>

አፍሪካዊነትን የሚያስጠሉ ሁለት ወይ ሦስት ወቅታዊ ክስተቶች (ነፃነት ዘለቀ)

አፍሪካዊነትን የሚያስጠሉ ሁለት ወይ ሦስት ወቅታዊ ክስተቶች

ነፃነት ዘለቀ

በዜና ስከታተላቸው ለጊዜው “ብው” ያልኩባቸውን መጥቀሴ እንጂ አፍሪካዊ መሆን በተለይ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የሚያኮራ ወይም የሚመኙት ሆኖ አይደለም – ርዕሴን እንደዚያ የሰየምኩት፡፡ አፍሪካ በሚገርም ሁኔታ ዓለምን እያሳቀችና ጥቂት የማይባሉ ዜጎቿን እያሳቀቀች ትገኛለች፡፡

• የኛው ጉድ በየሚዲያው እንደልብስ ተሰጥቶ ፀሐይ እየሞቀው ስለሆነ አሁን እዚህ ገብቼበት አልዳክርም፡፡ ሰለጠነ በተባለ ዓለም ውስጥ የዘርና የጎጥ ፓርቲና ድርጅት መሥርቶ መጃጃል ከየት እንደመጣ ማወቅ ስለማይቻል የኛን አለማንሳት ነው፡፡ ተስማምቶና ተዋህዶ የሚኖርን ሕዝብ እያጣሉ እንደ አዲስ ለማስታረቅና ለማስማማት የሚደረገውንም በየወንዙ የሚማማሉ የማይተማመኑ ጓደኛሞች ዓይነት ነገር እንተወው፡፡

• ዩጋንዳ ትገርማችለች፡፡ ዮሪ ሙሴቪኒ የተባለን በዕድሜም ባይሆን ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ከማለት አኳያ በአምባገነንነት የጃጀ ሽማግሌ ለማስመረጥ ፓርላማው ህጉን ጠመዘዘው አሉ፡፡ ይህን ስሰማ በውነቱ አፈርኩ፡፡ ሰዎች ወዴት እየሄድን እንደሆነ በግልጽ የሚናገር እጅግ አሣፋሪ ክስተት ነው፡፡ “የራሷ አሮባት…” እንዳልባል ፈርቼ እንጂ ብዙ ያስብላል፡፡ ይህ ሰው ዩጋንዳን መምራት ከጀመረ ከሦስት አሠርት ዓመታት በላይ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሥልጣን ዘመን አላጠገበውም፡፡ በዚህ ሁሉ የፈላጭ ቆራጭነት ዘመን የሥልጣን አራራው ጋብ አላለትም፡፡ በሚገርም ሁኔታ አሻንጉሊቶቹም አጸደቁለት፡፡ የግብጽ ፓርላሜንታዊ አሻንጉሊቶችም ልክ እንደዚሁ ለአልሲሲ የሥልጣን ዘመን መራዘም ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳያደርጉለት የቀሩ አይመስለኝም – ባለፈው ሰሞን ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ እነሱ እንኳን በሥልጣኔና በአስተሳሰብ ከሌሎቻችን የተሻሉ ናቸው የሚባሉ ነበሩ፡፡ በውነት አፍሪካውያንን ምን ነካን? ከዚህ ከዚህስ የይሉኝታን ገመድ በጣጥሶ የጣለው የኤርትራው መሪ ኢሣይያስ አፈወርቂ ይሻላል፡፡ አንድ ጊዜ ስለምርጫ ተጠይቆ ምን አለ አሉ – “እንደ ኢትዮጵያ ያለ ምርጫ ከፈለጋችሁ በየስድስት ወሩም ማድረግ እንችላለን፡፡” እውነቱን ነው፡፡ እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር፡፡ የርሱ በስንት ጣሙ!
• የሱዳኑ መሪ ቤት ሲፈተሸ አንድ አገር ሙሉ ዶላርና ዩሮ በየከረጪቱ ታጭቆ ተገኘ አሉ፡፡ እንዲህ ነው የሕዝብ ሰው ማለት፡፡ መቼና የት ሆኖ ሊጠቀምበት ያን ሁሉ ሶልዲ እንዳከማቸ እርሱን ራሱን መጠየቅ ነው፡፡ ግን ጭንቅላት የሚባል ነገር በተለይ ተማሩና ዐወቁ በተባሉ የሀገር መሪዎች ዘንድ እንዴት ጠፋ? አውነትም ምን ነካን?

እንዴ! ሰው ወዴት እየሄደ ነው!! ያስጨንቃል አኮ፡፡ ታዲያ ከነዚህ ሰዎች ጋር እንደሰው ተቆጥሮ በዚህች አፍሪካ መኖር ልክ ነው? እንደኔ እንዲህ ዓይነት መሪዎችና “ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት” የሚሉ ሁሉንም ትዛዛቸውን ያለማንገራገር የሚፈጽሙ ሆዳም አጃቢዎቻቸው ባሉባት ምድር መኖር ወርቃማ ጊዜን እንደማባከን እቆጥረዋለሁ፡፡ የአሁኑ ዘመንስ በርግጥም አጃኢብ ነው፡፡

Filed in: Amharic