በሽጉጥ ቅርጽ ነበር እኮ የቁጥሯ አጻጻፍ ፡፡ የጥንት አራዳ ሽጉጥ መታጠቅም ይችላላ ተብሎ ማሳያም ጭምር ነበር ያኔ! ታን …ታራራም- ታራራም….በራስ መኮንን ድልድይ ፒያሳ ዙርያ መሸለል ፡፡

ትዝ ይላችኋል? አራት ኪሎዎችና የምንሊክ ት/ቤት አራዶች « ሰይፉ ጢቦን» ፥ የቀበና ልጆችና የኮከበ ጽባህ ተማሪዎች ደግሞ « ሰገደን » አጅበው ፣ የትግል መሻኮቻ ቦሩ ሜዳን መርጠው ሲያቧቅሱ ! ያኔ የአካል ጥንካሬንና ጅዶን ለማየት ነበር ያ ሁሉ ቡቀሳ ፡፡ የዛሬዎቹንማ አራዶች ነን ባዮች እነ ሞንጆሪኖና ባህታዊ ተስፋ ማርያም በፕላዝማ ቲቪ ፣ በባርሴና ማንቼ ቅሪላ አደንዝዘዋቸው እርስ በራስ ያቧቅሷቸዋል አሉ ! እነርሱ ሲተላለቁ እነርሱ ደግሞ በአዱ ገነት ላይ ለ50 ቀጣይ አመት ሊገዙ ፡፡ በነሞር ዳፋ ቸሃ ተደፋ ድሮ እንደምትሉት ማለት ነው ፡፡

የሰሞዖን ልጅ በረከትና አባይ ጸህዬም ምትሃተ ደደቢትን ደግመውባቸው ፣ እግራና እጃችውን ቄጤማ አፋችውን ቆልማማ ስላደረጉ ፣ የልደታውን ጮሌ አራዳ – ሰበታ ፣ የቦሌውን ጆሊ – ሱሉልታ ፣ የአራት ኪሎውን- ቆሬ ፥ የንፋስ ስልኩን- አዋሬ ፣ የካዛችንሱን- ካራ ፣ የኳስ ሜዳውን – ቶራ ቦራ ፣ የጉለሌውን – እንጦጦ እምቢኝ አሻፈረኝ ያለውን ቂሊንጦ በትነዋችው እነሆ አዲስ አበባ ባለቤት የሌላት ከተማና የአራዶች ዲማንድና ሰፕላይ ያልተመጣጠነባት ከተማ እንደሆነች የመለስ ትሩፋቶች መጽሃፍ ደራሲ ሚንስቴር ዴ’ኤታ ኤርምያስ ለገሰ የጻፈውን መጽሃፍ ካነበባችሁ መቸም እጅጉን ሳትቆጩ አትቀሩም ፡፡

በያ’ ሰሞን አንድ ሶሻል ሚዲያ ላይ የወጣውን የጠቅላዩን መቃብር ፎቶ አይታችሁታል ? የሚያሳዝነው በሙታን መንደር ሌትና ቀን መቃብሩን የሚጠብቁት ጭቁን ወታደሮች ናቸው ፡፡ እናንት የጥንት አራዶች ባሰለጠናችኋት ከተማ የብላኔ መቃብር የሚጠብቁትን ወታደሮች ወይ በድብ ቁማር ወይ በበጨና ጠቆረ ዳርት ውርወራ አፍዝዛችሁ ያን የብላኔ መቃብር እውን ጠቅላያችን እውስጡ እንዳሉና እንደሌሉን ታሳዩን ነበር ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአራት ኪሎው አቡጃ በህይወት ቢኖር ኖሮ ፣ እነኝህ ሁለት ጭቁን ወታደሮች እንዲህ በብርድና በቁር አይንገላቱም ነበር ፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ መነሳት በኩል በአይሁዶችና ክርስቲያኖች መካከል የተነሳውን  እሰጥ አገባ ፣ ዘመን ቢገዝፍም አትረሱትም ፡፡ ከረሳችሁት እንዲህ ነበር ፡፡

MelesChristian: ‘The Lord is risen!’
Jew: ‘No, his disciples stole away his body.’
Christian:‘The guard at the tomb would have prevented any such theft.’
Jew: ‘No, his disciples stole away his body while the guard slept.’
Christian: ‘The chief priests bribed the guard to say this.’

ነገ ልክ እንደ ዩህዶቹና ክርስቲያኖቹ ክርክር የጠቅላዩ የብላኔ መቃብር ሲከፈት… ጠቅላዩ ከውስጡ ቢጠፉ ፣ ህወሃቶችና ብአዴኖች እንዲህ መተራመሳቸው አይቀርም ፡፡

ህወሃቶች መለስ አርጓል ሲሉ ፣

ብአዴኖች ደግሞ የለም ህወሃቶች መቃብሩን ገልብጠው ወስደውታል ይላሉ ፡፡

ክርክሩ ሰፍቶ ህወሃቶች የለም የትግራይ ልጆች የሆኑት መቃብር ጠባቂዎች ማንኛውንም የሬሳ ሰረቃ ሙከራ የማክሸፍ ብቃት አላቸው ሲሉ ፣

ብእዲኖቹ ደግሞ የለም ጠባቂዎቻችሁ እንቅልፍ በተጫናቸው ወቅት ህወሃቶች መቃብር ገልብጠው ወስደዋል ቢሏቸው…እጅ ላለመስጠት የሚታገሉት ህወሃቶች….የለም የትምክህተኞች አለቆች ዘቦችን በጉቦ በመደለል እንዲህ እንዲናገሩ ደልለው ነው አይነት እሰጥ አገባ አይነት የብላኔ መቃብሩ ወደፊት ጠቅላዩን እንዳልያዘ ሲነገር የምንሰማው ነገር ይሆናል ፡፡ ለማንኛውም በአጸደ ስጋ ያላችሁ የአዲስ አበባ አራዶች አትጠፋፉ…. ምከሩ ፡፡

Filed in: Amharic