>
5:13 pm - Friday April 19, 9163

ኢትዮጵያውያን በየመን ኤደን ከተማ በስታዲየም ውስጥ ታስረው ይገኛሉ -  አይ ኦ ኤም

ኢትዮጵያውያን በየመን ኤደን ከተማ በስታዲየም ውስጥ ታስረው ይገኛሉ-
አይ ኦ ኤም
በመሀመድ ሚፍታህ
በየመን አደን ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በስታዲየም ውስጥ መታገታቸው ተሰማ። እነዚህ አፍሪካውያን በደቡባዊ የመን በሚገኙ በአደን፣ ላዥ እና አቢያን ከተሞች ታስረው እንደሚገኙ በየመን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት፣ አይ ኦ ኤም፣ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦሊቪያ ሔዶን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከታገቱት አብዛኞቹ ወደ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሀገራት ለመሻገር የመን የገቡ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ቃል አቀባይዋ አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የሶማሊያና የጅቡቲ ዜጎችም መታሰራቸውን ኦሊቪያ ሔዶን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እነዚህ ኢትዮጵያውያን የተያዙት በየሥፍራው በተተከሉ የፍተሻ ጣቢያዎች ሲሆን በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላም ወደ ጦር ካምፖችና ኤደን ከተማ ወደ ሚገኘው ስታዲየም አምጥተዋቸዋል ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ ስደተኞቹ በተያዙበት ሥፍራ በመገኘት እንዳረጋገጡት ሥፍራው በጦርነቱ ምክንያት የፈራረሰ ሲሆን ስደተኞቹን ለማቆያ ብቁ አይደለም ብለዋል።
ወደ የመን ላዥ ከተማ ከመጣ 25 ቀን እንደሆነው የሚናገረው አወል ሼህ ናስር በታጠቁ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሎ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ታስሮ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።
አወል ወደ የመን ከገባ በኋላ መኪና በማጠብ ሥራ ላይ የተሰማራ ቢሆንም ፖሊስ መጥቶ ገንዘቡን ተቀብሎ እንዳባረረው ያስረዳል።
በኋላም በከተማው በሚገኝ የሀገሩ ልጅ ቤት ተደብቆ ሳለ ፖሊሶች መጥተው ከብበዋቸው ወደ ወታደራዊ ካምፑ እንደተወሰዱ ለቢቢሲ አረጋግጧል።
“ወደ ወታደራዊ ካምፑ የተወሰድነው 400 እንሆናለን፤ እዚያ ስንደርስ ግን ከ3ሺህ በላይ ስደተኞችን አይተናል።” የሚለው አወል በአንድ መጋዘን ውስጥ አስገብተዋቸው እንደቆለፉባቸው ያስታውሳል።
አወል እንደሚለው ከመጋዘኑ ለመፀዳዳትም ሆነ ንፋስ ለመቀበል መውጣት አይቻልም፤ ተፋፍገው እና በሙቀት ታፍነው ባሉበት ሁለት ስደተኞች በመታመማቸው በሩን ገንጥለው ልጆቹ አየር እንዲያገኙ እንዳወጧቸው ያስረዳል።
በዚህ ጊዜ ነው ጠባቂዎች በሥፍራው እንደሌሉ ተረድተው በቡድን በመሆን ያመለጡት።
በቁጥር በርከት ብለው ያመለጡት በድጋሚ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የሚለው አወል እርሱ ግን ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን በማምለጥ አማን መግባቱን ነግሮናል።
በአማን ከተማ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገረው አወል በየስፍራው የፍተሻ ጣቢያ በመኖሩ ወደ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሄዶ ለመመዝገብ እንኳ እንዳልቻሉ ይናገራል።
ከሰንዐ ወጣ በሚል የገጠር ከተሞች በአንድ ቀን ብቻ ከሶስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተይዘው ታስረዋል ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ በሰንአ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ከድር በከልቻ ናቸው።
የሰንዐን ከተማ የሚቆጣጠሩት የሁቲ አማፂያን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ከድር መንግሥት የሰጣቸውን የስደተኝነት ሰነድ እንዲቀይሩ እንደሚያስገድዷቸው ከቀየሩ ደግሞ የየመን መንግስት ወደሚያስተዳድራቸው ሥፍራዎች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።
አቶ ከድር “የሁቲ አማፂያን ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት ለመሻገር ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያንን እየያዙ ወደ ውትድርና ያሰማራሉ” ሲሉ ይከሳሉ።
እነዚህ በግዳጅ ወታደር የሆኑ ኢትዮጵያውያን በየመን መንግሥት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ኢትዮጵያውያን በገፍ መታፈስ መጀመራቸውንም ያስረዳሉ።
“በረሃብና በኮሌራ እየተሰቃዩ የሚሞቱ ኢትዮጵያውያንም አሉ” ይላሉ -አቶ ከድር።
በዚህም ባለፈው ሳምንት ብቻ ከሰንዐ ወጣ ብላ የምትገኝ ረዳ በምትባል አነስተኛ ከተማ አምስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ተናግረዋል።
በየመን ህጋዊ ወረቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ጭምር በአሁን ሰዓት የተለያዩ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ከድር ሁቲዎችን ትደግፋላችሁ በሚል መንቀሳቀስ መከልከላቸውን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሁቲ አማፂያን ታጣቂዎች አንዲሁም በየመን መንግሥት እንግልት እንደደረሰባቸውና ሕገወጥ ደላላዎች እንደሚያሰቃይዋቸው ያስረዳሉ።
በየመን የሚገኙ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ከከተማ ወጥቶና እንደልብ ተንቀሳቅሶ ጉዳያቸውን ማስፈፀም እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚያው የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም እንደሚናገሩት በሀገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የማይታወቁ እስር ቤቶች እንደሚገኙ፣ እስር ቤቶቹ ጠባብና የተፋፈጉ መሆናቸውን በዚህም የተነሳ ኮሌራን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች መገለጣቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
በአደን በእስር ላይ ከሚገኙት ወንዶችና ሴቶች በተጨማሪ 800 ሕፃናት እንደሚገኙበት የሚናገሩት የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ፣ ሕፃናት የሆኑ ብቻ ሳይሆን ታዳጊ ልጆችም ከእስረኞቹ መካከል እንደሚገኙበትና የተለያዩ መንገላታቶች እንደሚደርስባቸው አስታውቀዋል።
ቃል አቀባይዋ ያነጋገሯቸው አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ የገለፁ ሲሆን አይ ኦ ኤም እነዚህን ስደተኞች ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጿል።
Filed in: Amharic