>

የአድሎና የሴራ ፖለቲካ ማብቂያው የት ይሆን?!? (ሉሉ ከበደ)

የአድሎና የሴራ ፖለቲካ ማብቂያው የት ይሆን?!?
ሉሉ ከበደ
ያለፈውን አንድ አመት የተታለልንበት የተሞኘንበት አመት አድርገን እንቁጠረው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀያሰባት አመታት የተራበውን ቃላት  ሰብስቦ ፥የኢትዮጵያን ስም አንግሶ ፤አወድሶ ፥ በየመድረኩ እንደ ተዋጣለት ተዋናይ በሚማርክ አንደበት መነባንቡን ሲያሰማን አደነቅነው።ወደድነው ።. እውነተኛም ሰው ኢትዮጵያዊው ሙሴ ድንገት ተወለደ ብለንም ድምጻችንን ከፍ አድርገን አሞገስነው። ኢህአዴግ መሆኑ እስኪዘነጋን።
መታሰር ያልነበረበትን ራሳቸው ያሰሩትን ህዝብ ሲፈታ ደነቀን። ራሳቸው ካገር ያሳደዱትን የፖለቲካም የሀይማኖትም መሪ ሁሉ መልሶ ሲጠራ ደነቀን።ከንግዲህ ማሳደድ፤ ማሰር ፥መግደል  ፤ ሸፍጥ ፥ተንኮል ፤ በኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር ውስጥ አይኖርም ብለን ገመትን።  የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል ሲለን የኢትዮጵያ ህዝብ በነጻነት መሪውን የሚሚርጥበት ቀን ደረሰ ብለንም አመን። እስከመጨረሻውም ደገፍነው። ሞትንለትም። አሁን ግን ዶክተር አብይ ከነ ድርጅት ጓደኞቹ ሌላ አይነት ሰዎች መሆናቸው በአንድ አመት ድርጊታ ቸው አረጋግጠውልናል።
በማንም ላይ ይላከክ በምንም ምክንያት ነው ይበሉ ፥ በዚች ኢትዮጵያ በምንላት ምድር ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ሁሉ  በራሳችው እውቅናና ስውር ተሳትፎ የሚከናወን ነው። አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ፥  ይሁን። ለውጡን የማይሹት ናቸው፤ ጥቅማቸው የቀረባቸው ናቸው፤ ወያኔዎቹ ናቸው   አልን ። የነዚህ ወገኖች ድርሻ መኖሩ ባይካድም  ድፍን አንድ አመት ባለማቋረጥ ህዝብ እየተገደለ በሚሊዮን በአራቱም አቅጣጫ ከመኖሪያው ይፈናቀላል? ሀገሪቱ ጦር ሀይል አላት አንድ ነገር እናድርግ እንኳን አይባልም ? መንግስት አለ በተባለበት አገር ውስጥ በዚችው በኢትዮጵያ ምድር አስራሰባት ባንክ የዘረፈ ቡድን የዘረፈውን ገንዘብ ይዞ እዚችው ምድር ላይ ኑሮውን በሰላም ይቀጥላል? ሀያሰባት አመት ወያኔ የዘረፈው ይመለሳል ብለን ስንጠብቅ ነበር ። ለናሙና የሆኑ ሰዎች ታሰሩ ሀገሪቱን ያራቆተው ዘራፊ ጉዳይ እዚያ ላይ ቆመ።
 ሌሎች አዳዲስ ዘራፊዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው አመቱ ተጠናቀቀ። አመቱን በሙሉ ዶክተር አብይ ከህውሀት የተነጠቀውን ቁልፍ የስልጣንና የስራ ሀላፊነት የኦሮሞ ተወላጆችን ሲተካበት ነው የከረመው። ከህውሀት የበላይነት ወደ ኦነግ የበላይነት እንኳን በሰላም ተሸጋገርን። ኦነግም አርባ አመት በረሀ ለበረሃ ሲንከራተት ያልቻለውን ሎተሪ ወጣለት ኢትዮጵያ መዳፉ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ልትገባ ጥቂት ቀናቶች ይቀሩታል። እነለማ አብይ ይጨርሱታል። እንኳን ደስ ያለው።
እዚችው እነሱ የሚገዟት ምድር ውስጥ ኦነግ አዳዲስ ወጣቶችን መልምሎ የሚበቃውን ያህል ወታደር አሰልጥኖ አስታጥቆ በስላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲከፍት አያውቁም? አይሰሙም?  ያለፈውን እንኳን ትተን ሰሞኑን ሰሜንሸዋ እጣዬ ወሎ ከሚሴ ህዝብ ሲጨፈጨፍ ህዝቡ ማን እየጨፈጨፈው እንዳለ እየተናገረ ፥ ባሉት ባለስልጣናት በሙሉ ማን እንደሆኑ የማይታወቁ ናቸው እየተባለ በህዝብ ሞት ሲፌዝ እየሰማን ለውጥ የመሰለን አዲስ ነውጥ መሆኑን እንዴት አናምንም?
በእጩ ሂትለር ጃዋር መሀመድ ቄሮ ተብሎ ተደራጅቶ በሚዲያ እየተደገፈ ህዝብን የሚጨፈጭፍ ወጣት ሀይል አያውቁም? አላዩም? ጃዋር የፈለገውን ነገር ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያስነሳ ባደባባይ በቴሌቪዥን እየወጣ ሲናገር በሄደበት ሁሉ እንደከብት የሚከተሉት ያበዱ ህጻናት በመንጋ እየወጡ ወንጀል ሲፈጽሙ ህዝብን ሲያሸብሩ ንብረት ሲያወድሙ ሲቀሙ አያዩም አይሰሙም?
ምህዳሩ ሰፍቷል ዲስኩር ዶክተር አብይና ጓደኞቹ አሁንም አላቋረጡም ። የትኛው የዜግነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ ሀሳብ አራማጅ ነው ሀረር ሄዶ ደጋፊ መሰብሰብ የቻለው? ደቡብ ሄዶ ደጋፊ መጥራት የቻለው፧ ባራቱም ማእዘን የትኛው የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነው መንቀሳቀስ የቻለ? ባህርዳር ላይ መሳሪያ አቀባብለው በጠራራ ጸሀይ ባደባባይ  አርበኞች ግንቦት ሰባትን የመጡበት ሰዎች ባጋጣሚ ነው? በዜግነት ፖለቲካ ላይ የተነጣጠረ በራሳቸው ስልጣን ላይ ባሉት ሰዎች የተቀነባበረ ሴራ ደባ ነው።  እስክንድር ነጋ ያዘጋጀውን ህዝባዊ ስብሰባ ያደራጇቸውን ህገወጥ ስራ አጦች ልከው በህዝቡ ደህንነት ላይ   ስጋት ሲያሳድሩ ባጋጣሚ የሆነ ነገርነው? ምህዳሩ ሰፍቷል እህ!! አለመታደል ከሸፍጥ ፖለቲካ የተገላገልን መስሎን ነበር። አታለሉን።
አንድ አመት በቂ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ መረጥበት የትግል ስልት ተመለስ። የጠገበው ጅብ ሄዶ የራበው ነው የተተካው።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር።
Filed in: Amharic