(ኢ.ኤም.ኤፍ) በቅርቡ በአምስት ነጻ ፕሬሶች ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር በተያያዘ እስካሁን አስራ አንድ ጋዜጠኞች ለስደት መብቃታቸው ታወቀ። አቃቤ ህጉ በአዲስ ጉዳይ፣ ሎሚ፣ ጃኖ፣ አፍሮ ታይምስ እና እንቁ አዘጋጆች ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው። ጋዜጠኞችን በመክሰስ እና በማሰር በአሸባሪነት ሽፋን እስከ አስራ ስድስት አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት መፍረድን በነእስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርእዮት አለሙ ላይ የታየ እውነት ነው። አሁንም ሌሎች ጋዜጦች ላይ የሚደረገው ጫና እየበረታ እንጂ እየቀነሰ ባለመሄዱ ነው እነዚህ ጋዜጠኞች አገር ለቀው ለመሰደድ የበቁት።
እስካሁን ስማቸው የደረሰን ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው። 1-እንዳልካቸው ተስፋዬ (የአዲስ ጉዳይ መጽሄት አሳታሚ) 2-ኢብራሂም ሻፊ (የአዲስ ጉዳይ ምክትል ዋና አዘጋጅ) 3-እንዳለ ተሼ (የአዲስ ጉዳይ ከፍተኛ አዘጋጅ) 4-ሃብታሙ ስዩም (የአዲስ ጉዳይ አዘጋጅና አምደኛ) 5-ቶማስ አያሌው (የአፍሮ ታይምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 6-አስናቀ ልባዊ (የጃኖ መጽሄት አሳታሚ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 7-ግዛው ታዬ (የሎሚ መጽሄት አሳታሚ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 8-ዳንኤል ድርሻ (የሎሚ መጽሄት ሚዲያ ዳይሬክተር) 9 ሰናይ አባተ ቸርነት (የሎሚ መጽሄት ዋና አዘጋጅ) 10-አቦነሽ አበራ (የሎሚ መጽሄት ከፍተኛ ሪፖርተር) 11-ሰብለወንጌል መከተ (የሎሚ መጽሄት ከፍተኛ ሪፖርተር ናቸው) ከአምስቱ ተከሳሽ ጋዜጠኞች መካከል እስከአሁን ያልተሰደዱት የእንቁ መጽሄት አዘጋጆች ሲሆኑ፤ የመጽሄቱ አሳታሚ አለማየሁ ማህተመወርቅ አሁንም አገር ቤት ነው።
ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ከመንግስት በተላኩ ኃይሎች የ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ቢሮ ‹‹ያለ ንግድ ፍቃድ›› በሚል ሠበብ ታሸገ፡፡ እነዚህ ከየትኛው ወገን እንደተላኩ ያልታወቁት ኃይሎች በቢሮ ውስጥ የነበሩትን የሂሳብ ሠነዶች ‹‹ይዘን እንሄዳለን፣ አትሄዱም›› በሚል በተፈጠረው እሰጥ አገባ ምክንያት ስልክ ደውለው ቁጥራቸው ከ20 ያላነሱ የታጠቁ የፌደራል ኃይሎችን በመጥራት እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶችና ወረቀቶችን ጨምሮ እንዳናወጣ በመከልከልና በማስፈራራት አስቀድመው ታዘው ይዘውት የመጡት ወረቀት “ያልታደሰ ንግድ ፍቃድ” የሚል ቢሆንም፣ ንግድ ፍቃዱ የታደሰበትን ማረጋገጫ ሲመለከቱ ደግሞ ፊት ለፊታችን ወረቀቱን በመሠረዝ “ያለ ንግድ ፍቃድ” በሚል ጽፈው አሽገውታል፡፡ በወቅቱ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ለንባብ የምትበቃው ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ወደ ማተሚያ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳለች ይህ ችግር መፈጠሩ በሎሚ አባላቶች ላይ ግርታ ቢፈጥርም፣ በተወሰደው ሕገ-ወጥ እርምጃ ሳንደናገጥ ማተሚያ ቤት ከምንገባበት አንድ ቀን ዘግይተንም ቢሆን በተከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ማተሚያ ቤት ልናስገባ ችለናል፡፡ በወቅቱም ቢሮአችን እንደሚታሸግ ለምን አስቀድማችሁ በደብዳቤም ሆነ በስልክ አላሳወቃችሁንም ቢባሉም ‹‹የእናንተ ስፔሻል ኬዝ ነው፤ እኛ ከላይ ታዘን ነው›› የሚል ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ …እነዚሁ ኃይሎች ከመጀመሪያው ቀን በተለየ ሁኔታ በበነጋታው ተደራጅተው በመምጣት “ሠነዶችን እንፈልጋለን” በሚል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፌደራል ኃይሎች የታገዘ የ5 ሠዓታት ፍተሻ (ከብርበራ አይተናነስም) ካካሄዱ በኋላ በቢሮ ውስጥ የሚገኙትን የሂሳብ ሠነዶች በሙሉ ሰብስበው ወስደዋል፡፡ ሆኖም ግን የምንፈልገው የሂሳብ ሠነዶችን ይበሉ እንጂ፣ በቢሮው ውስጥ የሚገኙትን በተለያዩ ጊዜ የታተሙ የሎሚ መጽሔቶች፣ የአፍሮ ታይምስ ጋዜጦችና በእጅ ጽሁፍ የተተየቡ ወረቀቶችን አንድ በአንድ ሲፈትሹ ተስተውሏል፡፡ ይህ ከላይ የገለጽነው ተግባር የተፈጸመው ክስ ከመመሰረቱ አንድ ወር በፊት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሎሚ፣ ጃኖ እና አፍሮ ታይምስ ጋዜጦችን ደጋግመው ሲኮንኑ እና ሲያጣጥሉ እንደነበር ይታወሳል። አሁን የተደረገውም ክስ እስካሁን ሲደረግ የነበረው ክትትል እና የአፈና ውጤት ነው።