>

ከምንፈጃጅ እንበጃጅ  !!! (ሳዲቅ መሀመድ)

ከምንፈጃጅ እንበጃጅ  !!!
ሳዲቅ መሀመድ
ዘር አስጠላኝ።ለምን ሰው በሰውነት ማእቀፍ ውስጥ ብቻ አይኖርም? ሰው መሆን አይበቃምን? የሚል ውስጣዊ ሙግት ጋር ግብግብ ገጠምኩኝ።ቀናትን ዘለኩኝ። የዘር ምስጢር አምላክ በክህሎቱ የሰራው ነውና በርሱ ስራ መግባት መስሎም ተሰማኝ።አሁንም እራሴን ጠይቃለሁ።ዘር በሚሉት ነገር መንገፍገፌ ለምንድነው ብዬ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ።ለካስ ችግሩ ዘር አልነበረም።በመላው ኢትዮጵያ የጦዘው«ዘረኝነት» ቢሆን እንጂ።
የተጋጋለው ዘረኝነት
ዘረኝነቱ ተጋግሏል።ብዝሃኑ አቅሙ በቻለው መጠን ዘረኛ ሆኗል።የተማረውም ያልተማረውም፤ምእምኑም ሰባኪውም፤ጋዜጠኛውም ታዳሚውም፤ወጣቱም አዛውንቱም፤ሴቱም ወንዱም ሁሉም ወደ ዘሩ ዘሟል።አደጋዉ እዚህ ጋር ነው።ሰዎች ከሰብዓዊነት፣ከሚዛናዊነት፣የወልን ጥቅም ከማስከበር ምህዋር አፈንግጠው በዘር ኮርቻ ላይ ተፈናጠው ሽምጥ ሲጋልቡ አገር ትፈርሳለች።እናም ወዴት እያቀናን ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ግድ ነው።
በመልካም ነገርም ለመተባበርም ዘረኝነት ሚናው ገነነ።ክፉ ለመስራትና ወገንን ለመጉዳት በሚደረጉ ጥረቶች ዘረኝነት የብዙዎች ፍልስፍና ሆነ።እንቅስቃሴዎች በሙሉ በዘረኝነት መስፈርት ይቃኛሉ።አገርን አዳኝ የሆኑ ሸጋ ሐሳቦች ከየትኛው ዘር መነጩ የሚል ፍተሻ ይከናወንባቸዋ።ሰው ተጠራጣሪ ሆኗል።ያንንም ይህንንም ዘረኛ ነው ብሎ ይጠረጥራል። በዘሬ ምክንያት ሰዎች ይጠሉኛል ብሎያስባል።
 ህወሃት የሚሉትን የወል ጠላት በመታገል አብረው የተሰለፉ ሁሉ ዛሬ የወል ጠላታቸው መቀሌ ገብቶ ሲመሽግ ትላንት ህወሃት ሲፈጽመው የነበረውን የላሸቀ ተግባር ተረካቢ ሆነው በዘር ማማ ላይ ከፍ ሲወጡ መስተዋሉ እየተለመደም መጣ።በየመንደሩ በዘር የተደራጀ የጦር አበጋዝ ተበራክቷል።ተሰሚነትን ለማግኘት «ዘሬን ዘሬን» ማለቱ የግድ ሆኗል።ጨኸት በዝቷል።ሁሉም «ዘሬን ዘሬን» እያለ ይጮኻል።ዘረኝነት እንደገድል ማሚቱ ያስተጋባል።ትላንት ‹በርቼ-ጡር› በሚሉት የወል ባህላዊ እሴት ተሳስሮ የኖረው ዛሬ ዘረኝነትን ተንተርሶ ዘግናኝ ስድቦችን ባደባባይ መሳደቡን ቀላል አድርጎታል።
በማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ ወጥተው ገና በማለዳው እንደ ጠዋት ጸሎት የዘረኝነትን ዝማሬ የሚያሰሙ ተበራከቱ።በፕሮፋይላቸው ላይ ምሁር እንደሆኑ እየገለጹ በዘር ማእበል ውስጥ የሚከንፉ፣ዘረኝነትን መሰረት አድርገው ያለማመንታት የሚለፈለፉ በዙ።ሰዎች ባደባባይ ጸያፍ ዘረኝነትን አቀንቃኝ ለመሆን ሐፍረት የላቸውም።ባደባባይ ተናጋሪው የሚያስበን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው።ያሰው መናገር የሚችለውን ተናግሮ መናገር የማይችለውና ምስጢር የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ስጋቱ ያይላል።ብዙዎች በዘረኝነት ሰክረዋል።ስትደግፋቸው የተቃወምካቸው ይመስላቸውና ዘራቸውን ወደ መከላለክል ጎራ ይመጣሉ።ስትቃወማቸው ደግሞ ዘረኛ ስለሆንክ ነው ብለው ዘለው ይፈርጃሉ።ግራ የሚያጋባ ነገር አገሪቷ ውስጥ እንደወረርሽን ተሰራጭቷል።የኢትዮጵያ ነገር ያሰጋል።
ከሁሉም ባገር ነው ወደ ሁሉም በዘር ነው
መኖር፣መስራት፣መንቀሳቀስ፣መማር፣ማስተማር፣መሾም፣መሻርና ሌላም በዘር ሆኗል።በቃ ሁሉም ነገር በዘር አጉሊ መነጽር ነው የሚታየው።ጎረቤት አገር ሱማሊያ ባረፈባት የዘር ስንክሳር ሳቢያ የደረሰባት ተዘንግቷል።የመን ውስጥ እሳት እየተንቀለቀለ ነው።ዩጎዝላቪያ ተበታትናለች።ሶሪያዉያን አገራቸው ውስጥ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ተበታትነው አስጠንቃቂ መልእክተኛ ሊሆኑ ኢትዮጵያ ድረስ ዘልቀው በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተዋል።
የዘረኝነት ስካር መጨረሻው ጦርነት፣መገዳደል፣መፈናቀል፣መሰደድና አገርን ማፈራርስ ነው።እና ምን ይሻለን? ምንስ ያስተምረን? በየትኛው የመኖር ስሌት እንደራደር? ግራ ያጋባል።አገራችን ዉስጥ እየተከሰተ ያለው ግጭት ፈንድቶ ህዝብ ሲጨራረስ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ነው አደብ የሚያስገዛን? የከፋ እልቂት ከተፈጠረ በሗላ በሚቆፈሩት መቃብሮች ብዛትን ስናይ ነው የምንሰክነው? በሚሊዮን የሚቆጠሩ አገርን ለቀው የሚሰደዱት ሰዎች ሁኔታ ነው የሚያስተነፍሰን? ዛሬ የኔ ብለን «አካኪ ዘራፍ» የምንልባቸው ክልሎች ከብሄርና ከብሄረሰብ ግጭትም ባሻገር በጎሳ ግጭት ምክንያት ብትንትናቸው ወጥቶ በሚፈጥረረው ምስቅልቅልታ ነው የምንገራው? ወይስ ትላንት የባህር በሯን ያጣቸው አገር ብትንትኗ ሲወጣና ለማናችንም ሳትሆን ስትቀር  ነው ልክ የምንገባው? ማን ይንገረን ነጋሪ ያጣን ተናጋሪ ሆነናናላ። ደግሞ የርዋንዳን የዘር ማጥፋት ወንጀል 25ኛ አመት ለማስታወስ እዚያው ተገኘን ብለን እራሳችንን እናዳንቃለን። እኛ ርዋንዳን ለመሆን በቋፍ ላይ ያለን ከሳሪዎች መሆናችንን «እኮ ማን ይንገረን?» ኤዲያ።
ማቆሚያ የለሹ የማንነት ጥያቄ
የማንነት ጥያቄው መጦዙን ቀጥሏል።በትልቁ ክልል ውስጥ ሌላ ዘርን መሰረት ያደረገ ክልል ይቋቋም የሚል ንቅናቄ ይታታያል።በዚያው ክልል ውስጥ ዘረን መሰረት ያደረገ የልዩ ዞን ጥያቄ ይነሳል።የኔ ዘር አናሳ ነው በሌላው ዘረ ብዙ ተበድያለሁና ዞን ይሰጠኝ የሚል ጠዝጣዥ ጥያቄ  ላገሪቱ አሳማሚ ሆኗል።አብረው ቡና ወደ ሚጣጡ ጎረቤቶች ጉዳዩ ዝቅ ሲል ደግሞ ጎረቤቱ ለሁለት ይሰንጠቅ ከወዲያኛው ቀበሌ በኩል ልሁን በዘሬ ምክንያት አስተዳደራዊ በደል ይደርስብኛል የሚል መሬት ላይ የወረደ እንቅስቃሴ ይታያል።
መጠፋፋትን አመላካች የሆኑ ግጭቶች በዝተዋል። ሰዎች ይፈናቀላሉ።ንጽሗን ይገደላሉ።በአንድ አካንባቢ ህብራዊ-ማንነትን ይዘው የተጋቡና የተዋለዱ ሁላ ሲሻቸው ያባታቸውን ወገን ደግፈው ካልያም የናታቸውን ወገን ደግፈው ቃታ ስበው ደም ይቃባሉ።አገር ውስጥ በሚከሰት መፈናቀል ኢትዮጵያ ስሟ እየተጠራ ነው።እዚያም ጩኸት ይሰማል።እዚም ዋይታ ያስተጋባል።ህጻናት በለጋ እድሜያቸው የዘረኛ አዋቂዎች ሰለባ ሆነው በየመጠለያው እየማቀቁ ነው።
ነገሮች ‹ከድጡ ወደ ማጡ› እየሆኑ ነው።ጥሞና ያስፈልጋል።መረጋጋት ያስፈልጋል።መመካከር ያስፈልጋል።እስከ አፍንጫችን ድረስ የታጠቅነው የዘረኝነት ትእቢት መተንፈስ አለብት።ትእቢታችን አገር የሚያጠፋ ነው።ትእቢታችን ነጻ አወጣሃለው ለምንለው ብሄራችንም አጥፊ ነው።ትእቢታችን በጋብቻና በትዳር ከኛ ጋር ለተቆራኘው ወገናችን ጸር በመሆኑ ሰብሰብ ብለን የተሻልችና ለሁሉ የምትሆን አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለመስጠት እንስራ።
ህወሃታዊ የዘር መርዝ
27 አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ እግር-ተወርች የጠፈረው ህወሃት የቀበረው የዘር መርዝ አልመከነም።ይህንኑ ህወሃታዊ መርዝ ለማምከን የታገለው ህዝብ መዳረሻው ዲሞክራሲ ሊሆን ይገባ ነበር።የታሰበው ዲሞክራሲ በትላንቱ የህወሃት መርዝም ይሁን «የኔ ዘር ብቻ» በሚሉት ስግብግብነት የሚዘገይ ይመስላል።ሰላምና መረጋጋት የመኖር ዋስትና ናቸውና ከዘራችን በፊት ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንስጥ።
ለውጥ እየመጣ ነው ተብሎ አለም ኢትዮትዮጵያን እየጠበቀ ነው።በለውጥ ግስጋሴ ስሟ የተጠራው ኢትዮጵያ አገር ውስጥ በሚከሰት መፈናቀል ስሟ ገናና መሆኑ ያንገበግባል።እኛ እንሰማም።ያገር ፍቅር ስሜታችን በዘረኝነት ተደናቁሮ እዚያም ጩኸት ይሰማል።እዚም ዋይታ ያስተጋባል።ህጻናት በለጋ እድሜያቸው የዘረኛ አዋቂዎች ሰለባ ሆነው በየመጠለያው መማቀቃቸው ካልተሰማን ከሰውነት ጎራ የምናፈነግጥ ከሻፊዎች እንሆናለንና ቀኑ ሳይረፈድ እንንቃ።
ይህ ተሃድሶዊ ለውጥ ከተበላሸ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን።ለውጡን የሚያሳካው በታሪክ አጋጣሚ አራኪሎ ቤተ-መንግስት የገባው መሪ ብቻ አይደለም።ተመሪውም መሪዉን ይደግፍ።ጭፍን የሆነ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የመሪውን ስተት በገንቢ ትችት የማሳየት  ሐላፊነት አለበት።ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ሚሊዮኖችን ማንቀሳቀስ የሚችሉ በመሆናቸው ሰብሰብ ብለው ይህችን እየፈረሰች ያለች አገር ሊያድኑ ግድ ይላል።ተሰሚነት ህዝብ የሚችረውና የሚነፍገው ጌጥ ነው።የመሰማት እድሉን ከህዝብ የተቸሩ ሰዎች አገሪቷ እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ ለማንም የማይበጅ መሆኑን አስተውለው ተረጋግተው የማረጋጋትን ስራ መስራት አለባቸው።
ከምንፈጃጅ እንበጃጅ
ዘር ተመርጦ የተሰጠን የማንነት መገለጫ አይደለም።ዘር ፈጣሪ በኛ ላይ ጥበቡን ያሳየበት የእኛነት እሴት ነው።የዛሬው ዘራችን ዘላለማዊ አይደለም።የዛሬው ዘራችን ከሌሎች ጋር ተቀይጦ ነገ የሚለወጥና ሌላ ማንነት እንደሚሆን እናጢን።በሰውነት የምንጋራው አያሌ ጸጋ አለን።ከሁሉም በላይ ደምን እንጋራለን።ተመሳሳይ ደም።ቀይ የሆነ ደም።አሁን ግን የዘርን ቀይ መስመር እያለፍን ነውና ከመጠፋፋት ይልቅ መታረቅ፤አገርን ከማፍራርስ ይልቅ አገርን ወደ ማልማት እንሸጋገር።
ኢትዮጵያን «የኔ» በምንለው መልኩ ብቻ ልንቀርጻት ከተነሳን ከከሳሪዎች ጎራ እንሰላፋለን።ኢትዮጵያን «የኔ-የኔ» በሚሉት አባዜ ለመቅረጽ የሞከሩ ከስረዋል።ኢትዮጵያን እኔ በምሻው መልኩ ልገንባ ያሉ ሁላ ገናና የነበረችን አገር አዳክመዋል።ከገባንበት የኔ ሳጥን ውስጥ ወጥተን የኛ የምንለው እሳቤን አናቀንቅን። በመደማመጥ አገር ለማዳን እንነሳ።ኢትዮጵያን ማዳን ስንል ሁሉን ሊያግባባ የሚችል ተቀራራቢ ውህደት መፍጠር አለብን ማለት ነው።እስክንድር ነጋን፣ጀውሃር መሐመድን፣ኦባንግ ሜቶን፣አህመዲን ጀበልን፣አብራሃ ደስታን፣ካሚል ሸምሱንና ሌሎችን አጣጥሞ ላዲሱ ትዉልድ የሚመችን ኢትዮጵያዊነትን እንቅረጽ።አንዱ እንዱን ጥሎ ለማሽነፈ የሚያደርገው ጥረት ሁላችንንም ተሸናፊ ያደርገናል።ግዜው የመፈራረጃ እና እኔ የተሽልኩ ነኝ የምንልበት ሳይሆን የመጣውን አደጋ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይትን የምንመክትበት ነው።
በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ማንም መቀነስ የለበትም።በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መቀነስ ያለበት በዘር ማማ ላይ ከፍ አድርጎ አውጥቶን ሊፈጠፍጠን የደረሰውን የኔ የሚሉት አባዜ ነው።የኔ የምንለው ሰላም ነው።የኔ የምንለው አንድነትን ነው።የኔ የምንለው የተለያየ ሐሳብን አንሸራሽረን አሸናፊ የሆነ የወል ሀሳብን ጨምቀን ማውጣት ስንችል ነው።በኢትዮጵያ ውስጥ የኔ በላጭ ነው ብለን ከተጫረስን ምድሪቱ የሁላችንም መቀበሪያ ትሆናለችና ልብ እንግዛ።እንኳን መሬት ቀርቶ  የመኖራችንና ዱካ፣ የእስትን ፋሳችን መገለጫ የሆነችዋ ነፍሳችን የኔ የምንላት አይደለችም። ነፍሳችንም ባለቤት አላት።ባልሰራነው  መሬት ሳቢያ አንጨራራስ።ከመከራ በፊት እንመካከር።
በመግቢያዬ ላይ «ዘር አስጠላኝ» ብዬ ነበር።ለካስ አስጠሊታው ዘረኝነት ነው።ለካስ የተጠየፍኩት  ዘረኝነትን ነው።ነብያዊ ምሪት እንዳስተማረን «ዘረኝነት ጥንብ» ናት። ትገማለችም።ዘረኛው ግን አያሸታትም።ያማረ፣የጸዳ፣የመጠቀ፣የተራቀቀ፣የሚያሳድግ፣የሚያበለጽግ አብሮነትና ፍቅር እያለ ለምን ዘረኛ እንሆናለን? ዘረኝነትን በመቃወም እንነሳ።ከምንፈጃጅ እንበጃጅ።
ልብ ያለው ልብ ይበል!
Filed in: Amharic