>
5:13 pm - Wednesday April 19, 5054

"አራት ዓይነት ኢትዮጵያውያን" (ዳንኤል ክብረት)

“አራት ዓይነት ኢትዮጵያውያን” 
እኛስ ከየትኞቹ ወገን ነን? እርስዎ ከየትኛው ክፍል ነዎት? 
ዳንኤል ክብረት
በአሁኑ ጊዜ አራት ዓይነት ኢትዮጵያውያን🇪🇹አለን፡፡
፩ኛ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፤ ኢትዮጵያም በእነርሱ ውስጥ ያለች፦
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ልዩ ናት፡፡ በሀገራቸው ውስጥ ሆነው፣ ችግሯን እና መከራዋን ሁሉ አብረው ተቀብለው፤ ቢያዝኑም ሳይማረሩባት የሚኖሩ ናቸው፡፡ አቡነ ሺኖዳ «በአካል ካለችው ልብ በልባችን ውስጥ ያለችው ልብ ትበልጣለች» እንዳሉት በእነዚህ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያም ታላቅ ናት፡፡ በቀበሌው፣ በአስተዳደሩ፣ በአመራሩ፣ በአሠራሩ፣ በኢኮኖሚው፣ በኋላ ቀርነቱ ወዘተ ምክንያት በሚደርሰው ነገር አይለኳትም፡፡ እዚህ በዓይናቸው የሚያዩት ገጽታ በውስጣቸው ያለችውን ኢትዮጵያ ገጽታ አይቀይርባቸውም፡፡ የእነርሱ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት፤ ኩሩ ናት፤ ጀግና ናት፤ ነጻ ናት፤ ውብ ናት፤ ፍቅር ናት፤ ሥልጡን ናት፡፡ ሲሠሩ፣ ሲደክሙ፣ ሲያለሙ፣ ሲሠው፣ ሲከፍሉ፣ በልባቸው ላለቺው ኢትዮጵያ ነው፡፡ በሚያዩዋት ኢትዮጵያ እንጂ በልባቸው ባለቺው ኢትዮጵያ አይማረሩም፡፡
፪ኛ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ፣ ኢትዮጵያ ግን በእነርሱ ውስጥ የሌለች፦ 
እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ አንዳችም የኢትዮጵያ ጠባይ፣ ባህል፣ ፍቅር፣ ክብር፣ አመል፣ ስሜት፣ ወኔ፣ ቅንዐት በልባቸው ውስጥ የለም፡፡ ለእነርሱ ኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ብቻ ናት፡፡ ቦታ ብቻ ናት፡፡ በሰሜን ኤርትራ፣ በደቡብ ኬንያ፣ በምዕራብ ሱዳን፣ በምሥራቅ ሶማልያ እና ጂቡቲ የሚያዋስኗት ሀገር ብቻ ናት፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ኢትዮጵያ ብትወድቅ ብትነሣ፣ ብትሞት ብትድን፤ ቢያልፍላት ባያልፍላት፣ ብታድግ ብትደኸይ አይገዳቸውም፡፡ ሊጠቅሟት ሳይሆን ሊጠቀሙባት ብቻ ይፈልጓታል፡፡ ስለ እነርሱ እንድትኖር እንጂ ስለ እርሷ እንዲኖሩ አይፈልጉም፡፡ ለእርሷ አይሠውም፤ ለእነርሱ ግን ይሠውዋታል፡፡
፫ኛ) ከኢትዮጵያ የወጡ፣ ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ ልብ ያልወጣች፦
እነዚህ ደግሞ ወደውም ሆነ ሳይወዱ ከሀገር የወጡ ናቸው፡፡ በአካል ከሀገር ርቀዋል፡፡ በልባቸው ግን ኢትዮጵያን ፀንሰዋል፡፡ ደማቸው፣ ጠባያቸው፣ እምነታቸው፣ ዐመላቸው፣ ባህላቸው፣ ስሜታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ስሟን ሲሰሙ አንዳች ነገር እንደ ኤሌክትሪክ ይነዝራቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን፣ ቤታቸውን፣ አቆጣጠራቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ጸሎታቸውን ሁሉ ኢትዮጵያኛ አድርገውታል፡፡ ለእነርሱ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ቀን ነፍሳቸውም ሥጋቸውም እዚያው ኢትዮጵያ ትኖራለች፡፡ ቢሞቱ እንኳን ሥጋቸው እንዲመለስ ይፈልጋሉ፡፡
፬ኛ) ከኢትዮጵያ የወጡ፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ልብ የወጣች፦
እነዚህ ደግሞ የሚኖሩትም ውጭ ነው፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ ወጥታለች፡፡ ምናልባትም መልካቸው ብቻ ካልሆነ በቀር አንዳችም ከሀገራቸው ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር በዲኤን ኤ እንኳን ላይገኝ ይችላል፡፡ ለእነርሱ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ አንዲት ሀገር ናት፡፡ በቃ፡፡ ብትኖር ብትሞት ስሜት አይሰጣቸውም፡፡ አይኖሩባትም፤ አትኖርባቸውም፡፡ «ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ» የሚል ምሕላ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያን ከልባቸው ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸው ልብ አንዳትገባም አድርገዋታል፡፡ በዓለም ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ሁለት ቃላትን መተርጎም ከባድ ነው ይባላል፡፡ «ፍቅር እና ሀገር»፡፡ ልብ እንጂ ቃል አይተረጉማቸውምና፡፡
እኛስ ከየትኞቹ ወገን ነን? እርስዎ ከየትኛው ክፍል ነዎት?
Filed in: Amharic