>

የጉምዝ ሕዝብ (ከተማሪዎቼ እንደተረዳሁት) - ውብሸት ሙላት

የጉምዝ ሕዝብ (ከተማሪዎቼ እንደተረዳሁት)
ውብሸት ሙላት
በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ለሦስት ዓመታት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ከአምስቱ ብሔረሰቦች የተዉጣጡ፣ የመጡ 99 ተማሪዎችን አስተምሬያለሁ፡፡ 100 ነበር የተመደቡት፡፡ አንድኛዉ (ደፋላ የሚባል ተማሪ) እንደ ጀመረ ለሳምንት ያህል ሳይማር አቋረጠ፡፡ ዘጠና ዘጠኙም ተማሪዎች እንዲመረቁ አድርገናል፡፡ ከትምህርት (education) ወደ ሥልጠና (training) እንዲያዘነብል በማድረግ ክልሉ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ እጥረት ስለነበረበት (እንደዉም የለዉም በሚያስብል ደረጃ) ሦስት ዓመት ሰልጥነዉ ቢሄዱ ለወገናቸዉ ስለሚጠቅም ብለን ነዉ፡፡
እዚህ ላይ ለማንሳት የፈለግሁት በሦስት ዓመት ቆይታቸዉ ያወቅኳቸዉን ያህል የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ነዉ፡፡ የሽናሻ ተወላጆች ከብበዙ ሁኔታ ከአማራ፣ አገዉ ወዘተ ጋር ተመሳሳይ ናቸዉ፡፡የአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ ሽናሽኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የአፍ መፍቻ ቋንቋዉ አማርኛ ከሆነዉ ጋር በማይለይ ደረጃ አማርኛ ይችሉ ነበር፡፡ ይሄ ያዉ ያስተማርኳቸዉን የሚመለከት ነዉ፡፡ በትምህርትም ላይ በአማርኛ ማብራሪያ ሲሰጥ (እንደማንኛዉም የእንግሊዝኛ ቋንቋ እጥረት እንዳለበት ተማሪ) በደንብ የመረዳት አቅም አላቸዉ፡፡ በሃማኖት ረገድ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ክርስቲያን ናቸዉ፡፡
የበርታ ተወላጅ የሆኑት አረብኛ በደንብ ይችላሉ፡፡ ከበርታዎቹ ዉስጥ የአብዱልዉሃብ ወታደር የነበሩ ጭምር ይማሩ ነበር፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል መጠን (ሀና ኤልያስ የምትባል አመለ ሸጋ የሆች፣የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ እንደነበረች አስታዉሳለሁ) የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸዉ፡፡ አንዳንድ በርታዎች በእንግሊዝኛ ጥሩ የንግግር ችሎታ ነበራቸዉ፡፡ የሚቸግራቸዉ የጽሁፍ ነበር፡፡ ከከተማ አካባቢ የመጡት የአማርኛ ችሎታቸዉ ጥሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ አልፎ አልፎ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ትምህርቱን መረዳት የሚቸግራቸዉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እኔም፣ ከመካከላቸዉ የተሻለ አማርኛ ወይም እንግሊዝኛ ከሚችሉት መርጨ በሩጣንኛ (በርታ ቋንቋ) እንዲተረጉሙ እያደረግ አስተምር ነበር፡፡
ማኦ እና ኮሞ ቁጥራቸዉ አሁን የማስታዉሳቸዉ አራት ናቸዉ፡፡ ባባከር ሙሃመድ ባባከር፣ዜልፋ፣ተማም እና ከማል ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ዉስጥ በተለይ ሁለቱ ኦሮምኛ በደንብ ይችሉ ነበር፡፡ አማርኛ በጣም ስለሚቸግራቸዉ አልፎ አልፎ በኦሮምኛ አስተረጉምላቸዉ ነበር፡፡ ከበርታዎቹ ተማሪያዎች መካከል በተለይ አንዱ (ሙሃመድ ዑስማን የሚባልና ባልተቤቱ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ /ነፍሳቸዉን ይማረዉ/ በጣም የቅርብ ዘመድ የሆነች) እንግሊዝኛ፣ አረብኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሩጣንኛም አቀላጥ ስለሚናገር በኦሮምኛ እየተረጎመ ይነግርልኛል፡፡
 ከእነሱ መካከል በተለይ ዜልፋ፣ እጅግ ጸባይተኛ እና ዝምተኛ፣ አማርኛም እንግሊዝኛም በጣም ስለሚቸግራት፣በትምህርት ወቅት አንገቷን ደፋ አድርጋ ፊቷ ላይ ሁልጊዜ ጭንቀት ይነበብ ነበር፡፡ በኦሮምኛ ተተርጉሞ ሲነገራት በጣም ፊቷ እያበራ በኦሮምኛ ጥያቄም ትመልሳለች፤አስተያየትም ትሰጣለች፡፡ ለእኔም ወይ በእንግሊዝኛ ወይ በአማርኛ ይተረጎምልኛል፡፡
የጉምዝ ተማሪዎቼን ሁሉም ሰዉ የትኛዉ ጉምዝ እንደሆነ ሌላዉ ሰዉ በቀላሉ ይለያቸዋል፡፡ በሃይማኖት ረገድ የተወሰኑት ፕሮቴስታንት እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ አማርኛም እንግሊዝኛም የሚቸግራቸዉ የተወሰኑ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አማርኛም እንግሊዝኛም ጥሩ ችሎታም የነበራቸዉ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሽናል መባል የማያንሳቸዉ ቅርጫት ኳስ (ለምሳሌ አብርሃም አዳል) እና እግር ኳስ (አዲሱ ግራኝ-ሳላሃዲን ሰይድ ጓደኛ እንደነበር ሰምቻለሁ) ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በሚመረቁበት ጊዜም ከ99ኙም አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀዉ፣ ትምህርትን በጣም አቅልሎ የሚመለከተዉ፣ ሰንበታ ቀጀላም የጉምዝ ተወላጅ ነዉ፡፡ ከእነሱም መካከል በአማርኛም በእንግሊዝኛም ሲቸገሩ በጉምዝኛ እነ ሰንበታም ሌሎችም ይተረጉሙልኝ ነበር፡፡
ዘጠና ዘጠኙም ተማሪዎቼ በዕድሜ የምበልጣቸዉም፣እኩል የምንሆንም፣ የሚበልጡኝም ቢኖሩም እንኳን የብዙዎቹን ተማሪዎች ስም እና ጠባይና ዐመላቸዉን አሁንም አልረሳቸዉም፡፡ እርግጥ ነዉ ከተመረቁ አሁን ዘጠኝ ዓመት ሁኗቸዋል፡፡ የብዙዎቹን ተማሪዎች ቤተሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዳራ ሳይቀር ለማወቅ የሚያስችል ቀረቤታ ነበረኝ፡፡ እንደሚነግሩኝም፣ የብዙ ተማሪዎች ቤተሰቦች በስም (በዝና) ያዉቁኝ ነበር፡፡ የነበረንን ቀረቤታ ለመግለጽ ነዉ፡፡
ከተማሪዎቼ ተነስቼ ስለጉምዞች ትንሽ ነጥቦችን ልበል፡፡ አንድ ቀን ምሳ ሰዓት ላይ ዲኑ ስልክ ደወለልኝ፡፡ በግምት ሰባት ሰዓት ገደማ ይሆናል፡፡ ዲኑ (አቶ ታምሩ ካሳ) “ዉቤ ኧረ ልጆችህ፣ በጣም ጠቆር ያሉት አንድ ቦታ ቁመዉ እየጮሁ በቋንቋቸዉ ብቻ እያወሩ ነዉ፡፡ ምን እንደሆኑ ልጠይቃቸዉ ነበር ግን ፈራኋቸዉ፡፡ የሰላም አልመሰለኝም ሁኔታቸዉ ፡፡  እስኪ በፍጥነት ናቶሎና አግኛቸዉ” ይለኛል፡፡
ጋሽ ታምሩ በዕድሜም ወደ 60 ይጠጋል፡፡ ባለሥልጣንም የነበረ፣ በብዙ መልኩ ጥሩ የመግባባት ችሎታ ያለዉ፣ ሁለተኛ ደረጃ እያለሁም እንግሊዝኛ አስትምሮኛል፡፡ በፍጥነት ወደ ኮሌጁ፣ መርሆ ግቢ ሄድኩ፡፡ ጋሽ ታምሩ እንዳለዉ ፣ ወደ እኔ ቢሮ መግቢያ ቀረብ ብለዉ ሁሉም ጉምዞች ንዴት በተቀላቀለበት ሁኔታ ያወራሉ፡፡ ሰላም ካልኳቸዉ በኋላ፣ ከመካከላቸዉ አንዱን ወደ ቢሮ ይዤዉ ገባሁና ምን እንደተፈጠረ ስጠይቀዉ አንድ እኔ ሽናሻ እንደሆነ የማዉቀዉ ነገር ግን ኦሮምኛ በደንብ የሚችል (ምናልባት በከፊል ኦሮሞም ሊሆን ይችላል)   ስሙን ጠቅሶ  አንዱን ተማሪ መሳደቡን ነገረኝ፡፡ ምንም እንኳን ተሰደበ የተባለዉ አንድ የጉምዝ ተወላጅ ቢሆንም እንዲሁም ለምሳ ወደ ቤታቸዉ በሄዱቡት አጭር ሰዓት (ምናልባትም አንድ ሰዓትም ላይሞላ ይችላል) ሁሉም ተሰማምተዉ ተመልሰዉ ግቢ መጥተዋል፡፡ ቤት ተከራይተዉ ስለሚኖሩ በምን ፍጥነት ተሰማምተዉ እንደመጡ ገረመኝ፡፡
ለማንኛዉም እና ለምድን ነዉ ሁላችሁም በዚህ ሁኔታ የተሰባሰባችሁት ስለዉ ከንዴቱ ዉስጥ ሳይወጣ፣ለዚያም በጣም ጥሩ ድስፕሊን ያለዉ ልጅ ያልኩት ነዉ፣ “እዚያ ኦሮሞ ተሰብስቦ ወላጆቻችንን ያጠቃሉ፣ጉዳት አደረሱ፡፡ ገደሉ፡፡ ደግሞ እዚህም ሊሰደበን ነዉ ታዲያ?” አለኝ፡፡ በወቅቱ በአቶ አባዱላና እና አቶ ያረጋል አይሸሹም ርእሰ መስተዳድርነት ዘመን በኦሮሞና በጉምዝ መካከል ግጭር ተነስቶ የብዙ ሰው ሕይወት ጠፍቶ ነበር።
 እሱም እንዲረጋጋ፣ ሌሎቹንም እንዲያረጋጋ በፍጥነት መክሬ ወደ እነሱ ላኩት፡፡ እኔም በፍጥነት ለሌላ አስተማሪ ስልክ ደወልኩ፡፡ ለአንድ ስልክ ላለዉ ሽናሻ ተማሪም እንዲሁ ደወልኩ፡፡ ያንን ሰደበን የሚሉትን ተማሪ ወደ ግቢ እንዳይመጣ፣ እቤቱ እንዲቀመጥ ኋላ ላይ ግን እንዲያገኘኝ መልእክት ላኩኝ፡፡ ከሁኔታቸዉ፣ በድንገት አገር አማን ብሎ ወደ ኮሌጁ ለትምህርት ወይም ለጥናት ከመጣ ምናልባትም ሊገድሉት እንደሚችሉ ተረድቻለሁ፡፡
ይህንን ካደረግኩ በኋላ፣ ከመካከላቸዉ ለምሳዉ የገዛዉን ረጅም ዳቦ በእጁ እንደያዘ መጥቶ ከመካከላቸዉ የነበረዉን አብርሃም አዳልን (ለብሔራዊ ወይም ከእዚያ በተቻ በሚገኝ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የነበረ) ጠራሁት፡፡ ጠየቅኩት ስለሁኔታዉ፡፡ ተመሳሳይ ነገር ነገረኝ፡፡ ከነ ዳቦዉ ነዉ ቢሮዬ የመጣዉ፡፡ በመጨረሻም አብርሃምን ብታገኙት ኖሮ ምን ታደርጉት ነበር አልኩት እያሳሳቅኩ፡፡ ቃል በቃል ያለኝ “ያዉ እንገድለዉ ነበር” አለኝ፡፡ ጭካኔም፣ የዋህነትም፣ግልጽነትም፣ የባህልንም ሁኔታ አሰብኩ፤ ወይ ጉድ ብዬ ሁሉንም ወደ ግቢዉ ካፍቴሪያ ወሰደኳቸዉ፡፡
ከሁሉም ጋር አብረን ሻይ ቡና እያልን አወራን፡፡ ከእዚያ ቁጣቸዉም፣ቂማቸዉም ጠፋ፡፡ ተሳደበ የተባለዉን በኋላ ጠርቼ አወራሁት፡፡ በሚቀጥለዉ ቀን ሁሉም ነገር እንዳልነበር ሆነ እንደበፊቱ ቀጠለ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በወቅቱ ቢያንስ ከአንድ ዓመት በላይ ሕግ ተምረዋል፡፡ ግን በምን መልኩ እርምጃ ለመዉሰድ ከመቅጽበት እንደተሰባሰቡ፣ ቢያገኙት ሊወሰድት የነበረዉን እርምጃ፣ ለዚያዉም ደሴ ከተማ ላይ ነዉ፡፡
ከዚህ ባለፈ፣ ቢያንስ ተማሪዎቼ የነበሩት የዋህ፣ ምንም ነገር የማያሳፍራቸዉም የተጠየቁትን በሚያዉቀት ልክ ቀጥታ የሚመልሱ እንደነበሩ ከተማሪዎቼ ተረድቻለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ቀን ጧትም ከሰዓትም አንድ ሴክሽን ተማሪዎችን አስተምር ነበር፡፡ በጧቱ ክፍለ ጊዜ የነበረች፣ ነገር ግን ከሰዓት ያልመጣች ተማሪ ስለነበረች፣ “እንትና ምን ሁና ነዉ ያልመጣችዉ?” ስለ ጠየቅኩ፡፡ ከወደ ኋላ የተቀመጠች፣ ጓደኛዋ የሆነች አንድ ተማሪ ሁሉም የክፍሉ ተማሪ እየሰማት “ፔረዷ ምጥቶባት ነዉ” አለች፡፡ ጥያቄዬ ለምን አልመጣችም? ስለነበር ያልመጣችበት ትክክለኛ ምክንያት ጓደኛዋ የተናገረችዉ ነዉ፡፡ በተለምዶ ግን በዚህ መንገድ አንገልጸዉም፡፡ የጉምዝ ተማሪዎቼ ግን በቀጥታ ነዉ የሚገልጹት፡፡ ጥያቄ ስጠይቅም መልሱን ካለወቁት አላዉቀዉም የሚሉት ይበዙ ነበር፡፡ ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን እያነሳሁ በተለይ ስለጉምዝ ተማሪዎቼ መናገር እችላለሁ፡፡
በአጭሩ፣ አንድ ጉምዝን መሳደብ እንኳን ሁሉንም እንደመስደም ነዉ የሚታየዉ፡፡ ግዲያ እና ሌላማ የባሰ ነዉ፡፡ እርምጃዉም አጸፋዉም በጋራ ነዉ፡፡ ይሔ የጉምዝ ባህል ነዉ፡፡ ሲበዛ የዋህ መሆናቸዉንም ከተማሪዎቼ ተረድቻለሁ፡፡ የተነገራቸዉን ሁሉ ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ የተነገራቸዉን ይቀበላሉ፡፡ አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ፡፡ ግደሉ ቢሏቸዉ ሊገድሉም ጭምር፡፡ ይሔ ከክፋት ወይም በጣም አዉጥተዉ አዉርደዉ ለተንኮል ብለዉ የሚፈጽሙት አይመስለኝም፡፡ ሌላዉ በሰዉ ልጅ ሕይወት መጥፋት፣ ከሌሎች አንጻር አነስ ያለ ዋጋ (Value) ነዉ የሚሰጡት፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰዉን ለመግደል ካሰቡ ብዙም ማዉጣትና ማዉረድ ሳያስፈልጋቸዉ ሊገድሉ ይችላሉ፡፡ መግደል ብዙም የጥፋተኝነት ስሜት አይፈጥርባቸዉም፡፡
ይሄንን ታሪክ መጻፌ፣ አሁን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተክል ዞን በተለይም ዳንጉር የተከሠተዉን ዘግናኝ እልቂት ሳስብ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ያስተማርኳቸዉ ተማሪዎቼን እያስታወስኩ፣ የባህልና የአኗኗር ስልታቸዉን፣ ማኅበራዊ ስሪታቸዉን ሳዉጠነጥን በምን መንገድና ዘዴ አሁን የተፈጠረዉን ችግር ማስቆም እንደሚቻል ይጨንቀኛል፡፡ በተጨማሪም፣ ሌሎች አካላት ትንሽ ማባባሻም ከጨመሩበት እንዴት እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከጉምዝ ጋር በፍጥነት እርቅ ለማዉረድና ሰላም ለማስፈን ቀላል መሆኑን ሳስበዉ እጽናናለሁ፡፡ ለእርቅና ምህረት ፋጣን ልቦና አላቸዉ፡፡ በተቃራኒዉ ለመሔድ እንዲሁ!
ለዚያም ነዉ የጉምዝን ሕዝብ በሚመለከት መንግሥት (የክልሉም የፌደራሉም) የተለየ ፖሊሲ ያስፈልገዋል የምለዉ፡፡
Filed in: Amharic