>

የአዲስ ጉዳይ ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ የ7 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባት

• ፖሊስ ያቀረበባት ማስረጃ የለም

አዲስ ጉዳይ

ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም በአንዋር መስጂድ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ በአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ኃይሎች የታሰረችው የአዲስጉዳይ መጽሔት ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኘው በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ቀርባለች።
ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድምርመራውን በማጣራት ላይ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መምሪያ የቀረበች ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ በምርመራ ያላጣራሁት ነገሮች ስላሉ ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ብሎ በጠየቀው መሠረት ለሐሙስ ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እንዲቀርቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በዕለቱ የተጠርጣሪዎቹን የፍርድ ሂደት ለመከታተል በርካታ ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸው የተገኙ ቢሆንም ፖሊስ ግን በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ መቆየት አትችሉም በማለት ሁሉንም አስወጥቶ ችሎቱ በዝግ እንዲታይ አድርጓል።
ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ይሰየማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ችሎት 5፡50 ሰዓት የተሰየመ ቢሆንም የተጠርጣሪዎቹን የክስ መዝገብ የተመለከቱት ዳኛ ፎቶግራፈር አዚዛ መሐመድ የተያዘችበትን ምክንያት በተመለከተ ይዟት ለቀረበው ፖሊስ ጥያቄ ሲያቀርቡ “ሰው ስትገፋ አግኝቻታለሁ” የሚል መልስ ሰጥቷል፡፡
ዳኛው አዚዛ መሐመድ በፖሊስ የቀረበባትን የምርመራ ማካሄጃ ቀነ ቀጠሮ ጥያቄ ካዳመጡ በኋላ የተጠረጠረችው ከሁከት ጋር በተያያዘ መሆኑ እየተጠቀሰ፤ ወንጀሉን የሚደግፍ በቂ ማስረጃ ያለመስማታቸው እውነታ መደናገርን ፈጥሮባቸው እንደነበር ያገኘናቸው መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ፖሊስ ተጨማሪ የሚያጣራው ጉዳይ እንዳለ በመግለጽ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄውን በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ አዚዛ በማረፊያ ቤት በሚኖራት ቆይታ ከወዳጅ ዘመዶቿ ጋር የመገናኘት መብቷ እንዲከበር በማዘዝ ከ7 ቀናት በኋላ ሐምሌ 24 ማለዳ በተጠቀሰው ቀን ፍርድ ቤት እንድትቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፍርድ ቤቱን ሂደት የተከታተሉት የአዲስጉዳይ ባልደረቦች ከችሎቱ በኋላ ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድን ለመጠየቅ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ መምሪያ በመሄድ በአካል አግኝተዋታል።
አዚዛ ከባልደረቦቿ ጋር በነበራት አጭር ቆይታ በቁጥጥር ሥር የዋለችው በዕለቱ በ8፡30 አካባቢ ከአንዋር መስጂድ አጠገብ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀመጣ ሳለ መሆኑን ሂሳብ ለመክፈል ቦርሳዋን ስትከፍት መሆኑን ተናግራለች። በዚህ ወቅት ካሜራ መያዟን ያየችው አንድ የካፍቴሪያ አስተናጋጅ ለደህንነቶች ስልክ ሳትደውል አንዳልቀረችም አዚዛ ትገምታለች። ወዲያው የሲቪል ልብስ የለበሱ የደህንነት አባላት መጥተው እንደያዟት ተናግራለች።
አዚዛ በዚያን ወቅት መደበኛ ሥራዋን ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደነበረች ለባልደረቦቿ ተናግራለች። ያነሳችው ፎቶግራፍ ስላልነበረም ፖሊስ ካሜራዋን ወስዶ ፈትሾ ሊያቀርበው የሚችለው ማስረጃ ማግኘት አልቻለም።
በስፍራው ለስራ ከመገኘቴ በቀር በፖሊስ ሊያሳስረኝ የሚያስችል ምንም የወንጀል ድርጊት አልፈፀምኩም ብላለች አዚዛ።
አዚዛ ምንም አይነት ጥፋት ለመፈጸሟ ማስረጃ ባይቀርብባትም ፖሊስ ግን ለቀጣይ 7 ቀናት በእስር ላይ እንድትቆይ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል። አዚዛ በሚቀጥለው ቀጠሮ ፍርድ ቤት ስትቀርብ የእስር ቆይታዋ 13 ቀናት ይሆናል ማለት ነው።

Filed in: Amharic