>
5:13 pm - Wednesday April 18, 6198

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሰራጨትን ለመከልከል የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረበ አስተያየት፤ (ውብሸት ሙላት)

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሰራጨትን ለመከልከል የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረበ አስተያየት፤
ውብሸት ሙላት
ይህ ጽሑፍ የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሰራጨትን ለመከላከል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተዘጋጀዉን ረቂቅ አዋጅ የሚመለከት ነዉ፡፡
 የዚህ ጽሑፍ መንፈስም የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል ሕግ መዉጣቱን በመደገፍ ነገር ግን ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ የማይጻረር፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ካጸደቀቻቸዉና ዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ ደረጃ ከደረሱት የሰብአዊ መብት ሰነዶች፣ እንዲሁም እንዲያሳካ የሚታሰበዉን ግብ ስቶ በተቃራኒዉ የዜጎችን መብት ለማፈንና ለመጨፍለቅ በሚመች መልኩ የመንግሥት የአፈና መሣሪያ እንዳይሆን መፈተሸ ነዉ፡፡ በመሆኑም ከመግቢያዉ በመጀመር የተወሰኑ ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦችን በመምረጥ ቀረበ ነዉ፡፡
መግቢያዉና_ዓላማዎቹ
መግቢያዉ አጭር የሚባል ነዉ፡፡ የጥላቻንም ይሁን ሃሰተኛ ንግግሮችን ለመከልከል ያስፈለገበትን ምክንያቶች አሳማኝ በሆኑ መልኩ ይዟል የሚያሰኝ አይደለም፡፡  የመጀመሪያዉን የመግቢያ ሐረግ ብንመለከት “ሰብአዊ ክብርን የሚገረስሱና ሆን ተብሎ የሚሠራጩ ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” የሚል ነዉ፡፡  ይህ ሐረግ ስለ ሐሰተኛ ንግግር ነዉ፤የጥላቻ ንግግርን አልያዘም፡፡ ከዚህ የምንረዳዉ የክልከላዉ መለኪያ የሆኑት ሐሰተኛ ንግግር መሆኑ፣ ሆን ተብሎ መሠራጨቱ፣ እንደሁም ሰብአዊ ክብርን የሚጥስ መሆኑ ነዉ፡፡
ከመለኪያነትም አልፎ የክልክል ሕግ ለማዉጣት ምክንያት ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡ ሆን ተብሎ የሚነገሩ ሐሰተኛ ንግግሮች ሰብአዊ ክብርን እንዳይገረስሱ ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ነዉ ከዚህ ሐረግ እንደምንረዳዉ ሕግ ማዉጣት ያስፈለገዉ፡፡  ሐሰተኛ ንግግር በመሆኑ ብቻ ለመከልከል ሳይሆን ሆን ተብሎ ሰብአዊ ክብርን የሚገረስሰዉን ነዉ መከልከል የተፈለገዉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰዉ የጻፈዉ ወይም የተናገረዉ ነገር ሐሰት በመሆኑ ብቻ መከልከል አልተፈለገም፡፡
ሁለተኛዉ የመግቢያ ሐረግ ደግሞ “የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትሉት ግጭትና ጉዳት ለእኩልነት፣ለሰላም፣ለዴሞክራሲና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ጠንቅ በመሆኑ” የሚል ነዉ፡፡ ይህ አገላለጽ በራሱ ችግር የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ንግግር ቢደረግ የሐሰት መረጃ ቢሰራጭ ግጭትና ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል በሚል ምክንያት ንግግርን ማቀብ ይቻላል ወይ? ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (6) ይስማማል ወይ? ይሄ ደግሞ ወደ ቀጣዩ ሦስተኛዉ መግቢያዊ ሐረግን እንድንመለከት ያንደረድረናል፡፡
ሦስተኛዉ የመግቢያዉ ሐረግ እንዲህ ይላል፡፡ “መሠረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ዉስጥ ተቀባይነት ያለዉን ዓለማ ለማስፈጸም የሚወጡና ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸዉ በመገንዘብ” ነዉ ይላል፡፡
ይህ አገላለጽ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የሚኖሩ ገደቦችን ብቻ ሳይሆን በጥቅሉ መሠረታዊ የሚባሉ መብቶች ላይ እንዴት ገደብ ሊጣል እንደሚችል መርሖቹን ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ (ሰብአዊ) መብቶች ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ገደቦችን አንድ ወጥ መርሕ በማስቀመጥ መገደብን አልመረጠም፡፡
ይልቁንም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተዘረዘሩ መብቶችን ለእያንዳንዳቸዉ በምን ሁኔታ ሊገደቡ እንደሚችሉ ለይቶ ማስቀመጥን ተከትሏል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 26 ላይ የተገለጸዉ የግል ሕይወት መከበርና መጠበቅ መብት ገደብ ሊደረግ የሚችለዉ “ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደኅንነትን፣የሕዝብ ን ሰላም፣ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነጻነት የማስከበር ዓላማዎች ላይ የተመሠረቱ ዝርዝር ሕጎች መሠረት ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ሊገደብ አይችልም” በማለት ገደቦቹን በተናጠል አስቀምጧል፡፡
አንቀጽ 27 ላይ ዋስትና የተሠጠዉ የሃይማኖት፣የእምነትና የአመለካከት ነጻነት ሊገደብ የሚችለዉ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በተገለጸዉ አኳን ነዉ፡፡ እነዚህም፣ “የሕዝብን ደኅንነት፣ሰላምን፣ጤናን፣ትምህርትን፣የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ነጻነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ  መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል” በማለት በአንቀጽ 26 ላይ ከተገለጹት ገደቦችን በመጠኑ ለየት ባለ መልኩ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡
በአንጻሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ ጥበቃ የተሰጠዉ የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት ገደብ ሊኖረዉ የሚችለዉ” የወጣቶችን ደኅንነት፣የሰዉን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች  እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የዐደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች”ን መሠረት በማድረግ እንደሚሆን በማያሻመ ቋንቋ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡
ከላይ እንደቀረቡት ሦስቱ አንቀጾች ሁሉ አንቀጽ 29 ላይ ዋስትና የተሰጠዉ አመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት የሚገደብባቸዉ ሁኔታዎችም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 6 ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም  የወጣቶችን ደኅንነት፣የሰዉን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች  እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የዐደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች አማካይነት ካልሆነ በስተቀር በሌላ ምክንያት ክልከላ አይደረገም የሚሉት ናቸዉ፡፡
ከእነዚህ አንቀጾች የምንረዳዉ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ እያንዳቸዉ መብቶች በምን ሁኔታ ሊገደቡ እንደሚችሉ በተናጠል ማስቀመጥን የመረጠ መሆኑን ነዉ፡፡
መግቢያዉ ላይ ከተቀመጠዉ በተጨማሪም አዋጁ ማሳካት የፈለጋቸዉን ዓለማዎች አንቀጽ ሦስት ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ እነዘህም “ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲጎለብት ማድረግ፤  ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መስፋፋትን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከል እና መቀነስ ናቸው።” በማለት በሦስት ንዑሳን አንቀጾች ለይቶ አስቀምጧቸዋል፡፡ እነዚህ ዓላማዎችም ይሁኑ ከላይ በመግቢያዉ ላይ የተገለጹት ሕገ መንግሥታዊነታቸዉን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስም ቃልም ጋር የማይጋጭ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ መብቶች ላይ የሚኖሩ ገደቦች አስቀድመዉ በሕግ መታወቅ ያለባቸዉ መሆኑን እንደደጋፊ ምክንያት ማቅረቡ ከላይ ባየናቸዉ ምሳሌዎችም ላይ ቢሆን በሕግ መሠረት ብቻ ሊገደቡ እንደሚችሉ ስለተገለጸ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ረቂቅ አዋጁ የተከተለዉ የገደብ ፍኖት ሕገ መንግሥቱ ከጅምሩም አልተከተለዉም፤አልመረጠዉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተወዉን በጅምላ ለሁሉም መብቶች ገደብ የሚጣልበትን ሁኔታ ነዉ ረቂቁ አዋጁ የመረጠዉ፡፡ ይህ ዓይነቱ የገደብ ፍኖት በአዉሮፓዉያን ዘንድ የታወቀ ነዉ፡፡ ተግባራዊ ያደረጉትም ይሄንኑ ነዉ፡፡
እዚህ ላይ አንድ ሊነሳ የሚችል መከራከሪያን መገመት ይቻላል፡፡ ይኸዉም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 (2) ላይ የተገለጸዉን መነሻ በማድረግ የሚቀርብ ነዉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጹት የሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ተቀብላ ካጸደቀቻቸዉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጋር የተጣጣመ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ስለተገለጸ በእነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች ላይ የተቀመጡትን የመገደቢያ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባ የሚቀርብ ክርክር ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከእነዚህ የሰብአዊ መብት ሰነዶች በተሻለ ሁኔታ የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያደርግ በሚሆንበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነዉ የሚሻለዉን እንጂ መብት የሚያጣብበዉ ሊሆን አይችልም፡፡
 ሕገ መንግሥቱ ላይ የአመለካከትና ሐሳብን የመግለጽ መብትና ነጻነት የሚገደቡበት ሁኔታ ተዘርዝረዉ በተቀመጡበት፣ እንደዉም ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶቹ ጋር የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የማያጣብብም የማይጋጭም ስለሆነ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች በመተዉ ሌሎች ግቦችንና የሚገደቡባቸዉ ሁኔታዎችን መዉሰዱ ተገቢነትም አሳማኝነትም አይኖረዉም፡፡
ንግግር_የጥላቻንግግርና_ሐሰተኛ_መረጃ
ረቂቅ አዋጁ ዉስጥ የተካተቱ ሦስት ቁልፍ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ፡፡ እነዚህም ‘ንግግር’፣ ‘የጥላቻ ንግግር’ እና ‘ሐሰተኛ መረጃ’ የሚሉት ናቸዉ፡፡ ንግግር የሚለዉ ቃል ከተለምዷዊ ትርጉሙ የሰፋ ሐሳብን በመያዝ “በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልእክትን የማስተላለፍ ተግባር  እንደሆነ ብያኔ ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም፣ በቃል ብቻ ሐሳብ መግለጽ ላይ ሳይወሰን በጽሑፍም በምስልና ቅርጻ ቅርጽም ጭምር የሚተላለፍ መልእክት በሙሉ ንግግር ነዉ ማለት ነዉ፡፡
 ንግግር ይህን ትርጓሜ በመያዝ  የጥላቻ የሚሆንበትንም እንዲሁ ረቂቁ አዋጁ ሁለተኛ ብያኔ አስቀምጧል፡፡ የተሰጠዉ ብያኔም እንደሚከተለዉ ነዉ፡፡ “የጥላቻ ንግግር” ማለት የሌላን ግለሰብን፤ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ቀለምን፤ ጾታን፤ አካል ጉዳተኝነትን፤ ዜግነትን፤ ስደተኝነትን፤ ቋንቋን፤ ዉጪያዊ ገጽታን፤ መሰረት በማድረግ ፣ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል፤ የሚያንኳስስ፤ የሚያስፈራራ፤ መድልዎ እንዲፈጸም፤ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ነው።
ይህ ብያኔ ለብዙ ትችት የተጋለጠ፣ ዉሎ አድሮም ከታሰበለት ዓላማ ዉጭ ጥቅም ላይ ለማዋል ደረቱን ገልጦ የሰጠ አንቀጽ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተከሠተ ያለዉ እና የዜጎችንም መብትና የተለያዩ ማኅበራዊ መደብ ያላቸዉን ቡድኖች ጉዳት ላይ በመጣል የአገሪቱንም ሕልዉና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዐዉድን ነቅሶ ማዉጣት ተገቢ ነዉ፡፡
በዚህ ረገድ ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እየበዙ እና ዜጎችንም ብሔራቸዉንና ሃይማኖታቸዉን መሠረት በማድረግ ጉዳት እየደረሰባቸዉ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በተለይ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ ጥላቻ ወለድ ወንጀሎችም ተበራክተዋል፡፡
በዚህ ብያኔ ላይ ንግግሩ፣ ጾታን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ንግግር ለአገሪቱ አደጋ ነዉ ወይ? ወንድን የምትጠላ ሴት ‘እናንተ ወንዶች እንዲህ ናችሁ’ በማለት ባሏን ወይም የወንድ ጓደኛዋን ብትሳደብ፣ ወይም በተቃራኒዉ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት በዚህ መልኩ ቢናገር ሴቶችና ወንዶችን በሁለት ጎራ አለያይቶ የአገርን ሰላም ያዉካል፣ ጥቃት እንዲፈጸም ያነሳሳል የሚለዉ ተጠየቃዊ ነዉ ማለት አስቸጋሪ ነዉ፡፡
ልክ እንደዚሁ ሁሉ፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዉጫዊ የአካል ገጽታን ዜግነትን መሠረት አድርጎ የሚደረጉ ስድባና የሚያዋርዱ ንግግሮች ጉዳት ደረሰብኝ በሚለዉ ሰዉ አመልካችነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አማካይነት የሚታይ ቢሆን የተሻለ ነዉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አገራት (ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ) ከእነዚህም የበለጡ ሌሎች ማኅበራዊ አቋሞችን መሠረት አድርጎ የሚፈጸሙ ንግግሮችን የጥላቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ደንግገዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ትኩረታቸዉ ንግግሩ ላይ ብቻ ሳይገደብ በተጨባጭ ወንጀል ሲፈጸም መቅጣትንም ይጨምራል፡፡
የጥላቻ ንግግርን ብያኔ ከእንደገና በረቂቁ አንቀጽ 4 ላይ በማስቀመጥ ንግግሩ የሚተላለፍባቸዉን የመገናኛ ወይም የማሰራጫ ዘዴዎች ጨምሯል፡፡ ክልከላዉንም በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የጥላቻ ንግግሮች የያዙ መልእክቶችን መናገር፣ ጽሑፍ መጻፍ፣የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ወጤትችን መሥራት፣እነዚህን ድርጊቶች በድምጽ ወይም በምስል አዘጋጅቶ ማሳተም ወይም ማሰራጨትንም ይይዛል፡፡ እነዚህ አንቀጽ 4(1) ከፊደል ‘ሀ’ እስከ ‘መ’ ድረስ የተዘረዘሩት ናቸዉ፡፡
እነዚህ ድንጋጌዎች እንዳሉ አሁን ባሉበት ሁኔታ ከጸደቁ ፖሊስ እና ዓቃቤ ሕግ የማይኖራቸዉ ሥልጣን መኖሩ በራሱ አጠራጣሪ ነዉ፡፡ የተከለከለዉ በጽሑፍ አዘጋጅቶ ማሠራጨት ሳይሆን መጻፍም ጭምር ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ በድንገት የማስታወሻ ደብተሩ ላይ በማናቸዉም አጋጣሚ የጻፈዉን ጽሑፍ፣ ማሰራጨት ባይፈልግም እንኳን ሊያስቀጣዉ ይችላል፡፡ አንድ ሠዓሊ በግል ቤቱ የሚያስቀምጠዉ አንድ ሥዕል ሠርቶ ቢገኝ እና ፖሊስ ቢደርስበት በዚህ ድንጋጌ መሠረት ይቀጣል፡፡
በተለይ ከ ‘ሀ’ እስከ ‘ሐ’ ድረስ ያሉትን በማናቸዉም መንገድ ማሠራጨትን ወይም ሌላ ሰዉ ጋር መድረሳቸዉን በቅድመ ሁኔታነት አላስቀመጠም፡፡ እንደዉም ይህንን አቋም አጠናክሮ፣ ይሔዉ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ “ለሦስተኛ ወገን ወይም ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ በማሰብ ይዞ መገኘት” ክልክል እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይህ አገላለጽ ለትርጉም እጅግ ሰፊ ዕድል ስለሚሰጥ ግላዊነትንም (Privacy) ለከፋ አደጋ ያጋልጣል፡፡ አንድ ሰዉ ሞባይል ስልክ ቀፎዉን እንደ ማስታወሻ ቢጠቀም፣እዚያ ላይ የጻፈዉ ነገር በሙሉ እየተበረበረ ምን ጽሑፍ አስፍረሃል ሊባል ነዉ፡፡ የጻፈዉ ነገር በማስታወሻነትም ይሁን በግላዊ ባሕርይ ምክንያት ጽፎ በግሉ የያዘዉ ሁሉ ለማሰራጨት አስቦ ነዉ ሞባይሉ ወይም ኮምፒተሩ ላይ የጻፈዉ የመባል ዕድሉ እጅግ በጣም ሰፊ ነዉ፡፡ በዚያ ላይ ‘ለማሰራጨት አስቦ ነው’ ወይም ‘ለማሰራጨት አስቤ አይደለም’ የጻፍኩት የሚለዉን ማስረዳት ለፖሊስፕ ለተከሳሽም እጅግ አዳጋች ነዉ፡፡
በዚሁ አንቀጽ 4(1) (ሠ እና ረ) ላይ መልእክቶችን በብሮድካስት (በቴሌቪዥንና ሬዲዮ) እና በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨትን ለይቶ ከልክሏል፡፡ እንደዉም በማናቸዉም ሌላ ዘዴ ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግንም ጨምሮ አስቀምጧል፡፡ በእነዚህ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ላይ የተቀመጠዉ አገላለጽ ከላይ የቀረበዉን፣ ሳይሰራጩም ጭምር፣ ሊስቀጡ እንደሚችሉ የበለጠ ያጠናክራል፡፡ ማሰራጨትን በሚመለከት፣ ተሰራጭቷል ለመባል በመጀመሪያ ‘ሕዝብ’ የሚለዉ ስንት ሰዉ እንደሆነም አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዉ በስልክ አጭር መልእክት ለአንድ ሰዉ ላከ፡፡ ወይንም በፌስቡክ የዉስጥ መልእክት መላኪያ በመጠቀም ለአንድ ወይም ሁለት ሰዉ መልእክት ላከ፡፡ እነዚህ ለሕዝብ እንደ ደረሱ ይቆጠራልን? ለአንድ ሰዉ የተላከ መልእክት ኖሮ፣ መልእክቱ የደረሰዉ ሰዉ ለሕዝብ ቢያደርሰዉ የሚጠየቀው የትኛዉ ሰዉ ነዉ?
ሦስተኛዉ ብያኔ የተሰጠዉ ሐረግ “ሐስተኛ መረጃ” የሚለዉ ነዉ፡፡ ብያኔዉም “የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት የሆነና ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ክፍ ያለ ንግግር ነው” የሚል ነዉ፡፡
ይህ ድንጋጌ ለፖሊስም፣ ለዓቃቤ ሕግም ለዳኞችም ሰፊ ሥልጣን የሰጠ ነዉ፡፡ ‘የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ’ የሚለዉ አገላለጽ በንግግሩ ዉስጥ የተካተተዉን የሐሰትነት መጠን ወደመሆን ይወስደዋል፡፡በዚያ ላይ አመለካከትና ጥሬ መረጃን የለየ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ሁከትና ግጭት የማስነሳት ዕድሉ ከፍ ያለ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉም እንዲሁ ወደተፈለገበት አቅጣጫ ተጠምዛዥ ነዉ፡፡
ይህንን ሐሰተኛ መረጃ የማሰራጨት ተግባርን በግልጽ የከለከለዉ አንቀጽ አምስት ነዉ፡፡ በማናቸዉም መልኩ ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግ ወንጀል ነዉ፡፡ የሐሰት መረጃ ያሰራጨ ሰዉ እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ አሰራጩ ሰዉ በማኅበራዊ ሚዲያ ከአምስት ሺ ሰዉ በላይ ተከታይ ካለዉ፣ በብሮድካስት ወይም በየጊዜዉ በሚወጣ ህትመት (ጋዜጣ፣መጽሔት ወዘተ) ከሆነ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት፣ ወይም እስከ አስር ሺ ብር የሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡ በሐሰተኛ መረጃዉ ምክንያት ተነሳስቶ ጥቃት ከተፈጸመ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት የሚደረስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡  የሐሰት መረጃ ማሰራጨት፣ በዚህ መልኩ በሦስት ምድብ የተከፋፈሉ ቅጣቶችን ያስከትላል፡፡
የጥላቻ ወንጀልን ጥሎ ንግግርን አንጠልጥሎ
ከዚህ ባለፈ ግን የጥላቻ ንግግርን ወንጀል አድርጎ፣ በጥላቻ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ወንጀል አለማድረግም ሌላዉ የዚህ ረቂቅ ጉድለት ነዉ፡፡ አንድን ሰዉ የሆነ ብሔር ተወላጅ በመሆኑ ብቻ አንድ የሌላ ብሔር ተወላጅ በጥላቻ ተነሳስቶ የአካል ጉዳት ቢያደርስበት ወይንም ቢገድለዉ ከጥላቻ ንግግሩ በከፋ ሁኔታ ማኅበራዊ ሰላምን የሚነፍግ ብሎም የብሔር ግጭት እንደሚፈጥር እሙን ነዉ፡፡
ንግግርን ከተራ ስድብነት ወይንም ስም የማጥፋት ወንጀል ለይቶ የወንጀል ቅጣቱ ከፍ እንዲል ከተደረገ በተመሳሳይና እንደዉም የበለጠ አሳማኝ የሚሆነዉ በጥላቻ ተነሳስቶ መድልኦ የፈጸመ፣ጥቃት ያደረሰ ሰዉ በተለየ ሁኔታ ከፍ ያለ ቅጣት ሊቀመጥለት ይገባል፡፡ ስለሆነም የጥላቻ ንግግር በባሕርይዉ ወንጀል እንዲፈጸም ስለሚያነሳሳ ነዉ ወንጀል የተደረገዉ፡፡ በንግግሩ ተነሳስቶ ወይንም በንግግሩ ምትክ ሌላ ወንጀል ሲፈጸም የበለጠ የሚስቀጣ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
በተጸዉኦ ስም መጻፍ እንደ ወንጀል
የፌስ ቡክ (ቲዉተር፣ሊንክድኢን ወዘተ) አካዉንት (ስም) በትክክለኛ መጠሪያ ስምና አድራሻ የማይጽፍ ሰዉን በሚመለከት ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለዉም፡፡ ማንነቱ ሳይገለጽ በሌላ ስም በመጠቀም የጥላቻ ንግግር የሚያስተላልፍ ሰዉ ቢኖር፣ የፌስቡክ አድራሻዉ (አካዉንቱ) ሊዘጋበት ነዉ ወይስ ምን ሊደረግ ነዉ? ረቂቅ ሕጉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለዉ በስማቸዉ ለሚጽፉ ሰዎች ብቻ ስለሚሆን፣ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሰዎች ትክክለኛ ስማቸዉን ከመጠቀም ይልቅ ሌላ ስም መጠቀምን እንዲመርጡ ያበረታታል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ መንግሥት በትክክለኛ የተጸዉኦ ስም የማይጠቀሙትን በመዝጋት ወይም ወይም ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳይታዩ በማድረግ ሥራ ይጠመዳል ማለት ነዉ፡፡ በእርግጥ ይኼን እዉን ማድረግ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፡፡
በአጭሩ፣ ተፈጻሚነቱ በተጸዉኦ ስም የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሰዎችን ላይ እንጂ በሌላ ስም የሚጠቀሙትን አይጨምርም፡፡
ከኢትዮጵያ ዉጭ ሆነዉ የሚናገሩትንስ/ሚጽፉትንስ?
የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰት መረጃ ማሠራጨትን ወንጀል ለማድረግ የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ዉጭ ሆነዉ የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰት መረጃ የሚያሠራጭ ሰዎችን በምን መንገድ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚቻል ድንጋጌ የለዉም፡፡ ስለሆነም፣ በጥላቻ ንግግርም ይሁን በሐሰት መረጃ በወንጀል ሊከሰሱ የሚችሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩ ብቻ መሆናቸዉ ነዉ፡፡
በመሆኑም፣ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች የመሆን ዕድል ያላቸዉን ጽሑፎች አንድም በግል ስማቸዉ ለማይጠቀሙ፣ሁለትም ከኢትዮጵያ ዉጭ በሚኖሩ ሰዎች አማካይነት መሰራጨትን ያበረታታል እንጂ ዓላማዉን ማሳካት አይችልም፡፡ በተጨማሪም አድሏዊ  ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሆኖ መጻፍ ብቻ ያስቀጣል፡፡ ጉዳያቸዉ በሌሉበት የሚታይ ወንጀልም አይደለም፤ ምክንያቱም በሌሉበት ለመታየት ቅጣቱ ከአስራ ሁለት ዓመት በላይ የሚያሳስር መሆን ስላለበት ነዉ፡፡
በስርጭት_ላይ_ያሉትስ?
የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰት መረጃ ማሰራጨትን ለመቆጣጠር የተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ  ከአሁን በፊት ተዘጋጅተዉ የተሰራጩ፣ እና በሥራ ላይ ያሉ ወይም ተደራሽ የሆኑ ሰነዶች፣ካሴቶች ወዘተ ላይ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችና የሐሰት መረጃዎችን በሚመለከት ዕጣ ፋንታቸዉ ምን እንደሚሆን የሚገልጸዉ ነገር የለም፡፡
የመንግሥት የፖሊሲ ሰነዶች፣የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት፣ ግለሰቦች ያሳተሟቸዉ መጽሐፍት፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ካሴቶች፣ በዩቲዩብና መሠል ማሰራጫ ላይ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችን በሚመለከት የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ስርጭታቸዉ ይቀጥላል፡፡
ቀድሞ ስለተገለጸ ወይም ስለተጻፈ ወይም ስለተሰራጨ ተብሎ አሁንም ስርጭቱ ይቀጥላልን ወይስ ይቋረጣልን ያስቀጣልን  ከዚሁ ጋር ተያያዞ፣ እንዲህ ዓይነቱን የጥላቻ ንግግር የሚቆጣጠረዉ አካል (ብሮድካስት ባለሥልጣን) የሚታተሙ መጽሐፍትን ጋዜጣን፣ መጽሔትን፣ በኢንተርኔት የሚለቀቁ ንግግሮችን ሁሉ የማንበብ አቅምና ችሎታ እንዴት ሊኖረዉ ይችላል?  ወይንስ ደግሞ፣ ቢያንስ ለመጽሐፍ፣መጽሔት፣ ወዘተ…ሲሆን ቅድመ ሕትመት ምርመራና ፈቃድ (ሳንሱር) ሊኖር ነዉን?
የፍርድ_ቤት_ሥልጣን
የኢንተርኔት መከሠት የስም ማጥፋት ሕግን ሲበዛ ዉስብስብ አድርጎታል፡፡ አንድ አገር ላይ ተሁኖ የተለቀቀን ጽሑፍ፣የድምጽ ወይም የምስል መልእክት ኢንተርኔት ባለበት አገራት ሁሉ ይገኛል፡፡ የጥላቻ ንግግሩም ይባል የሐሰት መረጃዉ መነሻ የሆነዉ ድርጊት የሆነ አገር ላይ የለቀቃል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ ድርጊቱ ከተፈጸመበት በተጨማሪ ሌሎች አገርም ላይ ይፈጸማል፡፡
አሜሪካ ሆኖ ስለ አንድ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖርን ሰዉ ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ ዓይነት መደብ ሲከቀቅ  ይህንን ስም አጥፊዉን ጽሑፍ፣ንግግር፣ምስል ወዘተ በመላዉ ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወይም ሌላ ሰዉ ጭምር ሊያየዉ ይችላል፡፡
እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳት የደረሰበት ሰዉ መብቱን ለማስከበር የሚጠቀማቸዉ አማራጮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና አዳጋች እየሆኑ ነዉ፡፡  እየተወሳሰበ የመጣዉ፣ ኢንተርኔት ድንበር ስለማያዉቅ፣ መብትና ግዴታን የሚወስኑት ደግሞ በድንበር የተገደቡ አገራት በመሆናቸዉ ነዉ፡፡
በአንዱ አገር ስም የሚያጠፋ ነዉ የሚያሰኝ ጽሑፍ ወይም ንግግር በሌላ አገር ሕግ የተፈቀደ ይሆናል፡፡ ድርጊቱ በራሱ ስም የሚጠፋ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉም እንደየማኅበረሰቡ ሲለያይ፣ኢንተርኔት አገር ስለሌለዉ የተለየ ማኅበረስብ የለዉም፡፡ ስለሆነም በየትኛዉ ማኅበረሰብ አኳያ ጽሑፉ ወይም ንግግሩ ለመልካም ስም ተቃራኒ ነዉ ይባል?
በኢንተርኔት ዓለም የፍርድ ቤት ሥልጣን የሰከነ የሕግ ሥርዓት ላይ አልደረሰም፡፡ አይደለም በተለያዩ አገራት መካከል ስለሚኖረዉ ይቅርና በፌደራል ሥርዓት የሚመሩ አገራትም ከፈተና አልተላቀቁም፡፡
በተለይ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በሚመለከት ሕግ የማዉጣት ሥልጣኑ ለክልሎች ከሆነ የዉስብስብነት ደረጃዉ ይጨምራል፡፡ የኢትዮጵያን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በሚመለከት ሕግ የማዉጣት ችሎታ/ሥልጣን ለክልሎች የተተወ ነዉ፡፡ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የየትኛዉ ፍርድ ቤት ነዉ የግዛት የዳኝነት ሥልጣን የሚባል አለ ወይ?
በግል አመልካችነት ወይስ በክስ?
በጥላቻ ንግግር የሚቀርብ የወንጀል ክስ የግል ተበዳይ የሆነ ሰዉ ሲያመለክት (Upon Complaint) ነዉ ክስ የሚመሠረት ወይስ ደግሞ የሕዝብ ጥቅምን እንደሚጻረር እንደማንኛዉም ሌላ ወንጀል የግል ተበዳይ አቤቱታ ባያቀርብም (Upon Accusation) ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ይችላልን? ይሄም ሊመለስ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንዳንድ ሰዉ በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ የመገናኛ ዘዴ የጥላቻ ንግግር የሆነ ስድብ ወይም የሚያዋርድ ንግግር ቢፈጸምበትም እንኳን፣ ክስ ማቅረብ የማይፈልግ ይኖራል፡፡
በዚህን ጊዜ የግለሰቦቹ ምርጫን በማክበር የወንጀል ተግባሩን ምርመራ እንዳይጀመር ይደረጋልን? በሌላ መልኩ ደግሞ ቀጥታ ንግግሩ ያተኮረዉ አንድ ሰዉ ላይ ቢሆንም እንኳን ሌሎች ሰዎችን በማነሳስት የበለጠ ንትርክ ዉስጥ በመክተት በብሔር መካከል ጥላቻ እንዲበረታ የሚያደርግ ቢሆንስ? ለማንኛዉም እንዲህ ዓይነቶቹ ጉዳዮች የፖሊሲ አማራጮች ስለሆኑ ጥልቅ ፍተሻ በማድረግ የተሻለዉን አማራጭ መከተል የመንግሥት ሥልጣን ነዉ፡፡
ለማጠቃለል ያህል፣ረቂቅ አዋጁ በመግቢያዉ ላይ ከያዛቸዉ መነሻዎች ጀምሮ ዓላማዉንም ጭምር ከእንደገና በጥልቀት መፈተሽ አስፈላጊ ነዉ፡፡ በተጨማሪም ስለ ጥላቻ ንግግርም ይሁን ሐሰተኛ መረጃ መያዝና ማሠራጨት ወንጀል የሚሆኑትን መሆን ከሌለባቸዉ ከእንደገና አጥርቶ የመለየት ሥራ ማከናወንን ይጠይቃል፡፡
እንዲሁም፣ያላለቁ ጉዳዮች ስላሉት እና ደንብ በማዉጣት የማይሸፈኑ ስለሆኑ ድጋሜ ማጤን ተገቢ ነዉ፡፡ ከላይ የቀረቡት በጣም ጥቂት የሚባሉት ነጥቦች እንጂ፣ በዝርዝር ቢታይስ ብዙ ነገር አለዉ፡፡ ሰዉ የመሰለዉን ሐሳብ በግላዊ ቁሳቁሶቹ ላይ ማስቀመጥን ሳይቀር ወንጀል ማድረግ ሕጉንም አዉጭዉንም መጥላት ነዉ ትርፉ የሚሆነዉ፡፡
Filed in: Amharic