>
5:13 pm - Monday April 18, 2783

ኢሳት:- አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ደብረዘይት አየር ሃይል ግቢ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው

ሐምሌ ፲፰ (አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግንቦት7 ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሰኔ 18 ቀን 2006 ዓም ጀምሮ ደብረዘይት በሚገኘው የአየር ሃይል ግቢ ውስጥበአንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ታስረው ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

Andargachew Tisge by Samsonኢሳት የተለያዩ ምንጮችን አነጋግሮ ባሰባሰበው መረጃ አቶ አንዳርጋቸው በመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በሁዋላ ድበደባው ቆሞ፣ የማሰቃያ መርፌዎችን እየተወጉና በኤልክትሪክ ሾክ እየተሰቃዩ መረጃ እንዲያወጡ እየተገደዱ ነው።መርማሪዎች ከአቶ አንዳርጋቸው የሚፈልጉት መረጃ ከግንቦት7 ጋር በጋራ የሚሰሩ  አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የኢህአዴግን አመራሮችን እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉ አዛዦችን ስሞች ሲሆን፣ አቶ አንዳርጋቸው ግን እስካሁን ምንም አይነት መረጃ ባለመስጠታቸው ፣ መርማሪዎች ሲበሳጩ መታየታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ለወትሮው አንድ መረጃ ሲያገኙ በታላቅ ደስታ የሚፈነጩት መርማሪዎች፣ ምርመራቸውን ጨርሰው ሲወጡ የሚያሳዩት ብስጭት፣ እስካሁን ድረስ የሚፈልጉትን እንዳላገኙ የሚያሳይ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ገልጸዋል።አቶ አንዳርጋቸው እንዳስፈላጊነቱ በቀን ሶስት ጊዜ ምርመራ እንደሚካሄድባቸው የሚናገሩት ምንጮች፣ ምርመራውን የሚያካሂዱት የተመረጡ የህወሃት የደህንነት ሰራተኞች መሆናቸውንና በግቢው ለበረራ የሚሰለጥኑ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ወይም የደህንነት ሰራተኞች ወደ አካባቢው እንደማይሄዱ ገልጸዋል። ምሽት አካባቢ የሚሰማው የጣር ድምጽ የሚረብሻቸው የእለት ተረኛ ጠባቂ መኮንኖች በሁኔታው እያዘኑ አንዳንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደማይችሉ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

ስለ አቶ አንዳርጋቸው የእለት ውሎ ማወቂያ ብቸኛው ዘዴ የመርማሪዎች ፊት ነው የሚሉት ምንጮች፣ እስካሁን ድረስ ምርመራ በሚያካሂዱ የህወሃት አመራሮች  ዘንድ የደስታ ፊት እንደማይነበብ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የታሰሩበትን ቦታ ይፋ ለማድረግ እስካሁን ፈቃደኛ አልሆነም። የእንግሊዝ ባለስልጣናት ለአቶ አንዳርጋቸው የኮንሱላር የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ ቢያቀርቡም ኢህአዴግ ባለስልጣናት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ከዚህ በተቃራኒ ኢህአዴግ በአቶ አንዳርጋቸው እና በግንቦት7 ላይ ለሚሰራው ድራማ ግብአት ይሆን ዘነድ የተለያዩ ሰዎችን ማሰማራቱን ምንጮች ገልጸዋል። ቀደም ብለው በአገዛዙ ለስለላ ወደ ኤርትራ ተልከው እና ለተወሰኑ ወራት ግንቦት7 ትን ተቀላቅለው በመጨረሻ የኢህአዴግ የስለላ አባላት መሆናቸው ሲታወቅ የጠፉ እንዲሁም ፈንጅ ሊያፈነዱ ሲሉ ተያዙ የተባሉ እና በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለመጠቀም እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ያሳየው ቁጣ ያስደነገጣቸው ደህንነቶች ለማንኛውም በሚል በደንበር አካባቢ ጥበቃቸውን እያጠናከሩ ነው። የአቶ አንዳርጋቸውን መያዝ ተከትሎ ግንቦት7ትን የሚቀላቀሉ ሰዎች መጨመራቸውንም ከድርጅቱ የወጣው መረጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤልጂየም ብራሰልስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግ አቶ አንዳርጋቸውን ለመያዝ የሄደበትን እርቀት ከማውገዝ በተጨማሪ የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ አጥብቆ እንዲከታተል ጠይቀዋል። ኢትዮጵያውያኑ ዛሬ በአውሮፓ ህብረት ቆንስላ ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ድምጻቸውን በከፍተኛ ቁጣ ከማሰማት በተጨማሪ፣ ያዘጋጁትን ደብዳቤ ለአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናትና ለእንግሊዝ መንግስት ኮንስላ ጽ/ቤት ሃላፊዎች አስረክበዋል።

Filed in: Amharic