>
5:13 pm - Thursday April 20, 6620

ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ዜጎች  ዘርን መሰረት ተደርጎ ጉዳት ሲደርስባቸው ያማል!!!” ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 

ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ዜጎች  ዘርን መሰረት ተደርጎ ጉዳት ሲደርስባቸው ያማል!!!”
ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 
በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የሰላም መደፍረስና የዜጎችን የደህንነት ስጋት በአጭርና በዘላቂነት ለማስተካከል መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡
የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅሩን ያሳተፈ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን የሚገመግም ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በሃገሪቱ  የለውጥ ጎዳና ጉዞ ብዙ ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ሆኖም ከለውጡ ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀልና ጉዳት የእለት ከእለት ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡
” ባለፉት ወራትም በክልሉ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈጠረው ክስተት ሁሉንም ያሳዘነ ነው” ብለዋል፡፡
በተለይም ዜጎች በነፃነት ለመኖር ታግለው ያመጡትን ለውጥ ተጠቃሚ ሆነው ሳይጠግቡ የተከሰተው የአለመረጋጋት ችግር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረ ነው፡፡
” በተለይም ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ዜጎች ባላወቁት፣ባለሳቡትና ባልገመቱት መንገድ ዘርን መሰረት ተደርጎ እየደረሰ ያለው ጉዳት ያማል” ብለዋል፡፡
” ችግሮች ሁሉ የአፈፃፀም ክፍተቶች ናቸው እያሉ ምክንያት መደርደር አያዋጣም” ያሉት አቶ ደመቀ አሁን ላይ ዜጎች ተከባብረው የሚኖሩባት ሃገር መገንባት ግድ ከሚልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
” መንግስት ህግና ስርዓት እንዲከበር ካላደረገ የትኛውም ለውጥ ብናሞካሽና መፍትሄ ሰጠን ብለን ብናነሳ ህዝብን የሚያረካና የሚያረጋጋ አይደለም”ብለዋል፡፡
እስካሁን እየደረሰ ባለው ጉዳትና የዜጎች አለመረጋጋት ዋናው ተጠያቂ መንግስት መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለማስተካከልና ለማረም አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቅሰዋል፡፡
 አሁን ላይ በየአካባቢው የሚስተዋለው  የሰው ህይወት መጥፋት ፣ መፈናቀል፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለማስቆም መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከአጭር ጊዜ አኳያም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል በየአካባቢ ችግር ሲከሰት ፈጥኖ የሚደርስ የፀጥታ መዋቅር በቅርበት ማስቀመጥ፣ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የተቀመጠ አቅጣጫ ነው “ብለዋል፡፡
መተከል፣ጃዊና አካባቢ የበለጠ እንዲረጋጋና መፈናቀል እንዳይኖር ተጨማሪ የፀጥታ ሃይል ይላካል፤ በሌሎች የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎችም እንዲሁ፡፡
የፀጥታ መዋቅሩ ተጠያቂነት ባለው መንገድ ዜጎችን ከስጋት ነፃ በሆነ መንገድ እንዲታደግም ክትትል ይደረጋል፡፡
በብጥብጡ እጃቸውን ያስገቡ አመራርም ሆነ ሌሎች አካላት ተገቢውን የማጣራት ስራ በማከናወን መንግስት ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል፤ ይህን የሚያጣራ ግብረ ኃይልም መቋቋሙን አስታውቀዋል።
በዘላቂነት ደግሞ የኃይማኖት አባቶችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችንና ሌለውን የህብረተሰብ ክፍል  ያሳተፈ ውይይትና መግባባት መፍጠር  በውይይቱ የተቀመጠ አቅጣጫ መሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት፣ የአማራና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የፖለቲካና የፀጥታ አመራር አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ኢ.ዜ.አ
Filed in: Amharic