>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8547

‹የአብዲሳ አጋ ልጅ!!!› (ዳንኤል ክብረት)

‹የአብዲሳ አጋ ልጅ!!!›

ዳንኤል ክብረት

ከወራት በፊት አቶ ፍጹም አረጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ እያለ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮው ሄጄ ነበር፡፡
አንድ ረዘም ደልደል ያለ፣ ፈገግታ ከፊቱ የማይጠፋ ሰው አገኘሁ፡፡
ከዚያ በፊት በአካል አግኝቼው አላውቅም፡፡ እርሱ ግን እንደሚያውቀኝ ነገረኝ፡፡
በተደጋጋሚ ስሄድ እዚያው ቢሮ በሥራ ተጠምዶ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከመቀራረብ ብዛት ተግባባን፡፡
ከተግባባን ላይቀር ብለን ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ ማውራት ቀጠልን፡፡
በተለይም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ሀገሪቱ ታሪክ፣ በታሪክ ውስጥ የተከሠቱ ነገሮችን እንዴት ማረም እንደምንችል፣ የሕዝቦች መቀራረብ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል እናወራ ነበር፡፡
ከሚነግረኝ ነገሮች ሰውዬው የፍልስፍናና የታሪክ ዕውቀቱ ሰፋና ጠለቅ ያለ መሆኑን ተረዳሁት፡፡
በተለይ ደግሞ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አድናቂም ደቀ መዝሙርም መሆኑን ስረዳ ነገሮችን ሊያይበት የሚችለውን መነጽር ገመትኩት፡፡
ለሽመልስ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ የጠቅላላው ታሪካችን አካል ነው፡፡ የተሻለው የመግባቢያ መንገድ የጎደለውን መሙላትና ያለውን የጋራ አድርጎ ይዞ መቀጠል ነው፡፡ ችግሮቹን እኛው ፈጠርናቸው፤ መፍትሔውንም እኛው ማምጣት እንችላለን፡፡
አንዱ የሌላውን ታሪክና ባሕል ሊፈልገው የሚገባው ያለእርሱ ሙሉ ስለማይሆን ነው፡፡ የጎደለብንን ፍለጋ ወደ ሌሎች ወገኖቻችን መሄድ አለብን፡፡ እዚያ ስንሄድ ሌላ ነገር ሳይሆን የምናገኘው ጎድሎ የቀረብንን የራሳችንን ነው የምናገኘው፡፡ የኢትዮጵያ ተቃራኒ ትርክቶችን የማቃኛው መንገድ ማሟላት ነው፡፡ መግፋትና ማጥፋት አይደለም – ይላል ሽመልስ፡፡
የቤተ መንግሥቱን የሙዝየም ሥራ ለልዩ ልዩ አካላት በሚያስጎበኝበት ጊዜ – ያለፉትን ታሪኮቻችንን በጋራ መቀበል፣ ችግሮቹንም በጋራ ማረም፣ የዛሬውንም በጋራ መጻፍ እንደሚገባን በአጽንዖት ያነሣ ነበር፡፡
ከዚህ ሰው ጋር ላለፉት ስድስት ወራት አብሬው ሠርቻለሁ፡፡ እጅግ የተወሳሰቡ ነገሮችን ማቅለል፤ መክሊት ካለው ሰው ጋር ሁሉ መሥራት፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማየት፣ ሊሞግቱትና ሊከራከሩት የሚችሉትን ሁሉ በጨዋነት መስማትና መቀበል፣ ነገሮችን በቀናነት መውሰድ፣ እጅግ መንግሥትን ከሚቃወሙ አጥብቀው እስከሚደግፉ፤ ከወጣቶች እስከ አንጋፋዎች ለመነጋገርና አብሮ ለመሥራት መዘጋጀት ስጦታዎቹ ናቸው፤ – ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ ከቀልድና ጨዋታ ዐዋቂነት ጋር፡፡
ሽመልስ አብዲሳ፡፡
(ስንቀልድ የአብዲሳ አጋ ልጅ እንለዋለን)፡፡
ዛሬ የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡ ሽመልስ ኢትዮጵያን በተረዳበት መንገድ ክልሉን ከመራው ለኢትዮጵያ መጻዒ ዕድሏ ብሩኅ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ በሞያቸውና በዕውቀታቸው ቢያግዙት የምንፈልጋትን ሀገር ለማግኘት አንዱ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

Filed in: Amharic